የምርጫ ቅስቀሳ አጀንዳዎቻችን ምን ይሁኑ?

Views: 208

ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው መጪው ምርጫ፣ ሃምሳ ሚሊዮን ያህል መራጮች እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ትምህርት ለማስተማር የእውቅና ጥያቄ ላቀረቡ ቁጥራቸው 24 ለሚደርሱ ሲቪል ማህበራትም የመጀመሪያ ዙር እውቅና ጥር 13 /2013 ሰጥቷል። እነዚህ ማሕበራት አንድ ዜጋ ድምጽ ከመስጠቱ በፊት ምን ጉዳዮች ማጤን አንዳለበት ማስተማር አብይ ተግባራቸው እንደሆነ ይታመናል።

ሌሎች የሲቪክና የዴሞክራሲ ተቋማትም ታዛቢዎችን እንደሚመድቡ ይታወቃል።ዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ምርጫውን ለመታዘብም ታዛቢዎችን ማሰማራቱ አይቀርም። የምርጫ ቅስቀሳው በይፋ ሊጀመር 16 ቀናት ይቀሩታል። በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፓርቲዎች ምን ጉዳዮችን ላይ ያተኩሩ? ማን የአወያይነቱን ሚና ይውሰድ? የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አባሎቶቻቸው እንዴት መንቀሳቀስ ይገባቸዋል? የሚለውን ጉዳይ ዳዊት አስታጥቄ ባለሙያዎችን አነጋግሮ በሐተታ ዘ ማለዳ አዘጋጅቶታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማከናውን የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርጎ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህም መሰረት 6ተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ለፌደራል እና ለክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች እንዲሁም ለአዲስ አበባ እና ለድሬደዋ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤቶች ግንቦት 28 እና ሰኔ 05 / 2013 ምርጫ እንደሚካሄድ አሳውቆ እየሰራ ይገኛል።

በጊዜ ሰሌዳው ላይ ከተጠቀሱት ተግባራት መካከል አንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክት መረጣም በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የምርጫ ምልክት ማስገቢያ እና ውሳኔ መስጠት ሂደት ላይ ነው።

በተያዘው ሰሌዳ መሰረትም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከየካቲት 08/2013 እስከ ግንቦት 23/2013 ድረስ የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚያከናውኑ ይሆናል፡፤ በዚህም መሰረት ፓርቲዎቹ በምረጡኝ ዘመቻው ወቅት ምን ዓይነት ርእሰ ጉዳዮችን ማንሳት ይገባቸዋል? የትኞቹ አጀንዳዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ብለን ለማየት እንሞክራለን።

የአንድን አገራዊ ምርጫ ውጤት ከሚወስኑ አብይ ሒደቶች መካከል የምርጫ ቅስቀሳ ሂደት አንዱ ጉዳይ ነው። ለምን ቢባል ፓርቲዎቹ የሕዝብን ድምጽ ለመግዛት ፖሊሲዎቻቸውን በይፋ የሚያስተዋውቁበት እና በቃላቸው መሰረት ሊጠየቁ የሚችሉባቸውን ጉዳዮች የሚያነሱበት ብሎም ቃል የሚገቡበት በቃላቸውም መነሻነት በጊዜ ሂደት የሚዳኙበት መድረክ በመሆኑ ነው።

በእርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃሳባቸውን አቀራርበው መሰባሰብ ያቃታቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በበዙበት አገር፣ ህዝቡ ፓርቲዎችን በግልጽ ለመዳኘት የሚችልባቸውን መድረኮች ማግኘት አስቸጋሪ ነው። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት የፓርቲዎች ቁጥር ከግማሽ በላይ ቀንሳል። ቁጥራቸው ግን አሁንም ቢሆን ከሚፈለገው በላይ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ መራጩን ሕዝብ ከማደናገር ባለፈ በትላልቅ አገራዊ ጉዳዮች ወይም አጀንዳዎች ላይ እንዳያተኩሩ ያደርጋል። ከዚህም ባለፈ ተፎካካሪ ፓርቲዎቹንም በተያዙት አጀንዳዎች ላይ ሃሳባቸውን የሚያንጸባርቁበት መድረክ በእጣ ፣አልያም በተራ አንዲያቀርቡ ያደርጋል።ለዚህም ያለፈውን የ2007 አገራዊ ምርጫን አብነት ማድረግ ያቻላል።

