‹ክብር› የተነፈገው የመምህርነት ሙያ

Views: 194

ሙያውን እጅግ አብዝቶ ይወደዋል።አስደሳች ነገሩ ሁል ጊዜም ከእውቀት ጋር የተገናኘ እንደሆነም ይጠቀሳል። ተማሪዎችን ለማሳወቅም መገናኛ ብዙሃንን መከታተከል እና ለመረጃ ቅርብ መሆንም ግድ ይለዋል። የትኛዎቹንም የዓለም ክስተቶችን ለማወቅ እና ለመረዳትም ቅርብ ነው። ሙያው ኹለት ገጽታዎችም እንዳሉትም ይገልጻል ።በአስቸጋሪ እንዲሁም በፈተና የተሞላ ቢሆንም እንኳን አስደሳች ነገሩ ያመዝናል ። እንዴት ከተባለም ትውልድን ከመቅረጽ አኳያ እሳቤው እና ኃላፊነቱ ከባድ ስለሆነ። ሙያው ምንድ ነው? ካሉ መምህርነት ይላል። በአዲስ አበባ ከተማ በመንግስት ትምህርት ቤት የአማርኛ መምህር የሆነው ካሳሁን መኩሪያ(ስሙ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል የተቀየረ) ስለ መምህርነት ሙያ ሲናገር ።

መምህርነት እና ፈተናዎቹ
ካሳሁን ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ እስከ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአማርኛ መምህርት ማስተማር ከጀመረ ሰባት ዓመታት አልፈውታል። በአሁን ወቅት በመንግስት ትምህርት ቤት ውስጥ እያስተማረ የሚገኘው መምህሩ፤ በዚህ ሙያ ውስጥ ብዙ ፈታኝ ነገር እንዳለ ያወሳል። ‹‹በተማሪዎች ላይ የሚታየው የባህል ወረርሽኝ አንዱ ነው። የልጆች አስተዳደግም ቢሆን የመምህርነትን ሙያ ፈተና ውስጥ ቢከተውም ሙያችን ለአገር ያለውን አስተዋጽኦ በማሰብ እየሰራን እንገኛለን።››
ትውልድን በመቅረጽ እና በማነጽ በኩል ሚናቸው ከፍተኛ የሆኑ ብዙ መምህራን ተማሪዎቻቸው ትልቅ ቦታ ደርሰው ሲመለከቱ እንደነሱ የሚደሰት የለም ። ነገሩ ይህ ሆኖ ሳለ ግን በማህረሰቡ ዘንድ እና በመንግስት በኩል የተሰጠው ትኩረት አናሳ እንደሆነ ሲናገሩ ይሰማል።በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ የእንግሊዘኛ መምህር የሆነው ሳምሶን አክሊሉ ይህን ሃሳብ ይጋራል ‹‹ እኛ ብዙ ቅሬታ ነው ያለን። የጥቅማጥም ጉዳይ ቀርቶ የሚከፈለን እና የምንሠራው ክፍያ እንኳን ተመጣጣኝ አይደለም።››በማለት ነበር በምሬት የተናገረው።

ትዕግስት መኮንን እሷም ቅረታዋን ታሰማለች። ዛሬ ላይ ስሙን መጥቀስ በማትፈልገው የግል ትምህርት ቤት ውስጥ በቅድመ መደበኛ (ኬጂ) መምህርነት ለኹለት ዓመታት አስተምራለች። አሁን ላይ ደግሞ የሥራ ዘርፏን በመቀየር በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ እየሰራች ነው የምትገኘው። ታዲያ ትዕግስት ስለ ቀድሞ ትምህርት ቤቷ ስትናገር ‹‹ባለቤቶቹ እኛን ከምንም አይቆጥሩንም። ተማሪዎቹ ጥፋተኛ እንኳን ቢሆን እኛን ነው የሚቆጡት። ብቻ በአጠቃላይ ሥራው ‹ባርነት› ነው። ወላጆችም ቢሆኑ እንደፈለጉ ነው ተናግረውን የሚሄዱት ታዲያ ባለቤቱ ያለከበረን እንዴት ከሌላ ሠው ክብርን እንጠብቃለን?››በማለት ነበር ሃሳቧን በጥያቄ መልክ ያሰማችው ።

