ስጦታ – በገና በዓል

Views: 126

ከወደ ምሥራቅ አገር በኮከብ ብርሃን ተመርተው የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ ምክንያት በማድረግ ወደ ቤተልሔም መጡ – የጥበብ ሰዎች፤ ሰብአ ሰገል።
ወርቅ፣ እጣን እና ከርቤም አምጥተው ስጦታ አበረከቱለት። ሰብአ ሰገል እነማን ናቸው ከተባለ ከሥማቸው ትርጓሜ አንስቶ የጥበብ ሰዎች ይባላሉ። ጠቢባን እንደሆኑና ጠብቢነታቸውም ከዋክብትን በመመራመር እንደሆነ መጋቤ ሃዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶ/ር) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቴሌቪዥን ስርጭት ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

የሃይማኖቱ ሊቃውንትም ሰብአ ሰገል መጥተው ስጦታ ስለመስጠታቸው እና ስለመስገዳቸው ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ይሰማል። እኛም ስለ ሰብአ ሰገል ማንሳታችን ምክንያት ስላለን ነው። በርካታ ሰዎች የገና በዓል ሲቃረብ ስጦታዎችን ሲገዙ ይስተዋላል። በሌላ በዓላት ላይ የማይስተዋለው ስጦታ የመሰጣጠቱ ነገር በገና በዓል ላይ ጎልቶ እና ሰፍቶ እንመለከታለን። ለመሆኑ ገና እና ስጦታ ምን እና ምን ናቸው? ከውጭ የመጣ ባህል ነው ወይስ ሃይማኖታዊ መሰረት አለው? በማለትም ጠይቀናል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን መምህር የሆኑት መምህር ዳንኤል ሰይፈሥላሴም ታሪኩ ረዥም እንደሆነ በመግለፅ የገና በዓል እና ስጦታ ትስስር እንዳላቸው ለአዲስ ማለዳ ይጠቅሳሉ። ስጦታ መስጠት አክብሮትን እንዲሁም ፍቅር ለመግለፅ አልፎም ያለውን ነገር ከማካፈል ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ይታወቃል።
‹‹ሰብአ ሰገል ከሩቅ አገር ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታ ይዘው መተዋል። አመጣጣቸውም ከፋርስ፣ ከምሥራቅ የመጡ ሲሆን ነገዳቸውም ከነገደ ሴም፣ ነገደ ያፌት እና ነገደ ካም በመምጣት ወርቅ እጣን እና ከርቤ አበርክተውለታል።›› በማለት መምህር ዳንኤል ገና እና ስጦታ ስላላቸው ሃይማኖታዊ ትስስር ያወሳሉ።
የጥብብ ሰዎች ተብለው የሚጠሩት ሰብአ ሰገል እነዚህን ስጦታዎች ያበረከቱበት ምክንያት ሃይማኖታዊ ዳራ አለው። ስለምን እነዚህን ስጦታዎች ሰጡ ቢባልም ሊቃውንቱ በተለያየ መንገድ እንደሚገልጹት ያነሱት መምህሩ፤ ወርቅ ለመግንሥቱ፣ እጣን ለክህነቱ ወይም ለሊቀ ካህንነቱ፣ ከርቤ ደግሞ ለመሞቱ እንዳበረከቱለት ጠቅሰዋል።

‹‹ይህም የሚያሳየው ዘመድ ከዘመድ፣ ወገን ከወገን፣ የሚተዋወቅ ከማይተዋወቅ ጋር ሆኖ ሰላምታን የሚሰጣጡበትን የሚግባቡበት ነገር እንደሆነ ያሳያል። ሌላው ደግሞ የጌታችን መወለድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፣ የድኀነት ስጦታ ነው። እኛም የአክብሮት እና የአምልኮ ስጦታን መልሰን እንሰጣለን። ይህም እኛ እንድንከባበር ምክንያትም ሆኗል›› ሲሉ መምህር ዳንኤል አክለዋል።