በ 2007 በተደረገው ምርጫ ቅስቀሳን እና የክርክር መድረክን ብንመለከት በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከፀደቁት ዘጠኝ የመከራከርያ አጀንዳዎች ለፓርቲዎች በዕጣ ከተከፋፈሉት ነበሩ።ይህ ፓርቲዎች ወሳኝ በሚባሉ የክርክር መድረኮች እና አጀንዳዎች ላይ ሳይቀር እንዳይሳተፉ እንዳደረጋቸው ማየት ይቻላል።፡
በዚያው ዓመት ተፎካካሪ የነበረው መድረክ፣የተካሄደውን የመከራከሪያ አጀንዳ ፌደራሊዝም፣ የከተማና የኢንዱስትሪ ልማት ርእሰ ጉዳይ ላይ አለመሳተፉን ማሳያ አድርጎ ማንሳት ይቻላል።

የኢትዮጵያውን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በበኩሉ በመጀመርያው የክርክር አጀንዳ ማለትም የመድበለ ፓርቲና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚለው አጀንዳ ላይ አልተሳተፈም። ወሳኝ በሆኑት የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲ፣ የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ እንዲሁም በትምህርት ላይ በሚካሄዱ አጀንዳዎች ላይ ሳይቀር ተሳታፊ ያልሆኑ ፓርቲዎች ነበሩ።

ሰማያዊ ፓርቲም እንዲሁ ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው የፌደራሊዝም የክርክር መድረክ በተጨማሪ የከተማና ኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲና በጤና አጀንዳዎች ላይ ተሳታፊ አልነበረም። በአጠቃላይ የፓርቲዎች ቁጥር መብዛት ያመጣው ጣጣ እንደሆነ ግልጽ ነው።

የምርጫ ክርክር አጀንዳዎቻችን ምን ላይ ያተኩሩ?
በ2007 ምርጫ ወቅት ከቀረቡት አጀንዳዎች መካከል ፣ፌደራሊዝም፣የከተማና የኢንዱስትሪ ልማት፣ የመድበለ ፓርቲና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲ፣ የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ እንዲሁም የትምህርት እና ጤና ፖሊሲ አጀንዳዎች ይገኙበታል።

መጪውን አገራዊ ምርጫ ላይ መነሳት የሚገባቸውን አጀንዳዎችን የመምረጥ ሂደት ላይ ነው፡፡ባለፈው ሳምንት ማይንድ ኢትዮጵያ (Multi-stakeholder Initiative for National Dialogue Ethiopia (MIND – Ethiopia የተሰኘ ድርጅት ለብሔራዊ ውይይት የሚያግዙ አጀንዳዎችን ከነሐሴ ወር 2012 ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ፣በተለያዩ መድረኮች ሲያወያይ ቆይቶ ለምክክሮቹ የሚረዱ አጀንዳዎችን እየሰበሰበ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የማይንድ ኢትዮጵያ አባላት የሆኑት አቶ ንጉሡ አክሊሉ ከዴስቲኒ ኢትዮጵያ፣ አቶ ግርማ በቀለ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ እንዲሁም ልዑል በዕደ ማርያም መኮንን ከዕርቀ ሰላም ኮሚሽን በጋራ በመሆን ጥር 14 /2013 በስካይላይት ሆቴል በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በጉዳዪ ዙሪያ ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

አቶ ንጉሡ እንደገለጹት፣ ለተወያዮቹ የቀረበው ጥያቄ ‹‹አጀንዳዎቹ ምን ይሁኑ?፣ ቅደም ተከተላቸውስ? ምን ይሁን የሚሉት ጉዳዮች ላይ በርካታ የአጀንዳ ጥቆማዎች እየተሰበሰቡ መሆናቸውንና በአንድ ቋት ገብተው የመምረጡ፣ የማደራጀቱና ቅደም ተከተል የማስያዙ ሥራ እነደሚከናወን ገልጸዋል።

ሊደረግ አራት ወራት በቀሩት አገራ ምርጫ የምርጫ አጀንዳዎቻችን ምን ይሁኑ በሚለው ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ጋዜጣ የሰጡን የ36 ዓመቱ ጎልማሳ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ጌትነት አክሊሉ. ፣በቀጣዩ ጊዜ በሚኖረው አገራዊ ምርጫ ፓርቲዎች እንዲያነሷቸው ከሚጠብቃቸው አጀንዳዎች መካካል የሥራ አጥነት ሁኔታ ፣የሰላም እና ደህንነት እና ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያ ጉዳዮች፣ እና የመኖሪያ ቤት እጥረት የሚሉት ጉዳዮች በቅድም ተከተል አንዲነሱ እንደሚፈልግ ይናገራል።

