የዐሥር ዓመቱ መሪ ዕቅድ ለሰማይ አልሞ ኮከቡን መምታት…?

Views: 211

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ወደ አመራር የፊት መስመር ከመጡ ወጣት መሪወች ውስጥ የብሔራዊ የፕላን ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) አንዷ ናቸው። ፍጹም ቀዳሚውን የዕድገት እና ተራንስፎርሜሽን ኹለተኛውን ምዕራፍ በአገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ለመተካት ከሚታትሩት ሰዎችም ውስጥ ስማቸው በጉልህ ከሚጠቀሱት ውስጥ ይገኛል። ባለፉት ኹለት ኣመታት ፍጹም አሰፋ የአስር ዓመቱን መሪ ዕቅድ በተመለከተ በማዘጋጀቱ ረገድ 12 ትልልቅ ጥናቶችን መርተዋል፤ በዚህም ውስጥ የአገር ውስጥ እና ውጭ ተቋማትም ተሳታፊ ሆኑ ሲሆን ኮሪያው የልማት ተቋምም አንደኛው እና ዋነኛው ነበር። ሰፊ ዕቅድ የተካተተበት የአስር ኣመቱ መሪ ዕቅድ በአሁኑ ሰዓት ተጠናቆ ለትግበራ ዝግጁ ሆኗል።

ፍጹም አሁን ካሉበት ኃለፊነት ቀደም ብሎ በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የኃላፊነት ስፍራዎች ላይ ያገለገሉ ሲሆን በዩኒቨርስቲው ቢዝነስ እና ኢኮኖሚ ትምህርት ክፍል ዲን ሆነውም አገልግለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርስቲው አምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድን በማዘጋጀት በኩልም ኮሚቴውን በመምራት ሰፊ ስራን ሰርተዋል። ፍጹም አሰራ (ዶ/ር) በቅርቡ ከአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ከሆነው ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሪቪው መጽሔት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለጋዜጣ እንዲመች ተደርጎ እንዲህ ቀርቧል።

የአስር ዓመቱን መሪ ዕቅድ ለማዘጋጀት ምን ያህል ጊዜ ወስዷል ወይም መሪ ዕቅዱ ለመዘጋጀት ምን ያህል ጊዜ ፈጀ?
ዝግጅቱ ወደ ኹለት ኣመታት ገደማ ወስዷል። በመጀመሪያ 12 አይነት ጥናቶች መካሔድ ነበረባቸው ይህም መሰረት ለመጣል ማለት ነው። እነዚህ ጥናቶችም በግልጽ እና ጥርት ባለ ሁኔታ የኢትዮጵያን ነባራዊ እና አሁን ያለውን ምጣኔ ሀብት ደረጃ የሚሳዩ ናቸው። ከዚህም ቀጥለን የምጣኔ ሀብትን ዕቅድ የሆኑትን አዕማድ መቅረጽ ጀመርን።

የተወሰኑ የአስር አመቱ መሪ ዕቅድ ግቦች ከመጀመሪያው እና ከኹለተኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር ተመሳሳይነት አላቸው በዚህ ምን ይላሉ?
በሚገባ ያልተጤኑ እና ያልተተገበሩ የነበሩ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ግቦች ወደ አስር ዓመቱ መሪ ዕቅድ እንዲካተቱ ተደርገዋል። በአሁኑ ሰኣት የኹለተኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ግመገማ ወደ መጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሷል።

አዲሱ የአስር ዓመቱ መሪ ዕቅድ እንደ ከዚህ ቀደምቶቹ ኹለቱ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ቀቢጸ ተስፋ እና የማይተገበር ነው ማለት እንችል ይሆን ?
ለዓለፉት አስርት ዓመታት ሲመዘገብ የነበረው ተከታታይ ዕድገት በመሰረተ ልማት ላይ ሚደረጉ ግል ዘርፉ መር የሆነ አካሔድ ውጤት ነው። ነገር ግን የሌሎች ሴክተሮች ማደግ ሚስችል ዕምቅ የሖነው ኃይል ግን አልተነካም ነበር። ይህ ማለት ደግሞ አሁን ባለው ሁኔታ የበለጠ ማሳካት እንችላለን ማለት ነው ፤ ለምሳሌ በሚቀጥለው አስር ዓመት የግብርና ምርትን አሁን ካለው በዕጥፍ መጨመር እንችላለን ማለት ነው።