ምን ስጦታ ይሰጥ?
የክርስትና እምነት ተከታዮች የገና በዓልን ለማክበር የበዓሉን ቀን በጨዋታ እና በጋራ ሆነው በምበላትና በመጠጣት ለማሳለፍ ሽር ጉድ ሲሉ ይስተዋላል። አቅም ያለው በግና ዶሮ ገዝቶ እንዲሁም በጋራ ቅርጫ በመቃረጥ ያሳልፋል።

እንደ መርካቶ ያሉ አካበቢዎች ወትሮ ከሚታይባቸው የሰው መጨናነቅ የበዓል ቀናት መዳረሻ ላይ ደግሞ ከሌላ ጊዜ በበለጠ ለየት ያደርጋቸዋል። የተለያዩ ገበያ ማእከላትም ራሳቸውን በነጭ እና በቀይ ቀለማት በማሽቆጥቆጥ ደንበኞችን ለመሳብ የተለያዩ ማጌጫዎች፣ የገና ዛፍ(በሰው ሰራሽ ዛፍ)፣ የባህል አልባሳትን ጨምሮ በነጭ እና በቀይ ያሸበረቁ ዘመናዊ አልባሳትንም በማዘጋጀት፣ ከተማውን በማድመቅ አውደ ዓመት መምጣቱን ይናገራሉ።

ሸማቾችም ቢሆን ቤታቸውን አስውበውና አሳምረው ከቻሉም ለራሳቸው እና ለልጆቸው አልባሳትን በመግዛት የተለያዩ ቁሳቁሶችን ሲሸምቱ የሚስተዋል ነገር ነው። ቀሪዎቹ ደግሞ ለወዳጅ ለዘመዶቻቸው ስጦታዎችን ለመስጠት ወደ ገበያ ያቀናሉ።

አዲስ ማለዳም የተለያዩ ቦታዎችን ለመቃኘት ሞክራለች። በቅኝቷም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በከተማው እንደ ከዚህ ቀደሙ የኤግዚቢሽን እና ባዛር ግብይት በስፋት አለመከወኑንም ታዝባለች።

ይሁን እንጂ ጆርካ ኤቨንት በመቻሬ ሜዳ ባዘጋጀው ‹ኢትዮ ገና ባዘር› ላይ ተገኝታ እንደታዘበችው፣ ቦታው ላይ የቤት እቃዎች፣ ሰው ሠራሽ የገና ዛፍ፣ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች፣ ባህላዊ እና ዘመናዊ አልባሳትንም ጨምሮ ለስጦታ የሚሆኑ ቁሳቁሶች እንደነበሩ ተተመልክታለች።

መሠረት ንጉሤን ያገኘናት ፒያሳ አካበቢ ነው። ስጦታዎችን መስጠት እንደሚስደስታት በመናገር በዚህም ለምትሰጣቸው ሰዎች ያላትን ፍቅር እና አክብሮት ለመግለፅ እንደሆነ ገልጻለች። በዚህ የገና በዓልም ለእናቷ የሃበሻ ቀሚስ እንዲሁም ለፍቅረኛዋ ደግሞ ሽቶ እና መነጽር (ስለሚወድ) ስጦታ ለመስጠት ማሰቧን ትናገራለች።
‹‹በእርግጥ እኔ ስጦታ የምሰጠው በብዛት በበዓላት ወቅት ነው። የምሰጠውም ፍቅር እና እክብሮቴን ከመግለጽ በተጨማሪም ሰው በእኔ ምክንያት ሲደሰት ማየት ስለሚያስደስተኝ ነው።›› ስትልም መሠረት ትናገራለች።

