ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ወራት ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኘ

Views: 98

ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የበጀት ዓመቱን የስድስት ወራት አፈፃፀም በሚመለከት ለመገናኛ ብዙኀን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ባለፉት ስድስት ወራት ኩባንያው 25 ነጥብ 57 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቀዋል።
የተገኘው ገቢ ከተያዘው እቅድ የ95 በመቶ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን አብራርተው፤ እቅዱን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት ያልተቻለው በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሳቢያ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም ሆኖ የተገኘው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ12 ነጥብ 5 በመቶ እድገት አሳይቷል ብለዋል። በተጠቀሰው ወራት የውጭ ምንዛሬ ግኝቱም 80 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሞባይልና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር በየጊዜው እድገት እያሳየ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገልጸዋል።
ከሞባይል ተጠቃሚ ደንበኞች መካከል 64 ነጥብ 3 በመቶው የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
እንደ ፍሬህይወት ገለፃ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 39 የተሻሻሉ ምርትና አገልገሎቶች ለደንበኞች ቀርበዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ ደንበኞች 50 ነጥብ 7 ሚሊዮን መድረሳቸውም ታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com