እምቦጭን ለማጥፋት ቃል ከተገባው ከግማሽ በታች ብቻ ተሰብስቧል

Views: 188

ከጥቅምት ዘጠኝ 2013 እስከ ሕዳር ዘጠኝ 2103 ለአንድ ወር ያክል በጣና ሐይቅ ተንሰራፍቶ የነበረውን የእምቦጭ አረም ለመንቀል ለተደረገው ዘመቻ ማስፈጸሚያ የሚውል ቃል የተገባው 95 ሚሊዮን ብር ቢሆንም 44 ሚሊዮን ብር ብቻ ገቢ እንደተደረገ አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

እምቦጭን ከጣና ሐይቅ ላይ የሰው ኃይልን ተጠቅሞ ለማስወገድ በተደረገው የአንድ ወር ዘመቻ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት እንዲሁም ከክልል መንግሥታት ቃል የተገባው ገንዘብ ከግማሽ በታች ወደ አካውንት ገቢ መደረጉን ፤ 95 ሚሊየን ብር ቃል ተገብቶ 44 ሚሊዮኑ ብቻ ገቢ እንደተደረገ የጣና ሐይቅ እና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጂ የሆኑት አያሌው ዘውዴ(ዶ/ር) አስታውቀዋል።

አያሌው (ዶ/ር) ጣና ሐይቅን የሸፈነውን የእምቦጭ አረም ለመንቀል በተካሄደው ዘመቻ በሰው ኃይል በኩል ሙሉ በሙሉ ተሳክቶ 85 በመቶ የሚሆነውን አረም መንቀል እንደተቻለ አረጋግጠዋል። አሁንም ግን የማገላበጥ፣ የማጓጓዝ ፣የማቃጠል እንዲሁም አልፎ አልፎ የቀሩ አረሞችን የመንቀል ሥራ ይቀራል ብለዋል። በተለይ ደግሞ አረሙ ተነቅሎ መወገድ ባለበት መንገድ መወገድ ካልቻለ አሁንም ድካሙን ከንቱ እንደማድረግ ነው ምክንያቱም እንደገና የመብቀል እድል ያገኛል በማለት ገልጸዋል።

መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ ዘመቻውን አሥጀምሯል ነገር ግን ጣና የሁሉም ሀብት በመሆኑ ጣና ጣና የሚል ሁሉ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። በተለይ ደግሞ ለዘመቻው ቃል የተገባው ገንዘብ ገብቶ ዘመቻው ላይ ተሳታፊ ለነበሩ አርሶ አደሮች ያልተከፈለ ከ 20 እስከ 30 ሚሊየን ብር የሚደርስ ክፍያ ባለመከፈሉ አርሶ አደሮቹ ቅሬታ አሰምተዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስኪያጂ እምቦጭን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማወገድ በተደረገው ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ ከተለያየ ሥፍራ የሚመጡ ሰዎች እንዳሉ ተናግረው በአካባቢው የሰው ኀይል ችግር ስለሌለ ተሰባስበው ከመምጣት ይልቅ ያወጡትን የትራንስፖርት ወጭ ቢልኩ የተሻለ ነው ብለዋል።

ለተለያዩ ተግባራት ባለሀብቶችን እርዳታ እንዲያደርጉ መጠየቅ የተለመደ በመሆኑ እምቦጭን ለመንቀል በተደረገ ዘመቻ ወቅት ባለሀብቶችን ከመጠየቅ እንደተቆጠቡ ነገርግን ጣና በቱሪዝም ሀብቱም ሆነ በኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭነቱ እንዲሁም ለአካባቢ ሥነምህዳር መጠበቅ አስፈላጊ በመሆኑ የአንድ ወገን ብቻ ኀላፊነት አይደለም ሲሉ ተናግተዋል።

አክለውም ገንዘቡ ቃል በተገባው መጠን ገቢ ያልተደረገው ቃል የገቡ ክልሎች እንዲሁም ተቋማት ቁርጠኝነት ወስደው ቃላቸውን ባለመጠበቃቸው እና አስተባባሪ ኮሚቴዎች ባግባቡ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው እንደሆነ አያሌው (ዶ/ር) ገልጸዋል። ሥራው በየቀኑ ማስታወስ እና መወትወት ይጠይቃል ብለዋል።
የጣና ሐይቅ እምቦጭ በሚባል በመጤ አረም መወረሩ ከታወቀ ዘጠኝ ዓመታት አልፈዋል። በሐይቁ ዙሪያ በሦስት ዞኖች የሚገኙ 30 ቀበሌዎች እንዲሁም አንድ የከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ከ4300 ሄክታር በላይ የሚሆነው የሐይቁ አካል በእምቦጭ መወረሩ የሚታወስ ነው።

ጣናን ከእምቦጭ አረም ነፃ ለማውጣት ከጥቅምት ዘጠኝ እስከ ህዳር ዘጠኝ በተደረገው የአንድ ወር ዘመቻ 90 በመቶ የሚሆነውን የእምቦጭ አረም ከሐይቁ ላይ ለመንቀል ታቅዶ በአንድ ወሩ ዘመቻ 85 በመቶውን መንቀል ተችሏል። ቀሪው ሦስት እና አራት ቀበሌዎች አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ከሐይቁ ጥልቀት የተነሳ መነቀል እንዳልተቻለ አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

በዘመቻው 360 ሽሕ ሰዎች ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ ግለሰቦች የተቋማት ሠራተኞች በጎ ፈቃደኞች የጉልበት ሠራተኞች እና ሌሎችም እንደሚሰተፉ ተገምቶ እንደነበር አያሌው (ዶ/ር) አስታሰው ከእነዚህ ሰዎች መካከል ደግሞ በቀን 12 ሺሕ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እስከ 18 ሺሕ ሰዎች ተሳትፈዋል በዚህ ረገድ ስኬታማ ነበርን ሲሉ ተናረዋል።

ለዘመቻው ማስፈጸሚያ ከፌዴራል መንግስት ከገንዘብ ሚኒስተር ከሁሉም የክልል መንግስታት ከፌድራል ተቋማት ከሚንስትር መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ከዲያስፖራ ትረስት ፈንድ እና ከልማት ተቋማት ቃል የተገባ ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደተያዘ አዲስ ማለዳ ያገኘችው ማስረጃ ያሳያል።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com