አሁንም ከፒያሳ አልራቅንም፤ በአንድ ሱቅ ጎራ ብለናል ሥሜ ይቆይ ካለን መልከ መልካም ወጣት ነጋዴ ጋር ተገናኘን። በመደብሩ ውስጥ የተለያዩ ነገሮችን ይዟል። ለአብነት እንጥቀስ እንኳን ካልን የሴቶች የመዋቢያ ምርቶች፣ የስጦታ ካርድ፣ ሻማ፣ የጆሮ ጌጥ፣ የሴቶች ልብስ እና በቀይና ነጭ ያሸበረቁ ኮፍያዎችንም አካቷል።
አዲስ ማለዳም ወደዚህ ወጣት ጠጋ ብላ ‹ገበያው እንዴት ነው?› ስትል ጥያቄ አቀረበች። ወጣቱ ነጋዴም የመከፋትም ሆነ የመደሰት ስሜት ሳያሳይ ‹‹ገበያው አሁን ይሻላል። ከዚህ ቀደም በጣም ተቀዛቅዞብን ነበር። አሁን ግን ይሻላል። ያው አሁን ደግሞ ያለነው የገና በዓል ዋዜማ ላይ አይደል? ሴቶች ራሳቸውን ለማስዋብ በዓሉን አምረው እና ደመቀው ለመታየት የተለያዩ ነገሮችን ይገዛሉ። እንዲሁም ወንዶች ለሚስቶቻቸው፣ ለፍቅረኛቸው፣ ለእናቶቻቸው እንዲሁም ለእህቶቻቸው ስጦታ ለመስጠት የስጦታ ካርዶችን፣ ሻማዎችን፣ ሽቶዎችን እና ሌሎች ነገሮችንም ይገዙናል›› በማለት ነበር የገና በዓል መዳረሻ አካባቢ አስታያየቱን የሰጠው።

በገና በዓል የሚስተዋለው ስጦታ መስጠት ስርዓት መሠረቱ ከውጭ የመጣ እንዳልሆነና ሰባ ሰገል ስጦታ ከመስጠታቸውም ጋር የተያያዘ እንደሆነ ቀደም ሲል አመላክተናል። ሰዎች የተለያዩ ስጦታቸውን እንደሚሰጣጡ የሚታወቅ ቢሆንም፣ በጎ ነገር ለሰው መስጠት አሁን እየጠፋ ያለው ነገር እንደሆነ መምህር ዳንኤል ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል።

ስጦታ መስጠት በጎ ነገር በመሆኑ አሁን ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት መምህር ዳንኤል፤ ‹‹አሁን ላይ ሁሉም ሰው ራሱን ተቀባይ ብቻ አድርጓል፤ ራሱን ተበዳይ አድርጓል። በተለያየ ነገር ውስጥ ነው ያለነው ነገር ግን ስንሰጥ ነው የምንሞላው።›› በማለት ተናግረዋል።
ጨምረውም እንዲህ አሉ፤ ‹‹ሰው ሲሰጥ ነው የሚሞላው፤ ሲቀበል አይደለም። ይህም ሰው ሙሉነት እንዲሰማው ያደርጋል። ስለጎደለን ነገር ብቻ ብናስብማ እስከ ዕለተ ሞታችን አንሞላውም። ጌታችንም ያስተማረን መስጠትን ሲሆን ለዚህም ራሱን አሳልፎ እስከመስጠት ነው የደረሰው።›› ሲሉም ይገልጻሉ።

መምህር ዳንኤል በሮማውያን ዘመን የነበረውን ነገር ያስታውሳሉ። ‹‹ሮማውያን አገር ወረው፣ ሰው ዘርፈው ዝም ብሎ መውሰድ ነበር ሥራቸው። በዚያ ዘመን ጌታችን ግን ራሱን ሰጠ። በዚህም ሳቢያ ጠቢባን እጅ መንሻ አቀረቡ። እረኞችም ቢሆኑ ስጦታ ሰጡ። ከብቶች እንኳን በበረት ውስጥ የሚሰጡት ነገር ባይኖራቸው ብርድ ነበርና ትንፋሻቸውን ገብረዋል። መላዕክትም ምሥጋና፣ ከዋክብት ደግሞ ብርሃናቸውን። ሁሉም ያለውን አበርክቷል። ለዚህም ነው የስጦታ ወቅት የሚባለው።›› አሉ።

በገና ጨዋታ የለም ሌሉ ጌታ
‹በገና ጨዋታ የለም ሌሎ ጌታ
በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› ይህ አባባል በውስጡ ብዙ ሐሳቦች የተካተቱበት እንደሆነ መረዳት አያስቸግርም። የገና በዓል ከሃይማኖታዊ ትርጓሜ ባሻገር በማኅበራዊ ትስስር ላይ ሁሉም ሰው እኩል ሆኖ የሚደሰትበት ጌታ እና ሎሌ እኩል ሆነው የሚያሳልፉት እንደሆነ አመላካች ነው።

