የእለት ዜና

ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መጠን ተመዘገበ

ታህሳስ 27/2013 የወጣው የማዕከላዊ ስታስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው ባሳለፍነው ታህሳስ ወር አጠቃላይ አገራዊ አማካኝ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ20.4 በመቶ አድጎ 19 በመቶ ላይ መድረሱን በሪፖርቱ ተመላቷል። ያለፈው ዓመት 19 ነጥብ አምስት እንደነበርም ተገልጿል። ይህም የዋጋ ግሽበት ፍጥነት እና መጠን ከዚህ ቀደም ታይቶ እንደማይታወቅም ታውቋል።

ካለፈው ዓመት 2012 ታህሳስ ወር ጀምሮ እስከ ታህሳስ 2013 ድረስ ባሉት 12 ወራት ውስጥ አማካይ የምግብ የዋጋ ግሽበት በ23.1 በመቶ ዕድገት እንዳሳየም መረጃው ያመላክታል። የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ የዋጋ ግሽበት ረዘም ያለ ጊዜ የዋጋ ግሽበት ሁኔታ የሚያሳይ እንደሆነ ከማዕከላዊ ስታስቲክስ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የዋጋ ግሽበት ሁኔታ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር በማነፃፀር የሚገኘው ውጤት ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት ሁኔታን ይገልጻል። በመሆኑም ካለፈው ዓመት ታህሳስ ወር 2012 ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮው ዓመት ታህሳስ ወር በ18.2 ከመቶ ከፍብሏል በማለት መረጃው ያስረዳል።

እንደ ማዕከላዊ ሪፖርት ስታስቲክስ በያዝነው ወር ጤፍ፣ስንዴ፣ገብስ፣በቆሎ እና ማሽላ የዋጋ ቅናሽ ያሳዩ ሲሆን ለምግብ ዋጋ ግሽበት መረጋጋት ከፍተኛ አሰተዋጽኦ እንዳላቸው ተገልጿል። በተጨማሪም አትክልት እና አንዳንድ የጥራጥሬ ዓይነቶች መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ አስመዝግበዋል።

በሌላ በኩል ስኳር፣ የምግብዘይት፣ድንች እና ቡና ያሳዩትን የዋጋ ጭማሪ በዚህም ወር በመቀጠላቸው ለዋጋ ግሽበት ምጣኔ መጨመር አስተዋጽኦ ማድረጉን ከመረጃው ለማወቅ ተችሏል። ያለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ዋጋ ከአሁኑ ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር በንጽጽር ዝቅተኛ ስለነበር የዋጋ ግሽበቱ በያዝነው ወርም ከፍ ብሏል።

በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎች ላይ የታየ የዋጋ ግሽበት የታህሳስ ወር 2013 ካለፈው ዓመት ታህሳስ ወር 2012 ጋር ሲነፃፀርም የ14.3 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ከምግብ ነክ ያልሆኑ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይም በአልኮልና ትምባሆ፣ አነቃቂዎች(ጫት) የዋጋ ግሽበት ሁኔታ እንዲሁም፣ የቤት እንክብካቤናኢነርጅ(ማገዶናከሰል)፣የቤትመስሪያእቃዎች፣ህክምና እና ጌጣጌጥ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነው።

የታህሳስ ወር 2013 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ህዳር ወር 2013 ጋር ሲነፃፀር በ0.1ከመቶ ቅናሽ አሳይቷል። ምግብ ነክ የሆኑ የዋጋ ግሸበትበት በየከተሞቹ ሲታይ አዲስአበባ በ20.6 ከመቶ ሲሆን ዝቅተኛ ቁጥር የተመዘገበው በሶማሌ5.1 ከመቶ ነው። በትግራይ በ38.4 ጭማሪ እንዳሳየ መረጃው ያመላክታል።
የታህሳስ ወር 2ዐ13 የአገር አቀፍ ጠቅላላ የችርቻሮ ዋጋ መመዘኛ መስፈርት ከታህሳስወር 2ዐ12 ጠቅላላ ጋር ሲነፃፀር በ18.2 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በአዲስአበባ በ17.1ከመቶ በሶማሌ በ9.7ከመቶ እና በትግራይ በ30.8 ከመቶ ጭማሪ ማሳየታቸውን ነው በሪፖርቱ የተገለው። በጥናቱ የተሸፈኑ የገበያ ቦዎችዎች ውስጥ አዲስ አበባ፣ትግራይ፣አፋር፣ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ድሬዳዋ፣ሐረሬ፣ጋምቤላ እና የደቡብ ብሄር እና ብሄረሰብ ሕዝቦች ይገኙበታል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የምጣቤ ሀብት የትምህርት ክፍል መምህር በላይነህ ካሳ(ዶ/ር) በአገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለሚገኘው የዋጋ ንረት እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀሰው የውጭ ንግድ መዳከም ነው በማለት ተናግረዋል። የውጭ ንግድ ሳይኖር ከውጭ አገራት ገቢ ብቻ የምናደርግ ከሆነ ከፍተኛ የሆነ የዶላር እጥረት ይከሰታል ይህ የዶላርን ዋጋ እንዲጨምር ያደርጋል ገቢ በምናደርጋቸው እቃዎች ላይ ዋጋ እንዲጨምር የሚያደርገው አንዱ ምክንያት ደግሞ የዶላር ዋጋ ጭማሪ ነው ብለዋል።

አክለውም የኑሮ ውድነት መጨመር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ቢሆንም መንግሥት ያለበት ውስጣዊ እና ውጫዊ አለመረጋጋት ትኩረት እንዲነፍገው አድርጎታል ብለዋል። የአገር ውስጥ ምርት የሆኑ የምግብ ሰብሎች ላይ ዋጋ እንዲጨምር ራሳቸውን የቻሉ አምራች የሆኑ ቦታዎች ላይ ያሉ አለመረጋጋቶች እና መፈናቀል ከነዚህ አካባቢዎች የምናገኘውን ገጸ በረከት እያሳጣን ይገኛል በማለት ተናግረዋል።

መንግሥት የራሱ የሆነ ሥራ ቢኖርበትም የንግድን ሂደት የሚቆጣጠርበት አሠራር መዘርጋት ይኖርበታል፤በአገር ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ሕብረተሰቡ ላይ ጫና የሚያሳድሩ የንግዱ ማሕበረሰብ ክፍሎች መኖራቸውን በላይነህ(ዶ/ር) ገልጸው ለዚህ እንደ ምሳሌ በትግራይ የነበረውን አለመረጋጋት የተጠቀሙ እና ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ያሳዩ ነጋዴዎችን መጥቀስ እንችላለን፤ይህንን አሠራር ለመቀየር ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት አለብን ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!