ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የንግድ ፖሊሲ እያዘጋጀች ነው

Views: 383

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የንግድ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚንስትር ዴኤታ እሸቴ አስፋው ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።
ይህ የንግድ ፖሊሲ ከሁሉም የዓለማችን አገራት ጋር ተወዳዳሪ ሊያደርገን የሚችል ሲሆን በእኛ አገር ሕጎች ሁሉ የሚቀዱት ከፖሊሲ በመሆኑ የንግድ ፖሊሲ የግድ መኖር አለበት። ንግድ ደግሞ የንግድ ሚኒስትር ሥራ ብቻ አይደለም ከግብር አከፋፈል ሥርዓት ጋር ብናያይዘው እንኳን ሕግ ያስፈልገዋል ይኽ ደግሞ ከገቢዎች ወይንም ከጉምሩክ ተቋማት ጋር አብረን እንድንሠራ ያደርገናል ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የግብርና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲየኢንደስትሪ ፖሊሲ እንዳላት ሁሉ የንግድ ፖሊሲ አለመኖሯ በንግዱ ዘርፍ ወደ ኋላ እንድትቀር አድርጓታል ሲሉም ሚንስትር ዲኤታው ገልጸዋል። ለዚህም ደግሞ እንደ ምሳሌም የዓለማቀፉ የንግድ ድርጅት (WTO) አባል አገር መሆን አለመቻሏን ጠቅሰው ይኽ በንግዱ ዘርፍ በርን ዘግቶ እንደመቆየት ይቆጠራል ብለዋል።

አሁን የዓለማቀፉ የንግድ ድርጅት (WTO) አባል እንድንሆን የሚያሻግር እና ዓለማቀፍ ጥራቱን የጠበቀ ንግድ ውስጥ ለመግባት ከአውሮፓ ከአሜሪካ እና ከአፍሪካ አገራት በንግድ እንድንተሳሳር እንዲሁም በንግድ ተወዳዳሪ እንድንሆን የሚያደርገንን ፖሊሲ ነው እያዘጋጀን ያለነው። እንዲሁም በሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት ፈጣን እና ተደራሽ የሆነ እድገት ለማስመዝገብ የፖሊሲው መቀረጽ ቁልፍ ተግባር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በ1941 የወጣ የኢንደስትሪ ፖሊሲ እንደነበራት እሸቴ አስታውሰው ይኽ ፖሊሲ አሁን ካለው ሁኔታ ጋር አብሮ መሄድ የማይችል እና ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ በመሆኑ በክለሳ እና በመሻሻል ላይ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።

የንግድ ፖሊሲው፤ የሕግ ማሻሻያ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችል የመሬት አሰጣጥ ሥርዓታችን ቀልጣፋ ፈጣን እና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን እንዲሁም ከባንክ የብድር አሰጣጥ ጋር ያለውን ሂደት አጭር ለማድረግ እና የንግድ ሥራ አመቺ እንዲሆን ለሚታቀዱ ሕጎች ሁሉ መሰረት ይሆናል ተብሎ ተጠብቋል። ከዚህ በፊት ይኽንን ሥንሠራ በሌሎች መነሻዎች እንጅ የንግድ ፖሊሲን መሰረት በማድረግ አልነበረም ሲሉም እሸቴ አስፋው ጨምረው ገልጸዋል።

እንደ ንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስትር ደግሞ አንድ ተቋም ወይንም ግለሰብ የንግድ ፍቃድ እንዲሁም የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር(TIN) አውጥቶ እና ሌሎች ነገሮችን አሟልቶ የንግድ ሥራን ለመጀመር የሚወስደው ጊዜ 32 ቀናትን የሚፈጅ በመሆኑ ከአፍሪካ አገራት ጋር ሲነፃፀር በንግድ ሥራ መጀመር ከአፍሪካ ምርጥ ከሚባሉት ሩዋንዳ ኬንያ እና ግብፅ ጋር ሰፊ ልዩነት አለን ብለዋል።

በሩዋንዳ አንድ የንግድ ሥራ ለመጀመር አራት ቀናት ብቻ ይወስዳል ይኽ ማለት በስምንት እጥፍ ትበልጠናለች ማለት ነው ሲሉ ገልጸዋል። ይኽንን ረጅም ጊዜ የሚወስድ የንግድ ፈቃድ የማውጣት ሂደት ቀልጣፋ እና በአጭር ጊዜ የሚፈፀም ለማረግ አገልግሎቱን በኢንተርኔት ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ያገነችው መረጃ ያመላክታል።

በኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ ባለመኖሩ ብዙ የአፍሪካ አገራት ከዓለም የንግድ ድርጅት ጋር በመሆን የአፍሪካ ነፃ ገበያ ውስጥ እንዳንገባ አድርጎናል። እኛ ግን የንግድ ፖሊሲ እና መዳረሻም ስላልነበረን በንግዱ ዘርፍ ላይ ያሳረፈብን ተፅዕኖ በብዙ የኢኮኖሚ ዘርፎች ጉዳት አድርሶብናል ሲሉ ሚኒስትር ዲኤታው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የንግድ ፖሊሲውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ካፀደቀው በኋላ በዚህ ዓመት በሥራ ላይ ይውላል። የኢንደስትሪ ፖሊሲውም በተመሳሳይ መልኩ በዚህ ዓመት በሥራ ላይ እንደሚውል ሚኒስትር ዴኤታው አሳውቀዋል።

በገንዘብ ተቋማት ላይ ከፍተኛ የሕግ አማካሪ እና ባለሙያ በመሆን ረጅም ዘመናትን ያገለገሉት ምሕረትዓብ ልዑል ከዚህ በፊት ተፅፎ የተቀመጠ የንግድ ፖሊሲ ባይኖርም እንደ መነሻ የሚወሰዱ የተለያዩ ከንግድ ጋር የተያያዙ እንደ የአምስት ዓመት የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ያሉ መነሻ ሃሳቦች አሉ ፖሊሲው እነርሱን እንደመከለስ ጭምር ሊወሰድ ይችላል ብለዋል።

ጠቀሜታውን ሲያስረዱም የንግድ ፖሊሲው እንደ መንገድ ማሳያ ይቆጠራል ስለዚህ የምንሄድበትን መንገድ አቅጣጫ አውቀን ከተጓዝን ግባችንን በቀላሉ መምታት እንችላለን። የዓለማቀፉ የንግድ ድርጅት (WTO) አባል አገር ለመሆንም ይረዳና ሲሉ ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com