የገና በዓል በትግራይ ክልል

Views: 208

በመላው አለም በሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሀይማኖታዊና ትውፊታዊ ስነ ሥርዓታቸውን ጠብቀው በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ አንዱ ነው። በተለይም በአሜሪካና በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ውስጥ በአከባበር ስነስርዓቱ ጥቂት ልዩነት ቢኖረውም በዓሉን ከአዲስ ዘመን መባቻ ጋር በማያያዝ የተለያዩ የእንኳን አደረሳችሁ መልክቶችና ልዩ ልዩ ስጦታዎችን በመለዋወጥ በልዩ ሁኔታ ያከብሩታል። የገና በዓል
በአገራችን ኢትዮጵያም በክርስትና እምነት ተከታዮች፤ በይበልጥም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ዘንድ የገና በዓል አርባ አራት የጾም ቀናትን አሳልፈው የሚያከብሩት በዓል እንደመሆኑ በታላቅ ጉጉት የሚጠብቁትና በልዩ ድምቀት የሚያከብሩትም በዓል ነው።
ይኸው በዓል ታድያ በአገራችን በተለያዩ ክፍሎች በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ ክዋኔዎች ይከበራል። በአብዛኞቹም ቦታዎች ወጣቶች በጭፈራና ደስታ፣ በገና ጨዋታና ዝማሬ ሲያከብሩት፤ በከተሞች አካባቢም የተለያዩ የገና ዛፎችን በማዘጋጀትና በደማቅ መብራት እና ጌጣጌጦች በማሳመር፣ ስጦታዎችን በመለዋወጥ እንዲሁም ከወዳጅ ዘመድ ጋር እንኳን አደረሳችሁ በመባባልና በጋራ በመብላትና በመጠጣት በልዩ ሁኔታ ያከብሩታል።
በዘንድሮው የአገራችን የገና በዓል ታዲያ በአለም አቀፉ ኮሮና ወረርሺኝ እና በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ባሉ ሁከት እና ብጥብጦች ሳቢያ የቀደመውን ውበትና ድምቀቱን እንዲሁም ልዩ የሆነውን የአከባበር ስነ ስርዓቱን እንዳሳጣው ብዙዎች ይናገራሉ። አዲስ ማለዳም ከሌሎች አካባቢዎች ለየት ባለ መልኩ በትግራይ ክልል በመቐለ ከተማ የገና በዓል አከባበር ምን ይመስላል በማለት አጠር ያለ ዳሰሳን አድርጋለች።

ለወትሮው በዓል አይደለም የልጅን ልደት ለማክበር የትግራይ እናቶች ድል አድርጎ መደገስን ያውቁበታል። በተለይም ደግሞ በዓል እና አውዳመት የትጋሩን ቤት እና ደጅ መመልከት በእጅጉ የሚያስደስት በዓይን የሚበላ በአፍንቻ ሚማግ ሰፊ ድባብ ፍጹም አውድዓመት ጸጋ ነው። ለጭፈራው እና ለውቡ የባህል እንቅስቃሴውስ ተጋሩን ማን ብሎት። ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይጨፈራል፣ አውዳዓመት ይከበራል ፍቅርም ይፈሳል። በትግራይ ደስታ ይቀዳል፤ የጥቂት ምክንያ ድል ያለ ድግስን እና ፌስታን ለማድረግ የሚግደው ነገር የለም። ቤሻቸው ልጃገረዶች ብቻቸውን ተሰባስበው ይጨፍራሉ፣ ሲያሰኛው ኮበሌዎች ደስታቸውን ያስተጋባሉ ትግራይ የደስታ መንደር ተጋሩ የደስታ ሰዎች ናቸው።

