ከአሜሪካ ሰማይ ሥር

Views: 213

በአስገራሚ ሁኔታ ልዕለ ኃያሏን አሜሪካን ለመምራት ዕድል አግኝተው ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ጎራ ያሉት፤ ከቀናት በፊት የቀድሞው የተባሉት 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአጨቃጫቂነት ነበር የሥልጣን ዘመናቸውን ያጠናቀቁት። በአራት ዓመታት ቆይታቸው ከበርቴው ትራምፕ ለአፍታ እንኳን ስለ እርሳቸው ሳይወራ እና በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ሳይነቀፉም ሆነ ባደረጉት አንድ ንግግር እንኳን ሳይተቹ ያሳለፉት መአልት አልነበረም ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ትራምፕ አንድ ጊዜ በግልጽ የጋዜጣዊ መግለጫ በል ሲላቸው ደግሞ በትዊተር የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አንድን ጉዳይ አንስተው ስድብ የቀላቀለ ሐሳባቸውን በሚያሰሙበት በዛው ቅጽበት ዓለም አጀንዳውን ሁሉ አጠንክሮ ሲዘልፋቸው እና ሲተቻቸው ይከራርማል።

በዘመናዊ አሜሪካ የመሪነት ታሪክ ምናልባትም የመጀመሪያው ናቸው የሚባልላቸው ትራምፕ አራሩን የሥልጣን ዘመናቸው ከነገ ዛሬ ከሥልጣናቸው ተባረው በሕግ ሊጠየቁ እና የሥልጣን ዘመናቸው ሳያልቅ ኃላፊነታቸውን አስረክበው ይሰናበቱ ይሆን በሚል እንደ ልብ አንጠልጣይ ተከታታይ ድራማ ዓለም ዐይንና ጆሮውን ከወደ አሜሪካ ሳይነቅል በንቃት የተከታተለው። የ‹‹ወተር ጌት›› ቅሌትን የተከናነቡት 37ኛው ፕሬዘዳንት ሪቻርድ ኒክሰንን ዕጣ ፋንታ ይገጥማቸው ይሆን ወይስ ሕጋዊ መንገድ ተከትሎ አሜሪካ እና አሜሪካዊያን መሪያቸውን ያሰናብቷቸው ይሆን የሚለው ጉዳይ በብዙ ሰዎች ዘንድ ተጠባቂ ነበር። ይሁን እንጂ የየማለዳው የጋዜጠኞች የአፍ ማሟሻ የነበሩት ነጋዴው፣ የቴሌቪዥን አቅራቢው፣ በኋላም አጨቃጫቂው ዶናልድ ትራምፕ በጊዜያቸው የነጩን ቤተ መንግሥት ሕይወት ጉዞ ለኹለተኛ የንግሥና ዘመን አጥብቀው ቢሽቱትም ታግሎ መሸናነፍ ያለ ነው እና ሳይወዱ በግዳቸው ለአሸናፊያቸው ዴሞክራቱ ጆ ባይደን ለመልቀቅ ተገደዋል።

ከመጀመሪያው አሜሪካ መሪ ለመሆን የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ጀምሮ አወዛጋቢነታቸው የጀመረው ትራምፕ በአንድ ወቅት ‹‹እኔ ካለሻነፍኩ ይህ ምርጫ ተጭበርብሯል ማለት ነው፣ የታጠቁ ይህን ያህል ደጋፊዎች እና ወታደሮችም አሉኝ እርምጃም ይወስዳሉ›› ሲሉም እስከ መደመጥ ድረስ ደርሰው ነበር። ይህን ዓይነት ንግግር ከወደ የዲሞክራሲ እናት እና የነጻነት ሁሉ ምንጭ ነኝ ከምትለው አሜሪካ መስማት ግርምትን መፍጠር ብቻ ሳይሆን እንዴት እንዴት ነው ይህ ጉዳይ እኚህ ሰው ግን በእርግጥም ወደ ሥልጣን ቢመጡ ከአሜሪካ የለመድነውን የአንጻራዊ ዲሞክራሲ አካሄድን በእርግጥ ያስቀጥሉ ይሆን ብለው የጠየቁም አልጠፉም። ይሁን እንጂ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ብቻ ዶናልድ ትራምፕ የኒውክሌር ቁልፉን ይረከቡ ዘንድ ዕድል እና ጊዜ ገጥሟቸው በአሜሪካዊያን አባባል “Mr President” ለመባል በቅተዋል።

