የእለት ዜና

ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞቹን ቁጥር 50 ሚሊዮን በላይ ማድረሱን አስታወቀ

ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ወራት ያሉትን የደንበኞች ቁጥር 50 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ማድረሱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ አስታወቁ።

ይህ የደንበኞች ቁጥርም ካለፈው ተመሳሳይ አመት ጋር ሲነፃፀር የ 11 ነጥብ ኹለት በመቶ እድገት ማሳየቱን አክለው ተናግረዋል።
በዚህም የአገልግሎት አይነቱ ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 48.9 ሚሊዮን ፣ የመደበኛ ብሮድባንድ ደንበኞች 309 ነጥብ አራት ሺሕ ፣ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 981 ሺሕ እንዲሁም የዳታ እና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 23 ነጥብ አምስት አራት ሚሊዮን እንደሆኑም ተናግረዋል።

በዚህም አጠቃላይ የሞባይል ኔትዎርክ የህዝብ ሽፋን 95 በመቶ እና የቆዳ ሽፋን 85 ነጥብ አራት በመቶ ሲሆን ይህም የቴሌኮም ስርጭቱን 50 በመቶ አድርሶታል ብለዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ስራ አስፈፃሚ እንደተናገሩት ባለፉት ስድስት ወራት 25 ነጥብ አምስት ሰባት ቢሊዮን ብር ገቢ እንደተገኘ በዚህም የእቅዱን 95 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

ይሕ የተገኘው ገቢው ካለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ12 ነጥብ ሶስት በመቶ እድገት እንዳሳየም አክለው አስታውቀዋል።
ይህንን ለማሳካትም የኔትወርክ ማስፋፋት ፣ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ እንዲሁም የደንበኞችን ፍላጎት እና ወቅታዊነት የተላበሱ 21 አዳዲስ እንዲሁም 18 ነባር የአገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ምርት እና አገልግሎቶችን በማሻሻል ለደንበኞች ማቅረብ በመቻሉ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም የተገኘው ገቢ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የገቢ ድርሻ የሞባይል ድምፅ 49 በመቶ ድርሻ ሲኖረው ዳታ እና ኢንተርኔት 26 ነጥብ ሦስት በመቶ ዓለም አቀፍ ጥሪ 10 ነጥብ ሦስት በመቶ እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች 11 በመቶ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች ሦስት ነጥብ አራት በመቶ ድርሻ አላቸው ብለዋል።

የውጪ ምንዛሬ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 80 ነጥብ ኹለት አንድ ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ማግኘታቸውን በዚህም ከእቅድ በላይ ወይም የእቅዱን 105 ነጥብ ሦስት በመቶ እንዳሳካ ይህም ካለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የአምስት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ እድገት ማሳየቱን አስታውቀዋል።

ይህ የተገኘው የውጪ ምንዛሬም አዳዲስ የሆኑ የገቢ ምንጮችን በመተግበር እና የውጪ ምንዛሬን የሚያሳጡ የቴሌኮም ማጭበርበር ተግባራትን በተለያዩ ስልቶች በመከላከል እና ዓለም አቀፍ ቢዝነስ አጋሮች ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር ስራዎች በመሰራታቸው ነው ብለዋል።

ከህግ ማስከበሩ ጋር ተያይዞ ሰሜን ሪጅን ተብሎ የሚጠራው ስፍራ ላይ የቴሌኮም አገልግሎት እንደተቋረጠ ያስታወሱት ፍሬህይወት የቴሌኮም አገልግሎቶችን እንደገና ለማስጀመር ጥረቶች እየተደረጉ እንዳሉ ጠቁመዋል።

በዚህም በአሁኑ ሰአት መቋሌ ብሮድባንድ እና ድምፅ አገልግሎት እንዲሁም ውቅሮ ፣ አዲግራት ፣ ነጋሺ እና እዳጋ ሀሙስ አካባቢዎች የስልክ አገልግሎት መጀመሩን ተናግረዋል።

ሌሎች አካባቢዎችንም የስልክ አገልግሎት ለማስጀመር የጥገና ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ እና የደረሰው ውድመት እና ስርቆት ከፍተኛ ስለሆነ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ለመግባት ግን ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚወስድ አክለው ተናግረዋል።

የህግ ማስከበሩ ሂደት ካመጣው ጫና በዘለለ የተለያዩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በስራችን ላይ ችግር ሆኖብን ነበር ነገር ግን ኔትዎርካችን ሳይነካ መክተን አልፈናል ብለዋል።

በአጠቃላይ የኩባንያው የግማሽ አመት አፈፃፀም በአለማችን እና በአገራችን የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ እንዲሁው በተለያየ ጊዜ አገራችን ላይ ከነበረው የፀጥታ ችግር አንፃር የቴሌኮም አገልግሎቱን ለመስጠት እና ለማስፋፋት ካለው ፈታኝ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ውጤቱ አመርቂ ነው ሲሉ ስራ አስፈፃሚዋ አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com