የእለት ዜና

ሩዋንዳ፤ ጨለማ የማይጨከንባት አገር

የአዲስ ማለዳው ዓምደኛ አዲሱ ደረሰ፥ በቅርቡ ሩዋንዳን በሥራ አጋጣሚ የመጎብኘት እድል አጋጥሟቸዋል። ኢትዮጵያ እንደ አገር ከሩዋንዳ፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከሩዋንዳውያን ምን ይማራሉ በሚል እሳቤ ይህንን የጉዞ ማስታወሻ ከትበዋል።

የሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊን በታኅሣሥ አጋማሽ ስጎበኛት ከገረሙኝ ነገሮች አንዱ የሌሊቱ አነጋግ ነው። በርግጥ በኢትዮጵያም ሌሊቶች ቶሎ የሚነጉበት ወቅት አለ። የኪጋሊ ግን የተለየ ነው። ከጥዋቱ 11፡30 ፍክት ብሎ ነግቷል፤ ለአንድ ሰዐት ከጠበቁ ደግሞ ጸሐዩ ሊያቃጥልዎ ይችላል። ጨለማዋ ግን ድቅድቅ ነው። ለዐይን እንኳን ያዝ ሳያደርግ፤ ድቅድቅ ጨለማ ይሆናል፤ እንዳጨላለሙም እንደዚያ በፍጥነት እና በጉልበት የሚነጋም አይመስል።

ሩዋንዳ ታሪኳም እንዲሁ ይመስላል። በዘር ጭፍጨፋው ዘመን ድቅድቅ የታሪክ ጨለማን ተከናንባ ነበር። ከሁቱ ወገን የነበሩትና በወቅቱ የሩዋንዳ ፕሬዘዳንት የነበሩት ጁቬናል ሃቢሪማን ከቡሩንዲ ሹማምንት ጋር አብራ የያዘችው አውሮፕላን ከኪጋሊ የአውሮፕላን ማረፊያ እንደተነሳች ጋየች። የዚያች አውሮፕላን በአየር ላይ መጋየት፤ የሩዋንዳ ድቅድቅ የታሪክ ጨለማ ማስጀመሪው ፊሽካ ሆነ።

ሁቱዎች እና ቱትሲዎች በጣም ተመሳሳይ ናቸው፤ ተመሳሳይ ቋንቋ፣ ባህል እና አሰፋፈር ያላቸው ሕዝቦች ናችወ። ቱትሲዎች ቀጭን እና ከሁቱዎቹ ጋር ሲነጻጸር ረጃጅሞች ናቸው፤ ኢትዮጵያውያንን ይመስላሉም ይባላል። ኪጋሊን ለመጎብኘት ስንቀሳቀስ መኪናችንን ሲሾፍር የነበረው ሩዋንዳዊ፥ ሕዝቡ በጭፍጨፋው ወቅት ‹‹ቱትሲዎች ዝርያቸው ከኢትዮጵያ ስለሆነ ወደ አገራቸው ለምን አይሄዱልንም›› ይባል እንደነበር አጫውቶኛል። ቱትሲዎችን ገሎ ወደ ወንዝ የመጣል ልምዱ የመጣውም ሬሳቸውን ወደ ዘር ምንጫቸው ኢትዮጵያ እንዲሄድ በማመን እንደነበር የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ማግኘት ይቻላል።

የሁቱዎችና የቱትሲዎች ግብግብ በታሪክ ውስጥ አዲስ ነገር ባይሆንም፤ በግላጭ የወጣው ግን ቤልጂየም ቀኝ ገዢዎች ሩዋንዳን ከረገጡ ከ1916 (እ.አ.አ.) ጀምሮ ነበር ይባላል። ቤልጂየሞቹ ሁቱና እና ቱትሲ የሚል መገለጫ የተጻፈበት መታወቂያ እግራቸው ከመርገጡ ማደል ጀመሩ። በእሱም አላበቁም፤ ቱትሲዎቹ የተሻሉ የሰው ዘሮች እንደሆኑ የሚያሳዩ ትርክቶችን ይነዙ ገቡ። ቱትሲዎችም ትርክቱን አምነው ተቀበሉት።

