የበዓል ግብይት በኮቪድ ጥላ ውስጥ

Views: 127

የኮረና ወረርሽኝ ወደ አገራችን ከገባ ማግስት ወዲህ ሥርጭቱን ለመግታተት ሲባል ከአራት በላይ አውደ-ርዕዮች ሳይካሄዱ ቀርተዋል።የበሽታው ሥርጭት ይበልጥ እየጨመረ በሄደበት እና የጽኑ ሕሙማን ቁጥር ከፍ እያለ ባለበት ሁኔታ በከተማችን አዲስ አበባ የገና በዓል ዓውደ-ርእዮች እየተከናወኑ ያገኛሉ።ሸማቹ ግብይቱን እንጂ ወረርሽኙን የዘነጋበትን የግብይት መድረኮች የመሰረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ በመቃኘት ዳዊት አስታጥቄ በሐተታ ዘ ማለዳ አቅርቦላችኋል።

የበዓል ግብይት በኮቪድ ጥላ ውስጥ
በአገራችን የኮሮና ቫይረስ በሽታ (ኮቪድ-19) ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ ስብሰባዎች፣አውደ-ርዕዮች ብሎም የሃይማኖት ተቋማት ሁሉ እስከ መዘጋት ደርሰዋል።በዚህም የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበሽታውን አስከፊነት በመረዳት በሽታው በሃገራችን እንዳይስፋፋና ጉዳት እንዳያደርስ የተሰራው ስራ ከፍተኛ አስተዋጽዎ አድርጓል።

በኮቪድ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ዝግ የነበሩት አውደ-ርዕዮች ነበሩ። ይህም በብዙ መልኩ የሸማች እና ሻጭን ሰንሰለት አቋርጦ ነበር።እንደ አገርም ተጽእኖው ከባድ ነበር።

እንደ አዲስ አበባ ቻምበር ንግድና ማህበራት ዘርፍ ጥናት መሠረት በአዲስ አበባ ከኮቪድ 19 በፊት በየአመቱ 24 የሚሆኑ አለም አቀፍ አውደ-ርዕዮች ታዘጋጅ እንደነበር አመላክጠቷል።

ኢትዮጵያም በወረርሽኙ የተነሳ ለበዓል ከሚዘጋጁ አውደ-ርዕይ ውጪ ከትላልቅ ስብሰባዎች፣ኮንፍረንሶች እና ሌሎች አውደ-ርዕዮች ታገኝ የነበረውን 300 ሚሊየን ዶላር ማጣቷን የአዲስ አበባ ቻምበር ንግድና ማህበራት ዘርፍ ባጠናው ጥናት ማረጋገጡን ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል።
በዚህ ዓመት የገና በዓል ግን የቀድሞውን ድባብ የመለሰ የሚመስል አውደ-ርዕዮች በመካሄድ ላይ ናቸው።

ከበዓል ጋር ትልቅ ቁርኝት ያለው የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ዘንድሮ ምንም ዓይነት ዝግጅት ባይከናወንም በጊዮን ሆቴል ግቢ፣በኦሮሞ ባህል ማዕከል፣ በመቻሬ ሜዳና በአነስተኛና ጥቃቅን በተደራጁ ነጋዴዎች ደግሞ የአዲስ አበባን አወራ ጎዳናዎች ያዘው፤ በፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ሜክሲኮ፣ እስታዲየምና የተለያዩ ቦታዎች ሻጭ እና ሸማችን ለማገናኘት ደፋ ቀና እያሉ ነው።

በእነዚህ አውደ -ርዕዮች በመሰረታዊነት የሚገኙት አልባሳት እና ሸቀጣ ሸቀጦች ሲሆኑ እንደ ጠጅ ያሉ ባሕላዊ መጠጥም በተለያየ መጠን ተዘጋጅቶ ለገበያ ቀርቧል።
አዲስ ማለዳ 4 ኪሎ ሚኒሊክ መሰናዶ ት/ቤት ፊት ለፊት በተዘጋጀው አውደ- ርዕይ ተገኝታ በቃኘችው መሠረት የአንድ ሊትር ጠጅ ዋጋ 160 ብር እየተሸጠ መሆኑን ተመልክተናል። በዚሁ አውደ-ርዕይ ቆዳ እና ባሕላዊ አልባሳት ያሉ ሲሆን የተለያዩ ጫማዎች እስከ 700 ብር፣ቀበቶ 100 ብር እና የተለያዩ መጠን ያላቸው ቦርሳዎች እስከ 400 ብር እየተሸጠ ይገኛል።

ከመሰረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦች ውጪ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን እና መሰል ቁሳቁሶችን ደግሞ የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ፣ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን ባዛሮች ክፍት ሆነዋል።

የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ባዛሮች ለሕዝብ ክፍት ቢደረጉም በእነዚህ የመገበያያ ቦታዎች ኮቪድ 19 እንዳይስፋፋ ሰዎች ከሰዎች ጋር ያላቸው ቅርርብ ከአንድ ሜትር በላይ መሆን እንዳለበት በሚመከርበት ወቅት እንደዚህ ዓይነት የግብይት መድረኮች አካባቢ ተጨማሪ የበሽታውን ሥርጭት ለመቆጣጠር እየተወሰዱ ያሉ ጥንቃቄዎች እጅግ ዝቅተኛ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ኢንስቲቲዩት ”እንድናገለግልዎ ማስክዎን ያድርጉ” NO MASK NO SERVICE በሚል መሪ ቃል የማስክ አጠቃቀም ዙሪያ አዲስ ጉዞ ይዞ ብቅ ብሏል።

በአዲሱ የአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር የዓለም አገራት ክትባት በመስጠት ላይ ቢሆኑም ክትባቱን ለሁሉም ዜጎች ማዳረስ ግን ትልቁ ፈተና እንደሆነ ይታወቃል ።ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ክትባት ማስገባት የሚያስችሉ የላቦራቶሪና ሌሎች ዝግጅቶችን ስታጠናቅቅ 20 በመቶ ዜጎቿ ላይ ክትባቱን እንደምትጀምር የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ክትባቱ መስጠት ሲጀመር ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎችና ዳር ድንበር የሚጠብቁ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ እንደሚያገኙም ተናግረዋል።
ክትባቱ የአገርን አቅም በእጅጉ የሚፈትነው ሲሆን ዜጎች ግን በተቻላቸው አቅም ራሳቸውን እንደሚጠብቁ ይመከራል።

በዓል ሲመጣ የበዓልን ድባብ ከሚፈጥሩት ጉዳዮች መኸል አንዱ የሆነው በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚከወኑ የበዓል ግብይቶች የሚከወኑባቸው አውደ- ርዕዮች ናቸው።ለበሽታውም ሥርጭት እንደዚህ ያሉ የግብይት መድረኮች ድርሻቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል። የበሽታውን ሥርጭት መግታት እና በጥንቃቄ ግብይት ማከናወን አዳጋች እንደሆነ ታዝበናል።

በእርግጥ በተለያዩ የአገሪቱ ቦታዎች ላይ ያሉ የጸጥታ ስጋቶች በአቅርቦት እና ፍላጎት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ አንዳለ ቢታመንም በከተማችን አዲስ አበባ የተለያዩ አውደ-ርእዮች ተዘጋጅተዋል።

በበዓል ወቅት በአብዛኛው የእንስሳት ተዋጽኦዎችን በብዛት መጠቀም የተለመደ ጉዳይ ነው ።ከእዚህ ውስጥ በግ፣ፍየል፣በሬ ፣የወተት ተዋጥኦዎች ያገኙበታል።
ኢትዮጵያውያን ለበዓል በብዛት የሚሰሩት የዶሮ ወጥ እንደመሆኑ ለግብአት የሚጠቀሟቸውን እንደ እንቁላል ያሉ ምርቶችን ስንመለከት በተለምዶው የፈረንጅ እንቁላል የምንለውን ጨምሮ 5 ብር የሃበሻ እንቁላል ደግሞ እስከ 6 ብር እንደሚሸጥ ታዝበናል።

አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በታዘበችው የሾላ ገበያ የአንድ ኪሎ ቅቤ ዋጋ ለለጋ ቅቤን ጨምሮ ከ320 እስከ 370 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል።
በተለመወዶው 02 ተብሎ በሚጠራው የአትክልት ገበያ የአንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩት ዋጋ 13 ብር እስከ 16 ብር እየተሸጠ ሲሆን ነጭ ሽንኩርት እስከ 60 ብር እየተሸጠ ተመልክተናል።

