በአዲስ አበባ የወርቅ ማቅለጫ ሊገነባ ነው

Views: 388

በአዲስ አበባ ከተማ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የወርቅ ማቅለጫ እንደሚገነባ የማአድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህንን የወርቅ ማቅለጫ መገንባት እንደ ኢትዮጵያ ላለች የወርቅ ማዕድን ላላት አገር ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ የማአድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናግረዋል።

ሚድሮክ እና ሌሎች የተለያዩ ኩባንያዎች ወደ ወርቅ ማምረት እንደሚገቡ እና እነዚህ ኩባንያዎች ምናልባትም ከኹለት እስከ ሦሥት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገቡ የወርቅ ምርታችን ይጨምራል ብለዋል።

እንደ ታከለ ገለፃ ከአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ በአካባቢው ማህበረሰብ በተነሳበት ተቃውሞ የማእድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የሚድሮክ ወርቅን የምርት ፈቃድ አግዶበት ኩባንያው ከኹለት አመት በላይ ምርት አቋርጦ እንደነበር ይታወቃል።

የተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ በማግኘታቸው የአካባቢው ማህበረሰብ እና የክልሉ ተጠቃሚነት በመረጋገጡ የማእድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የኩባንያውን ፈቃድ እንደመለሰለት አስታውቀዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ወደፊት የወርቅ ምርቷ እየጨመረ በመጣ ቁጥር ማቅለጫው መኖሩ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም አስረድተዋል።
አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ በመንግስት እና በባለሀብት የተደገፈ የወርቅ ማቅለጫ እና ላብራቶሪ እንደሚገነባም ኢንጂነሩ አክለው ተናግረዋል።
አገራት ስለዶላር የሚያወሩት ባላቸው የወርቅ ክምችት ነው ያሉት ሚኒስትሩ እንደ አገር የውጪ ምንዛሬ እጥረት እንዳለብን ይታወቃል ፤ ለዚህም አገራችን የሚያስፈልጋትን የውጪ ምንዛሬ ለማግኘት የወርቅ ክምችታችን መጨመር እንዳለበት አስረድተዋል።

ወርቅ ላይ ያለውን ዋጋ ማስተካከል ብቻ ሳይሆን ያመረትነውን ወርቅ ደረጃውን በጠበቀ ቤተሙከራ እና ማቅለጫ አስታከን የወርቅ ክምችትን ማሳደግ ይገባናልም ብለዋል።

በማአድንና ነዳጅ ዘርፍ እምቅ ሀብት ያለባቸው 50 ቦታዎች መለየታቸውን ከነዚህም መካከል 22 ቦታዎች በማአድን ዘርፍ 28 ቦታዎች ደግሞ በነዳጅ ዘርፍ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቦታዎቹ ከዚህ ቀደም ጨረታ ወጥቶባቸው ሳይሰጡ የቀሩ ፣ ውሳኔ ሳገኙ የቆዩ ፣ እንዲሁም ለባለሀብቶች ተሰጥተው ወደ ተግባር ባለመግባታቸው የተነጠቁ ቦታዎች መሆናቸው አዲስ ማለዳ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

የተለዩት ቦታዎች በኦሮሚያ ፣ ትግራይ ፣ ቤንሻንጉምዝ ፣ አማራ ፣ አፋር ፣ ሶማሌ እና ኦሞ እንደሚገኙም ተመላክቷል።
በማአድን ዘርፍ ከተለዩት ቦታዎች አብዛኞቹ በኦሮሚያ የሚገኙ ሲሆኑ በነዳጅ ዘርፍ ከተለዩት ደግሞ 15 የሚሆኑት በሶማሌ ክልል እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አለም አቀፍ የጨረታ ሰነድ እንደተዘገጀ እና ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ባለሀብቶች ጨረታ እንደሚወጣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

የተጣሩት ቦታዎች ላይም እሰራለሁ የሚል ማንኛውም ባለሀብት ቢመጣ ክፍት እንደሆነ የተናገሩት ሚንስቴሩ በዚህም እውቀት ያለው ፣ ገንዘብ ያለው ፣ ልምድ ያለው ኢንቨስት ማድረግ እንደሚችል አስታውቀዋል።

መስራት ለሚችሉ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች ተጣርተው ቦታዎቹ እንደሚሰጡም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን በተመለከተ ለረጅም ጊዜያት የተጠኑ ጥናቶችን በጋራ በማደራጀት ለምርት ዝግጁ የሆኑ ቦታዎች መለየታቸውም ገልፀዋል።

በዚህም ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልግ አካል ግማሹ ስራ በመንግስት ተሰቶለታል በዚህም የት ቦታ ላይ ፣ ምን አይነት ማአድን ፣ የሚገኝው የማአድን መጠን በጥናቱ የተመላከተ ስለሆነ ኢንቨስተሩ ምንም ሳይቸገር ወደ ስራ መግባት ይችላል ተብሏል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በማአድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ፈቃድና ውል አስተዳደር ዳይሬክተር አበበ በዳሳ እንደተናገሩት ይህ የወርቅ ማቅለጫ መገንባቱ ለአገራችን እድገት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

አገራችን ወርቅን ለማስቀለጥ ወደ ውጪ አገራት ትልካለች በዚህም በBar (ወርቅ ማቅለጫ )240 ዶላር ወጪ ታደርጋለች ማቅለጫው ሲገነባ የምናወጣው ገንዘብ አይኖርም እንደውም ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ወርቆችንም በማቅለጥ የውጪ ምንዛሬን ያሳድጋል ብለዋል።

ወርቅ ማቅለጫውን ለመገንባት 60 ሚሊዮን ዶላር ሊፈጅ እንደሚችል ይገመታል ሲሉ ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com