በአዳማ የተመረጡ ነጋዴዎች ቫት አልተጠቀማችሁም በሚል ያለአግባብ ቅጣት እንዲከፍሉ መገደዳቸውን አስታወቁ

Views: 216

በአዳማ ከተማ የሚገኙ በተለያየ ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ የተመረጡ ነጋዴዎች ተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) እየተጠቀማችሁ አይደለም በሚል ያለ ምንም ማስረጃ ከ50 ሺሕ ብር ጀምሮ እስከ 100 ሺሕ ብር ድረስ ቅጣት እንዲከፍሉ መደረጋቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ። ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ያሰሙት ነጋዴዎች እንደሚናገሩት ቅጣቱን መክፈል እንዳለባቸው የሚያሳይ የቅጣት ደብዳቤ እየተሰጣቸው እንደሆነ እና ከህግ አግባብ ውጪ እጅ ከፍንጅም ሆነ ያለ ቫት ስንሸጥ ሳንገኝ በየሱቃችን እየመጡ ቫት እንደማትጠቀሙ ታውቋል በሚል ከ 50 ሺሕ ብር ጀምሮ 100 ሺሕ ብር ድረስ ቅጣት ክፈሉ በሚል አስገዳጅ ሁኔታ ላይ እንዳሉ አስታውቀዋል።

ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ያሰሙት ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የሕንፃ መሳሪያ መደብር ባለቤት እንደተናገሩት ቫት ሳትቆርጡ ሸጣችኋል በሚል የ50 ሺሕ ብር ቅጣት እንዲከፍሉ ያሚያስገድድ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ተናግረዋል።

እንደ ነጋዴው ገለፃ ያለ ቫት ሰርተው እንደማያውቁ እና እጅ ከፍንጅም ሳይዧቸው ከገቢዎች ነው የመጣነው የሚሉ ሰዎች ወደ ሱቃቸው መጥተው ያለ ቫት እንደማትሰሩ በተደረገ አሰሳ ታውቋል ይሕንን ቅጣት ክፈሉ በሚል ደብዳቤ ሰጥተዋቸው እንደሄዱ ተናግረዋል።

መቼ ነው አሰሳ የተደረገው ምን እቃስ ያለ ቫት ስሸጥ ተገኘሁ ብለን ስንጠይቃቸው ምንም አይነት ምላሽ አይሰጡንም እኛን አትጠይቁን የበላይ ትእዛዝ ነው እያሉን ይሄዳሉ ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ገልጸዋል።

የበላይ አካል ጋር ተሰብስበን ስንሄድ ደግሞ ማንም ብሶታችንን የሚያደምጠንም ሆነ መፍትሔ የሚሰጠን አካል ማግኘት አልቻልንም እንዲያውም ያመናጭቁናል ይሰድቡናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

50ሺሕ ብር የማያገኝ ነጋዴ ሳይቀር 50ሺሕ ብር ክፈሉ እየተባሉ እንዳሉ የተናገሩት ነጋዴው እየደረሰብን ያለው ነገር በጣም የሚያሳፍር ነው ሰው በአገሩ ሰርቶ መኖር አልቻለም ብለዋል።

ሌላኛው ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን የተናገሩት ነጋዴ እንዳሉት በአዳማ ከተማ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው መስራት ከጀመሩ 15 አመታትን እንዳስቆጠሩ እና እንደዚህ አይነት ሁኔታ ግን ሲገጥማቸው ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ከዚህ ቀደም እንደዚ አይነት አሰራር አጋጥሟቸው እንደማያውቅ ተናግረዋል።
አንድ ሰው ያለ ቫት ሲሰራ ሳይያዝ ያለ ቫት እንደምትሰራ ታውቋል በሚል ቅጣት ክፈል የሚል ደብዳቤ እየደረሳቸው እንዳለ ይህ ደግሞ አግባብነት የለውም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

እንደ ነጋዴዎቹ ገለፃ ከ600 በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎች ላይ በየሱቃቸው በመሄድ የቅጣት ደብዳቤዎቹን እየሰጧቸው እንዳሉ ተናግረዋል።
ለምን እንደሆነ ስንጠይቅ የበላይ ትዛዝ ነው እየተባልን ነው ያለነው ያሉት ነጋዴዎቹ የበላይ አመራሮች ጋር ቀርበን ለማውራት ሞክረናል ግን የሚሰማን አካል አላገኘንም ብለዋል።

ቅጣት የተጣለባቸው ነጋዴዎችም አንከፍልም ብለው እየተከራከሩ እንዳሉ እና የሚመለከተው አካል ችግራቸውን ተመልክቶ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው የአዳማ ከተማ የገቢዎች ኃላፊ ጌትነት ለገሰ እንደተናገሩት አዳማ ከተማ ላይ እየተደረገ ያለው ሕግ የማስከበር ስራ ነው ብለዋል።
ማንኛውም ነጋዴ ያለ ቫት ሽያጭ ሲያከናውን መቀጣት እንዳለበት በሕጉ ተቀምጧል በዚህም ባለሙያዎች አዘጋጅተን ማሽኖቻቸው ላይ ማጣሪያ ተደርጎባቸው ያለ ቫት እንደሚጠቀሙ ስለታወቀ ነው የቅጣት ወረቀቱን እየሰጠን ያለነው ብለዋል።

አሁን በሕመም ምክንያት እረፍት ላይ እንደሆኑ የተናገሩት ኃላፊው ያለአግባብ ነው ቅጣት የተጣለብኝ የሚል ቅሬታ ያለው ነጋዴ እኔን ሊያነጋግረኝ ይችላል ብለዋል።
ሕግ መከበር አለበት ስለዚህ አሁንም የሕግ ማስከበር ስራውን አጠናክረን እንቀጥልበታለን ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com