የባይደን አስተዳደር የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ለኢትዮጵያ ስጋት ይሆን?

Views: 247

ተሻለ አሰፋ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ/ሕወሓት የሕግ ማስከበር እርምጃውን መውሰዱን ተከትሎ፥ በጦር ሜዳ ያገኘው ድል በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ላይ አልተደገመም ሲሉ ይተቻሉተ። ተጨባጭ አብነቶችንም በመጥቀስ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል፤ መፍትሄ ነው ያሉትም ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።

ታሪካዊ ዳራ
የኢትዮ-አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በዳግማዊ ንጉሠ ነገሥት ምንሊክ ዘመነ መንግሥት ታኅሣሥ 17/1896 መጀመሩን በታሪክ ድርሳናት ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። በዚህ 117 ዓመታት ባስቆጠረው የረጅም ዘመናት ዲፕሎማሳያዊ ግንኙነት እስካሁን የሕንድ ዝርያ ያላቸውን አዲሲቷን ተሿሚ አምባሳደር ጌታ ፓሲን ሳይጨምር 28 አምባሳደሮች፣ ቆንስላዎች ወይም ልዩ ተጠሪ በመሆን በመዲናችንን በመመደብ የአሜሪካ መንግሥትን አገልግለዋል።

ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ አንዳንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ የሚሉበት ወቅት የነበረ ሲሆን በተለይ በቀዳመዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የኹለትዮሽ ግንኙነት ሁለገብነት ማለትም በምጣኔ ሀብት፣ በወታደራዊ፣ በትምህርት፣ ወዘተ የተላበሰ ሲሆን በዘመነ ኢሕአዴግ’ም በተለይ በጸረ-ሽብርተኝነት አጋርነት እና በእርዳታ ድጋፍ ላይ የተመሰረተ ስሙር ግንኙነት ነበራቸው። ይሁንና ከደርግ ጋር በመሰረታዊነት በነበረው የኹለቱ መንግሥታት የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ሳቢያ ግንኙነቱ የተቀዛቀዘ ብሎም ከኢትዮጵያ በተጻራሪ በመቆም ለወራሪው የዚያድ ባሬ ሶማሊያ እንዲሁም በወቅቱ ሽምቅ ተዋጊ ለነበሩት ሕወሓት እና ሻእቢያ ድጋፍ ታደርግ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነበር።

ድኅረ ሕወሓት እስከ የሕወሓት መቃብር
ኢሕአዴግ የ2007ቱን ብሔራዊ ምርጫ መቶ በመቶ አሸንፊያለሁ ብሎ ባወጀ ማግሥት የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ እየበረታ በመምጣቱ በተለይ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አልፎ አልፎም በሌሎች ክልሎች ተቃውሞ በርትቶ በመጋቢት 2010 ጥልቅ ተሃድሶ አድርጊያለሁ በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ሆኗል። በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን መምጣት በአገር ውስጥም ሆነ በተቀረው ዓለም ተስፋን የፈነጠቀ ሆኖ አልፏል። ሽግግሩ ከባድ ተግዳሮት የተሞላ ቢሆንም በተለይ በውጪ መንግሥታት ዘንድ ዐቢይ ዓይን ተጥሎባቸው ከርመዋል። የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው በራሱ እንደ አንድ ማሳያ መውሰድ ይቻላል።

በመጀመሪያዎቹ የጠቅላይ ሚኒስትር የሥልጣን ወራት የአሜሪካም መንግሥት ድጋፉን አሳይቷል። አገሪቱ እያካሄደች ያለችውን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግር እንደሚደግፍ በውጪ ጉዳይ ሚስትሩም ሆነ ተቀማጭነታቸውን እዚሁ መዲናችን ባደረጉት አምባሳደር አማካኝነት በተደጋጋሚ አቋሙን አስታውቋል። በርግጥ የሪፐብሊካን ፓርቲ በመወከል ላለፉት አራት ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆዩት ተሰናባቹ አጨቃጫቂው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተለይ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የሦስትዮሽ ድርድሩን በታዛቢነት በሚሳተፉበት ወቅት ባልተገባ ሥልጣናቸው የኢትዮጵያን እጅ በመጠምዘዝ ለግብጽ መንግሥት መወገናቸውን በአደባባይ አስመስክረዋል። ከዚህም ባሻገር ከሱዳኑ የጊዜያዊ መንግሥት ጋር ባደረጉት የስልክ ግንኙነት ኢትዮጵያ ድርድሩን የማትቀበል ከሆነ ግድቡን ‹‹በቦምብ ማጋየት ነው›› ሲሉ የእብሪት ንግግር ማድረጋቸው ይፋ በመሆኑ እንዲሁም መንግሥታቸው ለኢትዮጵያ ይሰጠው ከነበረው ድጋፍ 130 ሚሊዮን ዶላር ማገዳቸውን የኹለትዮሽ ግንኙነቱ ላይ ጥላ አጥሎበት ነበር።