እነሆ ታዲያ በሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች እና ደጋፊዎቻቸው በሆኑት የክልሉ ልዩ ኃይላት የተደረገው በመሰረተ ልማት ላይ የደረሰው ውድመት ክልሉን ለጽልመት እና ከግንኙነት ውጪ ማድረጉ የሚታወስ ነው። ይህ ታዲያ ለሳምንት ወይም ለቀናት አይደለም ከኹለት ወራት በላይ ሆኗል ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስም ክልሉ መናገሻ መቐለ ውጭ የስልክ ግንኙነት እና መደበኛ የየብስ መጓጓዣ አልተጀመረም። ይህ ብቻ ሳይሆን በክልሉ አሁንም ከመቐለ ውጭ ባንክ አገልግሎት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መቼ እንደሚከፈቱ ባይታወቅም በጉጉት የሚጠበቁ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ናቸው። በአንድም በሌላም ታዲያ አዲስ ማለዳ በቀደመው ዕትሟ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ለማስቃኘት ሞከረችበት አግባብ ቢኖርም በበዓላት ወቅትስ ትግራይን እንኳን አደረሰሽ፤ አውደዓመትስ እንዴት ይዞሻል ለማለትያህል ወደ መቐለ ስልኮችን በመደወል ያለውን ድባብ እና የሰውን እንቅስቃሴ ለመታዘብ ሞክረናል።

ለወትሮው ባንኮች በእጅጉ የሚጨናነቁበት ከአገር ቤትም ሆነ ከባህር ማዶ በርካታ ገንዘቦች ወደ ክልሉ የሚላኩበት፣ በችግር ምክንያት እንኳን ዕጅ አጥሯቸው አውደ አመትን ለማክበር ላይችሉ ይቀራሉ ተባሉ ግለሰቦች እንኳን ካላሰቡት ዘመድ ወይም የሩቅ ሰው በባንክ ገንዘብ ሚላክበትም አጋጣሚ ጥቂት እንዳልሆኑ ነው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ግለሰቦች ከመቐለ የሚናገሩት። አሁንስ ትግራይ ውስጥ ምን እየተደረገ ይሆን? የገበያው ሁኔታ ምን ይመስላል? ባንኮች፣ የስልክ ግንኙነት፣ የመጓጓዣ ጉዳይ እና መሰል ጉዳዮች ባልተሟሉበት ሁኔታ እንዴት ነው ‹‹አከባብራ በዓል ኣብ ትግራይ›› በትግራይ የበዓል አከባበር የሚሉ ርእሰ ጉዳዮችንም ለማንሳት ሞክረናል።

ይህ አጋጣሚ በእጅጉ የስነ ልቦና ችግር እና ድብርትን የፈጠረበት ሁኔታእንዳለም አዲስ ማለዳ በመሐል አገር ሚኖር አንድ ትግራይ ተወላጅን አግኝታ ለማነጋገር ባደረገችበት ወቅት ለማረዳት ችላለች። ምክንያቱ ደግሞ ለአዲስ ዓመት እና በትግራይ በተለይም ደግሞ በአዲግራት በሰፊው በሚከበረው የመስቀል በዓል ላይ ኮቪድ 19ኝ ፍራቻን ሳይታደም መቅረቱን እና ለገና በዓል አቅዶ የነበረው ወደ ቤተሰቦቹ የሚያደርገው ጉዞ ደግሞ በዚህ መጥፎ አጋጣሚ መስተጓጎሉ በእጅጉ እንደጎዳው ለአዲስ ማለዳ አስተያየቱን የሰጠው ግለሰብ ይናገራል።

ከረጅም ቀናት እርሱ እንደሚለው ከወር በላይ በትግራይ የሚኖሩ ቤተሰቦቹ ጋር ለመገናኘት ሳይችል ቀርቶ ከፍተኛ ችግር ጭንቀት ውስጥ ነበረው አዲስ ማለዳ እንግዳ በቅርቡ ድምጻቸውን ከመቐለ መስማቱ እንዳረጋጋው እና የአውሮፕላን ትኬት ቆርጦ ለመሔድ ቢያስብም የሚሆነው አይታወቅም እዚህ ደግሞ ሚስት እና ልጆች አሉኝ እነርሱን ይዤ ለመሔድ ነበር ሀሳቤ ነገር ግን አሁን ደግ ጥያቸው መሔድ አልፈልግም በሚል ሀሳቡን እየከበደውም ቢሆን የጉዞውን ጉዳይ እንዳስቀረው አስታውቋል።
ይህ ውዥንብር በክልሉ ውስጥ ያለው ነገር በአጭር ጊዜ ወደ ነበረበት ከተመለሰ እና ነገሮች በተረጋጉ ጊዜ ወደ ትግራይ ቤተሰቦቹን ይዞ በመሔድ ትግራይ ካሉ ቀሪ አዘመዶቹ ጋር የአዘቦት ቀንም ቢሆን ድል ባለ ድግስ ያለፉትን በዓላት ለማክበር እንዳቀደም ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