‹‹መንግስት ለመምህራን ትኩረት አልሰጠም። ለምሳሌ እንኳን ልዩ ጥቅምን ከመስጠት አንጻር የተሰሩ ሥራች አሉ ብሎ ድፍሮ መናገር አይቻልም።›› ሌላው ይላል ካሳሁን ፤‹‹ቀድሞ በነበረው ሥርዓት መምህርነት እንዲዋረድ፣ ዝቅ እንዲል ወይም ሙያው ዝቅ እንዲል ያደረገው መንግስት ነው።ለዚህ እንደ ማሳያ የመምህራን ማህበራት ጠንካራ በመሆናቸው መንግስት ላይ ጫና ፈጥረው ነበር። ይህ በመሆኑም እንደ መፍትሔ የታሰበው መምራንን ማስጨነቅ፣ በተለያየ መንገድ ጫና ማብዛት፣ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዳያገኝ ማፈንም ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው። እንደውም አንዳንዶቹ ላይ ያልሰሩትን ሥራ ሠርተሃል በማለት እስከማባረር ተደርሷል።›› በማለት የሚናገረው የአማርኛ መምህሩ ካሳሁን ነው።

አሁን ላይ በመንግስት በኩል እየተሰሩ ያሉ መልካመ ሥራዎች አሉ ለአብነትም የቤት አበል ክፍያም መስተካከሉመ በጥሩ ጎብ ይነሳል። ይሁን እንጂ ለባለሙያተኞቹ የሚሰጠው ‹ክብር› የለም በሚባል ደረጃ ላይ መድረሱም ይጠቆማል። ‹‹ለዚህ አንዱ ማሳያ አብዛኛው መምህርራን የተለያዩ ትምህርቶችን በመማር የሥራ ዘርፋቸውን እየቀየሩ ነው። እድገት እንኳን ሲኖር ፓለቲካዊ አመለካከታችን ድርሻ አለው ። አስተዳደራዊ ሥራዎችም ቢሆኑ በመመሪያው እና ሥራው በሚያዘው መንገድ ሳይሆን ነገሩን በቅርበት (ጓደኝነት) የሚሰጥ መሆኑም ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል ።››ሲልም ያክላል-ካሳሁን።

ድሮ እና ዘንድሮ
ሰለሞን መኩሪያ ይባላል። የሦስት ልጆች አባት ነው። በትምህርት ሕይወት ካለፈ ብዙ አመታትን አሳልፏል። እርሱ ተማሪ በነበረበት ጊዜ የነበረውን ነገር ያስታውሳል። መምህራኖቻቸውን በጣም እንደሚወዱ እና እንደሚያከብሩ በመግለጽ ። ‹‹ተማሪዎቻቸውን በጣም የሚማቱ እና ኃይለኛ የሚባሉ መምህራኖች ነበሩን። እነርሱንም ቢሆን በጣም እንወድ ነበር። ለምሳሌ በእኛ ጊዜ የገና በዓል ሲከበር ከተማሪዎች ገንዘብ ሰብስበን እናዋጣ እና እናከብር ነበር።በዚህም ጊዜ መምህራኖቻችንን እንጋብዝና ሥጦታም እንሰጣቸው ነበር።›› ያለ ሲሆን አሁን ግን ይህ ነገር ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለም።

‹‹እኛ ተማሪ በነበርንበት ጊዜ ለመምህራኖቻችን ብዕር፣ የተለያዩ መጸሐፍት እና ሌሎቸ ሽልማቶችን እንሰጥ ነበር። አሁን ግን ፍጹም የለም በሚባል ደረጃ ይህ ነገር አይታይም። እኔም ለዚህም ነገር ምስክር መሆን እችላለሁ። በመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን ጓደኞቼም ቢሆኑ ይህ ነገር እንደ ቀረ ነው የነገሩኝ።›› ሲል የሰለሞንን ሃሳብ በመጋራት የሚናገው የእንግሊዝኛ መምህሩ ሳምሶን ነው። ይልቁንም ትምህርት ቤቶች ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው ለሚወጡ ተማሪዎች የተለያዩ ሽልማቶችን እንደሚሰጡ ነው የሚናገሩት- መምህራኑ።

ትዕግስት ከዚህ ቀደም የነበረውን ነገር ታስታውሳለች ‹‹የድሮ መምህራን እኮ የሚሰጣቸው ክብር በራሱ ደስ የሚል ነበር ። አሁን ላይ ሳስበው ወደዚህ ሙያ ዳግም የመመለስም ሃሳብ የለኝም።›› ስትል ፤ ሳምሶን በበኩሉ ‹‹ማህበረሰቡ ይቅር እና አሰሪዎቻችን መጀመሪያ ለእኛ መች ክብር አላቸው? ሲል ይጠይቃል። ‹‹ክብራችንን ተትን መብታችን እንኳን ማስከበር አልቻልንም።›› ሲል ነገሩን በምሬት ያስረዳል።

ካሳሁን መናገሩን ቀጥሏል ‹‹ከዚህ በፊት በመምህርነት ሙያው ውስጥ ጥሩ የሚባል እርሾ ነበር። ይህም ማክበር እና መውደድ ነበር። መምህሩ ሌላውን ለማሳወቅ ዋጋ እየከፈል አንደሆነም ብዙዎች ይረዱት ነበር። የቀድሞ ማህበረሰብም ይህንን በይበልጥ ይረዳል። አሁን ላይ ባለው ማህረሰብ ግን መምህርነት የድህነት ተምሳሌት አድረጎ መቁጠር በስፋት ይታያል።›› እንደውም ይላል ‹‹ ብዙ መምህራን ከሌሎች ሠዎች ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር ‹እኔ እኮ መምህር ነኝ› ብለው ደፍረው መናገር የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።››

