የእለት ዜና

በቀንጢቻ ማአድን የሚያወጣ ድርጅት ወደ ሥራ ሊገባ ነው

በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ቀንጢቻ የሚገኘውን የቂንጢቻ ታንታለም ማውጫ ውስጥ African mining and energy (AME) የተሰኘ የማአድን አውጪ ድርጅት በ25 ሚሊየን ዶላር በጀት ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከድርጅቱ ለማወቅ ችላለች።

መንግስት የማዕድን ዘርፉን ለባለሀብቶች ክፍት ማድረጉን ተከትሎ ከዚህ ቀደም ባወጣቸው ኹለት ጨረታዎች ላይ ብቻውን ተሳትፎ ኹለቱንም አሸንፎ እንደነበር እና አገሪቷ ላይ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ፍቃድ ሳያገኝ መቅረቱን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የAfrican mining and energy (AME) የባለድርሻዎች ግንኙነት ስራ አስኪያጅ እና የኤሚ ፋውንዴሽኑ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሳሚ ሚሊዮን እንደተናሩት ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የማአድን ስራዎች ላይ የተሰማራ ሲሆን በዘርፉም ከ100 ዓመት በላይ ልምድ ያለው ድርጅት ነው ብለዋል።
መንግስት የማአድን ዘርፉን ለኢንቨስተሮች ክፍት ማድረጉን ተከትሎ መቀመጫውን አውስትራሊያ እና ደቡብ አፍሪካ ያደረገው African mining and energy ድርጅት የቀንጢቻውን የታንታለም እና ሊቲየም ማአድን ለማውጣት ፍላጎት ስላለው መምጣቱን ተናግረዋል።

አፍሪካ ውስጥ 12 አገራት የማአድን ማውጣት ስራ ላይ ተሰማርቷል በዚህም ደቡብ አፍሪካ ላይ የነዳጅ ማውጣት ፣ ቦትስዋና ላይ የአልማዝ ፕሮጀክት ፣ ኮንጎ ላይ የታንታለም እና ሊቲየም ማውጣት ስራ ከሰራቸው ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

በዚህም ማህበረሰብ አቀፍ የማአድን ማውጣት ስራን የሚሰራ ተቋም እንደሆነ የተናገሩት ስራ አስኪያጁ ከዚህ በፊትም ኹለት ጨረታዎች ወጥተው ኹለቱም ላይ ብቸኛ ተወዳዳሪ እንደነበር ተናግረዋል ማህበረሰብን ያማከለ እንዲሁም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራዎችን እንደሚሰራ በዚህም ከትርፉ ከ10 እስከ 15 በመቶ ለማህበረሰቡ ጥቅም ላይ የሚያውል መሆኑን አስታውቀዋል።

አሁን የመጨረሻዎቹ ምዕራፍ ላይ ነን ማሟላት ያለብንን ሰነዶች በሙሉ አዘጋጅተን ጨርሰናል በቀጣይ ሳምንት ሙሉ ለሙሉ መረጃዎቹን ለማአድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል በዚህም በዘርፉ ፍላጎት ያለው እንዲሁም መስፈርት የሚያሟላ ተቋም ነው ፍቃድ ማግኘት ብቻ ነው የቀረን ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ፍቃድ እንዳገኘንም ቦታውን የማፅዳት እና ማስተካከል ስራው የመጀመሪያ ነው የሚሆነው በመቀጠል ደግሞ የታንታለም እና ሊቲየም ማቅለጫ እንገነባለን ምናልባትም በኹለት አመት ውስጥ ስራችንን አጠናቀን እንጨርሳልን ብለዋል። በቀጣይም ለማህበረሰቡ ስለ ማአድን ስራው ማስተማሪያ የሚሆን ልምድ የሚያገኙበት ትምህርት ቤትም እንከፍታለን ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ይህንንም እቅድ ለማሳካት ወደ 250 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገምቷል ቦታው እንደተሰጠው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ እንደሚገባም አስረድተዋል በዚህም በያዝነው ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ፍቃድ አግኝተን ወደ ስራ እንደምንገባ ባለ ሙሉ እምነት ነን ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የማአድና ነዳጅ ሚኒስትር ታከለ ኡማ የማአድን እና ነዳጅ ዘርፉን ለአገር ውስጥም ለውጪም ባለሀብቶች ክፍት ማድረጋቸውን እንዲሁም መስፈርቶች ማዘጋጀታቸውን እና ገንዘብ ስላለው ብቻ ልምድ የሌለው ድርጅት እንደማይገባ እንዲሁም ልምድ ስላለው ብቻ ገንዘብ ሳያቀርብ እንደማይገባ ተናግረው የነበረ መሆኑ ይታወሳል ።

(AME) የማአድን ማውጣት ስራ ብቻ ሳይሆን (AME) foundation እንዳለው እና የተለያዩ የእርዳታ ስራዎችን ለአፍሪካ ሲሰራ መቆየቱን በዚህም ከ11 ሚሊየን በላይ ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩን እና አሁን ቀንጢቻ አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች የውሀ ማውጫ መሳቢያ እንዲሁም ትምህርት ቤት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጡን አዲስ ማለዳ ካየቻቸው መረጃዎች ለማወቅ ችላለች።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ለማውራት የማአድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ፍቃድና ውል አስተዳደር ዳይሬክተር አበበ በዳሳ ለማግኘት በተደጋጋሚ በፅሁፍ መልክትም ሆነ በድምፅ ጥሪ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም።

ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com