የቀንድ ከብት ገበያውን ስንመለከት ደግሞ የመጨረሻ ትልቅ የሚባለው ሰንጋ እስከ 35 ሺህ ብር እየተሸጠ እንደሆነ ታውቋል።ይህም አምና ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ብዙም ለውጥ እንደሌለው አዲስማለዳ ያነጋገረቻቸው ነጋዴዎች ነግረውናል።

አነስተኛ መጠን ያለው የሚባል በግ እስከ ሶስት ሺሕ ብር ሲሸጥ ትልቅ የሚባል ዓይነት ደግሞ እስከ 5 ሺሕ ብር እንደተሸጠ ለማወቅ ችለናል።የፍየልም ዋጋ ስንመለከት ከ4 ሺሕ ብር እስከ 7 ሺሕ ድረስ እየተሸጠ እንደሆነ አውቀናል።

ለበዓል ሥጋ መብላት ፈልጎ አቅሙ ለማይችል ሰው ደግሞ በአማራጭነት ስጋ በኪሎ መግዛት ቢፈልግ በሸማቾች ሱቅ በኩል ባሉ ሥጋ ቤቶች አንድ ኪሎ ሥጋ 180 እስከ 220 ብር ሲሸጥ በሌሎች ሥጋ ቤቶች እስከ 500 ብር እንደሚሸጥም አውቀናል፡

የዋጋ ቁጥጥር ነገር
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚፈጥሩ አስመጭና አከፋፋይ የንግድ ተቀማት ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል።ምን ያክል ተጽእኖ ያሳራል የሚለው አጠያያቂነቱ እንዳለ ሆኖ ማለታችን ነው።

ቢሮው ከተለያዩ የሸማችና የንግዱ ማህበረሰብ እየደረሰን ነው ባለው ጥቆማ መሰረት አስመጪና አከፋፋዮች የንግድ ተቀማት ምክኒያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በፈሳሽ ዘይት ምርት ላይ እያደረጉ እንደሚገኙ የደረሰውን ጥቆማ የሚከታተልና የሚያጣራ ግብረ ሀይል አሰማርቶ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
ማንኛውም አስመጭና አከፋፋይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እያደረገ መሆኑ ከተረጋገጠ አስፈላጊውን እርምጃ ቢሮ እንደሚወስድ ያስጠነቀቀ ሲሆን በተለይ ቀደም ብለው ከቀረጥ ነጻ ገብተው በመሸጥ ላይና በመጋዘን የተከማቹ የዘይት ምርቶች ላይ ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደማይቻልና አስታውቋል።

አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በቃኘችው የዘይት መሸጫ ሱቆች አንድ ሊትር ፈሳሽ እስከ 95 ብር እየተሸጠ መሆኑን እና ከበዓል በፊት ከነበረው ዋጋ እስከ 15 ብር ጭማሪ ማሳየቱን አውቀናል።

ዋሲሁን በላይ የኢኮኖሚ ባለሙያ ናቸው። ዋጋን መቆጣጠር ሕጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ባሻገር ማየት ተገቢ ነው ይላሉ።ሻጭ ለሚሸጠው ቁሳቁስም ሆነ አገልግሎት የመጨረሻውን ከፍተኛ የመሸጫ ዋጋ ጣሪያ የማስቀመጥ መብት እንዳለው ይታወቃል። ነገር ግን ገበያውን ለማረጋጋት እና ለሸማች ጥበቃ ለማድረግ በማሰብ በብዙ አገራት የተመረጡ ቁሳቁሶች የመሸጫ ዋጋ ጣሪያ የሚወሰነው በህግ ነው (ይህን የማድረግ ስልጣን የመንግስት ነው)።

ነገር ግን የኢኮኖሚስቶች ስጋት ዋጋን መቆጣጠር አልያም የዋጋ ጣሪያ ማስቀመጥ ለአጭር ግዜ ለችግሮች መፍትሄ ሲያመጣ ይችላል ነገር ግን ጥያቄው የዚህ አይነቱ ዋጋን የመቆጣጠር ዘዴ ለረጅም ግዜ እንዴት መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል የሚለው ጥያቄው ነው ይላሉ።