ቱትሲዎች የተሻልን ሕዝቦች ነን የሚለው ትርክት ያመጣው የማኅበራዊ ከበሬታና እርሱም ይዞት የመጣውን ኢኮኖሚያዊ ትሩፋትም ሲያጣጥሙ ከረሙ። የሁቱዎቹ የውስጥ ለውስጥ ማጉረምረም በየመንገዱ ፈንድቶ ወጣ። ፕሬዝዳንት ጁቬናል ሁኔታውን ለፖለቲካቸው መጠቀምን ያዙ፤ ለኢኮኖሚው ማጥ ተጠያቂዎቹ ቱትሲዎቹ እንደሆኑ ይተርኩ ጀመር። በዚህ ምክኒያት በ1959 (እ.አ.አ.) ብቻ ወደ 20 ሺሕ የሚጠጉ ቱቲሲዎች ተጨፈጨፉ። ይህ ዋናው ጭፍጨፋ አይደለም፤ ከሱ በፊት የተካሄደ ጭካኔ የተሞላበት ፕሮቫ ነበር።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ቱትሲዎች ወደ ዩጋንዳ እና ብሩንዲ ይሰደዱ ጀመር። በተመሳሳይ ጊዜ በዩጋንዳ ያሁኑ ፕሬዝዳንት ፓል ካጋሜ የሩዋንዳ የጀግኖች ግንባርን አቋቁመው መንግሥትን ለመጣል እንቅስቃሴ እያደረጉ ነበር። ይህን የካጋሜ እንቅስቃሴ በሩዋንዳ ያሉ ቱትሲዎች እና መሃል ሰፋሪ ሁቱዎች እየደገፉት ነው በሚል የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጁቬናል ቱትሲዎችን ለሌላ ጭፍጨፋ ዳረጉ።

የቤተመንግሥት ጠባቂዎቻቸውን፣ ፖሊሶችን እና ወታደሮችን አሰማርተው ጭፍጨፋውን በሚገባ አሳለጡት። ንጽሃን ዜጎች በጭፍጨፋው እንዲሳተፉ ማበረታቻ የሚሰጡ ፖሊሲዎች ወጡ። ቱትሲዎችን የገደለ ንብረታቸውን ይውሰድ፤ የምግብ እና የገንዘብ ሽልማትም ይሰጠዋል የሚሉት ከማበረታቻዎቹ ጥቂቶቹ ነበሩ። በዚህ ያልተበረታታ ሰብኣዊነት ቢጤ የተሰማው ቢኖር ደግሞ መሣሪያ ጭንቅላቱ ላይ ተደቅኖ ቱትሲ ጎረቤቱን እንዲገድል ይገደድ ጀመር።

ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ጆሮ ዳባ ልበስ አለ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጸጥታ አስከባሪ 10 ወታደሮቹ መገደላቸውን ተከትሎ ሩዋንዳን ለቆ ወጣ። የቱትሲዎች እጣ ፋንታ በሁቱው ፕሬዝዳንድ እና በጨፍጫፊ ቡድኖቻቸው መዳፍ ላይ ወደቀ። የፕሬዝዳንቱ አውሮፕላን መመታትና የእርሳቸው መሞትን ተከትሎ ደግሞ ሩዋንዳ በሰው ልጅ እሬሳ ክምር ተሞላች።

ካጋሜ ተሳክቶላቸው ኪጋሊ ገቡ። በመጀመሪያ ሁቱ ፕሬዝዳንት አስቀድመው እርሳቸው ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኑ። ፕሬዝዳንቱ የዘር ፖለቲካ ትርክትን የማስቀጠል አዝማሚያ ታይቶባቸዋል በሚል ወደ ዘብጥያ ተወረወሩ። ካጋሜ ያለተቀናቃኝ መንግሥትን ተቆጣጠሩ። የሩዋንዳ የመተራረድ ታሪክ እንደጨለማዋም ባይሆን ቶሎ ነጋላት፤ አልጨከነባትም። እንዲያውም ታሪኳን ቀኝ ኋላ አዞረችው።

