ኮቪድ 19 እና የፎቶግራፍ ጥበብ

Views: 341

የተወለደው አዲስ አበባ ካሳንችስ አካባቢ ነው። ከጅማ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ድግሪው ማግኘት ችሏል። በአሁን ወቅት ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ኹለተኛ ድግሪው ለማግኘት በመማር ላይ ይገኛል። ባሳለፈውነ ሳምንት ደግሞ ማስተር ካርድ ፋውዴሽን ከቦቢ ፓውል ፎቶግራፊ ባዘጋጀው ‹አፍሪካን ኢን ኮንቴክስት› ተብሎ በተሰየመው የፎቶግራፍ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ ማሸነፍ ችሏል – ይሥሐቅ ልሳነ ክርስቶስ።

ወደ ፎቶ ግራፍ እንዴት?
ከጅማ ዩኒቨርስቲ ‹በኢኮኖሚክስ› ከተመረቀ አራት ዓመታትን ያስቆጥረው ይሥሐቅ በቪዲዮግራፊ፣በዳይሬክቲንግ ወይም ደግሞ በፎቶግራፍ ለመሰማራት ፍላጎት እና እቅድ ነበረው። ድንገት የጀመረው የፎቶግራፍ ሥራው ግን ከመውደዱ በተጨማሪም ወደፊትም ደስተኛ ሆኖ እንደሚሰራበት በማመንም የትኞቹንም ትምህርት ቤቶች ደጅ ሳይረግጥ በኢነተርኔት በሚሰጡ የቀጥታ ትምህርቶችን በመከታተል ራሱን አስተማረ።

ታሪካዊ እና ዶክመንታሪ (ዘጋቢ ) ፎቶዎችን ማንሳት አብዝቶ የሚወደው ይስሐቅ ለወደፊት ብዙ ዓላማ አለውና ራሱን ከማስተመር አልፎ ተርፎም ራሱን ለውድድርም ማዘጋጀት ጀመረ።

ታዲያ እዚህ ጋር ለይስሐቅ አንድ አጋጣሚ ተፈጠረለት እሱም በአፍሪካ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የአዲስ ፎቶ ፌስት ወድድር ሲሆን ያነሳቸውን ፎቶዎች ላከ ፎቶዎቹም ተመረጠለት። በምላሹም ለእሱ እና መሰል ተወዳዳሪዎች የስልጠና ዕድል ተመቻቸላቸው።

‹‹በስልጠናው ላይም በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የፎቶ ግራፍ ፕሮጀክት እንዴት እንደሚሰራ ተምሬያለሁ። የተሻለ ትምህርት ለመጀመሪያ ጊዜ ወስጃለሁ›› ነው ያለው ወጣቱ የፎቶግራፍ ባለሙያ ይስሐቅ ለአዲስ ማለዳ ሲያስረዳ።

ስለ ሽልማቱ
ከወራት በፊትም ማስትካርድ ፋውንዴሽን እና ቦይፖል በጋራ በመተባበር አንድ የፎግራፍ ውድድር አዘጋጁ። ኹለቱ ተቋማት ያዘጋጁት ውድድር አፍሪካ የኮቪድ19 ወረርሽኝ (ኮሮናን) እንዴት በጥንቃቄ እንዳሳፈቸ የሚያሳይ ፎቶግራፍ ማወዳደር ነበር ።ይህ ውድድር ራሱን በራሱ ለማስተማር ሲጥር እና ሲሞክር ለነበረው ይስሐቅ አንዳች እንድልን ይዞለት የመጣ ይመስላል።

አሁን አሁን እንዲህ ዓይነት ማስታወቂያዎች ነገሬ ብሎ የሚመለከት እና የሚከታተል ካለም በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት የመታየታቸው ዕድል ሰፊ ነው። ዕድል ወደ ይስሐቅ በጣም እየቀረበችም ይመስላል። ከማኀበራዊ ትስስር ገጾች አንዱ በሆነው ኢንስታግራም ይህን ማስታወቂያ ተመለከተች ተመልክታም ዝም አላለችም እንዲወዳደርም ነገረቸው እንጂ -የይስሃቅ ጓደኛ ቢታንያ።

ይህን መልዕክት የደረሰው ይስሐቅ ቀድሞ ተዘጋጅቶበት የነበረውን ሥራውን መላክም ቻለ። ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ እየተካሄደ በጥንቃቄ እዴት እንዳሰለፈወችው በቦሌ መድሃኒዓም ቤተ ክርስትያን በመገኘት እንዴት እንዳሰለፈች የሚያሳ ፕሮጀክት መስራቴን የምታውቀው ቢታኒያ በላከችልኝ ሊንክ (ማስፈንጠሪያ) ያሉኝን መረጃዎች ላኩኝ በኋላም ከኢትዮጵያ እኔ አሸንፌያለሁ ›› ሲልም ለአዲስ ማለዳ የተወዳደረበትን መንገድ አስታውሷል።
ይስሐቅ ለመወዳደር ከቀረቡት መስፈርቶች መካከል ሲያስታውስ ‹‹ፎቶ ግራፎቹ ጥሩ ታሪክ የሚናገሩ መሆን አለባቸው ሥላለው ሁኔታ መግለጽ የሚችሉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ሙያዊ መስፈርቶቹን ጨምሮ ከጥራቱ ባሻገርም አፍሪካ ኮቪድን እንዴት እንዳሳለፈች የሚገልፅ መሆን ነበረበት።››