እኛም የሻተውን ፈጣሪ እንዲያሳካለት ምኞታችንን ለግሰነው ተሰነባበትን። እውነት ነው በትግራይ በኩል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ መሽቲ በነጋ ቁጥር መሻሻሎች እየታዩ ቢሆንም ነገር ግን አሁንም ድረስ ከመቐለ ውጪ ያሉ ከተሞች ከመሐል አገር ጋር ብቻ ሳይሆን በዛው በክልሉ ውስጥ ካሉ ከተሞች ጋርም የመገናኘት ችግር እንደተጋረጠባቸው በመሆኑ የበዓል ብቻ ሳይሆነ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ላይም ሳንካ እንደገጠማቸው ይታወቃል። ይህንንም በተመለከተ አዲስ ማለዳ በቀደመው ዕትሟ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በክልሉ ውስጥ ለማሳየት የስልክ ቆይታዎች አድርጋ ነበር። በእርግጥ መሻሻሎች ካለፈው ዕትም በኋላም መኖራቸውን አሁንም መረጃዎች እየወጡ ይገኛል።

በትግራይ ክልል በመንግስት እየተከናወነ ያለውን የህግ ማስከበር ሥራ ተጠናክሮ በቀጠለበትና ጊዜያዊ አስተዳደር የመመስረትና ክልሉን መልሶ የማደራጀት ሥራዎች እየተሰሩ ባሉበት በዚህ ወቅት በክልሉ ዳግም ሰላም እየተመለሰና በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎችም ወደ መደበኛ ህይወትና ሥራቸው እየተመለሱ እንደሚገኙ እየተገለፀ ይገኛል። የተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማትም እየተከፈቱና ነጋዴዎችም ወደ ቀደመው የገበያ ሥርዓት እየተመለሱ ውይይቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ስራ አስፈፃሚ ሙሉ ነጋ አስታውቀዋል።

ቢሆንም ግን አሁንም ቢሆን 4.5 ሚልየን የሚሆን የትግራይ ህዝብ አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልገው፤ እንዲሁም በመቐለ ከተማ ብቻ 350 ሺህ ሰው እገዛ እንደሚያስፈልገው እና ከመላው የትግራይ ክልሎች ተፈናቅለው መቐለ የገቡ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች መጠለያ እንደተሰጠ እና የተወሰነ እገዛም እየተደረገ መሆኑ የትግራይ ማህበራዊ ጉዳይ ሃላፊ አቶ አብርሃ ደስታ ከትግራይ ቴሌቭዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ መግለፃቸውም የሚታወስ ነው።

ሰላማዊት አሸናፊ (ሥሟ የተቀየረ) የ35 አመት ወይዘሮ ስትሆን የሁለት ልጆች እናት ናት። በመቐለ ከተማ በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥራ በመስራት ላይም ትገኛለች። በመቐለ ከተማ በህግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ በመቀጠሉና የመከላከያ ሰራዊት ወደ ከተማዋ ሙሉ ለሙሉ በመግባቱ አንፃራዊ ሰላም እና መረጋጋት እየታየ እንደሆነ ገልፃ እስከ ምሽት አስራ ኹለት ሰዓት ድረስ ብቻ ተጥሎ የነበረውም የእንቅስቃሴ ገደብም በአሁኑ ሰዓት እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ እንደተራዘመ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራት የስልክ ቆይታ ታስረዳለች።

