መረጃ የማግኘት ነጻነት ይከበር!

Views: 106

አንድ አገር ሕግ አውጪ ፣ ሕግ ተርጓሚ እና ሕግ አስፈጻሚ አካላት በአንድ ተዋቅረው እና ተሰናስለው በሚያካሒዱት እንቅስቃሴ እና መግባባት ይገነባል። ይህም አንዱ በአንዱ ላይ ጣልቃ ሳይገባ እና ሳይነካካ ሳይሆን አገርን ለማስቀጠል እና ሕግን አክብሮ ለማስከበር የሚሰራ ለአንድ አላማ የቆሙ የመንግሥት ዋነኛ አካላት ናቸው። ይህ ታዲያ በዲሞክራሲያዊ ስርኣት ውስጥ የሚተገበር እና አገረ መንግሥት ዲሞክራሲን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው እንዲኖረው እና እንዲተገብረው ከሚያደርጉ ጉዳዮችም የእነዚህ ተቋማት እና ሦስቱ አዕማዳት መጠንከር እና ያለ ጣልቃ ገብነት መስራታቸው ዋነኛው መሰረት ነው።

እነዚህ ሦስት ዋነኛ መሶሶዎች ታዲያ በአራተኛ የመንግስት አካልም ይደገፋሉ ይነቀፋሉ ወይም ደግሞ ከሚያስተዳድሩት ሕዝብ ጋርም ይገናኛሉ ድልድያቸውም ይሆናል እርሱም አራተኛው መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ነው። አራተኛው መንግሥት በመባል የሚታወቀው ይኸው አካል ታዲያ በአንዳንድ አገሮች ሲታፈን እና በአፈሙዝ ሲመራ፤ በሌላ አገራት እና በተለይም ደግሞ የዲሞክራሲ ስርዓትን ገንብተን ጨርሰናል ወይም እያበበ ይገኛል በሚሉት ዘንድ ደግሞ በአንጻራዊነት በነጻነት በሚመስል መንገድ ሲሰሩ ይስተዋላሉ። በእኛ አገርም ይህ ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ቢያሳይም በመጣበት ወይም በተነሳበት ፍጥነት ሲገሰግስ ግን አይታይም።

እንደ አራተኛ መንግሥትነት እንደሚቆጠር በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ቢታወቅም ቅሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጉዳይ ግን ከዚህ በእጀጉ የራቀ እና ሩቅ አጥናፍ ላይ ነው የሚገኘው። መገናኛ ብዙኃንን እንደሚገባው ባለማክበር እና የሚገባውን ትኩረት አልመስጠት የሚያስከትለውን ጉዳት ወይም ደግሞ በማፈን የሚመጣው አጸፋ እና ውጤት መንግሥት ከማንም በላይ የሚታዘበው እና የሚያውቀው ለመሆኑ አያጠራጥርም።

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን በመንግሥት ቸርነት ብቻ የሚኖሩ እና መንግሥትም ፊቱን ባዞረባቸው ማግስት ሕልውናቸው አደጋ ላይ የሚወድቁ ዳዴ ከማለት ወደ ዕቅፍ የሚመለሱ የኋሊት ዕድገትን የሚያስመዘግቡ መገናኛ ብዙኃን ምንዱባን እንደሆኑ መገንዘብ አያቅትም። ለዚህ ደግሞ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ብቻ የቀረው እና በተግባር እምብዛም የማይታየው የአራተኛ መንግስትነታቸው አቋም ነው። የመገናኛ ብዙኃን ሳንካ ተብለው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት እና ከሚያስጎነብሳቸው ብርቱ ጉዳዮች መካከል ከመንግሥት አናቂ ሕግ ባለፈ መረጃ የማግኘት ነጻነት ወይም መብት አለመከበር ጉዳይ ነው። በዚህም ረገድ በተለያዩ ጊዜያት አንድ ጊዜ ከፍ ሲል ሌላ ጊዜ ዝቅ እያለ ወጥ ያልሆነ አካሔድን የሚጓዘው የመገናኛ ብዙኃን እድገት በመረጃ ያለማግኘት ችግር ተሸብቦ ዘመኑን እንዲገፋ የተፈረደበት እስኪመስል ድረስ መፍትሔ የታጣበት ጉዳይ ነው።