ይሁንና ዶናልድ ትራምፕ ‹‹ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር….›› እንደሆነባቸው የታወቀው በመጀመሪያዎቹ የኃላፊነት ቀናት ጀምሮ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የተኩት እና ከእርሳቸው ቀድሞ አገርን ሲያስተዳድር የነበረው ቀዳሚያቸው ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ በእርግጥም በችሎታቸው ተወዳዳሪ አይገኝላቸውም የተባለላቸው እና አሜሪካን በአስቸጋሪ ጊዜ ያስተዳደሩ ግሩም የመሪነት ብቃታ አላቸው ተብለው የሚሞካሹ መሆናቸው ነው። የሆነው ሆኖ ነጩን ቤተ መንግሥት ናኝተውበት ለመሪነት የሚያበቃ ሥነ ምግባርን ግን ሳንታዘብባቸው የተሰናበቱን መሪም እንደሆኑ ደግሞ የዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኀንን እግር ጥሎን መታዘብ ብቻ በቂያችን ነው።

ትራምፕ ወደ ሥልጣን እንደመጡ በመጀመሪያ ያደረጉት ነገር ቀዳሚያቸው ባራክ ኦባማ የሠሩትን እና በበርካቶች ዘንድ አንድናቆት የተቸሩበትን ‹‹ኦባማ ኬር›› የተሰኘውን ለታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል መጠነኛ እና ነጻ የሕክምና እና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን የማሟላት አሠራርን በማስተጓጎል ነበር የጀመሩት። ተቃውሞው ከቀን ወደ ቀን እያየለባቸው እና በሌላ ጎን ደግሞ የውጭ አገራት በተለይም ደግሞ ከርዕዮት ዓለም ልዩነት እና ከልዕለ ኃያልነት መገዳደር ጋር በተያያዘ ባላንጣ ከምትባው ሩሲያ ጋር በመመሰጣር ነው ምርጫውን ያሸነፉት የሚለው መረጃም በአሜሪካ ምድር አልፎ ዓለምን አዳርሶ ነበር። ‹‹አይሞቃቸው አይበርዳቸው›› የተባለላቸው ፕሬዘዳንት ትራምፕ በእርግጥም በንግግራቸው እንዴት መሪ ሊናገር ይገባዋል የሚለውን መርኅም ሲከተሉ እና ቁጥብ ፖለቲከኛ ናቸው ለማለት አያስደፍርም።

ከአራት ዓመታት የውጣ ውረድ ዶናልድ ትራምፕ በርካታ ታሪካዊ ስህተቶችንም በአሜሪካ ላይ አስከስተዋል ተብሎም ይወቀሳሉ። እንደ እድል ሆኖ ደግሞ እርሳቸው በአደባባይ የካዱት እና ያጣጣሉት ርዕሰ ጉዳይ በአጭር ጊዜ ውስጥ አሜሪካንን ሲጎዳም የሚስተዋልበት እና እርሳቸውንም የሚያስወቅስበት አጋጣሚዎችም ነበሩ። ለአብነትም የፓሪሱን የአየር ንብረት ስምምነት አገራቸው አሜሪካን ከስብስቡ በማስወጣት አንድ ብለው ከዓለም መለየት የጀመሩት ትራምፕ ‹‹አየር ንብረት ለውጥ ብሎ ነገር የለም፤ እኔ ምንም አይገባኝም›› የሚልም ነበር መጨረሻ የመሰናበቻ ንግግራቸው ከፓሪሱ ስምምነት ሲለዩ። ታዲያ የለም ውሸት ነው ያሉት የአየር ንበረት ለውጥ አፍታም ሳይቆይ ነበር በርካታ የአሜሪካ ግዛቶችን ዶግ አመድ አድርጎ ምስቅልቅላቸውን ያወጣው ነበረው። በተደጋጋሚ በአውሎ ንፋስ እና ውሽንፍር መመታት የሰለቻቸው አወዛጋቢው ፕሬዘዳንት ለምን ይህን የሚፈጥረውን አውሎ ንፋስ ከመነሻው በኒውክሌር አንመታውም የሚልም ሳቅ እና ግርምትን የሚጭር ሐሳብ ይዘው ብቅም እስከ ማለት ደርሰው ነበር። ይህ እንግዲህ ከኢትዮጵያ ኮረብቶች እና ረባዳ መሬቶች ይነሳል የሚባለው ነፋስን መሆኑ ሲሆን የምትመታውም እናት አገር ኢትዮጵያ መሆኗ ነው።