የዋጋ ጣሪያ ማስቀመጥ ሸማችን ከአደጋ የመከላከል ጥቅም ስላለው ጥሩ ቢሆንም ለተጨማሪ አደጋም ሊያጋልጣቸው ይችላል። የዋጋ ጣሪያ በማስቀመጥ አምራች እና ሻጭን ለመቆጣጠር መንግስት ለአምራች እና ሻጭ ድጎማ ማድረግ ግዴታው እንደሆነ ያነሳሉ።

መንግስት 5 ሊትር ዘይት 300 ብር እንድትሸጡ ብሎ የዋጋ ጣሪያ ያስቀመጠ ከሆነ አምራች አልያም ከውጪ አስመጪ እና ሻጭን ግብር በመቀነስ፤ ቀረጥ በመቀነስ፤ በውጪ ምንዛሬ ቅድሚያ በመስጠት፤ ብድር በማቅረብ፤ ወዘተ ካልደጎመ ከገበያ ለቀው በመውጣት ሸማቾች ጭራሽ የዘይት ምርቱን ከገበያ ሊያጡት እና ከፍተኛ የዋጋ ንረት ላይ እንዲወድቁ ሊያደርግ ይችላሉ። ምክንያቱም የዘይት ምርት መሻሻል በፍጥነት ሊያሳይ ስለማይችል ነው ይላል ዋሲሁን።

እንደ አርሳቸው እምነት አቅርቦት ላይ የሚፈጠርን ድክመት ሰፊ ከሆነ በገበያ ላይ መንግስት በሚያደርገው ቁጥጥር ለመፍታት መሞከር አዋጪ አካሄድ ነው ብዬ አላምንም ይላሉ።

ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ በሶስት አካባቢዎች የተገነቡ ዘመናዊ እና ሁለገብ የአትክልት ፣ የፍራፍሬ እና የሰብል ምርቶች መገበያያ ማዕከላት አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን የላፍቶ አትክልትና ፍሬፍሬ የገበያ ማዕከል ፣ ጀሞ ሁለገብ የገበያ ማዕከል እና ፉሪ ሁለገብ የሴቶች የገበያ ማዕከል ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል ።

ለአገልግሎት ክፍት በተደረጉ ማዕከላት የላፍቶ አትክልትና ፍራፍሬ 556፣የጀሞ ሁለገብ የገበያ ማዕከል 126 እና ፉሪ ሁለገብ የሴቶች የገበያ ማዕከል 298 በጠቅላላው 980 ሱቆችን ለምርት አቅርቦትና ፍላጎት መጣጣም ማዕከላቱ የበኩላቸውን አስተዋጾ ሊያበረክቱ የሚችሉ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታውቋል።
የገበያ ማእከላቱ ከከተማው መኸል ርቆ የተገነባ ቢሆን፣ለመገበያየት በቂ ስፍራ ያለው እንደሆነ ሸማቾች ያነሳሉ።በዋጋ ረገድየላፍቶ ገበያ ማእከልን ስንመለከት የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ በተለይ በዋዜማው እስከ 17 ብር ሲሸጥ ነጭ ሽንኩርት ደግሞ ሌሎች ገበያዎች ላይ እንዳሉት በተመሳሳይ በኪሎ 60 ብር እየተሸጠ ታዝበና።

በበዓል ወቅት ሰው ሰራሽ ጭማሪ ማድረግ የተለመደ ተግባር ነው። መንግሥትም እንደዚህ ዓይነት ተግባራትን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርግ ቢስተዋልም እምብኣማ ውጤታማ ሲሆን አይታይም።ይልቁንም አቅርቦትን በማሳደግ እና ሕብረተሰቡ በቀጥታ ከገበሬ ማሕበራት(ዩኒየኖች) እንዲያገኝ ማድረግ የተሻለ አማራጭ ነው።
ግብይቱ ሲታሰብ የኮረና ወረርሽኙ ጉዳይ እየተዘነጋ ስለሆነ በገበያ ቦታዎች አስተባባሪዎችን ወይም በጎ ፈቃደኞችን መመደብ በድምጽ ማጉያ ጭምር መልእክቶችን ማስተላለፍ ተገቢ ይሆን ነበር አንላላን።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com