የእለት ዜና

የቡና ቦሎቄና የሰሊጥ የወጪ ንግድ ከፍተኛ መቀነስ አስመዘገበ

ከሐምሌ 2012 እስከ ታህሳስ 2013 ባሉት ስድስት ወራት ከሰሊጥ ቡና እና ቦሎቄ የውጭ ንግድ የተገኘ ገቢ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ 11 ሚሊየን ዶላር በላይ ዝቅ ማለቱ ታወቀ።

የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ዳሬክተር አያልሰው ወርቅነህ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት እነዚህን ሦስት ምርቶች ወደ ውጭ አገራት የሚልኩ የኅብረት ስራ ማኅበራት በዚህ የበጀት ዓመት አጋማሽ ከሐምሌ 2012 እስከ ታህሳስ 2103 ከ 21 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ የተገኘ ሲሆን ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከሐምሌ 2011 እስከ ታህሳስ 2012 ከ 32 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መደረጉን ገልጸዋል።

ለኅብረት ሥራ ማኅበራቱ የውጭ ንግድ መቀዛቀዝ እንደ ምክንያት ያስቀመጡት በአገራችን የተለያዩ ሥፍራዎች የተከሰቱ አለመረጋጋቶች እና የኮሮና ቫይረስ እንደሆኑ አስታሰው በእነዚህ ምክንያቶች በቂ የገበያ ትስስር ባለፉት ስድስት ወራት እንዳልነበረ ገልጸዋል።

አክለውም በተለይ በትግራይ ክልል የሚገኙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እንኳን ወደ ውጭ ንግድ የመላክ ሥራ ይቅር እና ተቋማዊ ቁመና ላይ አይደሉም ብለዋል። በትግራይ ክልል እየተካሄደ በሚገኘው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ምክንያት በተለይ በክልሉ የሚገኙ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት በተፈጸመባቸው ዘረፋ እንዲሁም ሠራተኞቹ በተለያዩ ምክንያቶች ባለመኖራቸው አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነም አስረድተዋል።

የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ እነዚህን የፈረሱ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚጎበኝ ቡድን ከሦስት ሳምንት በፊት አቋቁሞ በመላክ አሁን ያሉበትን ደረጃ አጥንቶ ተመልሷል ብለዋል። በመቀሌ ከሚገኘው የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበር ውጭ ሁሉም አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል ደረጃ ላይ እንዳልሆኑ ቡድኑ አረጋግጦ በመመለሱ ተቋማቱን ወደነበሩበት ደረጃ ለመመለስ እየሠራን እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ አምራች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር የገበያ ትስስር እንዲያደርጉ እና በክልሉ ያለውን የአቅርቦት ችግር እንዲፈታ ማድረግ እንደ አንድ የመፍትሄ እርምጃ ተወስዷል በማለት ተናግረዋል። ባጠቃላይ በክልሉ የሚገኙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የፋይናንስ ድጋፍ እንዲሁም የምርት አቅርቦት የሚሹ ናቸው ብለዋል።

አያልሰው በ2013 የበጀት ዓመት ታህሳስ ወር ብቻ ስምንት የኅብረት ስራ ማኅበራት ወደ የተለያዩ አገራት ምርታቸውን በመላክ ለሀገራችን የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በመጠን ሲገልጹም 849.8 ቶን የቡና፣ የቦሎቄ እና የሰሊጥ ምርት በመላክ 1.9 ሚሊዬን ዶላር ማስገኘት ችለዋል ብለዋል። ምርቶቹ ከተላኩባቸው አገራት መካከል አሜሪካ፣ ቻይና ፣እንግሊዝ እና ሳውዲአረቢያ እንደሚገኙበት ተናግረዋል። እንደ አገር ደግሞ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ተለያዩ አገራት በመላክ በመጀመሪያው ሩብ አመት 832.3ሚሊዮን ዶላር አግኝተናል ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በበኩሉ ሑመራ እና ሽራሮ የሚገኙ የማገበያያ ሥፍራዎች በተከሰተው ወቅታዊ ችግር ምክንያት መዘጋታቸውን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ነፃነት ተስፋዬ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አክለውም ከእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ምርቶች በዳንሻ አብራሃጅራ እና መተማ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በኩል እየደረሱን በመሆኑ ምንም አይነት መቀነስ አልታየም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ተመርቶ ወደ ውጭ ከሚላከው የሰሊጥ ምርት ማካከል 44 በመቶ ያክል በአማራ ክልል የሚመረት ሲሆን 31 በመቶው በትግራይ 13 በመቶው በኦሮሚያ ቀሪው ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በደቡብ እና በጋምቤላ ክልሎች እንደሚመረት አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ሰሊጥ እና ሌሎች የቅባት እህሎች በብዛት ወደ ቻይና እና ሌሎች የእስያ አገራት በዋናነት እንደሚላኩ መረጃው አስቀምጧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com