አጀንዳዎቹን ከመምረጥ አኳያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውጪ የሲቪል ማህበራት ተወካዮች ፣ከንግድ ማሕበረሰቡ በተለይ እንደ ገበሬ ማህበራት ያሉ የታችኛውን የማህበረሰብ ክፍሎች የሚወክሉ እና ብዙ ቁጥር ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍል የሚወክሉ ሰዎች በጋራ መቅረጽ እንደሚገባቸው ወንድሙ ኢብሳ ይናገራሉ።

ከእንደዚህ ቀደሞቹ የምርጫ ጊዜያት በገዢው ፓርቲ ተጽእኖ በተወሰኑ ወገኖች ብቻ የክርክር አጀንዳዎቹ ተመርጠው ለውይይት መቅረቡ ትክክል አለመሆኑን ይናገራሉ። እንደነዚህ ያሉ አካሄዶች ካልተስተካከሉ ምርጫውን ከማበላሸት ባለፈ ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣት አይችሉም።ይልቁንም በማህበረሰቡ ዘንድ መለያየትን ሊፈጥሩ ስለሚችሉ የክርክር አጀንዳዎቹ አሳታፊ እና በጣም ወሳኝ ጉዳዮችን መምረጥ እንደሚገባው ይመክራሉ።

‹‹ማን ያወያይ?
ማን ያወያይ? በሚለው ጉዳይ ላይ አወያዮቹ ኢትዮጵያውያን ዜግነት ያላቸው እንዲሆኑ የሚል መግባባት መኖሩን ማይንድ ኢትዮጵያ አስታውቆ አወያን መምረጡ ላይ መሥፈርቶች እየተዘጋጁ እንዳሉና መስፈርቶቹም በጠቅላላው የትምህርትና ልምድ ያላቸው፣ በሥነ ምግባራቸው የተመሰገኑ፣ ገለልተኛ ባለሙያዎች እንዲሆኑ እንደሚፈለግ አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከፓርቲዎች ጋር በመሆን ባደረገው ውይይት፣ ከምርጫ 2013 በፊትና በኋላ በቀጣይነት ሊደረጉ የሚገባቸውን የውይይት ነጥቦች መለየታቸውን አቶ ግርማ አስታውቀው፣ የፖለቲካ ምክር ቤቱ አባላት ከሆኑት 44 ፓርቲዎች መካከል 38 ፓርቲዎች በውይይቶቹ ላይ መገኘታቸውን ገልጸው በመስፈርቱ መሰረት ጥቆማዎችን በመቀበል ማን ያወያይ የሚለውን ጥያቄ አንደሚፈታ አስታቀወቀዋል።

ከዚህ ቀደም በነበሩ ምርጫዎች አወያዮች ሆነው የቀረቡ ግለሰቦች መሰረታዊ የሚባል ችግሮች ነበሩባቸው ማለት ግን እንደማይቻል ሃሳባቸውን ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር ለአዲስ ማለዳ ተናገግረዋል።

በክርክር መድረኩ ከሚነሱ ጥቅል አጀንዳዎች ሌላ በመገናኛ ብዙሃን ዝርዝሮቹን ማቅረብ ቢቻል መልካም እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ወጪዎቹ በማን እና አንዴት ይሸፈኑ?
ለውይይቶቹ የሚሆኑ ወጪዎች ከተሳታፊ ተቋማቱ በሚገኝ ገንዘብ የሚሸፈን ሲሆን፣ በአንድ ቋት ከሚቀመጥ ገንዘብ ወጪዎቹ እንደሚሸፈኑ አቶ ንጉሡ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ወደፊት ለሚደረጉ ውይይቶች ድጋፎችን ለማድረግ ፍላጎት ያሳዩ ለጋሾች መኖራቸውን በመግለጽ፣ ገንዘብ የሚሰጡ አካላት ግን በውይይቱም ሆነ በውጤቱ ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ ጥንቃቄ ይደረጋል ብለዋል።

