የእለት ዜና

የሳተላይት ኢንደስትሪያል ፓርኮች ሊገነቡ ነው

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ከ50 በላይ የሳተላይት ኢንደስትሪያል ፓርኮች እንደምትገነባ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የሳተላይት ኢንደስትያል ፓርኮች ከኢንደስትሪያል ፓርኮች በቅርብ ርቀት የሚገነቡ እና በዋነኛነት ለኢንደስትሪያል ፓርኮቹ ጥሬ እቃ የሚያቀርቡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚሳተፉባቸው እንደሆኑ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ የሚገነቡት የኢንደስትሪያል ፓርኮች እስካሁን ይገነቡ ከነበሩት የሚለዩ እና በአራት ዓይነት ምድብ የሚከፈሉ እንደሆኑ አዲስ ማለዳ ያገኘችው ማስረጃ ያሳያል። ከእነዚህም መካከል አምስት የሎጅስቲክ አምስት ልዩ የኢኮኖሚ እና 25 እድገት ላይ ያተኮሩ እንዲሁም ከ50 በላይ የሳተላይት ኢንደስትሪያል ፓርኮች እንደሚገኙበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ኀላፊ የሆኑት ሳንዶካን ደበበ ገልጸዋል።

ኢንድስትያል ፓርኮች እንደዚህ ቀደሙ በክልል ኮታ ሳይሆን በጥናት እና ለምርት ግብዐት ጥሬ እቃ ባላቸው ቅርበት እንዲገነቡ ጥናት ተጠንቶ፤ ፓርኮች የት የት ቦታ መገንባት አለባቸው ፣ ሲገነቡ ምን ሊያሟሉ ይገባል ፣ ምን ሲሟላለት ነው ፓርክ የሚገነባው የት ወረዳ ፣ የት ቀበሌ እና ምን ያሟላ የሚለው እየተጠና እንዳለ እና አልቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ይጠበቃል ሲሉ ሳንዶካን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ግንባታቸው ተጠናቆ በሥራ ላይ የሚገኙ 12 ያህል የኢንደስትሪያል ፓርኮች እንደሚገኙ እንዲሁም ሊገነቡ ከታቀዱ ኢንደስትሪያል ፓርኮች መካከል ደግሞ በሶማሌ ክልል ሊገነባ እቅድ የተያዘለት የአይሻ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንዱ መሆኑን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

በቀጣይ 20 ዓመታት ከሚገነቡ የኢንደስትሪያል ፓርኮች መካከል ሰባት ያህሉም በሱማሌ ክልል እንደሚገነቡ በኢንደስትሪያል ፓርኮች ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያስረዳል። 13ኛው የኢንደስትሪ ፓርክ በአፋር ክልል በመገንባት ላይ እንደሚገኝ እና የግንባታው 70 በመቶ መጠናቀቁን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት እና የማርኬቲንግ ኃላፊ የሆኑት በኃይሉ ከበደ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በአፋር ክልል በሰመራ ከተማ የሚገኘው ይህ ፓርክ ጠቅላላ ስፋቱ በ2 ሺሕ ሄክታር ላይ የሚገኝ ሲሆን ፓርኩ ሲጠናቀቅ የሎጀስቲክ ፓርክ በመሆን ሌሎቹን ፓርኮች የማስተሳሰር ከፍተኛ አስተዋፅዎ እንደሚያበረክት እና ብዙ አምራጮች የያዘ ፓርክ እንደሆነ የሕዝብ ግንኙነት እና የማርኬቲንግ ኃላፊው አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ2004 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ተገንብተው በሥራ ላይ በሚገኙ 12 ያህል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በቀጥታ ከ74 ሺሕ በላይ እንዲሁም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ከ186 ሺሕ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረም አዲስ ማለዳ ከኢንደስትሪያል ፓርኮች ኮርፖሬሽን ያገኘችው መረጃ ያስረዳል።

ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ንግድ ከ46 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘቷን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ተናግረዋል። አክለውም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የአገሪቱን የኤክስፖርት በመጠንና በዓይነት ከማሳደግ ባሻገር በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ10 ሺሕ 800 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢንደስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ኢንድትሪያል ፓርኮችን ገንብቶ እና በውስጡ መካተት ያለባቸውን የባንክ የጉምሩክ እና ለሠራኞቹ አስፈላጊ የሆኑ የመገልገያ ስፍራዎችን ያሟላል። ከዚያም ለሦስተኛ ወገን በኪራይ የማስተላለፍ እና ከአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ በምርት ወቅት የቁሻሻ አወጋገድ እና ሌሎች ቁጥጥሮችን ላለፉት አምስት ዓመታት እያደረገ ይገኛል ሲሉ በኃይሉ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com