እዚህ ወድድር ላይ ኹለት ፎቶግራፎችን መላክ ይጠበቃል። ይስሐቅ ወደ ስድስት ወራት ገደማ በኮቪድ ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት ያዘጋጀ ሲሆን በዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያ እንዴት ኮቪድን አሳልፋለች የሚለውን ለማሳየት ከሁለት ሺ በላይ ፎቶዎች በማንሳት በአዲስ ፎቶ ፌስት ለማሳየት እንዲሁም ለመማሪያ የተነሱ ነበር።

እንዲህ ዓይነቶቹ ሽልማቶች ከገንዘብ በተጨማሪም ሥራዎች ተቀባይነት እንዲያገኙ እና የተሰሩ ሥራዎችን በማስተዋወቅ በኩል እንዲሁም ለሌላ ሥራም ይሁን ውድድር ጉልበት አቅምም ይፈጥራሉ። ‹‹ሽልማቱ ለእኔ ብዙ ነገር ነው። ኢትዮጵያን ወክዬ መስራቴም ደስ የሚል ነገር ነው። አገራችን ኮሮናን እንዴት እንዳሳለፈች የሚያሳይ ፎቶዎቼምኤግዚብሽን ላይ ይቀርባሉ።ደግሞም የገንዘብም ሽልማት ነበረው። ከአዘጋጆችም ጋር ቢሆን የእኔ ፎቶግራፎች በኬንያ ኤግዚቢሽን ላይ እንደሚታይም ተነጋግረናል። ከዚህ በተጨማሪም ኬንያ ሄጄ የእነሱን ባህላዊ ነገራቸውን በሌላ ሰው እንዲሰራ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸውልኛል። ዶክመንታሪም ፎቶ (ዘጋቢ) እንደምሰራም ነግረውኛል ›› ይስሐቅ ይህን ያለው ከሽልማቱ ጋር ተያይዘው ስለመጡት መልካም ነገሮች ሲጠቅስ ነው ።

ሽልማቱን የተቀበለው ይስሃቅ ሲናገር ገንዘቡ 2መቶ ዶላር ይሁን እንጂ ከገንዘቡ ውጭ ሽልማቱ ተከትለው የሚመጡ ብዙ ነገሮች እንዳሉ በመናገርም ሥራው ተቀባይነት ማግኘቱ እንዲሁም እውቅና መሰጠቱም ቢሆን በጣም እንዳስደሰተው ይናገራል ‹‹ ብዙ አገራት የሚወክላቸው ሥራ አለን ብዬ አላስብም።ኢትዮጵያ ግን በዛ ፎቶግራፍ ማሳየቱ ትልቅ ደስታ ፈጥሮልኛል። በተጨማሪም ያ ፎቶ (ያሸነፈበት ፎቶ ) ባይኖር ኮቪድን እንዴት እንዳሰለፍን የሚወክል ነገር ላይኖር ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም እኔ የኢትዮጵያን ነገር እንዳያሳይ አድርጎኛል። ከኢትዮጰያ ውጭ በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር እንድችልም አድርጎኛል ።››

በፎቶ ግራፍ ውድድር ላይ አሸንፋለሁ ብሎ መጠበቅ ከባድ እንደሆነ የሚገልጸው ይስሃቅ ብዙ ሠዎች ለመወዳደር ሥራዎቻቸውን ያስገባሉ ሲልም ይጠቅሳል። ቢታንያን በተደጋጋሚ የሚያመሰግነው ወጣቱ ተሸላሚ ‹‹ቢታንያ ተወዳደር ብላኝ ተወዳደርኩ በኋላ ደግሞ ማሸነፌ ተነገረኝ ግን እንዳሸነፍኩ ሲነግረኝ ማሸነፍ ብቻም ሳይሆን ለወደፊት ከእኔ ጋር መሥራት ፍላጎት እንዳላቸው በመግለፅ ጭምር ነው።›› ሲልም ይሰማል።

