የትግራይ ሰብኣዊ ድጋፍ ጉዳይ

Views: 265

በሰሜናዊ የአገራችን ክፍል የሕግ ማስከበሩ ሂደት ከተጠናቀቀ ወዲህ ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እና የሕክምና አቅርቦቶችን የያዘ የሰብዓዊ ድጋፍ በትግራይ ክልል ለሚገኙ 1.8 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ደርሷል በማለት መንግሥት ተናግሯል።
በአጠቃላይ በክልሉ 2.5 ሚሊዮን እርዳታ ፈላጊዎች አሉ ቢልም ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ቁጥሩን 4.5 ያደርሱታል። ዓለም ዓቀፍ ተቋማት በመንግሥት እርዳታ እንዳናደርስ መንገዶችን ተዘግቶብናል በማለት ለጊዜውም ቢሆን እርዳታ እነዳይሰጥ ጭምር ከልክለዋል። ዳዊት አስታጥቄ የትግራይ ሰብኣዊ እርዳት አቅርቦት ጋር ያሉ ጉዳዮችን በ ሐተታ ዘ ማለዳ አቅርቦታል።

ቅደመ ሕግ ማስከበር በትግራይ በሴፍቲኔት ልማት መርሃ-ግብር ተጠቃሚ የነበሩ 1.8 ሚሊዮን በትግራይ ክልለ የሚገኙ ዜጎች እንደነበሩ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ አሳውቀዋል። በተጨማሪም በትግራይ ክልል ባለፈው የክረምት ወቅት የደረሰው የተፈጥሮ አደጋ በአዝርዕት ላይ ጉዳት አድርሷል፣ የመሬት መንሸራተት፣ የጎርፍ አደጋ እና በበረሀ አንበጣ ወረርሽኙም በክልሉከፍተኛየሆነ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች እንዲኖር አድርጓል።

በሕግ ማስከበር እርምጃው ምክንያትደግሞ ተጨማሪ ዜጎችን የእለት ደራሽ እህል ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓል፣የህግ ማስከበር እርምጃው የተከሰተበት ወቅት ደግሞ ምርት የሚሰበሰብበት ወቅት መሆኑ ራሳቸውን ይችሉ የነበሩ ዜጎችን ሳይቀር እርዳታ ጠባቂ ከማድረጉም በላይ አሁን ያለውን የሰብአዊ እርዳታ የሚሹ ዜጎች ቁጥር እንዲያሻቅብ ብሎም የእርዳታ አቅርቦቱም አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል።

ከሰሞኑም በማሕበራዊ ሚዲያ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጭምር በክልሉ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ተከስቷል ፣መንግሥት የተረጂዎችን ቁጥር አሳንሷል ፣እርዳታም እየደረሰ አይደለም ፣እኛም ገብተን እንዳንረዳ መንገድ እየዘጋብን ነው ፤የሚል ወቀሳ እየተሰነዘረበት ያገኛል።

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ፤ መንግስት በትግራይ ክልል ሲያካሄድ የቆየውን ህግን የማስከበር እርምጃ ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የዜጎች መሰረታዊ ፍላጎቶች ማለትም የምግብ፣ የመጠጥ ውሃ፣ የህክምና እና የመድኃኒት፣ የደህንነት፣ ባንክ፣ ትራንስፖርት የመሳሰሉት አገልግሎቶች አሁንም ያለመሟላት እና ከፍተኛ የሆነ የህግና ስርዓት ያለመከበር ስጋት እንዲሁም ጥቃት ያለባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ከታማኝ ምንጮች አረጋግጫለሁ በማለት በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በክልሉ የመብራት፣ የውሃ እና የባንክ አገልግሎቶች በበርካታ አካባቢዎች መቋረጣቸው ደግሞ ሌላው ሰብአዊ ቀውሱን ያባባሰው ጉዳይ ነው። በመብራት የሚሰሩ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት አገልግሎት መስጠት አቁመዋል። ወፍጮዎችም እንዲሁ። ገንዘብ ያለውም ሰው ቢሆን በባንኮች መዘጋት ምክንያት በገንዘባቸውን አውጥተው መጠቀም አላቻሉም።ከመቀሌ ውጪ ያሉ የመንግሥት ሰራተኞችም ደመወዛቸው እየተከፈላቸው አይደለም ሲልም ገልጿል።

