የእነ ዳውድ ኢብሳ ቡድን ምርጫ ቦርድን ዋሽቶኛል ሲል ከሰሰ

Views: 395

የእነ ዳውድ ኢብሳ ቡድን የሆነው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ምርጫ ቦርድ እንደዋሸው እና የወሰነውን ውሳኔ እንደማይቀበለው አስታወቀ።
በኦነግ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ተከትሎ ምርጫ ቦርድ የአመራሮቹን ልዩነት ለመፍታትና የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ኹለቱም ቡድን የተካተቱበት ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂዱ ባሳለፍነው ታኅሳስ 9/2013 መወሰኑ ይታወሳል። ውሳኔውን የእነ ዳውድ ኢብሳ ቡድን እንደማይቀበለው አስታውቋል።

ቦርዱ ጉዳዩን አቃሎታል ሲልም የእነ ዳውድ ኢብሳ ቡድን ምርጫ ቦርድን ወቅሷል። የእነ ዳውድ ኢብሳ ቡድን የኦነግ የህዝብ ግንኙት ኃላፊ ባቴ ኦርጌሳ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት ምርጫ ቦርድ በፓርቲው አመራሮች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት እየሄደበት ያለው መንገድ ስህትት በመሆኑ እንደማይቀበሉት አረጋግጠዋል።

“አሁን ባለው አለመግባባት የሥራ አስፈጻሚ አባላቱ ኃላፊነታቸውን በመወጣት የአባላቶቻቸውን እና የፓርቲውን ጥቅም የሚያስጠብቁበት ሁኔታ ላይ እንዳልሆኑም በግልጽ ይታያል። በዚህም የተነሳ ለዚህ መፍትሄ ይሆን ዘንድ ኹለቱም ቡድኖች በጋራ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያከናውኑ ቦርዱ ወስኗል። ለዚህ ዝግጅት ኹለቱም ወገኖች የሚገኙበት የመጀመሪያ ስብሰባቸውንም በቦርዱ ስበሰባ አዳራሽ እንዲያከናውኑ የተወሰነ ሲሆን ጊዜው ለኹለቱም አመራሮች የሚነገር ይሆናል።” ሲል ቦርዱ ታኅሳስ 9/2013 ባወጣው በግለጫ መግለጹ ሚታወስ ነው።

ይሁን እንጅ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው የቦርዱ ውሳኔ ትክክል እንዳለሆነ በማመን ውሳኔውን ውድቅ ማደረጋቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የቦርዱን ውሳኔ ውድቅ ማድረጋቸውንና ምርጫ ቦርድ በስብሰባ አዳራሹ በሚያካሂደው ስብሰባ እንዳማይገኙ ያሳለፍነው ታኅሳስ 19/2013 በድብዳቤ አሳውቋል።

ምርጫ ቦርድ የኹለቱን ቡድኖች ልዩነት ለመወሰን ባሳለፈው ውሳኔ በአመራሮቹ መካከል ያለው አለመግባባት በፓርቲው ውስጥ እንደማይፈታ እና የቦርዱን ውሳኔ እንደሚፈልግ በመረዳት ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

በውሳኔው መሰረት በዳውድ ፊርማ የተከናወነው እና የብሔራዊ ምክር ቤት ውሳኔ ነው ተብሎ ለቦርዱ የቀረበው የፓርቲውን ምክትል ሊቀመንበር፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት እስከሚቀጥለው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ ከኃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩ የተወሰነው ውሳኔ የስብሰባው በትክክል መካሄዱን የሚያሳይ ቃለጉባኤ የሌለው፣ ምን ያህል የምክር ቤት አባላት እንደተሳተፉበት እና በምን አይነት ድምጽ አሰጣጥ (አብላጫ ድምጽ የተወሰነ መሆን አለመሆኑን) የማያሳይ በሊቀመንበሩ ፊርማ ብቻ የተላከ ውሳኔ በመሆኑ ህጋዊ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ወስኗል።

ነገር ግን የእነ ዳውድ ኢብሳው ቡድን ምርጫ ቦርድ ያቀረበው ውሳኔ ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ ለቦርዱ ስብሰባው በትክክል መካሄዱን የሚሳይ ቃለ ጉባኤ ማስገባቱን አስታውቋል። በመሆኑም ምርጫ ቦርድ የዋሸውን ውሸት እንዲያስተካክል ቃለ ጉባኤ የተላከበትን ደብዳቤ ቁጥር ጠቅሶ ቡድኑ በደብዳቤ ማሳወቁን ጠቁሟል።

በተጨማሪም ቦርዱ በድርጅቱ ምክትል ሰብሳቢ አራርሶ ቢቂላ ፊርማ የተላከለትን የድርጅቱን ሊቀመንበር የታገዱበትን ስብሰባ የሚገልጸውን ቃለጉባኤ ተመልክቶ በቃለጉባኤው ላይ የተገኙት ሥራ አስፈጻሚ አባላት ከስምንቱ አምስት መሆናቸውን ከአምስቱ መካከልም አንዱ አባል ከዚህ ቀደም በዜግነታቸው የተነሳ ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የተቀነሱ በመሆናቸው ሥራ አስፈጻሚው ስብሰባ የሚጠበቀውን 2/3ተኛ መልአተ ጉባኤ ያልተሟላበት አይደልም ብሏል። በመሆኑም ከድርጅቱ የሥራ አስፈጻሚ የተላከው የሊቀመንበሩ እገዳ ውሳኔ ህጋዊ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ወስኗል።

ምርጫ ቦርድ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የፓርቲው ሊቀመንበርም ሆነ በሊቀመንበሩ ታግደዋል የተባሉት ሥራ አስፈጻሚዎች ህጋዊ የድርጅቱ አካላት ሆነው ይቀጥላሉ ብሏል። ነገር ግን የእነ ዳውድ ኢብሳ ቡድን ቦርዱ የመወሰን ስልጣን የለውም ሲል ውሳነውን አጣጥሏል።

ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ከእነ ዳውድ ኢብሳ ቡድን የቀረበበትን ውንጀላ እና ክስ በተመለከተ ከአዲስ ማለዳ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com