አምራች ኢንዱስትሪዎች በአሁኑ ሰዓት መስራት እና ማምረት ከሚችሉበት ከስድሳ በመቶ በታች ነው እየሰሩ የሚገኙት። በዚህም ረገደፍ ደግሞ ሌሎች አዳዲስ ተጨማሪ ኢንዱስተሪዎች ላይ ለማቋቋም መዋዕለ ነዋይ ሳናፈስ ያሉትን ኢንዱሰትሪዎች የመስራት አቅማቸውን ወደ ሰማንያ በመቶ ማሳደግ ከፍተኛ የሆነ እመርታ ይኖረዋል ማለት ነው፤ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አምርተው ወደ ውጭ የሚልኩት መጠንም ቀስ በቀስ እያደገ ነው የሚገኘው። ቴክኒካሊ ከፍተኛ የሆነ የምርት ዕድገት በሌበት ከፍተኛ የሆነ ዕድገት ሊኖር አይችልም። በርካታ ሴክተሮች አይ ሲ ቲን ቱሪዝምን እና ማዕድን ዘርፎች ከዜሮ እየተነሱ ነው ማለት ይቻላል።ስለሆነም ዕቅዶቹ ሰፊ እና እነዛን ዕቅዶች ለማሳካት ደግሞ አጠንክረው ሊያሰሩን የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል፤ ድህነትንም ለመግታት እና ለመቁረጥ ቢያንስ በአስር በመቶ ማደግ ይኖርብናል።

በአስር ዓመቱ መሪ ዕቅድ ላይ እንደተጠቀሰው በመጪዎቹ አስር ዓመታት ኹለት ሦስተኛው የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት የሚመጣው ከግሉ ዘርፍ ነው። ይህ ታዲያ አገሪቱ እንደከዚህ ቀደሙ ዓይነት ዕድገት እንድታስመዘግብ ይረዳታል ብለው ያስባሉ?
የባለፉትን አስር ዓመታት የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን በጥልቀት ብንመለከት፤ በጣም በርካታ አፈጻጸም ችግሮችን በግልጽ ልናገኛቸው እንችላለን። ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያን ብንወስድ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገታቸውን ሰላሳ በመቶ አውጥተው ኢንቭስት አድርገው ያደጉት በአስር በመቶ ነበር። ኢትዮጵያ ደግሞ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገቷን ሰላሳ ሰባት በመቶ የሚሆነውን ኢንቨስት ያደረገች ቢሆንም ዕድገቷ ግን አጥጋቢ የሚባል አይደለም አልነበረም። የግሉ ዘርፍ መር ኢንቨስትመንት ባሉት አፈጻተም ችግሮች እንኳን እያሉበት ከፍተኛ ዕድገት ካስመዘገበ የግሉ ዘርፍ ባነሰ ካፒታል ተሸለ ነገር መስራት ይችላሉ ማለት ነው።

የግሉ ዘርፍ ገና ዳዴ በማለት ላይ መሆኑ እየታወቀ እንዴት ይህን ያህል ተስፋ ሊጥሉበት ቻሉ?
አገር ውስጥ የግሉ ዘርፍ ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማምጣት አጣብቂኝ ውስጥ እንዳለ ይታወቃል። የውጭ ኢንቨስተሮች ካፒታልም ሆነ ክህሎት በእርግጥ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ጠንካራ የሆነ አገር በቀል ግል ሴክተር ከሌለ ግን ልማቱ ቀጣይነት አይኖረውም፣ የልማቱ ከፍፍልም ወደ ሕዝቡ በእርግጥ መውረድም አይቻለውም አይዳረስምም።

በሌላ በኩል ደግሞ ዕውቀት ሽግግር፣ ልምምድ ለውውጥ እና የካፒታል ዕድገትን በተመለከተ ረገድ የውጭ ባለሀብቶች ላይ ትኩረት አድርገን ደግሞ እሰራለን። በትክክለኛ ፖሊሲ የውጭ ባለሀብቶችን በአገር ውስጥ የግሉ ዘርፍ ላይ የሚሰማሩበትን መጠን እና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ማመጣጠን ይቻላል። በዚህም ምክንያት ነው በቅርቡ ወደ ስራ የገባው የኢንቨስትመንት ሕግ በርካታ ሲክተሮችን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆኑ ያደረገው።