የሽልማቱ ሙሉ ሂደት የተጀመረ ከኹለት ወራት በፊት የነበረ ሲሆን ውጤቱ የተነገረው ደግሞ ከሳለፈውው ሳምንት ጀምሮ ነበር።ይስሐቅን ለሽልማት ያበቃው ፎቶ አንድ ዲያቆን በቦሌ መድኒዓለም ቤተክርስትያን መግቢያ በር ላይ በመሆን የፊት ጭምብል ወይም ማስክ አድርጎ ሙዳይ ምጸዋት ለመቀበል ተቀምጦ የሚያሳይ ፎቶግራፍ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ለመረዳት ችላለች።

ከተነሱት ፎቶግራፎች ውስጥ ለውድድር ይሆና ብሎ መለየትም በራሱ ከባድ እንደሆነ የሚያነሳው ይስሐቅ ይሁን እንጂ ይላል እኔን በማገዝ በኩል የፎቶግራፍ ባለሙያ የሆነው አሮን ስሜነህ ካለው የተጨናነቀ እና የተጣበበ ጊዜ ውስጥ ጊዜውን መስዋዕት አድርጎ ፎቶግራፎች በመምረጥ ለአሸናፊነት እንድበቃ ድጋፍ አድርጎልኛል ሲል በምስጋና ነው የሚገልጸው።

ቀጣይ እቅዶች…
ኮቪድ እንደ አንድ ጉዳይ ብቻ በመያዝ የተለያዩ ፎቶግራፎችን ሲያስቀር የነበረው ይስሐቅ ከዚህ ጎን ለጎንም የኢትዮጵያ የተለዩ ገጽታዋን የሚያሳዩ ፎቶዎቸን በማንሳት ምስሎችን ያስቀራል። የበለጠም የማስቀረት ዓላማ እንዳለውም ለአዲስ ማለዳ ይናገራል። ጨምሮም ይህንን ብሏል ‹‹ዓላማዬም የኢትዮጵያን ልዩ የሆነውን ገጽታ ማሳየት ነው። ለምሳሌም የገና በዓል፣የጥመቀት፣ የአደዋን በዓልን በተመለከተ በተከታታይ ፎቶግራፎችን አነሳለሁ። እንደውም የጥምቀት በዓልን የሚያሰዩ ፎቶችን ለሦስት ዓመታ አንስቻለሁ። ዓለም ስለኢትዮጵያ የማያውቀውን ገጽታም ለማሳየት እቅድ አለኝ።ከዚህ ውጭም በከተማው ላይ ያለውን እኛል ሊያሳዩ የሚችሉ አኗኗራችን አስመልክቶም ነገሮችን ዶክመንት አደርጋለሁ (እሰበስባለሁ)። ይህንንም በመውዳደራቸው ውደድሮች ላይ ጭምርም እንደ አንድ ግብዓት አስገባለሁ።›› ብሏል።

በአንድ ወቅት ወደ ሰሜን ተራራ የመሄድ እድል እንደገጠው የሚገልጸው ይስሐቅ፤ አኗኗራቸው እንዴት እንደሆነ ጥንካሬያቸውንም ጭምር ሊያሳዩ የሚችሉ ነገሮች እንዳሉ በመጠቆም ከዚህ በኋላ በስፋት ወደ ክፍለ አገር በማቅናት ብዙ ያልታዩ ነገሮች በፎቶ አማካኝነት የማሳየት አላማው እንዳለውም ነው የሚጠቅሰው።

ከይስሐቅ ጋር ያለን ጨዋታ ቀጥሏል ባለሙያው የፎቶግራፍ ስራውን የሙሉ ጊዜ በመስጠት ሳይሆን ባለው ትርፍ ሰዓት እየሰራ ሲሆን በተመረቀበት የሙያ ዘርፍም እየሰራ ይገኛል። በአሁን ወቅት ደግሞ ኹለተኛ ድግሪውን በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን እየተማረም ይገኛል ። ትምህርቱ ሲያጠናቀቅም ወደ ፎቶግራፍን ሙያውን የሙሉ ጊዜ ሥራው ለማድረግ ዕቅድ እንዳለውም ይጠቅሳል።

ከአዲስ አበባ ወጣ በማለትም በየክፍለ አገሩ በመጓጓዝ የተለያዩ ፎቶዎችን በማንሳት ፎቶግራፍን ወደ ሙሉ ጊዜ ሥራ ለማድረግ ዓላማን አንግደቦ በእቅድ ላይ ተመስርቶ ሥራውን ጎን ለጎን እየሠራ ይገኛል።

ኮቪድ እና መልካሙ አጋጣሚ
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በአትዮጵያም ይሁን በሌሎች የዓለም አገራት ያልጎዳው ዘርፍ አለ ብሎ ለመናገር አዳጋች ይሁን እንጂ በተቃራኒው ደግሞ የከፈታቸው የሥራ ዕድሎች እንዲሁም ክስተቱን እንደ ጥሩ እና መልካም አጋጣሚዎች የተጠቀሙበት ግለሰቦችም ይሁኑ የተለያዩ ተቋማት ስለመኖራቸው አይሸሸግም። ከነዚህ ግለሰቦች ውስጥ ተጠቃሹ ደግሞ አንዱ ይስሐቅ ነው።

