አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተፈናቃዮች የላከው ድጋፍ አልደረሰም ተባለ

Views: 395

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በጸጥታ ችግር ምክኒያት ለተፈናቀሉ ዜጎች የላከው ሦስት ሺሕ ኩንታል የምግብ ድጋፍ ለተፈናቃዮች አለመድረሱ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ብር የሚገመት የምግብ እህል ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ የተደረገውን ድጋፍ የክልሉ መንግሥት ተፈናቃዮች በእርዳታ እጥረት እየተቸገሩ ባሉበት ወቅት አሶሳ ላይ እንዲራገፍ ማደረጉን የአዲስ ማለዳ ምንጮች አረጋግጠዋል። ድጋፉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ ሺሠማ ገብረስላሴ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ባሳፍነው ታኅሳስ 17/2013 ርክክብ ተደርጎ ነበር።

በቤኒሻንጉል ክልል ተፈናቃዮች የሚገኙት መተከል ዞን ውስጥ ቢሆንም ከከተማ አስተዳደሩ ለተፈናቃዮች የተላከው ድጋፍ የተፈናቀሉ ዜጎች እየተቸገሩ ቢሆንም አሶሳ ከተማ በመራገፉ መድረስ እንዳልቻለ ለተፈናቃዮች የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ የሆኑ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል።

ከከተማ አስተዳደሩ የተደረገው ድጋፍ በክልሉ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ምላሽ ለመጠት እየተሠራ ላለው ሥራ አጋዥ እንደሚሆን በክልሉ አመራሮች በወቅቱ ቢገለጽም እንደተባለው ለዜጎች አስቸኳይ ችግር ሊደርስ አልቻለም። በክልሉ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እንዲደረግ ከከተማ አስተዳደሩ የተላከው ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር የሚገመት የ አንድ ሺሕ ኩንታል ስንዴ፣ አንድ ሺሕ ኩንታል ጤፍ እና አንድ ሺሕ ኩንታል በቆሎ መሆኑ ተመላክቷል።

ለተፈናቃዮች እንዲደርስ የተላከው ሦስት ሺሕ ኩንታል የምግብ ድጋፍ አሶሳ የተራገፈው ያለ ምክንያት አይደልም ሲሉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል። ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ድጋፉ አሶሳ የተራገፈው በክልሉ ካለው የጸጥታ ችግር ጋር በመመርኮዝ ሲጓጓዝ ተዘረፈ በሚል ሰበብ ድጋፉ ሊቀር ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ያደረገውን ድጋፍ ከአዲስ አበባ ተፈናቃዮች ወደ ሚገኙበት መተከል ዞን ለማድረስ የሚፈጀው የመንገድ ርዝመት ከ550 ኪሎ ሜትር የማይበልጥ ነው የሚሉት የአዲስ ማለዳ ምንጮች ድጋፉን በአሶሳ በኩል መተከል ለማድረስ ከ አንድ ሺሕ በላይ ኪሎ ሜትር ይፈጃል ብለዋል። ይህም ድጋፉ በአስቸኳይ ለተፈናቃዮች እንዳይደርስ ታስቦ የተደረገ ያስመስልዋል ተብሏል።

ሰሞኑን ከመተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጅ ቀበሌ በተፈጠረው ችግር የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ በፈቃደኝነት የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ የሚያሰባስቡ አስተባባሪዎች ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ሕዝብ እየተሰቃየ የተገኘ ድጋፍ ባልሆነ መስመር ወስዶ ማራገፍ ጤነኛ አሰራር አይደልም።” ሲሉ ድርጊቱን ኮንነውታል። አስተባባሪዎቹ ድጋፉ በአፋጣኝ ሊደረስላቸው ሊመገባቸው ተፈናቃዮች ቅርብ በሆነው መስመር በቀጥታ መጓጓዝ ሲገባው ለምን አሶሳ ተራገፈ ብለው የክልሉን የመንግሥት አካላት ጠይቀው አይመለከታችሁም የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ለአዲስ ማለዳ ታናግረዋል።

አስተባባሪዎቹ አክለውም በቡለን ወረዳ በተፈጠረው ችግር በቀጥታ ሰላባ የሆኑና በስጋት የተፈናቀሉ ዜጎች ብዛት ወደ 50 ሺሕ እንደተጠጋ ተናግረዋል። ነግር ግን አስቸኳይ ድጋፍ ማድረግ የተቻለው ቀድመው ወደ ቡለን ወረዳ ከተማ ለገቡ 32 ሽሕ የሚጠጉ ዜጎች ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህም የሆነበት ምክንያት ቦታው ላይ የደረሰው ድጋፍ በማለቁ መሆኑ እንደ ምክንያት ቀርቧል።

አዲስ ማለዳ በባለፈው እትሟ ከቡለን ወረዳ ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎች በቂ ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑን መዘገቧ የሚታወስ ሲሆን ችግሩ እስካሁን ድረስ እንዳልተቀረፈ ማረጋገጥ ተችሏል።

በክልሉ በተደጋጋሚ በሚፈጠሩ ችግሮች የተፈናቃዮች ቁጥር እያሻቀ ምምጣቱነ የክሉ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መለስ በየነ አረጋግጠዋል። በተፈናቃዮች ልክ አስቸኳይ ስብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የጸጥታ ችግርና የመንገድ መዘጋጋት እንቅፋት መሆኑን እንደ ምክኒያት አንስተዋል።

የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ ድጋፉን አሶሳ በማራገፍ ለተፈናቃዮች በወቅቱ እንዳይደረስ አድርጓል ተብሎ ለቀረበበት ትችት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያደረገው ድጋፍ በመተከል ዞን ለተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ ቦታው ይጓጓዛል ብሏል። ኮሚሽኑ ትችቱን መሰረተ ቢስ ነው ሲልም አጣጥሏል ። ድጋፉን የጫኑ ተሸከርካሪዎችን ወደ መተከል ማጓጓዝ አስቸጋሪ በመሆኑና እጀባ ስለሚያስፈልግ መራገፉ አማራጭ የሌለዉ በመሆኑ እንጂ ሌላ ዓላማ ኑሮት አይደለም ሲልም ኮሚሽኑ አሳውቋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን በጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ97 ሺሕ በላይ መሻገሩን ሰላም ሚኒስቴር አስታቀውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com