በ2019 መገባደጃ ላይ ደግሞ ከቻይና የተነሳው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በብርሃን ፍጥነት ዓለምን ሲያጥለቀልቅ መላዕከ ሞት በአሜሪካ በእጅጉ በርትቶ ነበር። ይሁን እንጂ በመጀመሪያዎቹ ኮቪድ 19 በአሜሪካ በተከሰተበት ወቅት ‹‹ኮቪድ 19 የሚባል ወይም ደግሞ በራሳቸው አገላለጽ የቻይናዊያን ቫይረስ እኛ ጋር የለም›› ሲሉም ተደምጠው ነበር። ነገር ግን የአገራቸው ወረርሽኝ ቁጥጥር መሥሪያ ቤት (CDC – Center for Disease Control and Prevention) አስፈሪ ነገር ከፊታቸው እንዳለ በርካታ አመላካች እና አስደንጋጭ ምልክቶችን እና የጥናት ውጤቶችን በማጣቀስ ሲገልጽ መቆየቱ ነው። ይህ የካዱት እና እንደሚባለው አይደለም ያሉት ቫይረስ ከተርታው ሕዝባቸው አልፎ በራሳቸውም ደርሶ ገፈቱን ቀምሰውታል። እንዲያውም ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ዓለም ዐቀፍ ጋዜጠኛ ‹‹ዶናልድ ትራምፕ በ2020 መጥፎ የሚባሉ ገጠመኞችን አስተናግደዋቸዋል፤ እነዚህም ውስጥ አንደኛ በኮቪድ 19 ተያዙ ሲቀጥል ደግሞ ሥራቸውን አጥተዋል›› ሲል ነበር ስለ ሁኔታቸው ያስነበበው።

የምጣኔ ሀብት አቋም በዘመነ ትራምፕ
ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት ከቀዳሚው ፕሬዘዳንታቸው ባራክ ኦባማ ጠንካራ ምጣኔ ሀብትን ያላትን አገር ተረክበዋል ይባልላ። እንደ ምክንያት የሚቀመጡት ደግሞ ባራክ ኦባማ በፕሬዘዳንትነት በተቀቡበት ወቅት ከፍተኛ ሆነ የምጣኔ ሀብት ድቀት በአሜሪካ ላይ አጋጥሞ እንደነበረ እና ምናልባትም በ1929 (እ.አ.አ.) ከተከሰተው የመጀመሪያው ታላቁ ምጣኔ ሀባት ድቀት ጋር ሊስተካከል የሚችልም እንደነበር ይነገርለት ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት ወደ ሥልጣን የመጡት ኦባማ አገርን በከፍተኛ ሁኔታ ውስጥ ሆነው በማቆም ለተተኪያቸው ተረጋጋች እና በምጣኔ ሀብቷም የጎለበተች አገርን እንዲያስረክቡ ተችሏቸዋል የሚል ጽሑፎች ይነበባሉ።

