በከተሞች የሚገኙ ቤቶችን ሙሉ መረጃ የሚያቀርብ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊደረግ ነው

Views: 143

የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በአገራችን ያሉ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል ‹‹አዲስ ሶፍትዌር›› ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኀላፊ ታደሰ ከበበው ቴክኖሎጂ በከተሞች ያሉ ቤቶች ተመዝግበው ስለ ቤቶቹ ሙሉ መረጃ የሚገኝበት ሲሆን በ 2005 ጥናት ተጠንቶ እና አስፈላጊ መሆኑ ተረጋጦ የነበረ ቢሆንም ሳይተገበር ቀርቶ እንደገና በ 2012 ተጀምሮ ከአንድ ዓመት ከአራት ወር በኋላ አሁን ተጠናቆ ወደ ሙከራ ሥራ ገብቷል ብለዋል።

አዲሱ የመረጃ አያያዝ አስፈላጊ የሆነው በሦስት ምክንያቶች መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን ፤ አንደኛው የቤቶችን መረጃ ለመመዝገብ ማለትም መቼ እንደተሰሩ እና የሚሰጡት አገልግሎት ምንድነው የሚለውን ለማወቅ ሲሆን፤ ኹለተኛው ቤቶቹ የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎቶች ለማወቅ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ቤቶቹ የሚያስፈልጋቸው ጥገናና ሌሎች ነገሮች ለመለየት ይረዳል በተለይ ለመንግሥት ቤቶች። ሦስተኛው ለሪፖርት ማለትም የባለቤቶችን ማንነት በውስጡ የሚኖሩትን ሰዎች ብዛት ከእነርሱ መካከል ምንያህሎቹ ወንድ ምንያህሎቹ ሴት እንደሆኑ ለመለየት ይረዳል ሲሉ ገልጸዋል።

ሶፍትዌሩ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች የተሰራ ሲሆን 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገበት አዲስ ማለዳ ከሚኒስቴሩ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል። በአዲስ አበባ በተወሰኑ ወረዳዎች በሚገኙ የቀበሌ ቤቶች የመጀመርያ የሙከራ ሥራ እንደሚጀመርም ታውቋል። ሙሉ በሙሉ ሥራው ሲጠናቀቅ ደግሞ በአገራችን ባሉ ከተሞች ውስጥ ምን ያክል ቤቶች እንዳሉ ለማወቅ ይቻላል። ከቤቶቹ ምንያክሎቹ የመንግሥት ምንያክሎቹ የግለሰብ፣የጋራ መኖሪያ ቤት ፣የንግድ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት እንደተያዙ ለማወቅ እንደሚረዳም ታውቋል።

በከተማ የሚገኙ ቤቶችን መረጃ በቀላሉ ለማግኘት የሚረዳ አሰራር በብዙ አገራት የሚሰራ ሲሆን የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ግን ተሞክውን ከደቡብ ኮሪያ እንደወሰደ እና እርሳቸውም የደቡብ ኮሪያን ተሞክሮ እንዳዩ ታደሰ ገልጸዋል። በደቡብ ኮሪያ ያሉ ቤቶች የሚገኙበት ሥፍራ የተሰሩበት ጥሬ እቃ በውስጣቸው የሚኖሩ ነዋሪዎች እንዲሁም ቤቱ የሚሰጠው አገልግሎት ጭምር የመመዝገቢያ ቅጹ ውስጥ ይሞላል የእኛም አሠራር ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ነው ብለዋል።

ሶፍትዌሩ በአገር አቀፍ ደረጃ በከተማ ቤቶች መረጃ አያያዝ እና አስተዳደር ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የቤቶችን መረጃ ወጥ እና ተናባቢ በሆነ መንገድ ለመሰብሰብ ለማደራጀትና ለተጠቃሚዎች በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል። በተለይ ደግሞ የመንግሥት የሆኑ ቤቶች በመረጃ እጥረት ምክንያት በማን እንደተያዙ እና በምን አይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ስለማይታወቅ እንዲሁም ለተለያዩ ወንጀሎች እንዳይጋለጡ ለማድረግ ይረዳልም ተብሏል።

በሶፍትዌሩ ማንኛውም የከተማ ቤት በምዝገባ ውስጥ እንደሚገባ የገለጹት ቢሮ ኀላፊው ወደ ተግባር ሲገባ በከተማ ቤቶች ዙሪያ የሚስተዋለውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላት፣ ወጥ የሆነ የከተማ ቤቶች መረጃ አሰባሰብ ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ ለመተግበር፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የቤቶች ብዛት ለማወቅ፣ የከተማ ቤቶች መረጃ በቀላሉ ለአጥኚወች እና ለዉሳኔ ሰጭ አካላት ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የከተማ ቤቶች ፍላጎትና አቅርቦት በቀላሉ አውቆ ለማስተዳደር እንደሚረዳ ተናግረዋል።

አሠራሩ በአንድ ጊዜ ሁሉም ከተሞች ላይ ተግባራዊ ባይደረግም የመጀመርያው ሥራ ግን አዲስ አበባ ላይ ይጀመራል። በሁሉም ከተሞች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን እቅድ ታቅዶ ከሙከራ ትግበራው በኋላ የት የት ከተሞች ላይ እንደሚሠራ እና የሚሠራበት ጊዜ ቅደም ተከተል ይወሰናል።

የቢሮ ኀላፊው አክለውም በአዲስ አበባ ምዝገባው ሲካሄድ ኤምባሲዎች እንዲሁም የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ግልጋሎት የሚሰጡ ቤቶች ሁሉ በመመዝገቢያ ቅጹ ላይ ይመዘገባሉ ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com