ከሰበብ ባለፈ ትኩረት የሚያሻው የእሳት አደጋ ጉዳይ

Views: 143

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የገበያ ማዕከላትን በተለየ መልኩ ኢላማ በማድረግ በሚሊዩን የሚቆጠር ንብረት በማውደም ላይ ይገኛል።
ጉዳዩ በግለሰቦች ቸልተኝነት፣ በኤሌክትሪክ እቃዎች አጠቃቀም ጉድለት እየተባለ ሰበብ ከመደርደር ባለፈ ምክንያቱን በመጣራት ከጀርባ ያለውን ሴራ ጥብቅ ክትትል የሚያሻው ጉዳይ እንደሆነ ዳዊት አስታጥቄ በሐተታ ዘ ማለዳ ቃኝቶታል።

አሁን ላይ በየወሩ በሚባል ደረጃ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚነሱ የእሳት አደጋዎች ቁጥራቸው እየተበራከቱ ነው። የእሳት አደጋዎቹ በዚህ አይነት መጠን መከሰት የተለመደ ባለመሆኑ ዘወትር ከምናስባቸው ምክንያቶች ዞር አድርጎ ማሰብ የግድ ይላል።

ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የደረሱ አደጋዎችን እንኳን ብንመለከት በደቡብ በአማራ ፣ በሶማሌ፣ በኦርሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ እንዲሁም በድሬዳዋ መስተዳድሮች ተከስተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ባለፉት ስድስት ወራት 110 የእሳት አደጋዎች መድረሳቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቋል። በእነዚህ አደጋም የአምስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከ157 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

እንደ ፖሊስ መረጃ ከሆነ ለደረሱት የእሳት አደጋ መንስኤዎች ናቸው የተባሉት፣የኤሌክትሪክ መስመሮችን በአግባቡ አለመዘርጋት እና/ ወይም የኤሌክትሪክ ኃይልን በጥንቃቄ አለመጠቀም የአንበሳውን ድርሻ ሲይዝ፣ በቀላሉ በእሳት ሊቀጣጠሉ የሚችሉ ቁሳቁሶችንና ተቀጣጣይ ነገሮችን እሳት በቀላሉ በሚያገኛቸው ቦታዎች ማስቀመጥ፣ የቡታጋዝ እንዲሁም የሲሊንደር ፍንዳታዎች ሌሎች የቃጠሎው መንስኤ መሆናቸውን በፎረንሲክ ምርመራ መረጋገጡን ኮሚሽኑ ገልጿል።

የአብዛኞቹ የአደጋዎች መንስኤዎች በቸልተኝነት ያጋጠሙ መሆኑን በተለይ ደግሞ ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ሻማ ለኮሶ መርሳት እንዲሁም ሰዎች በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ መሳሪያዎችን ሲጠቀሙ ቆይተው በድንገት የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቋረጥ ሳያጠፉ ባሉበት ጥሎ በመሄድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲመጣ እቃዎቹ ግለው የእሳት አደጋ እንዲከሰት ምክንያት እንደሆኑ በምርመራው ውጤት መረጋገጡን የፖሊስ ኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል።

በአዲስ አበባ ብቻ ከደረሱት አደጋዎች መካከል 24ቱ በንግድ ተቋማትና በተለያዩ ድርጅቶች ላይ የደረሱ እንደሆኑ ፖሊስ ኮሚሽኑ አስታውቋል ። በቅርቡ በኮልፌ እፎይታ የገበያ ማእከል የደረሰው ቃጠሎ ለዚህ ማሳያ ነው።

በተነሳው እሳት ወደ 40 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት የወደመ ሲሆን ፣ በሰው ላይ የደረሰ ምንም ጉዳት እንዳልነበረም በወቅቱ ተገልጿል። የንግድ ማእከሉን የአደጋ መንስኤ ግን እየተጠራ ነው ከማለት የዘለለ በምርመራ ተደግፎ ይፋ የሆነ መረጃ የለም።

ሌላው በመዲናችን አያት አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሱቆች ከ ምሽት 3:00 ሰዓት ላይ እሳት ተነስ እንደነበር ነገር ግን ወደ ሌሎች ሳይስፋፋ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቆ ነበር።

በሱቆች ላይ የተነሳው የእሳት አደጋ በተደረገው ፈጣን ከፍተኛ ርብርብ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር ተችሏል ብሏል ከተማ አስተዳደሩ ።
ከንግድ ማእከላት ባለፈ ወደ ደን የመዛመት አዝማሚያ እያሳየ እንደሆነ ማሳያ ሊሆን የሚችል ክስተት ባለፈው ሳምንት ተከስቶ ነበረር። ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው በጉለሌ እጽዋት ፓርክ ውስጥ እሳት ተነስቶ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት መውደሙን እና የተከሰተው እሳት በውስጥ ሠራተኞች ቸልታ እንደተከሰተ የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጾ ነበር ።

