ጊዜ ወርቅ አይደለም!

Views: 212

የተለመደ ብሂል አለ፤ ‹ጊዜ ወርቅ ነው› የሚል። ብዙዎች በዚህ የሚስማሙ ይመስላል። ተርጓሚና የተግባቦት ባለሞያው በርናባስ በቀለ ግን አይደለም ሲሉ በሐሳብ ይሞግታሉ። እንደውም ጊዜ ከእድሜችን ተቀንሶ የሚሰጠን በመሆኑ ጊዜን ከወርቅ ጋር የሚያወዳድሩ ሁሉ የጊዜን ዋጋ አሳንሰዋልና በወንጀል መከሰስ አለባቸው ባይ ናቸው። ‹ትርፍ ጊዜ› የሚባል የለም፣ ጊዜ ሕይወት ነው ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለዋል። በሥራ፣ በሕይወትና በትምህርት ሰዎች ለጊዜ ያላቸውን የተሳሳተ ዕይታና መደበኛ የሚመስል አመለካከት በትዝብታቸው አካትተው፣ ለተሰጠን ጊዜ ኃላፊነት እንውሰድ ይላሉ።

ሰላማችሁ ይብዛልኝ፤ በሕይወት መንገድ በተሰመረላችሁ መስመር በትጋት እየሮጣችሁ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ። ሩጫው እንዴት ይዟችኋል? ወቅቱ ከባድና አስቸጋሪ እንደሆነ አውቃለሁ ግና አንባቢዎቼ ሁኔታ-መር ሳይሆን ዓላማ-መር እንደሆኑና ጊዜያቸውን በሚገባ እንደሚያስተዳድሩ ከማመን አልቦዝንም።

ባለፉት ወራት ከኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ ትምህርት ቤቶችና ብዙ መሥሪያ ቤቶች ዝግ እንደነበሩ ይታወቃል። የእናንተ መሥሪያ ቤት ሥራ ጀመረ? ያሠራችኋቸው የውኃ መታጠቢያ ገንዳዎችስ አሁንም አገልገሎታቸውን እየሰጡ ነው? ኮቪድ 19 ሲመጣ በየመሥሪያ ቤቱ ደጃፍ የተሰየሙ ግን ከኹለት ወር በኋላ ሥራቸውን ያቆሙ ባልዲዎችና ሮቶዎችስ ከደጅ ተነሱ? ወይስ ተመችቷቸው ቋሚ አድራሻቸው አደረጋችሁላቸው? ይቅርታ! ገና ከጅምሩ ነገር ነገር አለኝ አይደል? ይልቅ እርሱን ልተወውና በትዝታ ፈረስ የኋሊት ልውሰዳችሁና ትላንትናችንን እንቃኝ።

በወቅቱ ብዙ ሰዎች “ይህንን ጊዜ እግዚአብሔር ነው የሰጠን” ሲሉ ሰምቻለሁ። ጊዜውን በሚገባ የተጠቀሙና ለበጎ ዓላማ ያዋሉ ጥቂት ወዳጆችም አሉኝ። እናንተዬ፡- ግን ሰው እንዴት መሥሪያ ቤቱ ሲዘጋ ደስ ይለዋል? ‹ትምህርት የለም› ሲባልስ እንዴት የፍንጥር ይገባበዛል? መሥሪያ ቤትህ ሲዘጋ ደስ ብሎህ ከነበር ሥራህን (ሥራ ቦታህን) አትወደውም ማለት ነው። መሥሪያ ቤትህን ካልወደድክ ደግሞ ሕይወትህን አትወደውም። ‹ለምን?› ያልከኝ እንደሆነ ከሕይወትህ ዘመን እኩሌታ በላይ የሚሆን ጊዜህን የምታሳልፈው ሥራ ቦታህ ነውና። የሥራ ቦታችንን እና የእኛን ነገር አስመልክቶ በሚቀጥሉት ጊዜያት በሰፊው እመለስበታለሁ፤ አሁን ግን ወደ እለቱ ውጥን እናምራ።

