በመቀሌ የነዳጅ እጥረት ምክንያት መቸገራቸውን አሽከርካሪዎች ተናገሩ

Views: 52

የመቀሌ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ከጅቡቲ እየመጡ በመሆኑ ችግሩ እንደሚቃለል አስታውቋል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ አሽከርካሪዎች እንደተናገሩት፤ የነዳጅ እጥረት ለመንቀሳቀስ ፈተና ሆኖባቸዋል። የባለ ሶስት እግር ባጃጅ እና የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች በነዳጅ እጦት የተነሳ ከሚሰሩበት ጊዜ የማይሰሩበት እንደሚበልጥ ተናግረዋል።
በነዳጅ ማደያዎች በ21 ብር የሚሸጠው አንድ ሊትር ቤንዚን በጥቁር ገበያ እስከ 100 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የከተማ ታክሲ አሽከርካሪዎችም በተመሳሳይ የነዳጅ እጥረቱ ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ ያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ተንቀሳቅሰው መስራት አለመቻላቸው ለችግር እየዳረጋቸው እንደሆነም አመልክተው፤ አገልግሎት የሚፈልገው የከተማው ህብረተሰብ ጭምር በመቸገሩ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የመቀሌ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር የመንግስት አገልግሎት ዘርፍ ክትትልና ቁጥጥር የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ብርሃነ ወልደገብርኤል ለችግሩ በሰጡት ምላሽ እጥረት ያጋጠመው የነዳጅ ቦቴዎች መግባት ሳይችሉ በመቆየታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
አሁን ችግሩን ለመፍታት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባደረገው ጥረት ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ከጅቡቲ እየመጡ በመሆኑ በቅርብ ቀናት ችግሩ እንደሚፈታ ገልጸዋል።
የታክሲና ባጃጅ ባለ ንብረቶች እንዲሁም ህብረተሰቡ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በመሆን በጥቁር ገበያ የተሰማሩ ህገወጥ ነጋዴዎችን በማጋለጥ ሥርዓት ለማሲያዝ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የህወሃት ጁንታ ለጦርነት ዝግጅት በሚያደርግበት ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ መያዝ የሚችሉ ታንከሮችን ቀብሮ እንደነበር በአገር መከላከያ ሰራዊት መረጋገጡ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com