“በጸጥታ ችግር ከተጎዱ ኢንቨስትመንቶች ማገገም የሚችሉት አንድ በመቶ ያክሉ ናቸው” የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሚ

Views: 276

ኢትዮጵያ ውስጥ በጸጥታ ችግር ሰላባ ሆነው ከሚወድሙ የኢንቨስትመንት ልማቶች ውስጥ ከደረሰባቸው ጉዳት አገግመው ወደ ሥራ የሚመለሱት ከአንድ በመቶ በላይ እንደማይሆኑ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሚ አስታወቁ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ2008 እስከ 2013 ከ400 በላይ የኢንቨስትመንት ልማቶች መውደማቸውን ኮሚሽነሯ ተናግረዋል። ቁጥሩ በቅርቡ በትግራይ ክልል በተካሄደው የሕግ የማስከበር ዘመቻ በክልሉ የወደሙ ኢንቨስትመንቶችን ሳያካትት መሆኑን ኮሚሽነሯ አብራርተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም እጦት ምክንያት የኢንቨስትመንት ልማቶች መክሰር የተለመደ እየሆነ ነው ሲሉም ኮሚሽነሯ አክለዋል። በዚህም ኢንቨሰተሮች ሐብታቸውን አፍሰው ወደ ሥራ ለመግባት ሥጋት እየገባቸው መሆኑን ኮሚሽኑ ማረጋገጡን ሌሊሴ ጠቁመዋል።

በጸጥታ ችግር የወደሙ ኢንቨስትመንቶች አገግመው ዳግም ወደ ሥራ እንዳይገቡ የሚያደርጋቸው ዋናው ምክንያት በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው የኢንቨስትመንት ጠቃሚነት ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ በማኀበረሰቡ እምነት ስለማይኖራቸው ነው ተብሏል። ኮሚሽነሯ ታኅሳስ 21/2013 ከክልልና ከከተማ ኢንቨስትመንት ቢሮዎች ጋር በሐያት ሪጀንሲ ሆቴል በተወያዩበት ጊዜ ለክልል እና ለከተማ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊዎች የኢንቨስትመንት ልማቶች ለማኅበረሰቡና ለአገር ትልቅ ሚና እንዳላቸው ግንዛቤ እንድፈጥሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትምንት ኮሚሽን ላለፉት አንድ ወር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው የጋራ ውይይት ለኢንቨስትሮች የተሰጣቸው ድጋፍና በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው መጥፎ ግንዛቤ ኢንቨስተሮችን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ መሆኑን መረዳት መቻሉን ተመላክቷዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት ልማት ላይ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች የሚገጥማቸው ችግር የመጀመሪያው በጸጥታ መደፍረስ ውድመት ቢሆንም የመሬት አቅርቦት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት አሁንም እንቅፋት የሆኑ ችግሮች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ልማት አማካሪ በርኬሳ በሀይሉ በውይይቱ ላይ ጠቁመዋል።

በቅርቡ በትግራይ ክልል በተካሄደው ሕግ የማስከበር ዘመቻ የወደሙ የኢንቨስትመንት ልማቶች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንደማያውቁ ባለሀብቶች ለኮሚሽኑ መግለጻቸውን በርኬሳ ተናግረዋል። እንዲሁም የሠራተኞቻቸውን ደህንነት በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ማረጋገጥ አልቻሉም ተብሏል።

በኢትዮጵያ አሁን ያጋጠመውን የኢንቨስትመንት እንቅፋት የሚመለከተው ሁሉ ተባብሮ ካልተስተካከለ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚገጥም ኮሚሽነሯ ጠቁመዋል። ኢንቨስትመንት ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለውጭ ንግድ እና ለአጠቃላይ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት መሰላለ መሆኑን ያነሱት ሌሊሴ ኮሚሽኑ ከኢንቨስተሮች ጋር ባደረገው ውይይት ኢንቨስትሮች እየተደገፉ አለመሆኑን ተረድተናል ብለዋል። ኢንቨስትሮች በመንግሥትና በሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆን በጥናት ጭምር ኮሚሽኑ አረጋግጧል ተብሏል።

በመንግሥት በኩል የሚታዩት ክፍተቶች ታርመው ለኢንቨስትሮች በሚፈልጉት ልክ አገልግሎት በመስጠት ሁሉንም የኢንቨስትመንት ችግሮች በመፍታት በቀጣይ ዓመት የተሻለ ምርት ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ባለድረሻ አካላት በትኩረት መሥራት አንዳለባቸው ሌሊሴ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ከኢንቨስትሮች ጋር በነበረው ውይይት ኢንቨስተሮች በቢሮክራሲ ብዛት እንደተሰላቹ ለመገንዘብ መቻሉን ተናግረዋል። በመሆኑም ኢንቨስተሮችን በቢሮክራሲ ከማሰልቸት አሰራር መላቀቅና የአንድ መስኮት አገልግሎት(one-stop service) የክልል ቢሮዎች አንዲሰጡ ጠቁመዋል።

በውይይቱ ላይ ተገኝተው ጽሑፍ ያቀረቡት በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን የግል ዘርፍ ስፔሻሊስት ፋንቱ ፋሪስ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። እንዲሁም ለግሉ ዘርፍ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን አማራጭ መንገድ መሆኑንም አመላክተዋል።

ፋንቱ እንደሚሉት ከሆነ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ በአንድ አካባቢ የተወሰነ ኢንቨስትመንት አንደ አገር መቀየር ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል። አንዲሁም ኢንቨስትመንቱን ሊበረታቱ የሚችሉ ሕጎችን ማሻሻልና በረቂቅ ደረጃ የሚገኙትንም በፍጠነት አጽድቆ ወደ ሥራ መግባት ተገቢ ነው ብለዋል።

የኢንቨስትመንት አማካሪ የሆኑት ያለው አዱኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር በተፈጠረ ወቅት የኢንቨስትመንት ልማት እየወደመ አይደልም አንድ በመቶ ሙሉ በሙሉ ባያገገሙ የሚገርም አይደልም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። እንደ ምክኒያት የሚያነሱትም የነበራቸውን አጥተው ዳግምኛ ወደ ሥራ ለምግባት የሚያነሳሳቸው ምቹ ሁኔታ ስለማይኖር ነው ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com