ኪጋሊ እና በምላስ ቢቀመሱ የማይቆጩት መንገዶቿ
የዋና ከተማዋ ኪጋሊ አስፓልቶች ላይ ሶፍት እና ፌስታል አይደለም፤ አፈር ማግኘት ይከብዳል። እውነት ነው ኪጋሊ ጥዋት ጥዋት እንደ አዲስ አበባ ትጸዳለች። በአጭር ቆታዬ ያስተዋልኩት ግን ኪጋሊ ጽዱ የሆነችው ስለምትጸዳ ብቻ ሳይሆን የሚያቆሽሻት ስለሌለም ነው። እንደዛ የሰው ልጅ ሬሳ እንዳላቆሸሻት፤ ሩዋንዳኖች አሁን አስፓልቱን ለማቆሸሽ የሚያክል እንኳን ጭንቅላታቸው ውስጥ የቀረ ቆሻሻ ታሪክ ያለ አይመስልም።

ትህትና በኪጋሊ ሞልቶ ይፈሳል
በትሁት ቃላት የተዋቡ ዐረፍተ ነገሮች እኔ የምሰማው ባለ አራት እና አምስት ኮኮብ ሆቴሎች ስገባ ነው፤ በአዲስ አበባ። ኮኮቡ ባነሰ ቁጥር፤ ትህትናውም ሊቀንስ ይችላል። በኪጋሊ አስፓልቶች ላይ ትሁት ሰዎች ሞልተው ይፈሳሉ፤ ትህትናም እንደዚያው።

ከኪጋሊ ስመለስ ለቤተሰቦቼ የሩዋንዳ ማስታወሻ ልገዛላቸው ፈልጌ ገበያውን አላውቀውም። ሌላም እንቅፋት አለ። እንግሊዘኛ ታዋቂ ቋንቋ አይደለም፤ በኪጋሊ። አንዲት ኮረዳ በኪጋሊ አስፓልት ላይ አግኝቼ፤ እንግሊዘኛን እንደምትችል አረጋግጨ ችግሬን አዋየኋት። ከምትሄድበት ቀኝ ኋላ ተመልሳ፤ በመጀመሪያ ዶላር የሚዘረዘርበትን ቦታ አሳይታ ከዚያም የሩዋንዳ የባህል ልብሶችን ለመስፋት የሚውሉት ጨርቆች መሸጫ ቦታ ወሰደችኝ። መቼም ከዋና ጉዳይዋ ተመልሳ ነውና እንደኛ አገር እንደው ለሻይ ነገር ሸጎጥ ማድረግ የተለመደ ነው ብዬ ብሞክር፤ ቢላዋ ባንገቴ ይግባ አለች። ምክኒያቱስ ቢባል፤ እንግዳ ነኛ።

ነጋዴዎቹም ቋንቋቸው ባይገባኝም በምልክት አስደግፈው እንደማያስፈልግ ሲያመለክቱኝ፤ ያገሬው ባህል ነው ማለት ነው ብዬ እግዚአብሔር ይስጥልኝ ብዬ ሸኘኋት።

እንደግዳ ጎብኚ በመንገድ ሲታይ እየተከተሉ ዶላር ከሚጠየቅበት አገር ለመጣ እንደኔ ዓይነቱ ዜጋ መቼም ይሄ አጃኢብ ነው።

የሩዋንዳውያን ሕግ አክባሪነት
ሩዋንዳን ጠንቅቀው በሚያውቋት ኢትዮጵያውያን መካከል ሲንሸራሸር የሰማሁት አንድ ታሪክ አለ። ከዕለታት በአንድ ቀን ክርናቸው ላይ ኮኮቦችን ከሚደረድሩት የሩዋንዳ ጄነራሎች መካከል አንድኛው ቤቱን ለማስገንባት ያስጀምራል። ለግንባታው መሰረት ለማውጣት ወደ ታች ተቆፍሮ ከውስጥ የሚወጣው አፈር በአስፓልቱ ላይ ይታያል። ፕሬዝዳንት ካጋሜ ነገሩን ከመስማታቸው መኪናቸውን እያሽከረከሩ በቦታው ተገኝተው ቅጣት ተጥሎበት አፈሩን በቅጽበት ውስጥ እንዲያስነሳ አዘው እንደሄዱ፤ እንደዚያም እንደተደረገ በስፋት ይነገራል።