ባለፉት አስር ዐመታት ልማቱን በገንዘብ የደገፍንበት መንገድ ቀጣይነት ያለው አልነበረም። ምክንያ ደግሞ የገንዘቡ መጣበት የብድር አይነት ከፍተኛ ሆነ ወለድ ስለሚመዘገብበት ማለት ነው። አንደኛው የማክሮ ኢኮኖሚው የአለመረጋጋት ምንጭ ከፍተኛ የሆነ የብድር መጠን ነው። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት የመሻሻል ሁኔታዎች አሉ። ምክንያቱም በአሁኑ ሰዓት ከእነዛ ከፍተኛ የወለድ መጠን ከሚያስቡ አበዳሪዎች ዘንድ መበደር ሙሉ በሙሉ አቁመናል ። ባንኮችም ወለዳቸውን ሲከፍሉ በነጻነት ሆኗል።

የአገር ውስጥ የግሉ ዘርፍ በእርግጥ በጨቅላነት ዕድሜው ላይ ነው ሚገኘው፤ ሁሉም አገራት ደግሞ ይህ ደረጃ አልፈውበታል አልፈውበትም ነው እዚህ የደረሱት። በኢትዮጵያ ያለው ግሉ ዘርፍ ሰላሳ ዓመት እና ከዛ በታች ባለ ዕድሜ ላይ ነው ሚገኘው፤ በመሆኑም የመንግሥት ድጋፍ ያሻቸዋል ይህም ደግሞ ወደ ፊት እዲመጡ ያደርገዋል ማለት ነው።

ሌላኛው የአስር ዓመቱ መሪ ዕቅድ ላይ የተጠቀሰው 4ነጥብ 4 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት ነው። ከቀደመው የቤቶች ግንባታ ልምድ በመነሳት ይህ ዕቅድ በእርግጥ ተፈጻሚነቱ ላይ ምን ይላሉ?
ቁጥር በእርግጥ የሚያሳየው በቀጣይ አስር ዓመታ ውስጥ የሚኖረውን የቤት ፍላጎት ነው። ከፍላጎቶችም ውስጥ አስር በመቶ ብቻ ሚሆነው በመንግሥት የሚገነባ እና የሚሸፈን ሲሆን ቀሪ ደግሞ በግሉ ዘርፍ የሚሸፈን ይሆናል። ከዚህ በፊት የነበረው የአካሔድ እና አመለካከትም በመቀየር የቤት ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ ከቤት ባለቤትነት አመለካከት ወደ ለቤት ማግኘት ያለውን ጉዳይ ቅርበት እና አጋጣሚ ወደሚል ይሸጋገራል ማለት ነው። የግሉ ዘርፍም የቤት ግንባታውን ከመንግስት ጋር በጋራ በመሆንም መገንባት ይጀምራል። ለአገር ውስጥ እና ለውጭ በመኖሪያ ቤት ግንባታ ንግድ ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶችም ክፍት ነው። ይህን ደግሞ ለማመቻቸት መንግሥት የተለያዩ አዳዲስ መንገዶችን በመፍጠር ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ይሞክራል፤ ለምሳሌ የሞርጌጅ ወይም ቤቶችን በተራዘመ ብድር ለመግዛት የሚያስችሉ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው።

ሌላው በከፍተኛ ደረጃ በዕቅድ የተያዘው ጉዳይ ጠቅላላ ዕርሻ መሬትን ከ33 በመቶ ወደ መቶ በመቶ ከፍ የማድረግ ዕቅድ ነው ይህም ደግሞ የዝቅተኛ ቦታዎችን ለምርት በማዘጋጀት ረገድ ጋር በተያያዘ ነው በዚህስ ጉዳይ ምን ይላሉ?
ረባዳ መሬቶች ለረጅም ዓመታት ሳይነኩ እና ለዕርሻ ሳይሞከሩ ቆዩ ስፍራዎች ናቸው። እነዚህ ስፍራዎች ታዲያ በአሁኑ ሰኣት ታሳቢ ተደረጉት የእንስሳት መኖ እና ስንዴ እንዲመረትባቸው ነው። በእርግጥ አበሁኑ ሰዓት አበረታች እና አመርቂ ውጤቶችም እየተመዘገበ ይገኛል በተለይም ደግሞ በአፋር እና በሶማሌ ክልል ላይ የተመረቱት ስንዴ ምርት ለዚህ ማሳያ ናቸው።