ከሰሞኑም የአለም አቀፍ ተቋማት በትግራይ ክልል እርዳታ እየደረሰ አይደለም፣መንግስት ሰብአዊ እርዳታ እንዳናደርስ መንገዱን ሁሉ ዘግቶብናል፣ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥርም 4.5 ሚሊዮን ነው በማለት መግለጫ አውጥተዋል።
መንግሥት በበኩሉ ዕረዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች መተከልም ሆነ ትግራይ የሚገኙትንም ዜጎች በሚፈለገው መጠን እያዳረስኩ ነው ብሏል።

የቁጥሮች አለመጣጣም
ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚያወጧቸው መረጃዎች እና በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የሚሰጡ አሃዞች አለመጣጣም አዲስ ነገር አይደለም። በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎችን ቁጥር 4.5 ሚሊዮን ሲያደርስ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ 2.5 እንደሆነ ያስቀምጣል። ምናልባትም ተጨማሪ ዳሰሳ እያደረግን በመሆኑ ተጨማሪ 700 ሺሕ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ብለዋል ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ። ስለቁጥሮቹ በዝርዝር ሲያነሱ ፤ከሕግ ማከበሩ በፊት በልማታዊ ሴፍቲኔት መረሃ-ግብር ድጋፍ የሚደረግላቸው 1.8 ሚሊዮን ሰዎች፣ 600 ሺሕ የእለት ደራሽ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው እና 110 ሺህ ደግሞ ቀደም ሲል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በነበሩ ግጭቶች ተፈናቅለው ትግራይ የሚገኙ ሰዎች እና የእነዚህ ድምር 1.8 ሚሊዮን እንደሆነ ኮሚሽነሩ አንስተዋል።

የሕግ ማከበሩ እርምጃ ከተጀመረ በኋላ ደግሞ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ቁጥር ለመለየት በደቡብ፣ በምስራቅ እና በማስከላዊ ትግራይ አካባቢዎች ግብረ-ሃይል በመላክ ዳሰሳ እንዲሰራ ተደርጎ ሁለቱ ቡድኖች ባመጡት መረጃ መሰረት ተጨማሪ 700 ሺህ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ቀሪው አንዱ ቡድን መረጃውን ይዞ ሲመጣ ፣የተረጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል እርግጥ ነው።
በአሁኑ ሰዓትም በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ጠቅላላ 2.5 ሚሊዮን መሆኑን ምትኩ ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት የዓለም ምግብ ድርጅት መርሃ-ግብር እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ትግራይ ውስጥ የረሃብ አደጋ ተደቅኗል ብለዋል።የውጭ አገር ሚዲያዎች የዓለም ምግብ ድርጅትና የውጭ እርዳታ ድርጅቶችን ጠቅሰው በትግራይ ክልል የረሃብ አደጋው በህፃናት ላይ የጠና ነው ሲሉ አስነብበዋል።

እንደ አገር ግን ልምድ ያገኘንበት የ2008 ኤሊኖ ፣ከፍተኛ የድርቅ አደጋዎች እንዲሁም ሌሎች ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲደርሱ ፤ከማንም ቀድሞ የደረሰው የኢትዮጵያ መንግስት ነው ብለዋል።መንግስት ያለው ችግር የሚደብቅበት ነገር እንደሌለው እና ለችግሮች በአስቸኳይ እንደሚደርስ፤ግዴታም እንዳለበት ገልፀዋል።
ነገር ግን ከተለያዩ አካላት የሚወጡ መረጃዎች መሰረታቸው ጉዳዩን በማጮህ ዓለማ አቀፍ ማሕበረሰብ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ ብዙ አርዳታ የማሰባሰብ ፉክክር ያመጣው እንጂ አሃዞቹ መሰረት እንደሌላቸው ምትኩ ካሳ አንስተዋል።