በዚህም አሁን ለዝግጅት ምዕራፉ በፋይናንስ ሰበብ መጓተቶች እንዳይኖሩ ማይንድ ኢትዮጵያን ያዋቀሩ ድርጅቶች ወጪውን እየሸፈኑ እንደሆነ፣ በውይይትና በትግበራ ወቅት ደግሞ የተለያዩ ድጋፎችን ከለጋሾች ለማግኘት እንደሚቻል አስታውቀዋል።

በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ከፓርቲዎች ምን ይጠበቃል?
ፓርቲዎች በምረጡኝ ቅስቀሳና ዘመቻ ወቅት በሚያራምዷቸው ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለሞች እንዲሁም በሚያቀርቧቸው አማራጭ ሐሳቦች ላይ ክርክሮችን ሲያደርጉ፣ መከተል የሚገባቸው አስገዳጅ መመሪያዎች እንደሚኖሩ ያታወቃል።

እንደዚህ ያሉት ሕጎች ዓላማ በፓርቲዎች እንቅስቃሴና ባህርይ ላይ እንዲሁም ፣በምርጫ ዘመቻው ያላቸው ተሳትፎ ላይ ገደብ ለማድረግ ያለሙ ሳይሆኑ ሕገወጥነትን ለመዋጋትና የተሻለ ሥርዓት የመፍጠር ዓላማ እንዳላቸው መንግሥት ይታመናል። ወንድሙ ኢብሳም በዚህ ይስማማመሉ።

በምርጫው ክርክር ወቅት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ከሚመርጡት ቃላት ጀምሮ እስከ አካላዊ እንቅስቃሴያቸው ሳይቀር በጥንቃቄ እና በጨዋነት ማቅረብ ይገባቸዋል ይላሉ።

በ2002 የወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 662/2002 መራጮች በምርጫ ዘመቻው አማካይነት ስለፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲዎችና ስለዕጩዎች ባህሪ የተሟላ መረጃ እንዲሰጣቸው፣ የራሳቸውን በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲያደርጉ የሚያግዙ የሥነ ምግባር መርሆዎችን በዝርዝር ያስቀምጣል።

እንደዚህ ቀደሙ የሌላውን ድክመት በማውራት ላይ ከማተኮር ጥንካሬያቸውን ለማሳየት መታተር እንደሚኖርባቸው ምናልባትም የቅስቀሳ ይዘታቸውን በድጋሚ መከለስ እንደሚገባቸው አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን ይናገራሉ።

ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ኋላ ተመልሶ ከማውገዝ ይልቅ ቢመረጡጥ ሊሰሩ የሚችሉትን ሥራዎች በፖሊሲ ደረጃ በማቅረብ ሕዝብ አንዲዳኛቸው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ይላሉ።

መጪው ምርጫ ሌላው ያለበት እድልም እንበለው ተግዳሮት በኢንተርኔት ማኅበራዊ ድህረ ገጽንና የሞባይል የጽሑፍ መልዕክትን በመጠቀም መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የክርክሩ እና ምርጫ ዘመቻው አንዱ አካል በመሆኑ እሱም ብዙ የገንዘብ አቅም የማይጠይቅ ስለሆነ በጨዋነት መጠቀም እንደሚገባ ይመከራል።
የፖለቲካ ተንታኞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የዲሞክሪሲ ባሕል ባልዳበረባቸው አገራት በምርጫ ቅስቀሳ የምርጫ ውጤት ይለወጣል ብለው እንደማያምኑ ይገልጻሉ። ነገር ግን አገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውና የተቋማዊ ባህል ጅማሮ ላይ የምትገኝ በመሆኗ፣ ቅስቀሳው አስፈላጊ ሆኖ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በኢትዮጵያም የምርጫ ውጤት በምርጫ ቅስቀሳ የሚመሠረትበት ሁኔታ ገና አለመፈጠሩን በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪው ፕ/ር ካሳሁን ብርሃኑ ይገልጻሉ።

ቢሆንም ግን አገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚፈጥሩትን ሰበብ አቁመው፣ ጊዜያቸውን ተጠቅመው ለሕዝብ አማራጭ እንዲያቀርቡ እና የሚኖረውን እያንዳንዱን ቀዳዳ እንዲጠቀሙ ምሁራን ያስገነዝባሉ።