እንደ መምህራኑ እይታ እና በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ያስተዋሉት የተማሪዎች ሥነ ምግባር አሳሳቢ መሆኑን፤ በማህበረሰቡ በኩልም የሚታሰበው ትውልድን እያፈራ ሳይሆን ከተማሪዎች ጋር ሲጯጯህ እንደሚውል እና ጊዜውን በፍጭት የሚጨርስ አድርጎ የማሰቡ ነገር እየበረታ መምጣቱን ለአዲስ ማለዳ አልሸሸጉም።
መምሃራኖቹ አንድ ነገር ግን እርግጠኛ ናቸው። የዚህ ሁሉ ችግር የወላጆች አስተዳደግ፣ ተማሪዎቹ በራሳቸው እያሳዩ ያለው ከፍተኛ የሚባል የሥነ ምግባር ችግር እና መገናኛ ብዙሃኑም ተዳምረው ያመጡት እንደሆነ። ይህ ማለት ግን ሁሉም መምህራን ችግር የሌለባቸው ናቸው ብሎ ማሰብ እንዳልሆነም መምህራኑ ያሳስባሉ። አያይዘውም አሁን ቢሆን መምህሩን የሚሳደብ እና የሚያንጓጥጥ ተማሪ እንዳለ ሁሉ የድሮውን ጊዜ ክብር የሚያስትውስ ከጥሩ ቤተሰብ የተገኙ መልካም ተማሪዎች እንዳሉም ይናገራሉ።

የመምህራቹ የነገ ተስፋ
ዛሬ ላይ ነገሮች ጨለማ ይምሰሉ እንጂ ነገ ብርሃን እንደሚወጣ ያምናሉ- ያነጋገርናቸው መምህራን። ነገሮች በዚህ ችግር ይቀጥላል ብሎ ማሰብ ወይም ሙሉ በሙሉ መደምደም አይቻልም የሚሉት መምህራኖቹ እነዚህ ነገሮች በጊዜ ሂደት ውስጥ ይፈታሉ ብለው ተስፋም ያደርጋሉ። ጥቄዎቻቸውንም ቢሆን ለመንግስትም ይሁን ለግል ተቋም በማስረዳት እንደሚፈታም በፅኑ ያምናሉ።

ከዚህ ጋር በተያያዘም አዲስ ማለዳ የመምህራን ማህበር እየሰራ ስላለው ሥራ ጥያቄዋን አቅርባለች። ማህበሩ በበኩሉ የመምህራኖችን ችግር ለመቅረፍ እየሠራ እንደሆነ ይገልጻል።ከክልል እስከ ፌደራል ካሉ ተቋማት ጋርም የመምህራኑን ጥያቄም ለመመለስ እየተሰራ እና አሁም ቢሆን እየተመካከሩበት እንደሚገኝ የማህበሩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሽመልስ አበበ ተናግረዋል።

የሲቪል ሰርቫንት ሠራተኞች ደሞዝ ሲስተካከል ከዚህ በፊት በነበሩት መንግስታት የመምህራን ጉዳያቸው ያልታየ እና ትኩረት ያልተሠ ሲሆን ማህበሩ ግን ይህን ለማስተካከል ሚናውን መወጣቱንም ይገልጻል። ከዚህ በኋላም የቤት ጥያቄያውን ለመመለስ እየተሰራ እንደሆነ የማህነሩ ሽመልስ ይገልጻሉ።

መልዕክት
የመምህራን ጥያቄ የጥቅማ ጥቅም ብቻ አይደለም። የክብርም ጉዳይ እንደሆነ ነው የሚያነሱት ።በመሆኑም የትምህርት ፖሊሲውን ማስተካከል እንደሚገባ እንዲሁም ሥነ ምግባር ላይ መሠረት ያደረገ በተለይም ‹የግብረ- ገብ› ትምህርት ማስተማር ችግሮቹን እንደሚቀንስ በማመን መልዕክታቸውንም አስተላፈዋል። መምህራኖች ተገቢው ክብር እንዲያገኙም እና ዓለምን የቀየረሙያ መሆኑንም ሰዎች እንዲገነዘቡት ይፈለጋሉ ። ለዚህ መፍትሔው መንግስት ትኩረት ሰጥቶት የመምህራኖችን ሥራ አጉልቶ ማሳየት ፣መሸለም እና በማበረታት ያስፈልጋል። ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነቱም መቅረት እንዳለበትም ያሳስባሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com