በተለይ ሕወሓት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቅምት 24/2013 ባደረሰው ያልተጠበቀ ጥቃት፥ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የሕግ ማስከበር ብሎ በጠራው እርምጃ ወይም ‹‹ጦርነት›› ከመክፈቱ በፊትም ሆነ በኋላ በተለይ የቀድሞ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በመንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር ላይ ታች ሲሉ ከርመዋል። በዚህ ረገድ ኸርማን ኮህን፣ ሱዛን ራይስ እና አንዳንድ ሴናተሮች ይገኙበበታል።

በተለይ አንዳንድ የአሜሪካ ባለሥልጣናትም ሆኑ ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ በቅርበት ተገንዝበውት ይሁን ወይም ሕወሓት ከገነባው ጠንካራ ግንኙነት የተነሳ፥ ዘረፈ ብዙ ጫናዎች በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ እያደረሱ ይገኛሉ። ይህንን ሐሳቤን የሚያጠናክርልኝ በካሊፌርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይነስ ፕሮፌሰር የሆኑትና የአሜሪካ ሕገ መንግሥትን፣ ሰብኣዊ መብቶችን፣ የሕግ ተርጓሚው የመንግሥት አካል የአሠራር ሒደት እንዲሁም የአፍሪካን ፖለቲካ የሚያስተምሩት አለማየሁ ገብረማሪያም (በቅጽል ሥማቸው ‹አለማሪያም›) በገጸ ጦማራቸው ላይ በቅርቡ ባስነበቡት ረዘም ጽሁፍ ‹‹በፕሬዘዳንት ባይደን አስተዳደር ውስጥ በቅርቡ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሸሙት አንቶኒ ብሊንክን፣ የብሔራዊ ደህነንት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን እና ከዐሥር ዓመታት በላይ ከፍተኛ የአሜሪካ ዲፕሎማት የሆነችው አሁን ደግሞ በአገር ውስጥ ፖሊሲ ምክር ቤት ኀላፊ ሆና የተሸመችው ሱዛን ራይስን ጨምሮ አንድ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ሴራ የሚሠራ አለ›› በማለት ይከሳሉ። ‹‹ብሊንከን ይናገራል ቃላቱ ግን የሱዛን ራይስ ነው። ሱሊቫን ይናገራል ቃላቱ ግን የሱዛን ራይስ ነው›› ሲሉ ፕሮፌሰር አለማየሁ በተለይ ሱዛን ራይስ ሕወሓት ተመልሶ እንዲመጣ በትጋት እየሠሩ እንደሆነ ጽፈዋል።

የአለማየሁን ሐሳብ ለማጠናከር ለምሳሌ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሌንኬን በሕዳር 9 በለጠፉት የትዊተር መልዕክታቸው ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው ሰብኣዊ ቀውስ፣ ብሔርን መሰረት ያደረገ ግጭት እና የቀጠናው ሰላምና ደህንነት በጥብቅ ያሳስበኛል። ሕወሓት እና የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭቱን ለማቆም፣ ሰብኣዊ እርዳታ እንዲደርስ እና ሲቪሎችን ከለላ ለመስጠት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለባቸው›› ሲሉ ማሳሰባቸው አንደኛው ተጠቃሽ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የሰነዘሩት ማስረጃ ሆኖ ተመዝግቧል።

አለማየሁ አንቶኒ ብሊንከን በሴኔት የሹመት ማረጋገጫ ሒደት ወቅት ለሴናተር ክሪስ ኮኦን ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በግልጽ ‹‹በኢትዮጵያ ላይ የዲፕሎማሲ ጦርነት መግለጫ›› አወጣ ሲሉ ክሳቸውን ያጠናክራሉ። እንዴት ኢትዮጵያን ከሰሜን ኮሪያ፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና ቬተናም ጋር የአሜሪካ ጠላት አድረጋት ሲሉ ይጠይቃሉ፤ ደግሞስ ብሊንከን ኢትዮጵያን ከካሜሮን እና ኡጋንዳ ጋር በመፈረጁ በጣም መናደዳቸውን ጨምረው በመጣጥፋቸው ውስጥ አስፍረዋል።

ሱዛን ራይስ በበኩላቸው ትግራይ የተካሄደው ‹‹የጦር ወንጀል ነው›› ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ማስፈራቸው ከዚሁ የሴራ ጉንጎናው አንደኛው መገለጫ ነው ቢባል ውሃ አይቋጥር ይሆን?