አንድ ምርጫ ነጻ እና ፍትሃዊ የሚያሰኘው ውጤቱ ብቻ ሳይሆን በእያብዳንዱ ቀናት የሚካሄዱ ሂደቶ ጥርቅም ጭምር ስለሆነ፤ ነፃ፣ ፍትሐዊና ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንደዲካሄድ ፖለቲከኞች በተለይ ሥልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ድርጅት አመራር እና አባላት በሕጋዊነት ቅጽር ውስጥ ብቻ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።በተጨማሪም ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮችን ከማድረግ በመቆጠብ ወደ ፊት ሊያሻግር የሚችል ሃሳብ ማቅረብ እንዳለባቸው ምሁራን ይስማማመሉ።

ቀጣዩ ምርጫ ስለፍትሕ፣ ዴሞክራሲ፣ የፕረስ ነፃነት፣ ወዘተ ዓይነት አጀንዳዎች ብዙውን የክርክር ቦታ የሚወስዱ ሳይሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚደረግው የሥራ ፈጠራ፣ የቤት ዕጦት፣ የሕክምና ተቋማት ማስፋፍያ፣ የትምህርት ፍኖተ ካርታና ትምህርት ቤቶችን ማሻሻያ፣ በአገሪቱ ውስጥ የብሔራዊ ከበርቴውን ሊያሳድግ የሚችል የቀረጥ ሕግ፣ ሕፃናትና አዛውንት ተኮር መርሐ ግብር፣ የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ፣ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን መሠረታዊ ልማቶችን ማሻሻያ፣ ተገቢ የሆነ የሞኒተሪና የፊስካል ፖሊሲውን ቀርፆና የምርት አቅርቦት አሻሽሎ የኑሮ ውድነትን መቀነስ፣ በተለይም ደግሞ የሕዝብ ቁጥርን ጭማሪ ፍጥነት የሚገድብ ዕቅድን የተመለከቱ ክርክሮች ትኩረት የሚያገኙበት ይሆናሉ የሚል ግምትም አለ።

ይህ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች በተሻለ ዝግጅትና መሰናዶ በሰላም እንዲጠናቀቅ፣ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ራሳቸውን መግራት ይጠበቅባቸዋል። በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድኅረ ምርጫ ወቅት በሥርዓት ይመሩ ዘንድ የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብ መሰረት መንቀሳቀሰስ ይገባችዋል።

ይህ በፖለቲካ ፓርቲዎች ይሁንታ የሚፀድቅ የሥነ ምግባር ደንብ ገዥ ይሆናል ማለት ነው። ይህንን ደንብና ሌሎች የአገሪቱን ሕጎች በመጣስ የሚፈጸም ድርጊት፣ በፖለቲካ ፓርቲውና በደጋፊዎቹ ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚያስወስድ አውቀወው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።

ከ1960 ጀምሮ ያሉት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች፣ከእኔም ጭምር ፖለቲከኛ የሚለውን መሥፈርት የምናሟላ አይደለንም ይላሉ .ፖለቲከኛ የሕግ ባለሙያው እና የሰብአዊ መብት ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ።

ከራስ ጥቅም እና ክብር ይልቅ ለብዙሃን ድምጽ መሆን ሲገባቸው በሕዝብ ስም ሥራ እና ዝና ለማግኘት የሚሰሩት ፖለቲከኞችን ይዞ አገር ማሻገር አይችልም ስለሆነም በመጪው ምርጫ በፖለቲከኞች መካከል አዲስ የትብብር መንፈስ መኖር አለበት ይላሉ።

የህውሃት ግብኣተ መሬት መፈጸም በዚህ ምርጫ እንደ አገር ካሉ መልካም እድሎች ዋነኛው እንደሆነ እና ሴራን ቀንሶ ህዝብን ማስቀደም ከሁሉም ወገኖች በተለይ ከገዢው ፓርቲ ብልጽግና ይጠበቃል ይላሉ ወንድሙ።በተለይ ብልጽግና ከቀድሞው ኢህአዴግ መለየቱን የሚያስመሰክርበት፣ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድም የሚፈተኑበት ምርጫ ይሆናል ይላሉ።

መጪው ይህ ሲባል ግን መቶ በመቶ ከፈተና ይጸዳል ማለት እንዳልሆነ እና ይልቁንም ያለፉት የሕውሃት መራሹ ኢህአዴግ ክፉ የሴራ ውርሶች ሊጫኑት እንደሚችል ይጠበቃል ብለዋል። እንደዚህም ቢሆን ምርጫውን የሞት እና የሽረት አድርግን መውሰድ አይኖርብንም ይልቁንም የመልካም ምርጫ ጅማሬ አድርገን መውሰድ አለብን ይላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com