በዚህም ምክንያት ይህን የመሰሉ ዕቅዶች የማይሳኩ እና ሊደረስባቸው ማየደችሉ ባዶ ፍላጎቶች ብቻ ይመስላሉ ነገር ግን በእርግጥም ልንደርስባቸው እና ልናሳካቸው የሚችሉ ዕቅዶች ናቸው። የግሉ ዘርፍ በረባዳ መሬቶች ወይም ቆላማ መሬቶች ላይ አዝዕርቶችን በማብቀል የመሪነት ሚናውን የሚወጣ ሲሆን መንግሥት ደግሞ ይህን ለሚያደርጉ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ይሰራል።

የንግድ ባንኮች አብዛኛውን ጊዜ አትራፊ የሚባለውን ንግድ ዘርፍ ሲያበድሩ ይታያል። በአንጻሩ ግብርናው ዘርፍ ደግሞ እንደሚታሰበው ትርፍ ሚስገኝ አይደለም ይህን ለማሳታርቅ ምን ያደርጋሉ?
ባንኮች የሚሰሩበት እና በአብዛኛው ትኩረታቸውን የሚደርጉት ትርፍ በሚያገኙበት ስፍራ ላይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት የገንዘብ ድጋፎች እና የገንዘብ አቅም ወደ ፊት ልማት ግስጋሴ ላይ እንዲያተኩር ፍላጎት አለው። ስለዚህ ይህን ኹለት የተራራቀ ሀሳብ ወደ መሐል ለማምጣት መንግስት አዳዲስ የድጎማ አስራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ለማስተዋወቅ ይሞክራል እንጂ አስገዳጅ ስራዎችን መስራት በባንኮች ላይ አይቻለውም። ባለፉት ጊዜያት መንግሥት ባንኮችን የማስገደድ ስራ ይሰራ ነበር። የመንግስት ባንኮችም ወደ መንግስት ድርጅቶች ፊታቸውን እንዲያዞሩ እና የገንዘብ የማግኘት ዕድልንም ለግሉ ዘርፍ ያጠበቡበት ጊዜ ነበር። የግል ባንኮችም በተመለከተ ከዚህ ቀደም የግምጃ ቤት ሰነድ በመግዛት የመንግስት ፕሮጄክቶችን የማገዝ ስራ እንዲሰሩ ይደረግ የነበረ ሲሆን፤ ይህ አሰራር ግን ከዚህ በኋላ በፍጹም አይደረግም።

ባለፈው አስር ዓመት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበትን ያስተናገደችበት ነበር፤ ይህም አሁን ድረስ እየታየ ይገኛል። ይህን ችግር ለመግታት የታሰበ ስትራቴጂ ይኖር ይሆን?
የዋጋ ግሽበቱን በተመለከተ ለባለፉት ኹለት ዓመታት ስናጠናው ቆይተናል። ጠቅላላው መረዳታችንም የዋጋ ግሽበቱ በኢትዮጵያ የጨመረው የፍላጎት መጠኑ ከአቅርቦት መጠኑ በዕጅጉ በላቀ መልኩ በመከሰቱ ነው። ከፍተኛ ሆነ ፍላጎት የተከሰተበት ምክንያት ደግሞ ምጣኔ ሀብቱ ባለፈው አስር አመት ውስጥ በገንዘብ በመደገፉ እና ከፍተኛ ገንዘብ መጠን ወደ ምጣኔ ሀብቱ በመግባቱ ነው። በዚህም ምክንያት ግሽበቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ ሆኗል ይህንንም ለመቀልበስ እና ለማረጋጋት ከፍተኛ ስራ ይጠይቃል። ኢትዮጵያ የግሽበት ጉዳይ አችር ጊዜ አጋጣሚ ወይም ክስተት አይደለም።

ባደገ የምጣኔ ሀብት ባለቤቶች ዘንድ ከልክ ያለፈ የዋጋ ግሽበት ሲያጋጥም፤ በአቅርቦት ዘንድ ብዙም ችግር ስለማይኖር በጀት እና ገንዘብን የመያዝ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ነገር ግን በእኛ ነባራዊ ሁኔታ በሁሉም ሴክተር ላይ ምርታማነት በጣም ዝቅተኛ ነው በተለይ ደግሞ በአምራች ዘርፍ እና በግብርናው ዘርፍ ላይ። በተለይ ደግሞ የግብርናው ዘርፍ የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ ይኖርበታል። በእርግጥ ሌሎች ምርታማነታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ዘርፎችም አሉ ለዋጋ ግሽበት አስተዋጽኦ ያላቸው። የገበያ ሰንሰለቱም ዘመናዊ መሆን ያለበት ጉዳይ ሲሆን አላስፈላጊ የመሀል ላይ አካላትም መወገድ ይኖርባቸዋል። ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ዕቃዎች ላይም ላይ የሚታየው የዋጋ ግሽበት ያለ ሲሆን ይህም ደግሞ ከአለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ጋርም ይያያዛል።

