ኢትዮጵያ ከንግድ ዓውደ ርዕዮች በዓመት ታገኝ የነበረውን 2.9 ሚሊዮን ዶላር አጥታለች

Views: 103

ኢትዮጵያ በኮቪድ 19 ምክንያት ከአውደ ርዕዮች እና ከአለም አቀፍ የንግድ ባዛሮች ታገኘው የነበረውን 2.9 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ብር ማጣቷን የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ያስጠናው ጥናት ያመላክታል።

የጥናቱ አላማ የነበረው ኮቪድ 19 በዘርፉ ላይ ያደረሰውን ተፅዕኖ ለማሳየት እንደሆነም አዲስ ማለዳ ከንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአፍሪካን ትሬድ ሼር ፓርትነር ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና የጥናቱ ባለቤት አክሊለ በለጠ እንደተናገሩት ኮቪድ 19 በአለማችን ብሎም በአገራችን ሁሉም ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል።

በተለይም በከፍተኛ መልኩ የአገልግሎት ዘርፉን ሙሉ በሙሉ ጎድቶታል ብለዋል። ጥናቱ 12 የሚሆኑ ድርጅቶች መርጦ የተሰራ ሲሆን በአመት 24 የሚሆኑ ኤግዚቢሽኖችን ቢዘጋጁ በእንዳንዳቸው ኤግዚቢሽኖች 15 ተሳታፊዎች ቢሳተፉ አገራችን በትንሹ 2.9 ሚሊዮን ዶላር ታጣለች የሚል ግኝት ማመላከቱን ጠቅሰዋል።
በዋናነት ጥናቱ ትኩረት አድርጎ የሰራው በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድረው ዘርፍ ተኮር የንግድ አውደርይ ላይ እንደሆነም ተናግረዋል።

ከሚካሄዱት ኤክስፖዎች መካከል በአንድ አውደ ርዕይ ከ 200 እስከ 250 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የሚያስገኙ እንዳሉ በጥናቱ ተመላክቷል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከኮቪድ በፊትም ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ዘርፉ የአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለው ጠቅሰዋል።
ከሌሎች አገራት ተሞክሮ በመውሰድ ኮቪድ 19 እያለም ቢሆን ዘርፉ የሚሰራበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባዋል ብለዋል።

ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአለማችን መገኘቱን ተከትሎ በከፍተኛ መልኩ የሚተላለፍ እንዲሁም ገዳይ ስለሆነ በአለማችን የተለያዩ አገራት ከቤት እንዳይወጡ ተደርጎ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ቫይረሱ መምጣቱን ተከትሎ አለማችን ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳደሯል አገራችን ኢትዮጵያም በዚሁ ወረርሽኝ ከተጎዱ አገራት ምትጠቀስ ሲሆን ኮቪድ 19 ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል በዋናነት የንግዱን አለም ሲሆን በዋናነት በአገራችን ይዘጋጁ የነበሩ የአለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖች ስብሰባዎች ሙሉ በሙሉ ቆመው ቆይተዋል።

በአገራችን በአመት ወደ 83 የሚጠጉ የንግድ ኤግዚቢሽኞች እንደሚዘጋጁ ከእነሱም መካከል በሚኒሊየም አዳራሽ 50 በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ደግሞ ወደ 33 የሚጠጉ አውደ ርዕዮች እንደሚዘጋጅባቸው ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ንግድና አርፉ ማህበራት ምክር ቤት የንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አብርሀም ሀይለማርያም እንደተናገሩት የኮቪድ 19 መምጣት ዘርፉን ሙሉ ለሙሉ አስቁሞታል ብለዋል።

እንደ አዲስ አበባ ቻምበር ንግድ እና ዘርፍ ማሕበራት ምክር ቤት አራት የሚሆኑ አለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች እናዘጋጅ ነበር በዚህም ከ200 በላይ በንግድ ባዛር ላይ ይሳተፋሉ ነገር ግን በኮቪድ ምክንያት ተቋርጠዋል ብለዋል።

በአገራችን ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ የሚያሳድሩ የንግድ ኤግዚቢሽኖች የሚያዘጋጁ 700 የሚሆኑ አዘጋጆች እንዳሉ ከአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ኮቪድ 19 አብሮን የሚቆይ በሽታ ነው ስለዚህ ከኮቪድ ጋር እንዴት መስራት አለብን የሚለው ታውቆ መስራት እንጂ ኮቪድ እስኪወጣ መቀመጥ የለብንም ለዘርፉም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አክሊለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በቀጣይም ይህን የተዳከመውን ዘርፍ እንዲያንሰራራ እና የጉዳቱን መጠን ለመቀነስም ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራ እንደሚገባም ጥናቱ ምክረ ሀሳቡን አስቀምጧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com