የ‘ካፒቶል ሂል’ መወረር

Views: 134

‘ካፒቶል ሂል’ በዋሽንግተን ዲሲ ውሰጥ የሚገኝ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኝ ባለግርማ ሞገስ ታሪካዊ ሕንጻ ነው። ሕንጻው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤትን በቀኝ፣ የሕግ መምሪያውን ምክር ቤትን በግራ በኩል አቅፎ የሚገኝ ሲሆን በርካታ ቢሮዎችን በውስጡ አካትቷል።

ሰሞኑን የማይገመት፣ ፈጽሞ የማይታሰብ ጉዳይ የአሜካንን አንዳንዶች እንደሚሉት “ልቅ ዴሞክራሲ” ፈተና ላይ ጥሎታል የሚባል ክስተት ተፈጠረ። ሌሎች አሜሪካውያኑ ከኹለት መቶ ዓመታት በላይ እንዲህ ዓይነት ቅሌት አይተው አያውቁም ሲሉም የጉዳዩን ትልቅነት አበክረዋል። ይህ ፈጽሞ ያልተጠበቀ ክስተት የዓለምን ቀልብ ሰቅዞ ይዟል፤ መደበኛዎቹን የመገናኛ ብዙኀንንም ሆነ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮችን በከፍተኛ ሁኔታ ተሳታፊ እንዲሆኑ አደርጓቸዋል – የካፒቶል ሂል በፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራም ነውጠኛ ደጋፊዎች መወረር።

ጉዳዩ እንዲህ ነው። የአገሪቱ የሕዝብ እንደራሴዎች ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕን በማሸነፍ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት በመሆን የተመረጡትን በጆ ባይደን የምርጫ ውጤት ዙሪያ ተነጋገግሮ ለማጽደቅ ተሰብስበዋል። በድንገት በሺሕ የሚቆጠሩ ነውጠኛ ትራምፕ ደጋፊዎች ምክር ቤቱን ሰብረው ገቡ።

ትዕይንቱን ለማመን የተሳናቸው ታዋቂዎቹ የዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኀን የዕለቱን መርሃ ግብራቸውን በማጠፍ ነውጡን በቀጥታ አሰራጭተውታል። ይህ ያልተጠበቀ ክስተት በሚሆንበት ጊዜ ስብሰባ ላይ የነበሩ የሕዝብ እንደራሴዎች በፖሊስ ታጅበው ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል።

የምክር ቤቱን ወረራም ተከትሎ ፖሊስ እርምጃ የወሰደ ሲሆን በቀዳሚነት አንዲት ሴት በፖሊስ ተተኩሶባት እንደሞተች የተዘገበ ሲሆን ዘግይቶ ደግሞ ተጨማሪ ሦስት ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። በተቀሰቀሰው ግርግር ሳቢያ የዋሺንግተን ከንቲባ በከተማዋ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥለዋል። የካፒቶል ሂል አካባቢም ሙሉ በሙሉ ዝግ እንዲሆን ተደርጓል።

ከሞቱት በተጨማሪ እስካሁን ድረስ ከ50 በላይ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 47ቱ የተያዙት የተጣለውን የሰዓት እላፊ ገደብ በመጣሳቸው ነው ተብሏል። ከዚህ ባሻገር ቢያንስ 14 የሚደርሱ የፖሊስ አባላት ላይ የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከመካከላቸው ኹለቱ ሆስፒታል መግባታቸውም እንዲሁ ተዘግቧል።

ተሰናባቹ ፕሬዘዳንት ትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎቻቸው የአገሪቱን ምክር ቤት ከወረሩ በኋላ ከትዊተር እና ከፌስቡክ ታግደዋል። ይህ እርምጃ የተወሰደባቸው ደጋፊዎቻቸውን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠንካራ መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ በሚጠየቅበት ሰዓት “እወዳችኋለሁ” የሚል መልዕክት ከማስተላለፋቸው ባሻግር “ምርጫው ተጭበርብሯል” የሚለውን ያልተጨበጠ ክስም በማኅበራዊ ገፆቻቸው በማስተላለፋቸው ነው ሲሉ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

ትዊተር የተባለው የማኅበራዊ ገጽ ሦስት የትራምፕ መልዕክቶችን ከገጹ ላይ እንዲወገዱ አደርጓል፤ ከፖሊሲያችን ጋር የሚጻረሩ መልዕክቶች ናቸው ሲል ምክንያትነት አቅርቧል። ሌላው የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ፌስቡክ ትራምፕን ለ24 ሰዓታት ከገጹ እንዳገደ በገለጸበት መግለጫው፥ እየታየ ያለው ነውጥ ትራምፕ ማባባስ እንጂ ማብረድ ባለመቻላቸው እንደሆነ ምክንያቱን አስቀምጧል። ዩቲዩብ በበኩሉ የትራምፕን ቪዲዎች ከገጹ እንዲወርዱ ማድረጉም ታውቋል።

የትራምፕ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች መታገድ ብዙ አሜሪካኖችን አስደንግጧል፤ አንዳንድ ኢትዮጵያውያንን ደግሞ አስገርሟል። የማስደንገጡም ሆነ የማስረገሙ ጉዳይ የራሳቸው ሰብብ አላቸው።

እንደሚታወቀው ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ጉዳይ አሜሪካውያን የማይደራደሩበት ጉዳይ ነው። ሕገ መንግሥታቸውን መጀመሪያ ያሻሻሉትም በዚሁ ጉዳይ ላይ መሆኑ በታሪክ ተመዝግቧል። የመጀመሪያው ማሻሻያ ወይም እነሱ ‘ፈርስት አሜንድመት’ ብለው በሚጠሩት የታችኛው ምክር ቤት ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን የሚገድብ ሕግ ማውጣ እንደማይችል ደንግገዋ። አሜሪካውያኑን ያስደነገጣቸው የትራምፕ ከትዊተር፣ ፌስቡክ እና ዩቲዩብ የተጣለባቸው እገዳ ጉዳይ ነው።

“የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም” በሚለው ይትባህል መሰረት አሜሪካውያኖች ከኢትዮጵያውያን መማር አለባቸው ሲሉ በመሳለቅ ጭምር አንዳንዶች ሐሳባቸውን ከምር ይሁን ለቀልድ ባልለየ መልኩ አስቀምጠዋል። ምክንያታቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ እየደረሰ ያለው ተደጋጋሚ ውድመት፣ የሰው ልጆች ስቃይ፣ መፈናቀል፣ ስደት ብሎም ሞት የማኅበራዊ ትስስር መድረኮችን ዋናኛ ሰበብ አድርገው መከራከሪያዎቻቸው አድርገዋቸዋል፤ ገደብ ሊኖር ግድ ነው በሚል።

አሁን ፍጥጫው የሚኖረው ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ ነጻነት መከበር ቢኖርበትም ሕጋዊ ጥንቃቄ መኖሩን በሚደግፉት እና ምንም ዓይነት ገደብ መጣል የለበትም በሚሉት መካከል ነው። ይህ ተቃርኖ ባለበት ዓለም፥ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ ነጻነት በገደብ ወይስ ያለገደብ የሚሉት ጉዳዮች እያከራከሩ መቀጠላቸውን ብዙዎችን የሚያስማማ ይመስላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com