የመዋቅራዊ ለውጥ በማድረጉ ረገድ ላይ ያጋጠሙ መሰረታዊ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
አንደኛው እና ትልቁ ውድቀት የነበረው ባለፈው አስር ዓመት የመንግስት ውጤታማ ያልሆነ የቢሮክራሲ ችግር እና ደካማ መንግስታዊ ተቋማት መኖራቸው ነው። የተጀመረውን ልማት ከመደገፍ እና ለማስቀጠል ይልቅ በተቃራኒው ለልማቱ እንቅፋት ሲሆኑ ይታዩ ነበር። የሲቪል ሰርቪስን በሚመለከትም በብቃት እንዲሁን አዲስ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንዲሁም በውጤታማነት፣ እንዲሁም የአስር ዓመቱን መሪ ዕቅድ በመተግበር በኩል ያላቸውን ችሎታ በሚመለከት መዋቅሩ መሻሻል ይኖርበታል። ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት እና በመናበብ መስራት በተመለከተ መንግስት በዚህ በኩል ሰኬት አላስመዘገብ በመሆኑን በአሁኑ ሰኣት ቁልፍ የአፈጻጸም እና የስራ አተገባበር አመላካቾችን ይፋ አድርጓል።

የኢ መደበኛው ምጣኔ ሀብት ለአገር ውስጥ ተቅላላ ምርት እድገት ያለው ድርሻ ምን ያህል ሆኖ አገኛችሁት የአስር ዓመቱን መሪ ዕቅድ ለማዘጋጀት ባጠናችሁበት ወቅት?
በጣም ከፍተኛ ክፍል ነው። የኢመደበኛው ሴክተር ወደ መደበኛው ሴክተር መካተት ይኖርበታል ይህም ደግሞ ለማንም ሳይሆን ለራሱ ለሴክተሩ ሲባል ማለት ነው። ወደ መደበኛው ቅጥር ለመስፋት ገንዘብ ድጋፍም ማግኘት ይኖርበታል። የኢመደበኛው ሴክተር ምንም እንኳን ግብር ከፋይ ባይሆንም ነገር ግን የስራ ዕድልን በመፍተር በኩል ግን ጠቀሜታም አለው። ወደ መደበኛ ለማስገባት እና ከዛውም ተጠቃሚ ለመሆን ቀስ በቀስ መሰራት ይኖርበታል።

መንግስት በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማደግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ትኩረት አድርጎ ነበር። ነገር ግን የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፐርኮች ክልላዊ ኮታዎችን ለመሙላት በሚል በመሆኑ አፈጻጸማቸውም እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም። ከጥሬ ዕቃ እና አምርተው ወደ ገበያ ለማድረስ ካላቸው የአመቺነት አንጻርም ችግር አለባቸው። ከስተራክቸራል ትራንስፎርሜሽን በኋላ ኢንዱሰትሪ ፓርኮች ጠቀሜታ ይኖራቸዋል ብለው ያምናሉ?
የስትራክቸራል ትራንስፎርሜሽን ጉዳይ ምንም እንኳን ዘገምተኛ ቢሆንም ነገር ግን እየተፈጠረ ያለ ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ ሚሆነው በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ከእነርሱ ተመርተው ለውጭ ገበያ በሚበቁት ምርቶችም ነው። ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱት ምርቶች እና በጠቅላላው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡት መርቶች ድርሻቸው ቀስ በቀስ እየጨመረ መጥቷል። ከዚህ ቀጥሎ መንግስት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ መዋእለ ነዋይ የማፍሰስ እና ኮታ የመሙላት ስራዎች ላይ አይሳተፍም። ነገር ግን የምጣኔ ሀብት ጠቀሜታቸው ጉልህ የሆኑ እና የጥሬ ዕቃዎች አቅርቦትን በተመለከተም አመቺ በሆነበት ሁኔታ እና እንደተባለውም ሎጄስቲክ አቅርቦትንም በተመለከተ ታሳቢ በተደረገ ሁኔታ ነው የሚገነባው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጠቀሜታ ጠንካራ ሆኖ ይቀጥላል ፤ እስካሁንም ቆይቷል። ነገር ግን በጣም አነስተኛ ሆነ እና ኋላ ቀር የሆነ ከአርሶ አደሩ ጋር ያለው እና ከጥሬ ዕቃ አቅራቢዎች ጋር ያለው ግንኙነት ግን አሁንም ደካማ በመሆኑ አሁንም በርካታ ግብዓት ከውጪ እናስገባለን። ከዚህ በኋላ ግን የትኛውም የውጭ ኩባንያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኝ የዕውቀት ሽግግር ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች እንዲያደርጉ ይደረጋል። ትክክለኛ በሆነ እና ተገቢ በሆነ አካሔድ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ዘንድ የሚታየው ችግር ኃይል አቅርቦት፣ ውጭ ምንዛሬ ችግር እንዲሁም የግብዓት ችግር እንዲፈቱ ይደረጋል። ኢንዱሰትሪ ፓርኮች የስትራክቸራል ትራንስፎርሜሽን መሳሪያዎችም ይሆናሉ።