ውድ አንባቢዬ፤ እንደ አገር ካጋጠመን ተግዳሮት የተነሳ ትምህርት ቤቶችና መሥሪያ ቤቶች ዝግ ሲሆኑ በቤት መቆየትን ከኃላፊነት ነጻ እንደመሆን ቆጥረህ ነበር ይሆን? አንተስ ተማሪው፡- ትምህርት ቤቶችም ዝግ ስለነበሩ በቀነ-ገደብ (deadline) የምታስገባው የትምህርት ቤት ወረቀት (paper) ሥራ አለመኖሩ አዘናግቶህ ነበር? ሠራተኛ ከሆንክ ደግሞ ‹ዛሬ መጥቷል፣ ቀርቷል?› የሚልህ የቅርብ አለቃ አጠገብህ አለመኖሩ ጊዜው ያለ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ‹ፈታ› (በሸናና!) የምትልበት እንደሆነ አስበህ ነበር ይሆናል። እንግዲያውስ ፍቀድልኝና ልሞግትህ።

የተለመደው ሥራህ በእጅህ አለመኖሩ ከኃላፊነትና ተጠያቂነት እንደማትድን ስነግርህ ከሚወድህ ልቤ ነው፤ የተቀበልከውና የምትጠየቅበት ሌላ ነገር አለና። በምድር ላይ ስንኖር የኑሮ ከፍተኛና ዝቅተኛ ደረጃ እንዳለ የሚታወቅ ነው፤ ግን ተፈጥሮ ለሁሉም እኩል ያደለችን ነገር አለ፤ ሥሙ ‹ጊዜ› ይባላል። በምድር የምንቆይበት እድሜ የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ ግን በአንድ ቀን ውስጥ የተሰጠን ጊዜ ተመሳሳይ ነው። አንተም በቀን 24 ሰዓት ተሰጥቶሃል፤ ሌላውም እንደዚያው። ታዲያ ጊዜ ሲሰጥህ እንድትሠራበት (ኃላፊነት) ሲሆን በአግባቡ ካላስተዳደርክ ትጠየቃለህ። የሚገርመው ባለፉት ወራት እንደሆነው መሥሪያ ቤቶች ሊዘጉ፣ አንዳንድ ሥራዎችህም ሊቆሙ ይችላሉ፤ ግና ጊዜ የሰጠህን አካል (እግዜሩ) ሁሌም ያይሃል፤ ይከታተልሃል (የሰጠህ እንዳሻህ እንድታደርገው አይደለምና)።

ሰዎች ‹ትርፍ ጊዜ ሲኖረኝ› ሲሉ መስማቱ የተለመደ ነው። ሰው እንዴት ጊዜ ይተርፈዋል? ሰዎች ይህንን የሚሉት ከዋናው ሥራቸው ውጭ የሆነ ሰዓት እያሰቡ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ግን እርሱም ቢሆን ‹ትርፍ ጊዜ› አይደለም። ስለ ጊዜ ስናስብ አንድ ነገር እናስተውል! ትርፍ የሚባል ጊዜ የለም። ጊዜ ሁሉ ከእድሜህ ተቀንሶ እንድትኖር የተሰጥህ የአየር ሰዓትህ ነው። ከእንግዲህ ይህች ምን አላት? ‹ትርፍ ጊዜ እኮ ነው!› ሲሉህ አትስማቸው! አንተ ትርፍ ነፍስ የለህማ። የምትኖረው አንዴ ብቻ አይደል? ለምሳሌ፤ ይህ ቀን ኖረህበት የማታውቀው ልዩ ቀን ነው፤ ወደ ፊትም ተመልሰህ አትኖርበትም። መሽቶ በነጋ ቁጥር አንድ ቀን ወደ መጨረሻህ እየተጠጋህ ነው።

መልካም የሚመስል ግን ጊዜን የማይመጥን አንድ የተለመደ አባባል አለ፤ ይኸውም ‹ጊዜ ወርቅ ነው!› የሚል ነው። እኔ በግሌ በአባባሉ አልስማማም። ‹ለምን!?› አላችሁኝ? ጊዜ ወርቅ አይደለማ። በዚህ ጉዳይ ሙግቴን ለማጠንከር ጥቂት ልበል፡- ‹ወርቅ› የተባለውን ማዕድን በቅርበት ለማያውቅና ዋጋውን (value) ጠንቅቆ ላልተረዳ ሰው ወርቅ ምኑ ነው!? ስለዚህ ‹ጊዜ ወርቅ ነው!› ሲባል ሰውዬው ለጊዜ የሚሰጠው ለወርቅ ያለውን ዋጋ ይሆናል።