ዶናልድ ትራምፕ በሥራ አጥ ቁጥር፣ በጠቅላላ የአገር ውስጥ የምርት እድገት፣ በአማካኝ ወርሐዊ ሥራ ዕድል ፈጠራ፣ እና በአንድ አባውራ አማካኝ ገቢን በሚመለከት ተለያይቶ ሲቀመጥም የራሱ የሆነ ምስል ከሳች ቁጥሮችን ማግኘት ይቻላል። አገራቸውን ከኦባማ ሲረከቡ የነበረበት የምጣኔ ሀብት አቋም እና በእርሳቸው ዘመን ያደረሱት በንጽጽር መመልከት ይቻላል።

በኦባማ ዘመን የነበረው የአጠቃላይ አገር ውስጥ ምርት ዕድገት 2.6 በመቶ በመሆን ከቀዳሚው ፕሬዘዳንት ጋር በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ይገኛል። በወርሐዊ የሥራ እድል ፈጠራ በአማካኝ የኦባማ በ35 ወራት ውስጥ 227 ሺሕ ሥራዎችን መፍጠሩ ሲታወቅ የጠነከረ ምጣኔ ሀብት የተቀበሉት ዶናልድ ትራምፕ ግን በ36 ሺሕ ቀንሰው 191 ሺሕ ብቻ መፍጠር ችለው ነበር። መረጃዎችን በግልጽ በማስቀመጥ የሴኔት አባሉ እና የአሜሪካው የጥምር ምጣኔ ሀብቱ ኮሚቴ ዶን ባየር እንደሚሉት በአማካኝ አንድ አባውራ የሚያገኘው ገቢ በኦባማ ዘመን አራት ሺሕ 800 ዶላር ነበረ ሲሆን በትራምፕ ጊዜ ደግሞ ወደ አንድ ሺሕ 400 ዶላር ዝቅ ማለቱንም ያስቀምጣሉ።

በዲፕሎማሲ ረገድ
በርካታ ዓለም ዐቀፍ የዲፖሎማሲ እና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ተንታኞች እንደሚሉት ትራምፕ አሜሪካ አይታው የማታውቀውን ዲፖሎማሲ ኪሳራን አስከትለዋል የሚል ትችት ሲያግተለትሉ ይስተዋላሉ። ፕሬዘዳንቱ ባሰላፏቸው የኃላፊነት ዘመናት ላይ አሜሪካን ከዚህ ቀደም የነበራት ተቀባይነት እና ተሰሚነት በእጅጉ የቀነሰበት እና በየአገሩ ያሉ አምባሳደሮቿ እና መልዕክተኞቿ የተመደቡበት አገርን መንግሥታት ስለ ፕሬዘዳንታቸው ንግግር ማብራራት ሆኖም እንደነበር ያደባባይ ምስጢር ነው። በተለይም ደግሞ በአንድ ወቅት በአፍሪካ ላይ ከባድ ዘለፋ በማሰማት ከፍተኛ ትችት የተሰነዘረባቸው ትራምፕ ምንም ባልተፈጠረ መልኩ ይቅርታቸውን እንኳን ሳያሰሙ ድፍን አንድ አህጉር ዘልፈው ሕይወታቸውን ቀጥለው ነበር።

እዚህ ላይ ግን አንድ ያላሰቡት፤ ይህ ወቅት የዓለም መሪ ምጣኔ ሀብት ተርታ የምትመደበው ቻይና አፍሪካን ከምዕራቡ ዓለም ለመነጠል በምትሟሟትበት ወቅት ፕሬዘዳንቱ ይህን መሰል ዘለፋ ማካሔዳቸው ከፍተኛ ነጥብ የሚያስጥላቸው እንደሆነ አለመገንዘባቸው ነው። በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት በይፋ ንግግራቸውን ያወገዘ እና ማብራሪያ የጠየቀበት የዲፖሎማሲ አካሄዶችን የተከተለ ቢሆንም የተደረሰበት ደረጃ አልተገጸም ነበር። አሜሪካ አገራቸውን ባህር እና አህጉር ተሻግረው በጦርነት ሳይሆን በሰለጠነ መንገድ በዲፖሎማሲ ሲያስከብሩ የኖሩ መሆናቸው በራሱ ይህን አጋጣሚ እንደ ትልቅ ውርደት የቆጠሩበት አጋጣሚ እምብዛም የሚደንቅ አይደለም።

ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው ጊዜያቸው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አድርገው የሾሟቸው ኩባንያ ከማስተዳደር ባለፈ ምንም ዓይነት ሕዝብ ግልጋሎት ላይ ያልተመዘኑ መሆናቸውም የዲፖሎማሲው ጉዞ ወዴት ሊያመራ እንደሚችልም የተገመተበት ነበር።

የሆነው ሆኖ አጨቃጫቂው እና አወዛጋቢው መሪ ዶናልድ ትራምፕ አሁን ነጩን ቤተ መንግሥት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተሰናብተዋል። እንደዛ ቅንጡነቱ የዓለም ነገሥታትን ልብ የሚያቆመው ‹‹ኤርፎርስ ዋን›› የተሰኘውን ግዙፍ አውሮፕላንን ለተተኪያቸው እና ደርባባው የፖለቲካ ሰው ጆ ባይደን አስረክበው ወደ መጡበት የባህር ዳርቻዋ አገር ፍሎሪዳ አቅንተዋል። ይህ ሲሆን ግን ትራምፕ ባለቀ ሰዓት አንድ ጠባሳ ጥለው አልፈዋል።

እንዲያው ባላደጉት እና የዲሞክራሲ ጸዳል አልደመቀባቸውም በሚባሉ አገራት እንኳን የማይሞከር ጉዳይ፥ በአሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከስቷል። በዘመናዊት አሜሪካ ይህ ጉዳይ ማለትም የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ነን ባዮች አጥር እና በር ሰብረው አገሪቱን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠበቀውን ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እና እና የሕግ መምሪያ ምክር ቤት የሚገኙበትን ባለግርማ ሞገሱን ታሪካዊውን ‹‹ካፒቶል ሂል›› ማጥቃታቸው በእጅጉ ግርምትን የፈጠረ አጋጣሚ ነበር። አሜሪካ በምትታወቅበት ጠንካራ አሸናፊ ሳይን ብርቱ ተሸናፊ ነው እና በጆ ባይደን መረታታቸውን ያልተቀበሉት ትራምፕ ደጋፊዎቻቸውን ወደ ግዙፉ ቤት እንዲገቡ ማድረጋቸው ጉዳያቸውን በክስ እንደደመደም የፈለጉም ሳያስመስልባቸው አልቀረም ።

ከቀናት በፊት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ፍሎሪዳ የሚወስዳቸውን አውሮፕላን ለመያዝ ለአራት ዓመታት ከቆዩበት ነጩ ቤተ መንግሥት ‹‹ብላክ ሐውክ›› ወይም ደግሞ ጥቁሩ ንስር በተባለው ሔሊኮፕተር ከባለቤታቸው ሜላኒያ ትራምፕ ጋር ተሳፍረው የተተኪያቸውን በዓለ ሲመት ሳይታደሙ እና በአደባባይ መልካም ምኞታቸውን ሳይግልጹ ወደ መኖሪያቸው አቅንተዋል።

ጆ ባይደን ማናቸው?
በትራምፕ ወደ ቤተ መንግሥት መምጣት እና የኦባማ የሥልጣን ጊዜ ማብቃት ከቤተ መንግሥት ውሎ ያወጣቸው የዕድሜ ባለጸጋው እና የዕድሜውን ግማሽ ያህል ባለ ጎልማሳ ሰው ፈጣን የማሰብ ችሎታ አለው የሚባለው ሰው ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ተመልሶ መጥቷል። በአሜሪካ አንድ ዘመን የሥልጣን ቆይታ ዘመን ያህል ማለትም በአራት ዓመታት ያህል ዶናልድ ትራምፕን በዕድሜ በሚበልጡት አዲሱ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን፥ አዲስ ተስፋ እና ምዕራፍ ለአሜሪካ እንደሚያመጡ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎባቸዋል። በኦባማ ዘመነ መንግሥት ምክትል አሜሪካ ፕሬዘዳነት በመሆን ለስምንት ዓመታት አገራቸውን ለማገልገል የታተሩ ነባር ፖለቲከኛም ናቸው።