ታሪኩን በግሌ ማጣራት ባልችልም የሩዋንዳኖችን ሕግ አክባሪነት ለመመስከር የሚያስችል ሌሎች ነገሮችን በማስተዋሌ ለማመን አልቸገረኝም። የኮሮናን መምጣት ተከትሎ የእጅ ንጽሕናን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ጀሪካኖች አይደለም በኪጋሊ የሚታዩት። ከቆሻሻ ውሃ ማስወገጃ ታንከሮቻቸው ጋር ሲጠጓቸው ሳሙናና ውሃ የሚያወጡ ቴክኖሎጂዎች እንጂ። መተከላቸው አይደለም የሚያስገርመው፤ አንድም ዜጋ ሊነቅላቸው ወይም ሊያበላሻቸው ሳይሞክር ውሃ እና ሳሙና ብቻ እየተጨመረላቸው ለወራት ማገልገላቸው ነው።

ዜጎች ለመኪና አደጋ እንዳይጋለጡ በቀለበት መንገድ ላይ የተተከሉ ብረቶችን ነቅሎ እራሱን ለአደጋ የሚያጋልጥ የተማረ ዜጋ ከሞላባት አገር ለመጣ እንደኔ ዓይነቱ ዜጋ ነገሩ እጅን በአፍ ላይ ቢያስጭን አያስገርምም።

የሩዋንዳውያንን ሕግ አክባሪነት ለማስተዋል ሌላም ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በኪጋሊ አስፓልቶች ላይ የሚርመሰመሱትን ሞተር ሳይክሎች እንደ አማራጭ መጓጓዣ መጠቀም ካሰቡ በኪስዎ ላስቲክ አሊያም በራስ ቅል ላይ የሚጠለቁ ሹራቦችን እንዲይዙ ይገደዳሉ። ምክኒያት ካሉ ደግሞ ሲጓጓዙ የአደጋ ጊዜ የጭንቅላት ላይ ሄልሜት ማድረግ ግድ ስለሆነ፤ ይህንንም ሄልሜት ብዙዎች ስለሚያደርጉት በላብ አሊያም በሌሎች ላብ አማካኝነት ኮሮና እንዳይተላፍ በሚል ነው።

ሞተር ሳይክል መጠቀም አስቤ በቋንቋ አለመግባባት ምክንያት የተሰጠኝን ሄልሜት በቀጥታ አናቴ ላይ አስቀመጥቁት። በሰከንዶች ውስጥ ደርዘን የሚጠጉ የሞተር አሽከርካሪዎች ከበውኝ በማላውቀው ቋንቋ እያወሩ እንደ ግዑዝ አካል ይጠቋቆሙብኝ ጀመር። እንደምንም እንግሊዘኛ የሚችል ፈልጌ ጉዳዩን ስጠይቅ መጀመሪያ ላስቲክ ወይም ሹራብ ጭንቅላቴ ላይ ሳላጠልቅ ሄልሜቱን በማድረጌ እንደሆነ ተነገረኝ።

‹‹እርሱን አሊያዝኩም›› ብል፤ ‹‹በል ውረድልኝ!›› ተባልኩና ክብሬን ጠብቄ ወረድኩ። ሲጀመር ሄልሜቱ እራሱ ከማይደረግበት፤ አሊያም የአደጋ ጊዜ ቀበቶን ትራፊክን ለመሸወድ ብቻ ከደረት ላይ ጣል ከሚደረግበት አገር ለመጣ እንደኔ ዓይነቱ ዜጋ ነገሩ እጅን በአፍ ላይ ቢያስጭን አያስገርምም።