ሲቀጥል ወርቅ የጌጥና የቄንጥ እቃ ነው! ጊዜ ግን አይደለም። አንድ ሰው ያለ ወርቅ እድሜ ልኩን ሊኖር ይችላል፤ ያለ ጊዜ ግን መኖር አይችልም፤ በጊዜ ውስጥ እንድንኖር ተደርገን የተፈበረክን (የተሠራን) ነንና። በመጨረሻም ጊዜ ወርቅ ቢሆን ኖሮ ጊዜው (እድሜው) ከማለቁ የተነሳ ሊሞት እያጣጣረ ያለ አንድ ባለጠጋ ባለው ገንዘብ ሁሉ ወርቅ ገዝቶ እድሜውን ማስቀጠል ይችል ነበር፤ ግን ጊዜ ከሕይወት እስትንፋስ ጋር የተቆራኘ ነገር እንጂ ቁስ አይደለምና ያንን ሊያደርግ አይችልም። ስለዚህ ‹ጊዜ ወርቅ ነው!› ያሉ ሰዎች (የአባባሉ ባለቤቶች) ባሉበት በቁጥጥር ስር ውለው ተመጣጣኝ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል ባይ ነኝ (የጊዜን ዋጋ በማሳነስ ወንጀል መከሰስ አለባቸው!)። አይመስላችሁም!?

‹ታዲያ ለአንተ ጊዜ ምንድነው?› ብላችሁ ልትጠይቁኝ አስባችሁ ይሆናል። ጊዜ ሕይወት ነው፤ ጊዜና የሕይወት እስትንፋስ የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። የተሰጠንን የሕይወት ዘመን (እድሜ) እንደ ድፍን ብር ብንወስድ ጊዜ ማለት ደግሞ ድፍኑ ብር ሲዘረዘር ማለት ነው። የዘመንና የጊዜ ሁሉ ባለቤት ድፍን ብሩን (እድሜ) ሰጥቶሃል፤ እየዘረዘርክ ለተፈለገበት ዓላማ እንድታውለው (እንድታስተዳድረው) ሾሞሃል። ስለዚህ ጊዜ ካለህ ነገር ሁሉ የምትወደውና ደስ የምትሰኝብት ንብረትህ አይደለም፤ ሕይወትህ እንጂ። ጊዜ እጅህ ላይ ያሰርከው ሰዓትህ መቁጠሪያ ድምቀት የተሠራ ነገር አይደለም፤ የእድሜ ዘመንህ ምንዛሬ እንጂ።

በተለምዶ ‹በእድሜያችን ይህችን ቀን ስለጨመረልን ፈጣሪ ይመስገን!› ሲባል እንሰማለን። ቆይ ግን የዛሬው ቀን የተሰጠን በእድሜአችን ተጨምሮ ነው ወይስ ከእድሜአችን ተቀንሶ? ለምሳሌ፤ እኔ ወንድማችሁ ከተበጀተልኝ የእድሜ ዘመን ግማሹ ወጪ ሆኖ (ሥራ ላይ ውሎ) የቀረኝ እኩሌታው እንደሆነ አስባለሁ። መጋቢት 20/2013 ልደቴን ሳከብር የማስበው በእድሜዬ ሌላ አንድ ዓመት እንደተጨመረልኝ ሳይሆን ከእድሜዬ አንድ ዓመት እንደተቀነሰብኝ ነው። የልደት ቀናችንን ስናከብር የሽኝት ቀናችንም ትዝ ቢለን ጥሩ ነው። እኔ ወንድማችሁ መጋቢት 20 በመጣ ቁጥር የእለቱ ንጉሥ ሆኜ ልደቴ ሲከበር እቆይና እድሜዬ ከዘመን ባንክ (ከዘመን ቋት/ ክምችት ሥፍራ) አንድ በአንድ እየተመዘዘ ያልቅና መጨረሻ ላይ እኔ በሌለሁበት የሽኝት መርሃ-ግብር ይካኼዳል። ስለዚህ የልደት ቀኔ ሻማ፣ ኬክና ሥጦታዎች ስለ ሽኝት ቀኔ የሚሉት አንዳች ነገር አላቸው።

