የእለት ዜና

የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ 14 ሚሊየን ዶላር በላይ ከወጪ ንግድ አገኘ

የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ንዑስ ዘርፍ በመጀመሪያው ግማሽ በጀት አመቱ 14 ነጥብ 43 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ከውጪ ንግድ መገኘቱን ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በ2012 የመጀመሪያ ግማሽ አመት 20 ነጥብ አምስት ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ተገኝቶ እንደነበር ከመስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በዚህም በያዝነው በጀት አመት ከተገኘው ገቢ ጋር ሲነፃፀር 29 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን በዶላር አምስት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱን መረጃዎቹ ያመላክታሉ።

በያዝነው በጀት አመት የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ በውጪ ንግድ ለማግኘት የታቀደው 44 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እንደሆነም አዲስ ማለዳ ያየቻቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ የግብዓት አቅርቦት እና ገበያ ትስስር ዳይሬክተር ዘሪቱ አገኘሁ እንደተናገሩት የተገኘው 14 ሚሊዮን ዶላር ከሰባ በላይ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ወደ ተለያዩ አገራት በመላክ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ከተያዘው የ44 ነጥብ 96 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዕቅድ መሀል በግማሽ ዓመቱ 17 ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ስልሳ ሺሕ ዶላር እንደሚገኝ ታቅዶ እንደነበር ነግረውናል።

በመጀመሪያው ስድስት ወራት የወጪ ንግድ እንቅስቃሴው 14 ሚሊየን አራት መቶ 29 ሺሕ ሶስት መቶ 53 የአሜሪካን ዶላር ገቢ መሰብሰቡ የተገለፁ ሲሆን አፈጻጸሙም 80 ነጥብ ሶስት አራት በመቶ ብቻ ለማሳካት እንደተቻለ አመላክቷል።

ዳይሬክተሩዋ እንደተናገሩት የተገኘው ውጤት በብዙ ችግሮች መሀል ስለሆነ ጥሩ የሚባል ነው ብለዋል።ለብረታ ብረት ዘርፉ ከፍተኛ ተፅእኖ የሚያሳድረው የውጪ ምንዛሬ እጥረት እንደሆነም ተናግረዋል።

በስድስት ወራት ውስጥ የነበሩ ችግሮች የግብአት እጥረት ፣ ኢንዱስትሪዎች ሰፋ ያለ የማምረቻ ቦታዎች ይፈልጋሉ በዚህም የማምረቻ ቦታ እጥረት እንዲሁ እንደ ችግር መጠቀሳቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

የውጪ ንግዱ የተገኘው 75 ኢንዱስትሪዎች የገበያ መዳረሻቸውን ወደ ተለያዩ ስምንት የአውሮፓ ፣ 10 የመካከለኛ ምስራቅ የኤሽያ ፣ የአሜሪካ ፣ የሩቅ ምስራቅ ፣ የአውስትራሊያ እና 16 የአፍሪካ አገራት አድርገው እንደሆነ አስታውቀዋል።

በወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ከኤሌክትሪክ እና ኤሌክትሮኒክስ ምርት ዘርፍ 16 ሚሊየን አንድ መቶ 10 ዶላር ታቅዶ 12 ሚሊየን ዘጠኝ መቶ 59 የአሜሪካ ዶላር ሊመዘገብ መቻሉ፣ በመሰረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ አንድ ሚሊየን 850 ሺሕ ታቅዶ አንድ ሚሊየን አራት መቶ 69 ሺሕ ዶላር መሰብሰብን የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የሚላኩት ምርቶች መካከል ሞባይል ፣ ኤሌክትሪካል ኤሌክትሮኒክስ ፣ኢንጅነሪንግ ማሽነሪ እና የተለያዩ የመለዋወጫ ምርቶች እንዳሉበት ተናግረዋል።
በዋናነት በውጪ ምንዛሬ ከፍተኛ ስፍራውን ይዞ የነበረው ሞባይል ንግድ እንደሆነ በዚህም ከተገኘው 14 ሚሊየን ዶላር 12 ነጥብ 87 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የተገኘው በሞባይል ሲሆን 89 በመቶ የሚሆነውን እንደሚይዝ ተናግረዋል።

የግብዓት ችግር እንደ ዋና ችግር ነው ያሉት ዳይሬክተሯ የብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ የሚያመርቷቸው ምርቶች ለማምረት ጥሬ እቃ የሚያስገባው ከውጪ አገራት በመሆኑ ግብዓቶችን ከውጪ ለማስገባት የውጪ ምንዛሬ እጥረቱ አስቸጋሪ እንደነበርም ጠቁመዋል።

ችግሮቹን ለመቅረፍም በርካታ ስራዎች እየጠሰሩ ነው ያሉት ዘሪቱ ከነሱም መካከል ምን እንኳ የውጪ ምንዛሬ እጥረቱ እንደ አገር ያለብን ቢሆንም ኢንደስትሪዎቹ አቅማቸውን መሰረት ያደረገ የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት እንዲያገኙ ጥረቶች እየተደረገ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስድተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!