ሕግ ማክበራቸው አይደለም፤ ልጆቹ በትምህርታቸው ያልገፉ እንዲሁም በወራት ውስጥ ብቻ በተሠራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሕጉን ይህንን ያክል ወደ ተግባር መቀየራቸው አጃኢብ ነው። ሕግማ ይከበር- በኪጋሊ። ኪጋሊ አስፓልቶች ላይ ስዘዋወር የትራፊክ መብራቶችንም ትራፊኮችንም አላየሁም። ሁሉም ምልክቶችን ባገናዘበ መልኩ ሲያሽከረክር ተመልክቻለው።

የመንግሥት ፕሮጀክቶች ጥራት
በተለያየ አጋጣሚ ኪጋሊ ላይ ካጓጓዙኝ ሹፌሮች የተረዳሁት፤ የመንግሥት ፕሮጀክቶች እንደ ጦር እንደሚፈሩ ነው። የመንግሥትን ፕሮጀክቶች በተመደበለት ጊዜ፤ በጀት እና ጥራት አለማጠናቀቅ ከፍተኛ የአገር ክህደት ነው። ይህንን መረጃ ሩዋንዳን ከማስተዋወቅ የዘለለ ትርጉም እንዳለው ለማወቅ አንድ ምሳሌ ላንሳ።

የኪጋሊ ኩራት ሆነው እያገለገሉ ከሚገኙት ምልክቶች መካከል አንድኛው የኪጋሊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ነው። ይህ የመንግሥት እና የግል ኢንቨስትመንት ጥምር ውጤት የሚታይበት ቦታ የፕሮጀክቶችን የማስፈጸም ብቃት እና የእቅድ ጥራት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ሩዋንዳ በአንድ ቀን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እንግዶች ግልብጥ ብለው ቢመጡባት፤ ሠርገኛ መጣ . . . ብላ አትደነግጥም። ከራዲሰን ብሉ ሆቴል ጋር ተገናኝቶ የተሠራ እና በአንድ ግዙፍ ግቢ ውስጥ የሚገኝ ግዙፍ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አላት። ተሰብሳቢዎች ሳይጉላሉ እዚያው አድረው፤ ጥዋት ተነስተው እዚያው ስብሰባቸውን የሚያደርጉበት፤ አንድም መኪና አስፓልት ወይም ግቢ ውስጥ ሳይታይ ውጦ የሚይዝ የመኪና ማቆሚያ ያለው እና እንግዶቹን ሲያሻቸው ማናፈስ የሚያስችል ግቢ ውስጥ የተገነባ እጅግ ግዙፍ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ነው። የእቅዱን ጥራት በጨረፍታ የሚያሳየው፤ ስብሰባ ካለ መቼም ጋዜጠኞች አይጠፉም በሚል ከአዳራሹ ሥር ለሚዲያ ተቋማት የተዘጋጁት ቢሮዎች ናቸው።

ኪጋሊ እና የዘር ጭፍጨፋ ማስታወሻ ሚዩዚየሟ
እኔ ለመጎብኘት እድሉን ያገኘሁት ለ250 ሺሕ የተጨፈጨፉ ዜጎች የተሠራውን ሚውዚየም ብቻ ቢሆንም ሌሎች ከግማሽ ደርዘን በላይ የሚሆኑ ግን በአገሪቱ ዙሪያ እንዳሉ ተነግሮኛል። ሚዩዚየሙን ሲጎበኙ እጅግ በጣም ከባድ ስሜትን ይጭራል። የታሪኩ አካል እንደሆኑ ሊሰማዎት ይችላል። የዚህ ምክኒያቱ ደግሞ በጥንቃቄ ታቅዶ፤ መሬት ላይ የተቀመጠው የሚውዜሙ አሠራር ነው። በቪዲዮ፣ በኦዲዮ፣ በስዕሎች እና በቅርጻ ቅርጾች ተደግፎ ታሪኩ ይቀርብሎታል።

