የእለት ዜና

የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ሊወጣ ነው

የንግድ እና ኢንደስትሪ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅን ለማውጣት የንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስተር ከንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመሆን በረቂቁ ላይ ውይይት እያካሄደ ይገኛል።

በ1995 የወጣ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/95 የነበረ ሲሆን ከ 18 ዓመታት በኋላ በመሻሻል የንግድ እና ኢንደስትሪ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ተብሎ ለመውጣት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር እና የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በጋራ እየተወያዩበት መሆኑን የንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስትር ሚኒስትር ዴኤታ እሸቴ አስፋው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከ18 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/95 ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ለውጥ ብሎም የንግድ እንቅስቃሴና ዘርፉ ከሚፈልገው አሠራር ደረጃ አንፃር ብዙ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑን በማመን፣ በተለይም አዋጁ ለትርጉም የተጋለጡ፣ ለትግበራ የማይመቹና ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይሄዱ ድንጋጌዎችን የያዘ ብቻ ሳይሆን የንግድ ምክር ቤቶችን በእጅጉ ያዳከመ መሆኑ ለአዋጁ መሻሻል እንደ ምክንያት መነሳታቸውን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል ።

ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች ለመፍታት እና የቀደመው የንግድ እና ኢንደስትሪ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ አሉ የተባሉ ክፍተቶችን ለመሙላት አሁን የወጣው ረቂቅ መዘጋጀቱንም በኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የግልግል ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ዮሐንሥ ወልደገብርዔል ያስረዳሉ።

ስያሜው ንግድና ኢንዱስትሪ ማለቱ በራሱ ሌሎች የንግድ ዘርፎች ምን ሊሆኑ ነው የሚለውን ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን፣ እንደ ቱሪዝም፣ እርሻ፣ ትራንስፖርትና ሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች ሳይታሰቡ ነው ወይ? ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የሚባለው ለሚለው ጥያቄም ምላሽ ሲሰጡ እንዲህ ያሉ ብዥታዎችን ሁሉ ለማስቀረት ሁሉንም የቢዝነስ ዘርፍ በማጠቃለል የሚችል ረቂቅ ተዘጋጅቷል በማለት ተናረዋል።

ረቂቁ የቦርድ አባላት ሲመረጡ ስብጥራቸው ምን መምሰል እንዳለበትም ያስቀምጣል። በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የቦርድ አባላት ስብጥር፣ ከክልል የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች 50 በመቶ፣ ለአገር አቀፍ ደረጃ ከሚቋቋሙ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማኅበራት 40 በመቶ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚቋቋሙ የንግድ ሥራ ዘርፍ ማኅበራት 10 በመቶ፣ ያካተተ መሆን አለበት ይላል። የክልል የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች የቦርድ አባላት ስብጥር፣ ከግለሰብ ነጋዴዎች 10 በመቶ፣ ከሽርክና ማኅበራት 20 በመቶ፣ ኃላፊነታቸው ከተወሰነ የንግድ ማኅበራት 20 በመቶ፣ ከንግድ ሥራ ዘርፍ ማኅበራት 10 በመቶ ያካተተ መሆን እንዳለበትም ይገልጻል። ይህ ክፍፍል በቀድሞው አዋጅ የሌለ ሲሆን፣ በአዲሱ ረቂቅ ላይ ግን የቦርድ አመራር እንዲህ ባለው መንገድ መዋቀር ይኖርበታል ብሎ ደንግጓል።

የአዲስአበባ የንግድ ምክር ቤት በ1939 የተቋቋመ ሲሆን መንግሥታዊ ያልሆነ የነጋዴዎች ማሕበር እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ነገር ግን ይህ ማሕበር ሁሉንም የአገራችን ክፍል ባለመወከሉ በድጋሚ በ1970 በመላው ኢትዮጵያ ለማቋቋም የንግድ ምክር ቤቶች መቋቋሚያ አዋጅ የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶለት መቋቋሙን ዮሐንሥ ያስረዳሉ ይህ አዋጅ እስከ 1995 ካገለገለ በኋላ ድጋሚ መሻሻል ስለሚያስፈልገው እርሱን ለመተካት ረቂቅ ተዘጋጅቷል ሲሉ አስረድተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!