ከከባድ ሁኔታ ውስጥ ጥሩ ነገር ማውጣት ብሎም አጋጣሚ መቀየርም ይቻላል ብሎ ያምናል -ይስሐቅ። ‹‹ኮቪድ የሁላችንም ሕይወት ከባድ አድርጎታል።የብዙ ሰዎችን ሕይወት ጭምር ነጥቋል። እንደ ፎቶግራፍ ባለሙያም ሕይወታችንን ከባድ አድርጎታል። ከኮቪድ በፊት ታሪካዊ ፎቶዎችን ለማንሳት ብሎም በየመንገዱ ያሉ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳይ ፎቶዎችን ማንሳት ለእኛ በጣም ቀላል ነበር። ሠዎች በነጻነት በየመነገዱ ይታዩም ነበር በኋላ ደግሞ እንደፈለጉ እንዳይንቀሳቀሱ ማድረጉም ለእኛ ፈታኝ ሆኖብን ነበር›› ይቀጥልና እንዲህል ሲል ያክላል እንዲህ ዓይነት ችግር ሲገጥመን ለተሻለ አጋጣሚ መጠቀም ያስፈልጋል።

በማለት ፎቶግራፎችን ሲያነሳ የነበረበት የቤተክርስትያኑን ሁኔታ ምሳሌ በማድረግ ጠቅሳል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ስንመለከት ከመግቢያ በር ጀምሮ እስከ ቤተ መቅድስ ድረስ የመሳለም ሥርዓት አለ ይህም እውነትን የሚፈታተን ነገር ነበር። በጤና ባለሙያዎች በተቀመጠው መመሪያ መሠረት እና በአባቶች ምክር በኩል በተሰጠው ነገር ይህንነ ነገር እንዴት እያሳለፈች እንደነበር ማሳየት ችያለሁ ይላል። ‹‹ኮቪድ ይህንን ነገር እንዳሳይ ስለረዳኝ አመሰግናለሁ አይባልም ግን አጋጣሚውን እና ሁኔታውን ግን ተጠቅሜበታለሁ›› በማለት ነበር በሳቅ በታጀበ ንግግሩ ለአዲስ ማለዳ የገለጸው።

ኮቪድን እና ቀጣይ ሥራዎቹ
የኮቪድ ነገር አሁንም መቋጫ አልተገኘለትም። ከኮቮድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ፎቶ ግራፍ በማንሳት ላይ የሚገኘው ይስሐቅ ቀጣይ እቅዶቹንም ሲገልጽ በተለይም ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የፕሮቴስታንት፣ የእስልምና እምነት ተቋም በኮቪድ ምክንየት ዝግ ነበሩ። አሁን ላይ ግን ተቋማቱ በመከፈታቸው የካቶሊክ ተቋምን ጨምሮ እንዴት እንዳሰላፉ በፎቶግራፍ የማሳት ዕቅድ እንዳለውም ያስረዳል።

ከእምነት ተቋማት ውጭ የተለያዩ አካባቢዎች ለምሳሌ አራት ኪሎ እና ሌሎች ቦታዎችን ጨምሮ ድሮ ከነበሩ ፎቶዎች ውጭ አሁን ላይ ያለውን ሁኔታ የሚያሳይ ፎቶግራፍ ለማንሳት በግሉ ማሰቡንም አልሸሸገንም።

ፎቶ ግራፍ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አጉልቶ የሚያሳይ ነገር እንደሆነ ቢታወቅም በአገራችን ከኮቪድ ጋር ያለውን ጥንቃቄ ከዕለት ዕለት እየቀነሰ ስለመምጣቱም በግልጽ የሚታይ ነገር እንደሆነም ማንሳት ይቻላል። ይሁን እንጂ እንደነዚህ ዓይነቶቹን ክፍተት ከማሳየት ይልቅ ያለውን በጎ ጎን በማሳየት ሰዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደር እንደሚቻል ይስሐቅ ያስረዳል ።

እንደ ማጠቃለያ
በኪነጥበብ ዘርፍ ድጋፍ በማድረግ፣ እውቀትን በማስተላለፍ፣ መንገዶችን በማሳየት ድጋፍ የሚያደርጉ ጥቂት ሰዎችን ማመስገን ያስፈልጋል። በኪነጥበብ ዓለም ላይ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ምስጋና እንዲደርሳቸወ እንዲሁም ቁጥራቸው እንዲበዙም ምኞቱ ነው። ድጋፍ ያደረጉለትንም ሰዎች አመስግኗል- ተሸላሚው የፎቶግራፍ ባለሙያ ይስቅ ልሳነ ክርስቶስ።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com