ለወትሮውም በከተማዋ የገና በዓል እንደ ሌሎች የአገራችን ከተሞችን ያህል በድምቀት ባይከበርም፤ እንደ ቀድሞው ጊዜ በየጎዳናው አመት በዓልን ተገን አድርገው የሚዘወተሩ ገበያዎች እና ግርግሮች እንደማይታዩና የአመት በአል ስሜቱም ያን ያህል እንደሌለ በመግለፅ በአሁኑ ሰዓት በቀዳማዊ ወያኔና አዲ ሃቂ ገበያዎች ላይ ብቻ ማህበረሰቡ እየተገበያየ እንደሚገኝ ትገልፃለች።

በዛም ስላለው የገበያ ሁኔታ ስታስረዳ በአሁኑ ሰዓት ዶሮ እስከ አምስት መቶ ብር፣ በግ ከአንድ ሺህ ስምንት መቶ እስከ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልፃ፤ ጦርነቱ በታወጀበት የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በኪሎ እስከ ዘጠና ብር ይሸጥ የነበረው ቲማቲምም አሁን ቀንሶ በኪሎ ከአስር ብር እስከ 15 ብር ድረስ፣ በኪሎ እስከ ሃምሳ ብር ይሸጥ የነበረውም ሽንኩርት እስከ አስራ ስምንት ብር ድረስ ወርዶ እየተሸጠ እንደሚገኝ ትናገራለች።

በአሁኑ ሰዓት በመቐለ ከተማ አንድ ኩንታል ጤፍ ከአራት ሺህ ሶስት መቶ ብር እስከ አራት ሺህ ስምንት መቶ ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ የምትገልፀው ሰላማዊት ይህም በቀን ውስጥ አንዴ ወይ ሁለቴ የጭነት መኪናዎች ወደ ከተማዋ ገብተው ሲያራግፉ የሚገኝ እንደሆነም ገልፃለች።

ጎይቶም ገብረፃዲቅ (ሥሙ የተቀየረ) የ28 አመት ወጣት ሲሆን በመቐለ ከተማ በግል ሥራ ላይ ተሰማርቶ በመስራት ላይ ይገኛል። በመቐለ ከተማ ስላለው የገና በዓል አከባበር ሁኔታ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ ሲያስረዳ ከዚህ ቀደም እንደነበረው አይነት የአከባበር ስነስርዓትና የበዓል ስሜት በከተማዋ ላይ ሆነ በህዝቡ ላ እንብዛም እንደማይታይ ይናገራል።

አሁን ወቅት በክልሉ ባለው የአለመረጋጋት ሁኔታ ሳቢያ መንገድ ተመልሶ ሊዘጋ ይችላል፣ እቃዎችና ሸቀጣ ሸቀጦችም ዳግመኛ ላይገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት በህዝቡ ውስጥ ስላለ፤ ሁሉም ወጥቶ ባለው አቅም ሁሉ እየሸመተና ቀለብና ቁሳቁሶችን እያጠራቀመም እንደሚገን ያስረዳል።

መቐለ ከተማ ላይ ፍፁም የሆነ ሰላም እየሰፈነ እንደሚገኝ የሚናገረው ጎይቶም መከላከያ ሠራዊቱም ከህዝቡ ጋር ተላምዶ ከተማው ላይ አስቤዛውን እየሸመተ በጥሩ ሁኔታ ከህዝቡ ጋር በዓሉን እያከበረው እንደሚገኝም ይናገራል።

ከዚህ ቀደም በገና በዓል ወቅት በመቀሌ ከተማ በሚገኙ በአንዳንድ የገበያ ማእከሎችና ሱቆች ላይ የገና ዛፎች ተሰቅለው የበዓሉን መዳረስ በሚያስታውስ መልኩ ሞቅ ደመቅ ያለ እንቅስቃሴ ይታይ እንደነበር በማስታወስ በአሁኑ ወቅት ግን የልብስ ሱቆች፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃ መሸጫዎችና አንዳንድ የመዝናኛ ስፍራዎች እንደ ድሮው ባለ መኖራቸው በመዘጋታቸው የበዓሉን ድባቡ እንዳጠፉት ያስረዳል።

