93 ሆስፒታሎች ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የመድኀኒት ብድር አለባቸው

Views: 256

በአገራችን የሚገኙ 93 ሆስፒታሎች በብድር የወሰዱትን ውዝፍ የመድሀኒት ብር ስድስት መቶ 60 ሚሊየን እንዳልከፈሉ በዚህም ኤጀንሲው ፋይናንስ ላይ ጉዳት እንዳደረሰበት በበጀት አመቱ አጋማሽ እንደተረጋገጠ የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅርቢ ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

መድሀኒት ወስደው ክፍያ ያልከፈሉ 93 ሆስፒታሎች እንዳሉ ለአብነትም ጥቁር አንበሣ ጠቅላላ ሆስፒታል እንዲሆም ቅዱስ ፓውሎስ ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ እንደሚገኙበት አዲስ ማለዳ ከኤጀንሲው ያገኘችው መረጃዎች ያመላክታል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅርቢ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አብዱልቃድር ጋልጋሎ ዶ/ር በበጀት አመቱ አጋማሽ ላይ ኤጀንሲው መድሀኒቶችን ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በስድስት ወራት ውስጥ ከነበሩበት ክፍተቶች መካከል ለሆስፒታሎች መድሀኒት የሚሰጠው በብድር እንደሆነ ይታወቃል በዚህም ከአንድ አመት ጀምሮ የብዙ አመታት ብድር ያለባቸው ሆስፒታሎች በብድር የወሰዱትን መድሀኒቶች ገንዘብ አለመክፈላቸው ዋነኛው ችግር እንደሆነ ጠቁመዋል።

ምንም እንኳን መድሀኒት በዱቤ ከወሰዱ በኋላ በአንድ ወር ውስጥ መመለስ እንዳለባቸው የሚያዝ መመሪያ ቢኖርም ለብዙ አመታት ሳይከፍሉ የቆዩ ሆስፒታሎች አሉ ይህም በዋናነት የኤጀንሲው ፋይናንስ ላይ ከፍተኛ ጫና ያለው ሲሆን የፋይናንስ ጫናው ደግሞ መድሀኒቶች በምንፈልገው መጠን መግዛት እንዳንችል ያደርገናል ብለዋል።

መድሀኒቶቹ ታካሚዎች ጋር መድረስ ስላለባቸው ታካሚ በመድሀኒት እጥረት ምክንያት መጉላላት ስለሌለበት ብድር ላለባቸውም ሆስፒታሎች ሲሰጥ መቆየቱን አያይዘው አስታውቀዋል።

በዚህ ሆስፒታሎች በወቅቱ አለመክፈላቸው የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅርቢ ኤጀንሲ ላይ ጫና እየፈጠረበት እንዳለ ጠቁመዋል። በውዝፍ ዕዳ ላይ ያሉት ሆስፒታሎች ብድራቸውን ካልከፈሉ የፋይናስ አቅማችንን እያዳከመው ይሄዳልም ብለዋል።

ይህ በሆነበት ሁኔታ ሆስፒታሎች የመድሀኒት እጥረጥ አጋጠመን ቢሉ አግባብ የለሌው ነው የሚሆነው ብድራቸውን ከፍለው ብር ካላገኘን መድሀኒት በምንፈልገው መጠን ማስመጣት አንችልም ብለዋል።

በዋናነት ያጋጠሙት ችግሮች መካከል ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የአለም መድሀኒት አቅርቦት ሰንሰለቱ ከፍተኛ ጫና ውስጥ መውደቁ እንደሆነ ተናግረዋል።በዚህም ከፍተኛ የአቅርቦት ችግሮች እንዲፈጠሩ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ይህም የሆነበት ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መድሀኒቶች ወደ 80 በመቶ የሚሆኑት ከውጪ አገራት ስለሚመጡ እመንደሆነ እና በውጪ አገራት የሚገኙት መድሀቶች የሚመጡባቸው ኩባንያዎች በኮቪድ 19 ምክንያት የምርት መጠናቸው መቀነሱ ፣ ዋጋ መጨመር ስላለ እንደሆነም አስረድተዋል።

ሌላኛው ችግር ደግሞ የአገረ ውስጥ አምራቾች በኮቪድ ምክንያት ለማምረት የሚያስፈልጋቸውን ጥሬ እቃ በሚፈልጉት ጊዜ ፣ በሚፈልጉት አቅም ለማግኘት በመቸገራቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ኤጀንሲው 19 ቅርንጫፎች አሉት ያሉት ዳይሬክተሩ ሆስፒታሎቹ ካልከፈሏቸው ብድሮች በተጨማሪ የኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ መልኩ ጉዳት እንዳደረሰባቸው አክለው አስታውቀዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ከአገር ውስጥ እንዲሁም ከአገር ውጪ አቅራቢዎች ጋር በመሆን ወደ ስድስት ቢሊየን ብር የሚያወጡ መድሀኒቶችን ፣ የተለያየ የህክምና መሳሪያ እንዲሁም የተለያየ የህክምና ግብአቶች በመግዛት ወደ ኤጀንሲው መጋዘን እንዲገቡ እንዲሁም እንዲሰራጩም ተደርጓል ብለዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ወደ ኹለት ቢሊየን የሚሆን ከኮቪድ 19 መከላከል ጋር በተያያዘ የሚያገለግሉ የህክምና ግብአቶችን በድጋፍም የተገኙትን ጨምሮ ወደ ኤጀንሲው መጋዘን እንዲገቡ እና እንዲሰራጩ መደረጋቸውንም አስታውቀዋል።

በዚህም ባሳለፍነው ስድስት ወራት ኤጀንሲው ያሉትን መድሀኒቶች ለተጠቃሚዎች በማድረስ ረገድ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አስታውቀዋል።
የህግ ማስከበር ሂደቱ በነበረበት ወቅትም የህይወት አድን መድሀኒቶችን ሳይቆራረጥ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አስታውቀዋል። በዚህ የህይወት አድን መድሀኒቶች ላይ የሚፈጠሩ እጥረቶች ሰዎች የአንድ ወር ብቻ መግዛት እየቻሉ አንድ ታማሚ የሦስት እና የአራት ወራት መድሀኒት ስለሚገዛ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com