የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በአምስት ወራት 1.1 ቢሊየን ዶላር ለመሳብ ችሏል

Views: 187

የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ በሦስት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ዘርፎች አንድ ነጥብ አንድ ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ኢንቨስት የሚያደርጉ የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ወደ አገር ውስጥ ገብተው በመሥራት ላይ እንደሆኑ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በማምረቻ ዘርፍ ፣ በግብርና እንዲሁም በአገልግሎት መስጠት በሦስት ዘርፎች ወደ አገር ውስጥ የገቡት ኢንቨስተሮች ከእስያ አገራት በብዛት ከቻይና ከህንድ ከአውሮፓ እንዲሁም ከሌሎች የአለማችን አገራት የተወጣጡ ባለሀብቶች መሆናቸውን እና በመጀመሪያው እንዲሁም በኹለተኛው ሩብ ዓመታት ለ 90 የውጭ አገር ባለሀብቶች ኢንቨስት የማድረግ እድሉ ታቅዶ ለ 72 ባለሀብቶች ፍቃድ መሰጠት ተችሏል በማለት የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኑነት ኃላፊ መኮንን ኃይሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ተገንብተው ያለቁ 12 ያህል የኢንደስትሪ ፓርኮች መኖራቸው እንዲሁም በቅረቡ የተሻሻለው የኢንቨስትመንት ሕግ እና በቅርቡ የፀደቀው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ኢንቨስተሮችን የበለጠ ለመሳብ ረድቶናል ብለዋል።

በተሻሻለው የኢንቨስትመንት ሕግ መሰረት በመንግሥት የሚተዳደሩ እንደ ኢቲዮ ቴሌኮም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢንደስትሪያል ፓርኮችን ወደ ግል ይዞታ ማዘዋወር (ፕራይቬታይዝድ) ማድረግ እንደሚቻል አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገው ድርድር እና አዲስ የንግድ ፖሊሲ ማውጣቷ እንዲሁም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሀብቶች ምቹ አጋጣሚ መሆኑን ነው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኑነት ኃላፊው ያስታወቁት። የትኞቹም የውጭ አገር ባለሀብቶች የሚያመርተው ምርት ከአገር ውስጥ ገበያ በተጨማሪ በአፍሪካ ደረጃ እንዲያቀርቡ እድል ይሰጣቸዋል ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት አርብ ታህሳስ 23/ 2013 ወደ ትግበራ እንደገባ ይፋ የተደረገው እና ተግባራዊ መሆን የጀመረው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምነት ለኢትዮጵያውያ አምራቾች እና ላኪዎች ሰፊና የተረጋገጠ ገበያ ይፈጥራል ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ ማሞ ምህረቱ ከአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ መናገራቸው ይታወሳል።

የአፍሪካ አገራት መሪዎች አህጉሪቱ ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ እንድትገባ ስምምነት ላይ የደረሱት እንደ አውሮፓዊያን የዘመን አቆጣጠር ጥር 29 2012 18ኛውን የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ባካሄዱበት ወቅት እንደነበር አዲስ ማለዳ ያገኘችው ማስረጃ ያመላክታል።

የቴክኖሎጅ ሽግግር በማድረግ እና ከግብርና ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በሚደረገው ሽግግር ላይ የውጭ ኢንቨስተሮች በሰፊው ወደ አገር ውስጥ መግባት ትልቁን ድርሻ እንደሚወጣ መኮንን ገልጸዋል። በቅርብ ጊዜ የወጣ ሪፖርት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ውስጥ ሆነን እንኳን ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት በንግድ እንቅስቃሴ ቀዳሚ መሆኗን ከአፍሪካ አገርት ደግሞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች በማለት ገልጸዋል።

ኢንቨስተሮቹ ወደ አገር ውስጥ ገብተው ለመስራት የሚከተሏቸው የቅድመ ትግበራ ምዕራፎች መኖራቸውን መኮንን አስታውቀዋል። የመጀመሪያው ምዕራፍ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማውጣት እንደሆነ እና ይህንን የወረቀት ሥራ የሆነውን የመጀመሪያ ተግባር ካሳኩ በኋላ ቦታ አግኝተው ግንባታ ሲጀምሩ ደግሞ ኹለተኛውን ምዕራፍ ይጨርሳሉ ብለዋል። ሦስተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ ማምረት ወይንም አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት ወደ አገር ውስጥ ገብተው በሦስት ዘርፎች በማምረት በግብርና እንዲሁም አገልግሎት በመስጠት አንድ ነጥብ አንድ ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር መዋለ ነዋይ ካፈሰሱ ባለሀብቶች መካከል በአገልግሎት ዘርፍ የተመዘገቡት ፈቃድ ወስደው ወደ ቅድመ ትግበራ ሥራ ገብተዋል ሲሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አስታውቀዋል። አገልግሎት በመስጠት ዘርፍ ስንል የትምሕርት የጤና እና የሙያ ማማከር ሥራዎችን በውስጡ አካቷል በማለት ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com