ጆ ባይደን በፈረንጆች 1973 እስከ 2009 ድረስ የአሜሪካ ግዛት ሆነችውን ዴላዌርን በመወከል የምክር ቤት አባልም በመሆን የሠሩ የሕዝብ ሰው መሆናቸውንም የግል ማኅደራቸው በግልጽ ይናገራል። ለግማሽ ምዕት ዓመት ከሕዝብ ዓይን ያልጠፉት ጆ ባይደን በኦባማ ዘመን በምክትልነት ካገለገሉት በተጨማሪ ለ36 ዓመታትም በምክር ቤት ተመራጭነት መቆየታቸው ለፕሬዘዳንትነት ተወዳድረው ምረጡኝ ባሉ ጊዜ ለመረጧቸው ሰዎች አዲስ ፊትም አይደሉም።

የአራት ልጆች አባት የሆኑት እና በፔንሴልቫኒያ ግዛት ያደጉት አዲሱ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን፥ በልጅነት ዘመናቸው አፈ ተብ እንደ ነበሩ እና በትምህር ቤት የልጅነት ቆይታቸው አብረዋቸው ከሚማሩ ልጆች እና ከአስተማሪዎች እንዲሁም ሞግዚቶች ዘንድም በአፈ ተብነታቸው ይሾፍባቸው እንደነበር በአንድ ወቅት በአደባባይ ሲናገሩ ተሰምቷል። በኋላ ላይም ደግሞ በተለይም በከፍተኛ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ቤታቸው የአሜሪካ እግር ኳስ ተብሎ በሚጠራው ስፖርት ላይ ቁጥር አንድ ተጫዋች እና ቡድንም አደራጅ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል።

መታከትን እንደማያውቁ የሚያስረዳው እና የትጋታቸው መስክር የሆነው ጆ ባይደን፥ ከዚህ ቀደም ለሦስት ጊዜያት ያህል አሜሪካን ለመምራት የፕሬዘዳንትነት የምረጡኝ ዘመቻ አድርገው አልተሳካላቸውም ነበር። ይሁን እንጂ በ2009 የምን ጊዜም ጓደኛቸው እና አለቃቸው በሆነው ባራክ ኦባማ ዘመን ነበር ወደ ከፍተኛ ሥልጣን ብቅ ያሉት። ጆ ባይደን እና ባራክ ኦባማ ሳምንታዊ የምሳ መርሃ ግበር እንዳላቸው እና ባልንጀራነታቸውን እንደሚመካከሩም ስለ ባይደን ከተጻፉት ውስጥ ለማወቅ ተችሏል። በተመሳሳይ ባራክ ኦባማ በአንድ ወቅት ለ‹‹ኒው ዮርክ ታይምስ›› እንደተናገሩት አንድ ትልቅ ውሳኔ ለመወሰን በዋናነት የማማክረው ሰው ቢኖር ባይደንን ነው ሲሉ ተደምጠው ነበር። ለዚህም ምላሽ ደግሞ ባይደን በበኩላቸው ‹‹አንተ ውሳኔ ወስን እንጂ ውሳኔህን አክብሬ እስከ ሕይወቴ ፍጻሜ ድረስ እተገብረዋለሁ›› የሚል ማስተማመኛ ቃልም ሲናገሩ ይደመጡ ነበር።

በዓለ ሲመቱ
ቀዳሚያቸው በሌሉበት እና መልካም ዕድል ምኞት ሳይለዋወጡ የተደረገው እንግዳው የበዓለ ሲመት እጅጉን የሞቀ ነበር ለማለት ይቻላል። በርግጥ ትራምፕ ባይኖሩም ምክትላቸው የነበሩት ማይክ ፔንስ ከነባለቤታቸው በበዓለ ሲመቱ ላይ ታድመዋል። መርሃ ግብሩ ፍጻሜም ላይ በአዲሲቷ ምክትል ፕሬዘዳንት ካሚላ ሃሪስ ከባለቤታቸው በክብር ሽኝት አድርገውላቸዋል።