ከዚህ ጎን ለጎንም በዓሉ የአንድነት ጭምር ሲሆን በሰዎች ሁሉ ያለውን ልዩነት አጥፍቶ፤ በሠው እና በእግዚአብሔር የነበረውን ክፍፍል አስቀርቶ፣ ሰው እና መላዕክት በአንድነት የዘመሩበት ምንም አያውቁም የተባሉ እረኞች እንኳን ከጠቢባን ጋር በጋራ ምስጋናቸውን ያቀረቡበት እንደሆን ሊሂቃኑ ይጥቀሳሉ።

በሃይማኖታዊ ጉዳይ ያየን እንደሆነም ነገሩ ረቂቅ እንደሆነ ይነገራል። መምህር ደንኤል ሃይማኖታዊ ነገሩን እንዲህ በማለት ያስዳሉ፤ ‹‹የገና በዓል ዐብይ በዓል እንደመሆኑ የአምላክ ሰው መሆን የታየበት ነው። በዓለም ላይ የማይቻል ነው የተቻለው፣ የማይታይ ነው የታየው፣ የማይወሰነው ነው በእመቤታችን ማኅጸን የተወሰነው ይህ ሁሉ ረቂቅ ነው የሠውን ልጅ ፍልስፍና ሁሉ ያናጋ ሁኔታ ነው በማለት።

ከዚህ በተጨማሪም ለአዳም፣ ለአብርሃም፣ ለይስሃቅ፣ ለያዕቆብ እንዲሁም ለአባቶቻንን የተሰጣቸው ተስፋ የተፈጸመበት ነው። ሌላው ደግሞ በብሉይ ኪዳን የተሠሩት ሥርዓቶች ሁሉ የተፈጸመበት ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ የተነገሩ ትንቢቶች የተቆጠሩት ሱባኤዎች ሁሉ የተፈጸመብት ነው።

ይህንን ምክንያት በማድረግ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተለይም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ከአንድ ወር በላይ በመጾም፤ በዓሉንም በሥርዓተ አምልኮ፣ በማህበራዊ ተሳትፎና በአጠቃላይ ሁሉንም የሃይማኖት መገለጫዎች በሙሉ የሸፈነ በመሆኑም ሌሊት አባቶች በማህሌት በያሬዳዊ ዜማ ያከብሩታል። እንዲህ ባለ ክዋኔ በዓሉ ይከወናል በማለት መምህር ዳንኤል የበዓሉን አከባበርም ይጠቅሳሉ።

መልዕክት
የገና በዓል ሰው እና እግዚአብሔር የታረቁበት፤ ሰው እና መላዕክት ምስጋና ያቀረቡበት፣ ጠበብ እና ምንም የማያውቁ እረኞች በጋራ ስጦታ እና ምስጋና በማቅረብ እጅ መንሻ በመስጠት ረቂ የሆኑ ነገሮች የታዩብት እና የተስተዋለበት ጥልቅ ነገር እንደሆነም የሃይማኖቱ ሊቃውንት አስረድተዋል።

ከስጦታ መስጠት ባሻገርም የሰው ልጅ ሰው ሆኖ የከበረበት በዓል ሲሆን፣ እግዚአብሔር የነሳው ወይም የለበሰው ሥጋ የሰውን ልጅ ሥጋ እንጂ የአሜሪካዊ ወይም የራሺያዊ አይደለም። ስለሆነም እንግዚኢብሔር በሕዝባችን መካከል ያለው ክፍፍል አጥፍቶ አገራችንን ይጠብቅልን፤ አንድነታችንን ይጠብቅ፤ ደሃ የሚኖሩባት፣ ሽማግሌ የሚጦርባት፣ ህጻናት የሚያድጉባት አገር እንድትሆንልን እግዚአብሐየር ይፍቀድልን። መልካም በዓል ያሉን መምህር ዳንኤል ሰይሰ ሥላሴ ናቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com