በሰላሌ ዩንቨርሲቲ ሳይጠናቀቅ ከአራት ዓመት በላይ የሆነው ግንባታ ተገኘ

Views: 43

በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ጄኔራል ታደሰ ብሩ ግቢ ውስጥ የዩኒቨርስቲው ሁለገብ አዳራሽ ተጠናቆ ወደ ስራ መግባት ከነበረበት አራት ዓመታትን መቆየቱነተ የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣል ከፍተኛ የቁጥጥር ስራ እየሰራ እንሚገኝ በዚህም በቁጥጥር ስራው ወቅት የሰላሌ ዩንቨርሲቲ ውስጥ ግንባታው ተቋርጦ የቆየውን ሁለገብ አዳራሽ ቁጥጥር ሲያደርግ ማግኘቱን አስታውቋል። በዩንቨርሲቲው የሚገኘውን አዳራሽ ለመስራት ወደ 200 ሚሊዮን ብር በተገባ የኮንትራት ውል እንደነበርም የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሲሳይ ደርብ ተናግረዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ባለስልጣኑ በጅምር ላይ በሚገኙ እና መጠናቀቅ ባለባቸው ጊዜ ሳይጠናቀቁ አመታትን ያስቆጠሩ ግንባታዎች መኖራቸውን አስታውቋል
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ሲሳይ ደርብ እንደተናገሩት ተቆጣጣሪ ባለስልጣኑ የቁጥጥር ስራውን በተሳለጠ መልኩ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኮንስትራክሽን ቁጥጥር ከተቋቋመበት ዓላማዎች መካከል የኮንስትራክሽን ዘርፉን አፈፃፀሙ በብቃት፣ በምክንያታዊ ወጪ፣ በታሰበ ጊዜ በሚፈለገው የጥራት ደረጃ መተግበሩን እንዲሁም አገራዊ ፍላጎትን ማሟላት የሚያስችለውን አስተዋፅኦ በብቃት እየፈፀመ መሆኑን የማረጋገጥ ነው ብለዋል።

ይህንኑ መሰረት በማድረግ የተቋሙ የግንባታዎች ቁጥጥር ዘርፍ በመንገዶችና በሕንፃ ግንባታዎች ላይ ካካሄዳቸው በርካታ የቁጥጥር ተግባራት መካከል በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሰራው ሁለገብ አዳራሽ ግንባታው መጠናቀቅ በነበረበት ጊዜ ሳይጠናቀቅ አራት አመታት እንደቆየ ታውቋል ብለዋል።

ይህንን የመንግስትና የህዝብ ሃብት የፈሰሰበትን ግንባታ ስራ በታቀደለት ወቅት እንዳይጠናቀቁ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል በስራ ተቋራጩ እና በአማካሪ ድርጅቱ መካከል የነበሩ ውዝግቦች የፕሮጀክቱ እንቅፋት ሆነው መቆየታቸውም በቁጥጥር ወቅት ለማወቅ ተችሏል ብለዋል።

ሌላኛው ለፕሮጀክቱ መዘግየት ምክንያት የነበረው የግንባታ ፕሮጀክቶቹ ባለቤትነትን የተመለከቱ የሰነዶች ርክክብ በኹለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም በአዲ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በሰላሌ ዩኒቨርስቲ መካከል አለመደረጉ ነበር ብለዋል። ከዚህ ቀደም የሰላሌ ዩኒቨርስቲ ታደሰ ብሩ ግቢ በአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ ስር ይተዳደር እንደነበር ይታወቃል።

የኮንስትራክሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ይህንን ተቋርጦ የነበረውን ግንባታ የመንግስት እና የሕዝብ ሀብት በመሆኑ ግንባታውን ለማስቀጠል በማቀድ ስራ መጀመሩን አስታውቋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተጠናቆ እስኪያልቅ በተገቢው መልኩ በመቆጣጠር በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲጠናቀቅ አቅዶ እየሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።
ለዚህም ለግንባታው መጓተት ዋነኛው ምክንያት የነበረውን በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እና በሰላሌ ዩንቨርስቲ መካከል የነበረውን ችግር በመፍታት በኹለቱ አካላት መካከል የባለቤትነት ሰነድ ርክክቦሽ እንዲፈፀም ማድረጉን ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረትም ግንባታው የደረሰበት ደረጃ እና ቀሪ ስራዎች ተለይተው የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በባለቤትነት ግንባታውን ከፍፃሜ ማድረስ የሚያስችለውን ሕጋዊነትና አግባብነት ያላቸውን ሰነዶች ባሳለፍነው ሳምንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ርክክብ እንዲካሄድ መደረጉንም ነግረውናል።

በዚህም የኮንስትራክሽን ስራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ሙሉ በሙሉ ስራውን ወስዶ የሰላሌ ዩንቨርሲቲ እንዲሰራው ተስማምቷል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ስምንት የመንገድ ፕሮጀክቶች በደቡብ እና ኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ስድስት ነጥብ ሰባት ቢሊየን ብር የሚገመት ስራዎችንም ሳይጠናቀቁ ማግኘቱን አክለው ተናግረዋል።

የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 1097/ 2011 የተቋቋመ እንዲሁም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 439 / 2011 መሰረት የኮንስትራክሽን ስራዎችን እንዲቆጣጠር የተመሰረተ መንግስታዊ ተቋም ነው በዚህም በሚቀጥሉት አመታት የኮንስትራክሽን ስራዎች ላይ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ እየሰራን ነው በዚህም የተለያዩ የመንገድም ሆነ የሕንጻ ግንባታ እየተገኙ እንዳሉ አክለው ገልፀዋል።

የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የቁጥጥር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና የተሻለ የኮንስትራክሽን ስራ በአገራችን እንዲኖር ያደርጋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com