በየትኛውም ደረጃ ያሉ በተለይም ደግሞ የመንግስት ተቋማት ላይ ተቀምጠው ተቋማትን ከሕዝብ ጋር በቀጥታ ሳይሆን በመገናኛ ብዙኃን በኩል ለማገናኘት የተዋቀሩ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬቶች እና በውስጣቸው በኃላፊነት የተቀመጡ ግለሰቦች በማን አለብኝነት መረጃን ላለመስጠት ሲሞክሩ እና አንዳንድ ጊዜም ጋዜጠኛን ሲያስፈራሩ፣ በሴት ጋዜጠኞች ላይ ደግሞ ጾታዊ ትንኮሳዎችንም ሲያደርጉ ሚስተዋልባቸው አጋጣሚዎች በእጅጉ እየጠነከሩ መጥተዋል። በዚህም በኩል ታዲያ እንዲያውም የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች መረጃን መስጠት እንደውለታም እየቆጠሩ የመምጣት አዝማሚያም እየታየ ይገኛል። ይህ ደግሞ መረጃዎችን ለማግኘት እጅ መንሻ መጠየቅም በቅርብ ቀን ሊያጋጥም እንደማይችል ማረጋገጫ አይኖረንም። ለዚህም ደግሞ ማሳያዎች እና የእጅ መንሻ ጥየቃ ማቆጥቆጡን አዲስ ማለዳ በፒያሳ አካባቢ በሚገኘው የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በመገኘት በሕጋዊነት የመረጃ የማግኘት ቅደም ተከተሎችን ተከትላ ብትቀርብም መረጃውን ለማግኘት በመጀመሪ ደረጃ የአንድ መቶ ብር ክፍያ መፈጸም እንዳለባት በመጠየቋ ላለመክፈል በወሰደችው አቋም መረጃውን ሳታገኝ ቀርታለች። ይህ እንግዲህ በዕለት ተዕለት የመገናኛ ብዙኃን ወይም ደግሞ እንደሚባለው አራተኛው መንግሥት የሚገጥመው ዕለታዊ ፈተና ሆኖ ወደ በመቀንጨር እንደ ዕድሜው እንዳይሆን ያደረገው ጉዳይም ነው።

ምንም እንኳን በመገናኛ ብዙኃኑ ዘንድ ይህ ጉዳይ በጠቅላላው የሚታይ ችግር ቢሆንም በተለይም ደግሞ በሕትመት መገናኛ ብዙኃን ዘንድ ደግሞ ችግሩ ዕጥፍ ድርብ ሆኖ ይገኛል። የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ካላቸው ተደራሽነት ውስንነት እና ከተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው ማነስ ጋር ተዳምሮ ብዙም ትኩረት እየተሰጣቸው ባለመሆኑ መረጃዎችን ለማግኘት የሚኖረው ተጋድሎ በእጅጉ የበረታ እና እንደ ብረት እየጠነከረ ያለ ጉዳይ ሆኗል። አዲስ ማለዳ ከጊዜያት በፊት ከኢትዮጵያ ብርድካስት ባለሥልጣን ባረጋገጠችው መረጃ መሰረት በዐሥር ዓመታት ውስጥ 260 የሕትመት መገናኛ ብዙኃን የከሰሙ ሲሆን ለመክሰማቸው ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የመረጃ እጥረት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። በአንድ አገር የመገናኛ ብዙኃን ይህን ያህል ትልቅ ቁጥር ያላቸው ሲዘጉ እና ሲከስሙ ወይም ከንባብ ውጪ ሲሆኑ መንግስት እንደመንግሥት ሊያስደነግጠው እና ሊያስቆጨው ይገባል።

መረጃዎች በሚገባ መንገድ ከመንግሥት ተቋማት ወጥተው ወደ ሕዝብ በመገናኛ ብዙኃን በኩል እንዳያልፉ መረጃዎች የሚያዙ ከሆነ እና የማይሰጡ ከሆነ አሉባልታዎች እና መደበኛ ያልሆኑ መረጃዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ መሰራጨታቸው እሙን ነው። ይህ ደግሞ አገርን እና ሕዝብን ከማወናበድ እና ለውዝግብ ከመዳረግ የዘለለ ምንም አይነት ውጤት አያመጣም። መረጃ ሀብት በሆነበት በዚህ ዘመን ሕዝን በመረጃ ለማስታጠቅ ቆርጠው የተነሱ እና ሚዛናዊ የሆኑ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በመረጃ እጥረት እና በማን አለብኝነት በሚንቀሳቀሱ የመንግሥት ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች እየተንጓጠጡ እና እየተወረፉ የሚሰሩበት ጊዜ በአስቸኳይ ሊያበቃ ይገባል።

መንግሥት በትክክል መገናኛ ብዙኃን አራተኛ መንግሥትነታቸውን የሚስጠብቅ ከሆነ በጉያው ያቀፋቸውን እና መብት እና ግዴታቸውን የማያውቁ የስራ ኃላፊዎችን በሚገባ ሊያጠራ እና ሊገመግም ይገባል። ዲሞክራሲን ለመገንባት መገናኛ ብዙኃንን ያላቀፈ እና ያላካተተ እርምጃ ውጤቱ እንደማያምር ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል እና ከወዲሁ ችግሮች እንዲቀረፉ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ይሁን እንጂ እንዲህ ሳይሆን ቀርቶ መረጃዎች ለተመረጡ እና በግል ለሚታወቁ ግለሰቦች እና የመገናኛ ብዙኃን አካላት መስጠት የትም የማያደርስ እና የማያራምድ አካሔድ ነው። መጪው ጊዜ አገራዊ ምርጫ የሚካሔድበት እና በትክክል መረጃዎች ለሕብረተሰቡ መድረስ የሚገባቸው ጊዜ እነሆ በደጅ ነው እና ከወዲሁ መገናኛ ብዙኃንን ለይቶ መረጃ ማቀበል እና ለመረጃ በሮቻቸውን ዝግ ማድረግ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com