እንደዚህ ያሉ ቁጥሮችን በየዓመቱ ቁጥር ይፋ የምናደርገው ከብሄራዊ አደጋና ስጋት እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪዚደንት አስተባባሪ ጋር በመሆን እንደሆነ እና 4.5 ሚሊዮን የሚለው ቁጥር በጋራ ያላወጣነው በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ለእንደዚህ ዓይነት አሃዞች እውቅና አንደማይሰጥ ትክክለኛ አሃዝ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን ሰብዓዊ እርዳታ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የሚያሟሉት አጋር አካላት እንደሆኑ እና ምናልባትም የፌደራል መንግሥት እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ሊሸፍን አንደሚችል ተናግረዋል።

ለቁጥሮቹ መዛባት እንደ ምክንያትን ያነሱት በትግራይ ብዙ መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን ተከትሎ ፣ባንኮች ስለማይሰሩ፣ ከተማ ያሉትም ቢሆንም ገዝተው ለመብላት ይቸገራሉ በሚል ሊሆን እንደሚችል ኮሚሽነሩ አንስተዋል። ዋናው ግን ጉዳዩን በማጮህ ብዙ ብዙ መጠን ያለው እርዳታ መሰብሰብ ሊሆን እንደሚችል ኮሚሽነሩ ያላቸውን ግምት አስቀምጠዋል።

ዋናው ግን አርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ሳይሆን መንግሥት በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አደጋዎች እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉም ዜጎች እርዳታ የማቅረብ ግዴታ ያለበት መሆኑ ነው፣ይሄንንም እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ እንዳልሆነ የሚናገሩ አካላት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አስበው ነው ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ(ዶ/ር) ተናገረዋል። ሙሉ እንዳሉት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራውን ሲጀምር ለዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ትኩረት አድርጎ ነው። ነገር ግን የሰብአዊ ድጋፍ ስርጭቱ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይደርስ የጥፋት ቡድኑ እንቅፋት እንደነበረ አስታውሰዋል።

የጥፋት ቡድኑ የጭነት ተሽከርካሪዎችን አውድሞና የቀሩትን ይዞ መጥፋቱን ጠቅሰዋል።በጥፋት ቡድኑ ምክንያት ህዝቡ ያለ መብራትና ውሃ በመቆየቱ ለከፍተኛ ችግር ተዳርጓል ‘ድጋፉ እየቀረበ አይደለም’ በሚል ሃሰተኛ መረጃ የሚያናፍሱ አካላት የፖለቲካ ትርፍ በመፈለግ የሚፈጽሙት ድርጊት እንደሆነምጠቁመዋል።
የብሔራዊ አዳጋ አና ሥጋት ኮሚሽንም ፣መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታን በ 10 ክላስተሮች እየሰራ እንደሆነ አስታውቋል።ከእንዚህም አንዱ ፣ በሥነ ምግብ ክላስተር የጤና ሚንስትር ከየተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት አድን ድርጅት(UNCEF) በጋራ እየሰራ አንደሆነ፣ኮሚሽነር ምትኩ አንስተዋል።

ከሰሞኑም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት አድን ድርጅትም በሳምንቱ አጋማሽ ወደ መቐለ እና ማይፀብሪ 8 ሺህ ያህል ካርቶን ምግብና የህክምና አቅርቦቶች እና 2 ሺህ 700 ኃይል ሰጪ ብስኩቶችን ከ 5 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡር ለሆኑ እናቶች እና ጡት ለሚያጠቡ ሴቶች ወደ ስፍራው መላኩን አስታውቋል።
ጥር 3/2013 ላይም ስንዴ፣የስንዴ ዱቄት፣ ዘይት፣ፓስታ፣ሩዝ፣ መኮሮሪ በድምሩ 80,480 ኩንታል ድጋፍ መላኩን ገልፀዋል።በተጨማሪ ህፃናት እና አጥቢ እናቶች ሊኖሩ ይችላሉ ተብሎ በማሰብ 438 ካርቶን የዱቄት ወተት፣ 214 ካርቶን ብስኩት ልከናል ብለዋል።