በከተማዋ በአሁኑ ሰዓት ክፍት የሆኑት የአገልግሎት መስጫዎች መሰረታዊ የሚባሉ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆችና ማከፋፈያዎች፣ ቡና ቤቶች፣ ምግብ እና መጠጥ ቤቶች እንደሆኑ የሚገልፀው ጎይቶም ማህበረሰቡ የሚያገኛቸውን መሰረታዊ ነገሮች ብቻ ተገበያይቶ በዓሉን እያሳለፈ እንደሚገኝም ተናግሯል።

በእቃዎች እና በሸቀጣ ሸቀጦች ላይ ከሚታየው የዋጋ ንረት ጋርም ተያይዞ ከዚህ ቀደም ወደከተማዋ የሚያስገቡ መንገዶች በመዘጋታቸው እቃዎች እንደልብ ይገቡ ስላልነበረ እንዲሁም ባንኮችም አገልግሎት መስተጠትን በማቆማቸው የገንዘብ ስለማይንቀሳቀስ ሁሉም ነገር ያለ ልክ ተወዶ ነበር። በአሁኑ ሰዓት ግን የተለያዩ ባንኮች በመከፈታቸውና ህዝቡም የመገበያያ ገንዘብ እያገኘ በመሆኑ፣ መንገዶች ተከፍተውም የተለያዩ እቃዎች ወደ ከተማዋ በመግባት ላይ ስለሚገኙ በገበያው ላይ መረጋጋቶች እየታዩ እንደሆነም ጎይቶም ይናገራል።

ድሮ ድሮ በአመት በዓሎች ሰዎች ወደዚህ ወደዚያ ሲሉ ሻጩ ሆነ ገዢውን በየመንገዱ ታይ ነበር። አሁን ግን ያ በጣም ቀንሷል የሚለው ጎይቶም ከመቀሌ ውጪ ባሉ ከተሞች የስልክም ሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ በትግራይ ክልል ካሉ ቤተሰቦች ጋር መገናኘትም አለመቻሉን በማስረዳት፤ የስልክ አገልግሎትም በመቐሌ ከተማ እስከ አጉላ እና አላማጣ ድረስ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፆ የኢንተርኔት አገልግሎት ግን እስከ አሁን አለመጀመሩን ገልጿል።

ሌላዋ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገችው ወጣት በድምፀ ወያኔ የቴሌቭዠን ጣቢያ በጋዜጠኝነት በመስራት ላይ የምትገኘው ሰናይት ተስፋዬ ናት። (ሥሟ ለደህንነቷ ሲባል ተቀይሯል)

እርሷም በሥራ ምክንያት በተለያዩ የመቐለ አካባቢዎች በመዘዋወር የገበያውንና የበዓሉን ድባብ ስትቃኝ እንደቆየች ገልፃ፤ የገና በዓል ድባብ ከድሮው በጣም የቀዘቀዠ እንደሆነና መቋለ ተወልዳ እንደ ማደጓም በህይወቷ እንደዚህ አይነት የአመት በዓል ድባብ ተመልክታ እንደማታውቅ ታስዳለች።

አስቤዛና ሌሎች አቅርቦቶች አሉ፤ ነገር ግን ሰዉ እንደ ድሮው አይደለም። ድሮ ድሮ የገና ዋዜማ ሲሆን በየመንገዱ የገበያ መብዛትና የሰዎች መጨናነቅ ይታይ ነበር፤ አሁን ግን ያ የለም የምትለው ሰናይት ብዙሃኑ የከተማው ባንኮች ቢከፈቱም አብዛኞቹ የከተማዋ ግለሰቦች የግል ሥራን የሚሰሩ በመሆናቸውና ላለፉት ኹለት ወራት ያለ ስራ በመቀመጣቸው፤ የሚገበያዩበት ገንዘብ እንደሌላቸው፤ ይህም የገበያውንና የበዓሉን ድባብ እንዲቀዘቅዝ ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ትናገራለች።