በአሜሪካ አንድ የሚያስቀና እና ሁሉም ከዓለም ዳርቻ ያለ ሕዝብ በጉጉት የሚጠብቀው እና የሚደመምበት የበዓለ ሲመት ሥነ ስርዓት ነው። ምክንያት ደግሞ የፕሬዘዳንት መለዋወጥ እና አገር ለመምራት የሚደረገውን ቃለ መሐላ ለመታዘብ ብቻ አይደለም፤ በሒደቱ ውስጥ የሚታየው ሰላማዊው ሽግግር እና ቀዳሚ አመራሮች በስፍራው ተገኝተው ቀጣዩን አገራቸውን መሪ የሚያበረታቱበት እና ደስታውን ተጋርተው ከፍተኛ ሸክም ከፊቱ እንደሚጠብቀው የሚነግሩበት ሁኔታ ቀልብን የሚገዛ ነው። ቀደመው መሪውን ገድሎ በእሱ መቃብር ላይ ዙፋኑን ካላደላደለ የመራ የማይመስለው መሪ ባለባት ዓለም ይህ ከብርቅም በላይ ድንቅ ነው።

ጆ ባይደን 46ኛ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ሆነው ሲመረጡ እና በዓለ ሲመታቸውን ሲፈጽሙ ኹነቱ በእጅጉ ቀልብን የሚገዛ ነበር። ከዚህ ቀደም አሜሪካንን መርተው ግዴታቸውን ተወጥተው የጡረታ ዘመናቸውን የሚኮመኩሙ የቀድሞ አገሪቱ ፕሬዘዳንቶች (በሕይወት ያሉት በእርግጥ ትራምፕን ሳይጨምር አራት ናቸው) ትራምፕ ባይገኙም ቀሪዎቹ ሦስት ፕሬዘዳንቶች ቢል ክሊንተን፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ እና ባራክ ኦባማ ግን በአካል ተገኝተው ከካሜራ ጠፍተው በመክረማቸውም ከናፈቃቸው ሕዝብ ጋር ተያይተዋል።

አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ይህ ሒደት እና ዕድል ኢትዮጵያንም ሆነ መላው አፍሪካን እንዲገጥማት መቼ ይይሆን ሲሉ ጥያቄ አዘል ምኞታቸውን በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች አጋልጠዋል። በዚሁ ዝግጅት ላይ አንድ ቀልብን የሚገዛ ኹነትም ነበር። ተሰናባቹ ምክትል ፕሬዘዳንት አዲሲቷን እና በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያዋን ሴት ምክትል ፕሬዘዳንት ካሚላ ሃሪስ ጋር (ኹለቱም ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ነበሩ) ቆመው ሲጨዋወቱ እና ሲሳሳቁ የታዩበት መንገድ በእጅጉ ቀልብን የሚገዛ ነበር።

ካደረጉት ወቅቱ ወረርሽኝ መከላከያ የፊት መሸፈኛ ጭንብል አፈትልኮ ፌታቸው ላይ የሚታየው ጸዳል ማይክ ፔንስም ሆነ ባለቤታቸው በከፍተኛ ልዩነት ያሸነፉ ተተኪ ፕሬዘዳንት እንጂ ተሸንፈው ወደ መኖሪያቸው የሚያመሩ ተሰናባች በፍጹም አይመስሉም ነበር። ከግዙፉ ‹‹ካፒቶል ሂል›› ሥር ሆነው ሲጨዋወቱ የነበሩት ተሰናባች እና ተተኪ ምክትል ፕሬዘዳንቶች አሁን የመሰነባበቻ ጊዜያቸው ላይ ደርሰዋል እና በነጩ ቤተ መንግሥት የባለሥልጣን አሸኛኘት ቅደም ተከተል መሰረት ረጃጅም እና በርካታ ደረጃዎችን አብረው በመውረድ ተሰናባቹን ምክትል ፕሬዘዳንት እና ባለቤታቸውን አዲሲቷ ፕሬዘዳንት ካማላ ሃሪስ ካባለቤታቸው ጋር በመሆን ሸኝተዋቸዋል። ማይክ ፔንስ እና ባለቤታቸውም ከፊት ለፊታቸው ቆሞ ወደ ሚጠብቃቸው የፕሬዘዳንት ደረጃ ቅንጡ ሙሉ ጥቁር የመስክ ተሸከርካሪ በመግባት ምናልባትም ወደ ጡረታ ጉዟቸው ማዝገም ጀምረዋል።