የጤና ሚንስትር ተጠሪ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ ኤጀንሲም በበኩሉ 3 ሚሊየን 96 ሺህ 657 ብር ዋጋ ያላቸውን ህይወት አድን መድሀኒቶች ወደ ሽረ እያጓጓዘ መሆኑን አስታውቋል።በዋናነት ለእናቶች እና ህፃናት የሚውለውን ህይወት አድን መድሀኒቶች፣ የህክምና ግብዓቶች፣ ለፀረ ወባ፣ ሳንባ ነቀርሳ እና ኤች አይ ቪ ኤድስን ለማከም የሚረዱ እንደ Tetanus Antitoxin, propyithiouracil tablet, pethidine HCL Ampoule, hydrocortisone sodium succinct, Insulin isophane, soluble and biphasic የመሳሰሉ መድሃሐኒቶች ወደ ትግራይ እንደላከ ተነግሯል።

ለሽሬ ቅርንጫፍ ለሁለተኛ ዙር የሚሆን ከ3 ሚሊዮን 96 ሽ 657 ብር ዋጋ ያላቸውን ህይወት አድን መድሀኒቶች ማጓጓዙንም የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ ኤጀንሲ አስታወቋል።

በኤጀንሲው የመድሃኒት እና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ክምችት እና መጋዘን አያያዝ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ገዳምነሽ አስፋው እንዳሉት በዋናነት ለእናቶች ና ህፃናት የሚዉለዉን ህይወት አድን መድሀኒቶች ና ህክምና ግብዓቶችን እንዲሁም ፀረ ወባ: ሳንባ ነቀርሳ፣ ኤች. አይ.ቪ. ለማከም የሚረዱና ሌሎች መድሃኒቶች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

“ ትግራይ ያለው ችግር ዘርፈ ብዙ ነውና የሁላችንንም ኢትዮጵያውያን ርብርብ እና እገዛ እንደሚጠይቅ ተረድተናል፣ሁኔታዎች ተባብሰው ከቁጥጥር ውጭ ሳይሆኑ በፊት አስቸኳይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብሏል ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በመግለጫው ።

እንደ ኮሚሽነር ምትኩ ገለጻ፣ በአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል (ኢ.ሲ.ሲ) የሚኒስትሮች ኮሚቴ መሪነት አፋጣኝ ፍላጎቶችን ለማሟላት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከክልል ቢሮዎች፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅቶችና ከአለም ዓቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ የቴክኒክ ቡድኖችን ያካተተ የአስቸኳይ ጊዜ ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ ማዕከል (ኢ.ኦ.ሲ.) በመቀሌ ከተማ ተቋቁሟልም ብለዋል።

ተጨማሪ ፍላጎቶችን ለመለየት ባለ አራት ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበር ሥርዓት (የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ እና የምግብ ማከፋፈያ ቦታዎችን ያካተተ) ተደራጅቶ ወደ ስራ ተገብቷል። ተለይተው ለታወቁ ተጠቃሚዎች የድጋፍ ሽፋንን ለማሳደግ እንዲሁም በፍጥነት አቅርቦትን ለማዳረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ከልማትና ከሰብዓዊ አጋሮች ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊትም የሰዎችን እና የአቅርቦቶች እንቅስቃሴንደህንነቱ በመጠበቀ የሰብአዊ ዕርዳታውን ቅንጅት በከፍተኛ ደረጃ በመደገፍ ላይ ይገኛል።ስርጭቱ በብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ በአለም ዓቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ (ዩ.ኤን.ኦቻ) አስተባባሪነት በዓለም ዓቀፍና በአገር በቀል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በሴፍቲኔት መርሃ-ግብር (ፒ.ኤስ.ኤን.ፒ) እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ስርጭቱ የሚከናወነው ከአክሱም፣ አዲግራት፣ አላማጣ፣ መቀሌ ዙሪያ፣ ሽሬ እና መቀሌ ከተማ ከሚገኙ የማሰራጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን እና በአጠቃላይ 92 ማሰራጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል።በሂደቱ ለሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች ለምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስና የሕክምና አቅርቦቶች ስርጭት ቅድሚያ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።

መንግስት እና ሰብአዊ አጋሮች እ.ኤ.አ. ኖሼምበር 29 ቀን 2020 በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሠረት በቅንጅት እየሰሩ ይገኛሉ። ከዚህም አንዱ የተጠቃሚዎችን ብዛት በትክክል ለመለየት የጋራ የፍላጎት ዳሰሳና ግምገማ በማካሄድ ላይ እንደሆነ እና በክልሉም 700 ሺህ በላይ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ምትኩ ተናግረዋል።