ይህ በእንዲህ እንዳለ አራት የቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሺን፣ አውሬሊያ ብራዚል፣ ቪኪ ሃድልስተን እና ፓትሪሺያ ሃሽለች ባለፈው ሳምንት ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መጻፋቸው ይታወቃል። በትግራይ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ 60 ሺሕ ሰዎች ለስደት መዳረጋቸው፣ 2.2 ሚሊዮን ሕዝብ መፈናቀል እንዲሁም 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ እርዳታ ፈላጎ መሆናቸው እንዳሳሰባቸው ጠቅሰል። የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ውስጥ መገኘታቸው የኢትዮጵያን የድንብር ሉዓላዊነት የጣሰ ነው ሲሉም አክለዋል። በተጨማሪም በመላ አገሪቱ ውስጥ እየተስፋፋ የሄደው ብሔርን እና ሃይማኖትን ያደረገ ግጭት እናዳሰሰባቸው ገልጸዋል።

አምባሳደሮቹ በደብዳቤ መፍትሔ ብለው ያስቀመጡት መንግሥት የሲቪሎችን መብት እንዲያስጠብቅ፣ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ገለልተኛ አጣሪ እንዲጣራ እንዲያደርግ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታትም ሆኑ ሌሎች ተራድኦ ድርጅቶች ያልተገደበ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ‹‹ኢትዮጵያ ሁሉን ሁሉን ዐቀፍ ብሔራዊ ውይይት ያስፈልጋታል›› ሲሉ ምክረ ሐሳብ በማቅረብ ደብዳቤያቸውን ደምድመዋል።

እነዚህ ሁሉ ማስፈራሪያዎች፣ ዛቻዎች እና ምክረ ሐሳቦች የኢትዮጵያን መንግሥት በዲፕሎማሲ ለማንበርከክ የተደረጉ ማሳያዎች ናቸው። ይሁንና ከላይ የተጠቀሱት ሁሉ አንድ መልክ ማሳያዎች ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት በሕወሓት ላይ የተወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃው ‹‹ትክክል ነው›› በማለት ድጋፋቸውን የገለጹ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች አሉ።

ሐምሌ 27/2009 ተሹመው መስከረም 2010 ላይ በኢትዮጵያ ሥራቸውን በይፋ የጀመሩት ማይክል ሬነር፥ ምንም እንኳ የፕሬዘዳንት ትራምፕ ዘመነ መንግሥት ማብቃትን ተከትሎ በቅርቡ ቢሰናበቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደውን የሴራ ፖለቲካ ጠንቅቀው ያወቁ ይመስላሉ። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ትግራይን ያስተዳድር በነበረው ሕወሓት ላይ የወሰደውን እርምጃ የሚደግፍ አንድምታ ያለው ንግግር አድርዋል፤ ስጋታቸውን ከመግለጽ ባይቆጠቡም።

ማይክል ሬነንን በመተካት በቅርቡ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ተደርገው የተሸሙት እና የዘር ሐረጋቸው ከወደ ሕንድ የሚመዘዘው ጌታ ፓሲ፥ ኅዳር 23 በሴኔት የሹመት ማረጋገጫ ሒደት ወቅት ከሴናተር ቦብ ሜንዴዝ ለቀረቡላቸው ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት ከምላሽ መረዳት እንደሚቻለው ኢትዮጵያንም ሆነ ቀጠናውን በደንብ የሚረዱት ይመስላሉ።

