አንበጣን ለመከላከል የእስራኤል ቴክኖሎጅ ተግባራዊ አልተደረገም

Views: 380

በኢትዮጵያ ከሰኔ 2011 ጀምሮ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከል ለሚደረገው ዘመቻ ከእስራኤል መንግሥት የተላኩ ባለሙያች እና ቴክኖሎጂ ተግባራዊ አለመደረጉ በሙከራ ደረጃ ላይ ብቻ እንዲቀር መደረጉ ታወቀ።

አራት አባላት ያሉት የእስራኤል ቡድን ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖችን) ይዞ በመምጣት የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት የእውቀት ሽግግር ያደረጉ እና ወደ ሶማሌ ክልል በመሄድ ሥራቸውን እንደሚጀምሩ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም ቴክኖሎጅውን ለመተግበር አስቸጋሪ መሆኑን በግብርና ሚኒስትር የዕፀዋት ጥበቃ ዳይሬክተር በላይነህ ንጉሤ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ከእስራኤል የተላኩ ባለሙያዎች ያሳዩት የአንበጣ መድሃኒት ርጭት 200 ሊትር ፀረ¬-አንበጣ ኬሚካል ለአንድ ሄክታር የሚረጭ በመሆኑ እና አንበጣ የተስፋፋባቸው ቦታዎች በረሃማ በመሆናቸው የኬሚካል መበጥበጫ ውሃ እጥረት ጭምር በመኖሩ የነርሱን ቴክኖሎጅ አልተጠቀምንም በማለት ገልጸዋል። እኛ እየተጠቀምን ያለነው አንድ ሌትር ፀረ¬-አንበጣ ኬሚካል ለአንድ ሄክታር በመርጨት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በላይነህ አክለውም ካለው የአንበጣ መስፋፋት እና ከተከሰተባቸው ቦታዎች በረሃማነት የተነሳ 200 ሊትር ፀረ¬-አንበጣ ኬሚካል ለአንድ ሄክታር መርጨት አዳጋች ቢሆንም ከእስራኤል ከተላኩ ባለሙያዎች የወሰድነው ስልጠና እና ይዘዋቸው በመጡት ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) እየታገዝን አንበጣ የሰፈረባቸውን ቦታዎች በፎቶ እና በቪዲዮ የማስቀረት ሥራዎች ሠርተናል አሁን አንበጣ የመፈለግ ሳይሆን መብረር የጀመረውን አንበጣ በአውሮፕላን በመታገዝ የማጥፋ ሥራ ላይ ነን ብለዋል።
በአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ዙሪያ በቂ ክህሎት ያካበቱ የእሥራኤል ባለሙያዎች ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያንን በማሠልጠን የአንበጣ መንጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች እንደሚሰማሩ እና ይህንን ተግባር የሚፈጽሙ አራት ባለሙያዎችን የያዘ ግብረ ኃይል ህዳር 1/2013 አዲስ አበባ እንደገባ እና የኹለት ሳምንታት ቆይታ እንደሚያደርግ አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም መዘገቧ ይታወሳል።

የእሰራኤል መንግሥት ከባለሙያዎች በተጨማሪ 27 ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) እና ኹለት ጄኔሬተሮችንም ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) በመጠቀም በሌሊት የኬሚካል ርጭት በማድረግ የመከላከል ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይዘው መምጣታቸውን እና በሰው አልባ አውሮፕላኖች በመታገዝ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ መረጃዎችን በመሰብሰብ ውጤታማ የመከላከል ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችል ግብርና ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

በሱማሌ ክልል እና በምስራቁ የአገራችን ክፍል በሚገኙ አሸዋማ ስፍራዎች በኩብኩባ ደረጃ የነበረው አንበጣ መብረር በመጀመሩ አንበጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከሰተባቸው ክልሎች በተጨማሪ አሁን በከፍተኛ ፍጥነት በደቡብ ክልል አርባ ምንጭ አካባቢ በመነሳት እየተስፋፋ በምስራቅ ኦሮሚያ ጉጅ ቦረና እና ባሌ አካባቢዎች እንዲሁም በአፋር ክልል ጭምር እየተስፋፋ እንደሚገኝ በላይነህ አስታውቀዋል።

አንበጣ በተፈጥሮው በራሪ በመሆኑ እና እኛ አገር ላይ ብቻ ስላልተከሰተ ከኬንያ በኩል ወደ አገር ውስጥ በመግባት በምስራቅ ኦሮሚያ ጉጅ ቦረና እና ባሌ ከዚያም ወደ አርባ ምንጭ እንዲሁም ከጎረቤት ሶማሌ እና ከጅቡቲ ወደ አፋር እያለ ድጋሚ በመዛመት ላያ ይገኛል ዘላቂ የሆነው መፍትሄ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር አብሮ መስራት ብቻ ነው በማለት ተናግረዋል።አሁን ከጎረቤት ሶማሌ ጋር አብረን በመሥራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

መንግሥት በትግራይ ክልል እያካሄደ በቆየው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተጠምዶ የአንበጣን ጉዳይ ችላ ብሎታል በማለት እየተነሱ ያሉት ቅሬታዎች አግባብ እንዳልሆኑ ተናግረው በትግራይ ክልል ተከስቶ ለነበረው የአንበጣ ወረርሽን ባለሙያዎች ተልከው እንደነበር አስታውሰው አንበጣው በክልሉ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ወደ ቀይ ባሕር በመብረሩን ተናግረዋል። በላይነህ አክውለውም በ 13 አውሮፕላኖች እና በመኪኖች ታግዘን የፀረ¬-አንበጣ ኬሚካል እርጭቱን እየሠራን እንገኛለን አሁንም አንበጣን ለመከላከል የዘመቱ ከዘጠኝ ወራት በላይ ቤተሰቦቻቸውን ያላገኙ ባለሙያዎች ይገኛሉ ሲሉ ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com