ይኸው መልእክታቸውም፤ ‹ወደ ሞት አንድ እርምጃ ተጠጋህ!› የሚል ነው። ለማንኛውም መጋቢት 20 እንዳትረሱ (ብዙ ነገር እጠብቃለሁ/ ተስፋ ማድረግ አይጎዳምና)። እናንተስ ትላንት አልፎ ዛሬ ሲመጣ ሞት ከትላንት ይልቅ ዛሬ ወደ ደጃችሁ እየቀረበ እንዳለ አስባችሁ ታውቁ ይሆን? ለማንኛውም ግን አንድ ሰዓት ስትኖሩ ወደ ፍጻሜአችሁ አንድ ሰዓት ተጠግታችኋል ማለት ነው።

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩንቨርስቲ) የዓመቱን ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ክረምት የእረፍት ጊዜ ተሰጥቷቸው ወደ ቤተቦቻቸው የሚሄዱ ተማሪዎች እነዚያ ኹለት ወይም ሦስት ወራት የፍጹም እረፍት ጊዜ አድርገው ያስባሉ፤ እውነታው ግን እርሱ ጊዜ ከሚማሩበት ግቢ (ዩንቨርስቲ) የሚያርፉበት እንጂ በሕይወት ቀመር ስሌት የእረፍት ጊዜ ተብሎ የተሰጣቸው አይደለም። ብዙ ተማሪዎች ግን በዚያ ወቅት ከነገ ሕይወታቸው አንጻር ራሳቸውን ማዘጋጀት ሲገባቸው ትርፍና የእረፍት ጊዜ እንደሆነ በማሰብ ከነጋቸው ይተላለፋሉ። ይህ በቀጥታ የሚመለከታችሁ አንባቢዎቼ (ተማሪዎች) እረፍት የተሰጣችሁ ከምትማሩበት ዩንቨርስቲ እንጂ ከሕይወት እንዳልሆነ ሁሌም አስተውሉ።

አንባቢዬ፤ ታዲያ የሚያዘናጉህን ለምን ትሰማቸዋለህ? በቀረህ ጥቂት ጊዜ አንዳች ለትውልድ የሚጠቅም ነገር ጥሎ ለማለፍ ማቀድ ያለብህ አይመስልህም? ያለፈውን ወር ምን ሠራህበት? ይህን ሳምንትስ እንዴት አሳለፍክ? ባለፉት ወራት ኮቪድ የተነሳ መሥሪያ ቤቶች ተዘግተው ቤት በተቀመጥክባቸው ወራት ምን ምን ሠራህ? አሁንም ቢሆን ሥራ ጠፍቶ ቤትህ ቁጭ ካልክ ኹለት ወር ሆኖሃል? እንበልና በምድር የቀረህ 30 ዓመት ቢሆን ኹለቱ ወር የተቀነሰው ከዚያው ከእድሜህ አይደል? ወይስ የእድሜ አስመጪና አከፋፋይ አጎት አለህ!? አይሆንማ! ስለዚህ በጊዜህ የሚቀልድ ሰው በእድሜህ እየቀለደ እንደሆነ ላሳስብህ እወዳለሁ።

ከጊዜ ተላልፈው እርሱም (ጊዜ) በተራው የጣላቸው ሰዎች እንዲያዘናጉህ አትፍቀድላቸው። ለወዳጆችህ የከበረ ሥፍራ እንዳለህ አውቃለሁ፤ ደግ አደረግህ! ሊኖርህም ይገባል። ነገር ግን በጊዜህ ላይ በዋናነት ማቀድና መወሰን ያለብህ አንተ ነህ። ራስህንና የጊዜ አጠቃቀምህን አስተውለህ እንድታይ ስሞግትህ ከንጹህ ፍቅር ከመነጨ መነሻ አሳብ (motive) ነው። ጊዜህን ሚዲያ እና የአየሩ ሁኔታ እንዲመራው አትፍቀድለት፤ አንተው አስተዳድረው! ስላልሠራህበት ጊዜ በመጨረሻ አብሮህ የሚጠየቅ ማንም የለምና። አሳቤን በR. Whitley አባባል ላጠቃል፤ ‹ኃላፊነትን መቀበል የሚገባን ስለሠራነው ነገር ብቻ ሳይሆን መሥራት ሲገባን ሳንሠራው ለቀረውም ጭምር ነው።››

በርናባስ በቀለ የተግባቦት ባለሙያና ተርጓሚ ናቸው፤ በኢሜይል አድራሻቸው barnic@gamil.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com