በሰሜን ዲስትሪክት የፋይበር መስመሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰበት

Views: 613

ኢትዮ ቴሌኮም በሰሜን ዲስትሪክ ከፍተኛ የግንኙነት የጀርባ አጥነት የሆነው የፋይበር መስመር ላይ ከፍተኛ ሆነ ጉዳት እንደደረሰበት እና ይንንም ለመተካት እየሠራ መሆኑን አስታወቀ።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ፍሬሕይወት ታምሩ በመሥሪያ ቤቱ የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ሪፓርት ላይ እንደገለጹት በኢትዮ ቴሌኮም አደረጃጃት ላይ የሰሜን ዲስትሪክት ተብሎ በሚጠራው ክፍል የሚካተተው የትግራይ አካባቢ ላይ ፈጣን እና ከፍተኛ የግንኙነት ማስተላለፊያ የሆነው ፋይበር መስመር ላይ ጉዳት በመድረሱ ይህንንም ለመተካት ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ከመቐለ አቢ አዲ ያለው 98 ኪሎሜትር የሚሆነው የፋይበር መስመር ጥገና ተደርጎለት መጠናቀቁን ያስታወቁት ፍሬሕይወት ከአቢ አዲ ወደ ሽሬ የሚወስደው የፋይበር መስመርም በጥገና ላይ መሆኑን እና አስካሁንም እዳልተጠናቀቀ አስታውቀዋል።

እንደ ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጸ በፋይበር መስመሩ ላይ የገጠመው ጉዳት በአንዳድ ቦታዎች ላይ ከጥገና በላይም ከፍ የሚል እና እንደ አዲስ ተገዝቶ የመተካት ስራ እንደሚያስፈልገውም አስታውቀዋል። መስመሩን ስንዘረጋው ረጅም ዓመታት ፈጅቶብናል ያሉት ፍሬሕይወት ደረሰው ጉዳትም መጠነ ሰፊ እንደሆነም ተናግረዋል።

ከዚሁ በተጨማሪ በተመሳሳይ ስፍራ የኔትወርክ ማማዎች እና ሌሎች የቴኮም መሰረተ ልማቶች ላይ በውድ ዋጋ ተገዝተው የተገጠሙ እና አገልግሎት ሲሰጡ ነበሩ ዕቃዎች በመጥፋታቸው በአጭር ጊዜ ከገበያ ላይ ገዝተን የምንተካቸው አልሆኑም ብለዋል።አያይዘውም ለጊዜው ከሌላ ቦታ በማሸጋሸግ በክልሉ ግንኙነቶችን ለማስቀጠል ርብርቡ ተጠናክሮ እንደቀጠለም አስታውቀዋል። ይህንንም ተከትሎ በአሁኑ ወቅት መቐለ ከተማ የድምጽ ሞባይል ግንኙነት እና የብሮድባንድ ኢነተርኔት አገልግሎት መጀመሩን ገልጸው በውቅሮ፣ ነጋሽ፣ ዕዳጋ ሐሙስ እና አዲግራት የድምጽ ግንኙነት አገልግሎት መጀመሩን አስታውቀዋል።

ከጠፉ እና ከወደሙ ቴሌኮም እቃዎች ጋር በተያያዘ በትግራይ ክልል ግንኙነቶችን ሙሉ በሙሉ ለመመለስ በሚደረገው ርብርብ ላይ በርካታ እና ከፍተኛ ተግዳሮቶች ቢኖሩም የወደሙትን ለመጠገን እና የጠፉትንም ለመተካት ቀን ከሌት እየሰራን ነው ሲሉም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል። በርካታ ውዥንብሮች ስለነበሩ እና ኢትዮ ቴሌኮም በትግራይ በፈቃዱ ግንኙነት እንዳቋረጠ ተደርጎ ሲነገር ነበረውን ለማጥራት ከዚህ ቀደም በካሜራ የተቀረጹ ተንቀሳቃሽ መስሎችን በማስደገፍ አሳተናል ብለዋል። ከዚሁ ጋር አያይዘውም ፌደራል ወንጀል ምርመራ በቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ እና በቅርቡም ይፋ እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል።

ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ያስታወቀ ሲሆን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት የበጀት ዓመቱን የስድስት ወራት አፈፃፀም በሚመለከት ለመገናኛ ብዙኀን ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤
የተገኘው ገቢ ከተያዘው እቅድ የ95 በመቶ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን አብራርተው፤ እቅዱን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት ያልተቻለው በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሳቢያ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም ሆኖ የተገኘው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ12 ነጥብ 5 በመቶ እድገት አሳይቷል ብለዋል። በተጠቀሰው ወራት የውጭ ምንዛሬ ግኝቱም 80 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የሞባይልና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር በየጊዜው እድገት እያሳየ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገልጸዋል።

ከሞባይል ተጠቃሚ ደንበኞች መካከል 64 ነጥብ 3 በመቶው የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መሆናቸውንም የተጠቀሰ ሲሆን፤ እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገለፃ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 39 የተሻሻሉ ምርትና አገልገሎቶች ለደንበኞች መቅረባቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com