እርዳታው በፍጥነት ህዝቡ ጋር እንዳይደርስ የተረጂው ብዛት አንፃር ትልቁ ችግር ከዚህ በፊት የሚታወቁት 1.8 ተረጂዎች እንዃን ስም ዝርዝር አለመኖሩ ተግዳሮት እንደሆነ ተነግሯል።

ሌላው የጁንታው ታጣቂ በየቦታው መኖር እና ሽብር ለመፍጠር ቢቻላቸውም ለመዝረፍ የማቀድ ነገር መኖር ሹፌሮች እህል ይዘው አንደ ልብ እንዳይቀሳቀሱ እና እርዳታውን በፍጥነት ማድረስ አለመቻሉን አንስተዋል። የመሰረተ ልማት መውደምም እንዲሁ እርዳታዎቹን በፍጥነት ማድረስ ላይ የራሱ እክል ፈጥሯል ብለዋል።
በእርግጥ አንደ አገር ለትግራይ ክልል በቂ የሆነ ክምችት ቢኖርም በፍጥነት የማዳረስ ነገር ላይግን ውሱንነት መኖሩን ይህም ለትግራይ ክልል ከተላከው የእርዳታ እህል ውስጥ መሰራጨት የቻለው 52 በመቶ ብቻ እንደሆነ ምትኩ ተናግረወዋል።

ለዚህም ያመስላል ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልል እና አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ ወደ ሰብአዊ ቀውስ ሊያመራ እንደሚችል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም ማሳሰቢያ የሰጠው። በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ጨርጨር ወረዳ የሚገኙ የሲቪል ሰዎችደኅንነትና ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ የተመለከተው ኮሚሽኑ አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እና ድጋፍ ሊቀርብ ይገባል ብሏል።

የዲያስፖራው ጩኸት የጀመረው አሁን ቢሆንም በክልሉ አእርዳታ የሚሹ ወገኖች በህውሓት ጊዜም ነበሩ። ያም ሆኖ ግን ኑሮ ውድነቱና ድህነት እንደ ጉድ ተባብሶ ክልሉን ለችግር ቢዳርገውም የትግራይ መሪ ድርጅት ሕውሃትዳቦ የሚፈልገውን ሕዝብ ፕሮፖጋንዳ እየቀለበ ማክረም ችሎ ነበር።

ሆኖም ግን ህውሓት ያመጣውን እና አስቀድሞም የነበረውን ሰው ሰራሽ ርሐብ ከጦርነት ጋር ማዛመድ ልክ አይደለም።ምክንያቱም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተካሄደ ጦርነት የራሱ የሆነ ጉዳት ቢኖረውም 4 ሚሊዮን ሕዝብ ለርሐብ አይዳርግም።

እንደ መውጫ መንግሥት ሕግና ስርዓትን በማስከበር ዜጎቻችን ላይ ያለውን የደህንነት፣ የዝርፊያና የመደፈወ.ዘ .ተስጋት በአፋጣኝ እንዲያስቆም እንጠይቃለን ፤በሰላማዊ ሰዎች እና ባልታጠቁ ዜጎች ላይ የደረሰው አካላዊ ጥቃት፣ ዘረፋ እና የሞራል ድቀት በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ ፍትህ እንዲሰጥ አበክረን እንጠይቃለን በማለት ኦባንግ ሜቶ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ጥር 10 /2013 ባወጣው መጋለጫ አስታውቋል።

ጊዜያዊው የክልሉ መንግስት እስከታችኛው የፀጥታና የአስተዳደር መዋቅር መልሶ ለማዋቀር እየሰራ እንደሆነ ብንገነዘብም በዘላቂነት ስራው እስኪሳካ ከነዋሪው እና ከሌሎች እትዮጵያውያን የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ሰላምና ማረጋጋቱን ለማገዝ የሚችል ግብረ ኃይል በማሰማራትም ጭምር ህግና ስርዓትን በማስከበር የዜጎችን ደህንነት በመጠበቅ አስፈላጊው እርዳታ በወቅቱ እንዲደርስ ማድረግ ይገባል።

ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com