የሚውዚየሙ የኪነ ሕንጻ እቅድ ማንም አስጎብኚ እንዳያስፈልግዎ ሆኖ የተሠራ ነው። ከበር ተቀብሎ ምዕረፍ አንድ፣ ምዕራፍ ኹለት እያለ ጨርሰው ውጪ ሲወጡ ታሪኩን እንዲጨርሱ የሕንጻው አሠራር እራሱ ይረዳዎታል። ከተጨፈጨፉ ሰዎች ሥም ዝርዝር፤ እስከነምስላቸው እንዲሁም እስተትክክለኛ ፎቶግራፎች፣ የተረፉ ዜጎች ቂማቸውን ረስተው ጠባሳቸውን እያሳዩ እንዴት ታናናሾቸውን ስለዘር ጭፍጨፋ ዘግናኝነት እንደሚያስተምሩ እስከሚያሳዩ ቪዲዮዎች የሩዋንዳን የዘር ጭፍጨፋ ራስዎን የታሪኩ አንድ አካል አድርገው ያስቀዝፍዎታል።

ሲወጡ ሩዋንዳውያን ታሪካቸውን ከነክርፋቱም ቢሆን የተቀበሉበት መጠን ያስገርምዎታል። አይኮሩበትም፤ አያፍሩበትም… ታሪክ ነው። እነሱ ተሻግረዋል። የሚያሳዩት ጠባሳ እንኳን ሳይኖራቸው፤ በመጽሐፍ አነበብን ያሉትን ጠባሳ እንደቂም እየዘሩ በሀብት፤ በዝና እና በሥልጣን የከበሩ ዜጎች ካሉበት አገር ለመጣ እንደኔ ዓይነቱ ዜጋ ይሄ መቼም አጃኢብ ነው።

ሩዋንዳ፤ ዲሞክራሲ እና ፖል ካጋሜ
ካጋሜ የሩዋንዳን ጨለማ በመግፈፋቸው እና ኢኮኖሚዋን በማበርታታቸው የሚወደሱትን ያክል ሥማቸውን በመጥፎ የሚያነሱትም አይጠፉም። ገሚሱ በቀድሞው ፕሬዝዳንት የአውሮፕላን ፍንዳታ ጋር በተያያዘ የእርሳቸው እጅ እንዳለበት ያነሳሉ። ሌሎቹ ደግሞ በ2017 (እ.አ.አ.) የአገሪቱን ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል በማድረግ ለሦስተኛ ጊዜ መወዳደራቸው ዲሞክራሲያዊ አይደለም ሲሉ ያብጠለጥሏቸዋል።
ኪጋሊ በነበረኝ ቆይታ ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር ከሩዋንዳውያን ጋር የካጋሜን ሥም ማንሳት ብዙም የሚመች ስሜት እንደማይሰጣቸው ነው። ከፍራቻ ይሁን መጠኑን ካለፈ ከበሬታ፤ ሩዋንዳውያን የፕሬዝዳንታቸውን ሥም ሲያነሱባቸው ‹‹እባክህ ርዕሱ ይቀየርልኝ›› ዓይነት ፊት ያሳያሉ።

ከአንድ ሩዋንዳውዊ ጋር ካጋሜ ዲሞክራሲን ይፈልጋሉ ወይ በሚል ያደረኩትን ክርክር ግን ሳልጠቅስ አላልፍም። እንደዚህ ሩዋንዳዊ ከሆነ ዲሞክራሲ በግሪኮች ተሸምኖ በአውሮፓውያን ቁመት እና ወርድ ተለክቶ ተሰፍቶ አፍሪካውያን አላማረባችሁም መባላችን ስህተት ነው ይላል። እውነት ነው፤ የዜጎች መብት፤ የመሪዎች ምርጫን መሰረት ባደረገ መልኩ መቀያየር የምንስማማበት ጉዳይ ቢሆንም፤ ዲሞክራሲ ለእኛ ምን መምሰል አለበት የሚለውን ግን እኛ አፍሪካውያን ልንወያይበት የሚገባ ይመስለኛል ሲል ይሞግታል።