እርሷ በተገኘችባቸው በአዲ ሃቂ፣ ቀዳማይ ወያኔና፣ አዲ ሃውሲ ገበያዎች ሱቆች እንዳልተከፈቱና ነጋዴዎችም እቃቸውን ውጪ አውጥተው በመሸጥ ላይ እንደሚገኙ የምትገልፀው ሰናይት በገበያዎቹም ዶሮ ከአራት መቶ እስከ አምስት መቶ ብር፣ ሽንኩርት በኪሎ ከአስራ ሰባት ብር እስከ ኸያ አምስት ብር፣ ቲማቲም ከአስር ብር እስከ አስራ አምስት ብር፣ በርበሬ በኪሎ ከመቶ አርባ እስከ መቶ ሥልሳ ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልፃ፤ ከፍራፍሬዎችም ብርቱካን በኪሎ ሰማኒያ ብር፣ ሙዝ ደግሞ አርባ ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ታስረዳለች።

በተጨማሪም ፍርኖ ዱቄትና ጤፍ በመኪና መንገድ ላይ እየሸጡ እንደሚገኙ የምትናገረው ሰናይት ፍርኖ ዱቄት በኩንታል ሦስት ሺህ ብር፣ ጤፍ ደግሞ ከአራት ሺህ ኹለት መቶ ብር አንስቶ እስከ አራት ሺህ ስምንት መቶ ብር ድረስ እየተጠ እንደሚገኝ መታዘቧንም ለአዲስ ማለዳ ትገልፃለች።

‘’ፀጉር ቤት የለ! አሁን ሴቶች ፀጉራችንን ለበዓል መቆነን፣ መሰፋት እንፈልጋለን። ከሳምንት በፊት ነው ወረፋ ይዘን ለበዓል የምንጠብቀው የነበረው። አሁን ግን ይህን ማድረግ አልቻልንም፤ ፀጉር ቤቶች ሁሉ ዝግ ናቸው።’’ የምትለው ሰነናይት ልብስ እና ጫማ ለመገዛት እንኳን የተለያዩ ቡቲኮች በመዘጋታቸው ምክንያት መንገድ ላይ አንጥፈው የኮንትሮባንድ ልብስና ጫማዎችን ከሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ ለመግዛት እንደተገደዱ ትናገራለች።

ልብስ ቤት፣ ኮስሞቲክስ፣ ወርቅ ቤቶች፣ እንዲሁም የተለያዩ የንግድ ሱቆች በተከሰተው የፀጥታ ችግር እንዲሁም ታስረው የነበሩ ዘራፊዎችና ሌቦች በመፈታታቸውና እንደ ጉድ በከተማዋ ላይ በመበራከታቸው ምክንያት ‘’ማን ይጠብቀናል’’ በሚል ስጋት እንደማይከፍቱና አንዳንድ ነጋዴዎች ብቻ በድፍረት እየከፈቱ እንደሚገኙም ትናገራለች። ከዚህ በፊት ብዙ የገበያ ድንኳን እና ሱቆች ስለተሰረቁና ባዷቸውን ስለቀሩ፤ እንዲሁም ሌሎችም በመዘረፍ በስጋት እቃዎቻቸውን ሁሉ ወደየቤታቸው በመውሰዳቸው ምክንያት አብዛኞቹ የከተማዋ ሱቆች ዝግ መሆናቸውን ጨምራ ገልፃልናለች።

በመጨረሻም ከመቐለ ከተማ ያናገርናቸው ግለሰቦች በአንድነት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የመልካም ልደት በዓል ምኞታቸውን በማስተላለፍ ፈጣሪ ሰላሙን እንዲያመጣና እንደ ድሮው ተባብረን፣ ተሳስበን የምንኖርበትን ቀን እንድናይ አንድ ሆነን በጋራ እንፀልይ፤ ሰው እንደመሆናችን ፈጣሪን ከለመንነው ሁላችንንም ይቅር ይለናል። በማለት በመቐለ ከተማም ያሉ ሰው የለፋበትንና የደከመበትን ንብረትና ገንዘብ የሚቀሙ እና ለችግር የሚዳርጉ ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፤ ካልሆነም መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድባቸው ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com