የእለት ዜና

ኢትዮጵያ ዓለም ዐቀፍ የቡና የምርት መለያ ይፋ ልታደርግ ነው

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሆነ የቡና የምርት መለያ (ብራንድ) አዘጋጅታ በኢትዮጵያ እና በዓለም አገራት ሕጋዊ ለማድረግ የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

በዓለም ገበያ የኢትዮጵያን ቡና ይወክላል ተብሎ የተዘጋጀው ብራንድ “የኢትዮጵያ ቡና” ሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ብራንዱ ኢትዮጵያን በሚገልጽ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን በኢትዮጵያ ካርታ ላይ የተሰራ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) የባለስልጣኑን የ2013 የስድስት ወር እቅድ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለግብርና፣ አርብቶ አደርና አከባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥር 19/2013 ባቀረቡበት ወቅት አዲስ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ቡና ብራንድ ከአንድ ወር በኋላ ይመረቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ብራንድ አርማ ኢትዮጵያን በሚገልጹ መነሻ ሀሳቦች የተቀረጸ ነው ተብሏል። በዚሁ መሰረት አርማው የኢትዮጵያ ካርታን ያካተተ እና በአፈ ታሪክ የሚነገረውን ኢትዮጵያ የቡና መገኘ ናት የሚለውን ሀሳብ ያካተተ ነው ተብሏል። ኢትዮጵያ አስካሁን ለዓለም ገብያ የምታቀርበው የቡና ምርት በአቅራቢዎች ምርጫ በተሰየሙ ስያሜዎች እንደነበር ተጠቁሟል።

የተዘጋጀው ብራንድ በኢትዮጵያ በሕግ ከጸደቀ ብኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ ቡናዎችን ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ላኪዎች ብራንዱን መጠቀም ይችላሉ ሲሉ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል። ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ብራንዱን ኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ ከማጽደቅ ሂደቱ በተጨማሪ በዓለም አገራት ለማስመዝገብ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ባለስልጣኑ በጋራ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በዚሁ መሰረት የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(United Nations Industrial Development Organization) ለኢትዮጵያ በዓለም የቡና ገበያ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል የተባለው ብራንድ በአውሮፓ ለማስመዝገብ ቃል መግባቱን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አረጋግጠዋል። በተጨማሪም የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (United States Agency for International Development)የኢትዮጵያ ቡና ብራንድን በዩናይትድ ስቴት ለማስመዝገብ ፈቃደኝነት መሳየቱን ዋና ዳይሬክተሩ አክለው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የቡና ምርት ብራንድ በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስመዝገቧ በቡና ምርት የተሻለ ገቢ ማግኘት እንድትችል በር ከፋች እንደሚሆን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የተሰማሩ ቡና ላኪዎች የኢትዮጵያ ቡና መለያ የሆነውን ብራንድ በመጠቀም ለራሳቸውም ለአገራቸውም የተሻለ ገቢ እንደሚስገኙ ይጠበቃል ተብሏል።

ኢትዮጵያ በቡና ምርት ማግኘት የሚገባትን ያክል ገቢ እያገኘች አይደለም የሚለውን ቅሬታ በአዲሱ ብራንድ የኢትዮጵያን ቡና በተሻለ ሁኔታ ማስተዋወቅ እንደሚቻል ተመላክቷል። እንዲሁም ብራንዱ በራሱ አንድ የገቢ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገልግል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ አርብቶ አደር እና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ ኢትዮጵያን በቡና ምርት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል ስርአት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል። እንዲሁም ቡና አምራች የሆነው አርሶ አደር የሚያመርተውን ቡና በተሻለ ጥራትና ዋጋ ለዓለም ገብያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ ማግኘት የሚችልባቸውን አሰራሮች መቀየስ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የውጭ ንግድ መጠን በገቢ ከማሳደግ አኳያ የቡና ኤክስፖርት ከአምራች እስከ መዳረሻ ገበያ በማስተባበር፣ በመከታተል፣ በመደገፍና በመምረት በመጀመሪያ ስድስት ወራት ከ139 ቶን በላይ ቡና በመላክ 525 ሚሊየን ዶላር ለማስገኘት ችሏል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቡና ብራንድ ማስመዝገቧ በዓለም ገብያ የሚኖራትን ድርሻ ለማሳደግና የቡናን ምርት ለማስተዋወቅ ፈር ቀዳጅ እንደሚሆን የብራንድ ስትራቴጂስት ሳሙኤል አለማየሁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። እንደ ሳሙኤል ገለጻ ብራንዱ ኢትዮጵያን ቡና በዓለም ገብያ በስፋት ለማስተዋወቅ እድል ከፋች ቢሆንም ከደረጃ በታች የሚመረቱ ቡናዎችን በኢትዮጵያ ብራንድ የሚካተቱ ከሆነ ብራንዱ ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ሳሙኤል አክለውም ኢትዮጵያ የብራንድ ሥራ አለመስራቷ የዘገየ እንደሆነ ጠቁመው አሁንም የኢትዮጵያን ቡና በስፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነቱን ለማሳደግ ከፍተኛ የማስተዋወቅ ሥራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com