ካጋሜም ሕገ መንግሥቱን በማሻሻላቸውም ይሁን ለሦስተኛ ዙር በመወዳደራቸው ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ለአገሪቱ ባበረከቱት ነገር መገምገም ይገባቸዋል ይላል ሩዋንዳዊው ስሜት በተሞላበት መልኩ የአውሮፓውያንን ዲሞክራሲ በሞገተበት ንግግሩ። በፍራቻም ይሁን በስምምነት፤ አንድ ነገር ግን ጥርጥር የለውም- ሩዋንዳውያን ካጋሜን በሥራቸው እጅግ ያከብሯቸዋል።

እና ምን ይሁን ነው የምትለው
መቼም የአገሬ ልጆች ቧልት ተወዳዳሪ የለውም። የሩዋንዳ መንግሥት ከፍሎሃል እንዴ ከማለታችሁ በፊት ወደ ዋናው ነጥቤ ልምጣ። ኢትዮጵያውያን ሩዋንዳውያንን ልንመስል እንችላለን፤ እነርሱን ግን አይደለንም። ሩዋንዳውያን ዘራቸውን የሚገልጽ መግለጫ በመታወቂያቸው ላይ ያሰፈሩባቸው ቀኝ ገዢዎቻቸው ናቸው። እኔ በመታወቂያዬ ላይ ዘሬን ተሸክሜ እንድዞር የሆንኩት በገዛ ወንድም እህቶቼ አስገዳጅነት ነው።
ቀኝ ገዢዎቻቸውን ከትከሻቸው ላይ አሽቀንጥረው ከጣሉ በኋላ፥ መታወቂያውንም አሽቀንጥረው ጥለዋል። በዚህ ረገድ እኛም ትንሽ እየተሳካልን ይመስላል። ፈግፍገን አደብዝዘነዋል። ሩዋንዳውያ ግን ሁቱ እና ቱትሲነታቸውን ከፖለቲካዊ፣ ከኢኮኖሚያዊ እና ከማኅበራዊ ውይይቶቻቸው ውስጥ አስወግደውታል። አንድ ግለሰብ ሮበርት ይባላል፤ ኪጋሊ ተወልዶ ነው ያደገው፤ ሹፌር ነው፤ በተረፈ ሩዋንዳዊ ነው። ኪጋሊ መወለዱን እና ሩዋንዳዊነቱን የሚያገናኝ የዘር ዝባዝንኬ የለም፤ ሩዋንዳውያን በዘር ተከፋፍለው ከመጨፋጨፍ ወጥተው እዚህ ደርሰዋል።

መታወቂያ ላይ የሰፈረውን ዘር ማንዘር እንደማደብዘዛችን አስተሳሰቡን ከጭንቅላታችን ውስጥ ማደብዘዙ ግፋ ቢል እስካሁን የተሳካልን አይመስልም። አዳዲሶቹ ሹማምንቶቻችንም ኢትዮጵያዊነትን አቀንቃኞች ነን እንደማለታቸው፤ ያን ያክል ርቀት ለመጓዝ አለማቀዳቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። ‹‹በብሔር ፌደራሊዝሙ አንደራደርም›› ከሚለው መግለጫ፤ በጎጥ የተቃኘውን የፌደራል አወቃቀር ይዞ ለመቀጠል እስካለው ቁርጠኝነት ለዚህ ማሳያዎች ናቸው።

እኛ ዜጎችን ግን ከአስተሳሰባችን፣ ከውይይቶቻችን መሀል ዘር ማንዘርን እየጠቀሱ መዳኘቱን፤ እና የእኔ እና የእነሱ መባባልን የማስወገዱ ውሳኔ የእኛ የእራሳችን ነው፤ የግለሰብ ዜጎች። እኔ ከወሰንኩ ቆይቻለው፤ አዲሱ እባላለው፤ አዲስ አበባ ተወልጄ ያደኩ፤ አንድ ሳይንሳዊ የኅትመት ውጤት ላይ ሠራተኛ ነኝ፤ በተረፈ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ሌላው መረጃ ጥቅሙን ብዙ አላየሁትም፤ ስለጉዳቱ ግን አገሩ ሁሉ ማስረጃ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com