ቆሞ ወደ ሚጠብቃቸው ተሽከርካሪ እነዛን ለቁጥር የሚዳግቱትን ደረጃዎች በቄንጥ ሲወርዱ ማይክ ፒንስ በእያንዳንዷ ደረጃ መውረድ ውስጥ ከዓለም እና ከመገናኛ ብዙኀንም በዛው ልክ እየራቁ እና እየሸሹ መሄዳቸውን ተረድተውት ይሆን ወይስ በውስጣቸው አፍነው ይዘውት ይሆን? ኢትዮጵያ፣ አፍሪካ የማይክ ፔንስን ዓይነት ተሸናፊ መቼ ይሆን የምናገኘ? በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ጅምር እምብዛም የሚያስከፋ ባይንም ይህን ዓይነት ጉዞ ለመጀመር በእርግጥ ትክክለኛው መንገድ ላይ መሆን አለመሆናችንን ጊዜ ምላሽ ይሰጣል።

አሜሪካ ከቆፈን ጋር በምትታገልበት ብርዳማው ወር ላይ ወደ አዲሱ ቢሯቸው ብቅ ያሉትን ጆ ባይደንን ምክንያት በማድረግ በመላው አሜሪካ የፕሬዘዳንታዊ ሕዝባዊ ትዕይነት መደረጉ በራሱ አሜሪካዊያን ስልጡንነታቸውን ለራሳቸው ብቻ ይዘው ወደ መቃብር የሚወርዱ ስሱ፣ ለሌሎች የማያካፍሉ ብንልም ሊያስኬደን ይችላል። ጆ ባይደን አሁን ነጩን ቤተ መንግሥት በእርግጥም ለቤተ መንግሥቱ አዲስ ባይሆኑም ኖረውበት አያውቁም እና ኑሯቸውን ካደረጉ ሰልስታቸው ነው።

በዓለ ሲመቱ በተከናወነ የሰዓታት እድሜ፥ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን 17 ፕሬዘዳንታዊ አዋጆችን (Presidential Decree) በመፊርማቸው ተግባራዊ ማድረጋቸው ተዘግቧል። ማንኛውም ዜጋ ወደ ፌደራል ሥሪያ ቤቶች ሲሄድ የፊት ጭብል ማድረግ እንዳለበት የሚያስገድደው አንደኛው መሆኑ ደግሞ ፕሬዘዳንቱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመዋጋት ያላቸውን ቁርጠኝት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።

በቀጣይም የመጀመሪያዎቻቸውን 100 ቀናት ዕቅድ ይፋ ወደ ማድረግ እና በትውልድ ቅብብል የቆመችውን አገር አሜሪካንን ከፍ አድርጎ በሁሉም ረገድ ለማውለብለብ የሞት ሽረት እርምጃን ለማድረግ ይታትራሉ። ከአሜሪካ ሰማይ ሥር የለመለመ ተስፋ፣ የሚናፈቅ ነገ፣ የሚከፈት አዲስ ምዕራፍ ይኖራል በሚል ዜጎች ብቻም ሳይሆን አሜሪካንን አምነው የተጠለሉ መጤዎች አንኳን ትኩረታቸው ባይደን ላይ ነው።
መልካም የጡረታ ዘመን ዶናልድ ትራምፕ፤ መልካም የሥራ ዘመን ጆ ባይደን!

ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com