መንግሥት ላይ ያለው የውጭ ዕዳ በመጻኢው የመንግሥት የፋይናንስ ዘንድ ያለው ተጽዕኖ ምን ያህል ነው? አብላጫው ዕዳ ያለው ከቻይና ነው ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከምዕራቡ አለም የተላዩ አገራት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት አያሻክርም?
ገንዘብ ለምጣኔ ሀብት ልክ እንደ ምንተነፍሰው አየር ነው። ባለፈው አስር አመት ልማቱን ስንደግፍበት የነበረው የገንዘብ ድጋፍ ቀጣይነት ያልነበረው ነው። ለዚህ ደግሞ ገንዘቡ የሚገኝበት የብድር አይነት ከፍተኛ ወለድ የሚመዘገብበት መሆኑ ነው። ከፍተኛው የምጣኔ ኃብት ወይም ማክሮ ኢኮኖሚው አለመርጋት ዋነኛው ችግር እና እንደምክንያት የሚጠቀሰው ከፍተኛ የሆነ ብድር መጠን ነው። ነገር ግን አሁን በመጠኑም ቢሆን መሻሻሎች እየታዩ ነው ለዚህ ደግሞ እኛ ከፍተኛ ወለድ ከሚያስከፍሉ የገንዘብ ምንጮች መበደር ማቆማችን ነው። በቀጣይ ደግሞ የግብር አሰባሰብን እና የኢ መደበኛውን ንግድ ዘመናዊ በማድረግ እና ወደ ሕጋዊነት ለማምጣት አዳዲስ ፖሊሲዎችን እንቀርጻለን። ሌሎች ተጨማሪ የገቢ ምንጮችም በዚሁ ይኖራሉ፤ ለምሳሌ ካፒታል ማርኬት የተባለ አዲስ ዘዴ ከኹለት ሳምንት በፊት ይፋ የሆነውም አንዱ ነው። ከዚህም ባለፈ ደግሞ በርካታ ጠንካራ ገንዘብ ምንች መሆን የሚችሉ አሰራሮችም ያሉ ሲሆን ፤ የግሉ ዘርፍ ከምነግሥት ጋር በመሆን በጋራ የሚሰራው ስራ፣ ከውጭ አገራት ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ውጭ ምንዛሬ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የተወሰኑት እንደሆኑ መጥቀስ ይቻላል። ያለፈው የዕድገት ሁኔታ ቀጣይነት ያለነበረው እንደነበር ማንሳት ይቻላል፤ ለዚህም ደግሞ እንደምክንያት ማንሳት የሚቻለው የመንግስት በመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ሙሉ በሙሉ መሳተፍ ለማክሮ ኢከኖሚው መናጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ መፍጠሩ ነው።

የአሁኑ የዕድገት መሰረት ደግሞ በምርታማነት በኩል ሲሆን በአቅራቢዎችም ዘንድ ያለውን ችግርም ለመቅረፍ ይሰራል። ቀጣይነት ያለው ልማት በገንዘብ መደገፍ ፣ ብልጽግናን መጋራት፣ የግል ዘርፉ መር የሆነ ምጣኔ ሀብት እንዲሁም ተቋማዊ ችሎታ ከአስር ዓመቱ ዋና ዋና አዕማድ ጥቂቶቹ ናቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com