‹‹ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ አንድ ትንሽ ቡድን በሆነው ሕወሓት ለረጅም ዓመታት ስትመራ ቆይታለች፤ በዚህ ሁኔታ ላለፈች አገር ሽግግር ማድረግ አስቸጋሪ ነው›› በማለት ወቅታዊውን ሁኔታ የገለጹት ጌታ ፓሲ፥ ኢትዮጵያን ቀፍድደው የያዟት የመሬት ችግር፣ የሥራ አጥነት እና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እድገት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን በመጡ ጊዜ ከፍተኛ ተቀባይነት እንደነበራቸው ያስታወሱት አምባሳደሯ፥ ‹‹ምንም እንኳ ከሕወሓት እና አንዳንድ ቡድኖች ከፍተኛ ተግዳሮት ቢያጋጥማቸውም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት ልናግዛቸው ይገባል›› ሲሉ መናገራቸው በአዎንታዊነት የሚወሰድ ነው።

እዚህ ላይ ትልቁ ቁም ነገር የተሰናባቹም ሆነ የአዲስ ተሿሚዋ አምባሳደር መልዕክት ለኢትዮጵያ መንግሥት ትልቅ ዲፕሎማሲዊ ድል ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፤ ትግሉ ግን መቀጠል አለበት።

ምን ይደረግ?
የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ ከሕወሓት ጋር በገጠመው ጦርነት በሳምንታት ውስጥ ድል ቢቀዳጅም፥ ጥራት ያለው ወቅታዊ መረጃ በማቅረብ እና በዲፕሎማሲውም መስክ ግን ሽንፈት አጋጥሞታል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ከሕግ ማስከበሩ ጋር በተያያዘ ወቅታዊ እና ተከታታይ መግለጫ ያለመስጠት ችግር መዋቅራዊ መሆኑ ተደጋግሞ ተነስቷል። በቀደመው ጊዜ የመንግሥት ኮሚውኒኬሽን የሚባለው የመንግሥት አካል ይሠራው የነበረውን ሥራ አሁን በኀላፊነት እየሠራ ያለ አካል ባለመኖሩ መረጃ በሚፈለገው ፍጥነት፣ ጥራት እና ብዛት እየደረሰ ባለመሆኑ በጦርነቱ ዙሪያ ብዙ ውዥንብሮች ተከስተዋል። መንግሥት የተቆጣጠራቸውን ቦታዎች ለሰብኣዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶ፣ ለተራድዖ ተቋማት ክፍት አለማድረጉ ወንጀልን ሆን ብሎ ለመደበቅ የተደረገ ለመሆኑ እንደማሳያ ቢጠቀስ ምኑ ይገርማል።

በዲፕሎማሲ ግንባርም ቢሆን ኢትዮጵያ የተሳካ ሥራ አልሠራችም ማለት ይቻላል። እንደሚታወቀው አምባሳደርነት በአብዛኛው እንደ ትልቅ ሙያ ተቆጥሮ ችሎታንና አቅምን ያላቸውን ባለሙያዎች ከመመደብ ይልቅ፤ የፖለቲካ ታማኝ የሆኑ፣ ለአገር ውስጥ ፖለቲካው ተግዳሮት ናቸው የሚባሉትን ለማግለል ወይም ደግሞ ለሚኒስትሮች እና ለሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መጦሪያ ተደርጎ ተወስዷል። ይህ በመሆኑ ያልዘሩትን መልቀም እንዴት ይቻላል። የዲፕሎማሲ ሽንፈቱ በዋናነት መሰረቱ ይሄ ነው፤ የእውቀት እጦት፣ የችሎታ ማነስ።

የሆነው ሆኖ አንዳንድ የአሜሪካንን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ በቅርብ ያጠኑ ሰዎች እንደሚሉት፥ የአሜሪካ መንግሥት ከዚህ በኋላ ሕወሓትን ከመቃብር አውጥቶ እንዲደራደር አያደርገውም። የአፍሪካ ቀንድን ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ ያለው ብቸኛ አማራጭ ከኢትዮጵያ ጋር መሥራት አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው ሲሉም ይደመድማሉ።

ያም ሆነ ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት በተጠናና በሳል በሆነ መልኩ የአሜሪካ መንግሥትን አቋም በአዎንታዊ መልኩ ለመለወጥ ሸክሙ በዲፕሎማቶቹ ላይ የወደቀ ነው። መንግሥት የዲፕሎማሲ ጓዳውን ፈትሾ ፈጣን ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅበታል።

የማጠቃለያ ነጥቤ መንግሥት ዲፕሎማሲውን ጠበቅ አድርጎ መሥራት እንዲሁም የመረጃ ፍሰቱንም በተሳለጠ እና ወቅታዊነቱን በጠበቀ መልኩ ተቋማዊ በማድረግ ለለውጥ ይሥራ።

ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com