<ለከተማችን ውበት ድምቀት ከሆኑትና ከተማችንን ከጎርፍ ለመከላከል ከምንጠቀምባቸው ስፍራዎች መካከል አንዱ የሆነው የጉለሌ እጽዋት ፓርክን እሳት ለማጥፋት በርካታ የአዲስ አበባና የፌደራል ፖሊስ አመራሮች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ፣ የአዲስ አበባ የእሳት እና የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ባልደረቦች ፣ የመንገዶች ባለስልጣን፣ የአከባቢው አስተዳደር እና ህብረተሰብ ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል>በማለት ም/ከንቲባ አዳነች አበቤ ምስጋና መሰል መልእክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

በጉለሌ የዕፅዋት ማእከል የደረሰውን አደጋን በተመለከተ ለእሳቱ መነሳት ምክንያት ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ዛፍ ቆርጦ ለማስጫን ጨረታ ያሸነፈው ግለሰብ፣ ሥራውን እንዲሰሩለት የቀጠራቸው ሰራተኞች ምግብ ለማዘጋጀት ባቀጣጠሉት እሳት አደጋው መድረሱን በታክቲክ ምርመራ መረጋገጡን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሌላኛዋ የከተማ አስተዳደር ፣ድሬዳዋ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የምትጠቃው ከተማ ናት። በከተማው ብሎም እንደ አገር አስቀድሞ የአደጋ ስጋት ትንተና ባለመሥራቱ እና ሥራዎች በቅንጅት ስለማይሰሩ አስቀድሞ መከላከል ላይ ድክመት አለ ፣በመሆኑም በቅደመ አደጋ ስጋት መከላከል ላይ አቅዶ በመስራት ሃብት ማፈላለግ እና ተደራሽ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከተጠሪ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ የድሬዳዋ አስተዳደር አደጋ ስጋት ስራ አመራር ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃርቢ ቡህ ተናግረዋል።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ ስጋት መምህር የሆኑት ጥላሁን መንገሻ ለአደጋ ምላሽ መስጠት ላይ በርብርብ በመስራት ውጤታማ መሆን ቢቻልም አስቀድሞ መከላከል ላይ ድክመት ስላለ ይህንንም ለመቅረፍ አስቀድሞ የአደጋ ቦታዎችን፣ወቅቶችን እና አይነቶችን በመለየት ትንተና የመስራት እና የመዘጋጀቱ ስራ ለማከናወን በትኩረት እንደሚሰራ እንደሚገባ በአጥንኦት አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች በዚህ ዓመት በታኅሣስ ወር ብቻ በርካታ የእሳት አደጋዎች ደርሰዋል። በዚህም የተነሳ በሚሊዮኖች ብሮች የሚገመት ንብረት ወድሟል።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በቂ የምርመራ ክህሎት እና አቅም የሌላቸው ባለሙያዎች ባሉበት አገር ይባሱኑ እሳት አደጋን ለመከላከል እንደ አገርም በቂ ትኩረት ሳይኖር መንስኤዎቹን በቶሎ ማወቅ አዳጋች አእንደሆነ ይታመናል።

የእሳት አደጋዎቹ በተለያዩ ክልሎች የተከሰቱ ሲሆን ለአደጋዎቹ መከሰት እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት መካካል ሄድ መለስ የሚለው የኤሌክትሪክ ኃይል ከፍ ብሎ የሚነሳ ጉዳይ ሆኖ ይነሳል።

አደጋዎቹ በሚሊዮን የሚገመት ንብረት ያወደሙ ሲሆን ቄጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎችን ከሥራ ገበታ ውጪ ማድረጉ ይታወቃል። ነዋሪዎችም የተፈናቀሉባቸውም አጋጣሚዎች አሉ።

ባለፉት ወራት የእሳት ቃጠሎ አደጋዎች በቁጥር በርክተው መከሰታቸውን ማስተዋል ይቻላል። በየአካባቢው የሚነሱ አነስተኞቹን ትተን ትኩረት ያገኙትን ለአብነት ማንሳት እንኳን ብንችል ማሳያ ይሆናል።

እሳት አደጋዎቹ በከፈተኛ የትምህርት ተቋማትምጭምር የተከሰቱ ነበሩ። ታኅሣስ 8/2013 በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ህንፃ 3 በሚባለውና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ከሚኖሩበት ህንፃ የኤሌክትሪክ መቆጣጠሪያ ላይ የተነሳ የእሳት አደጋ ተከስቶ እንደነበር የዩኒቨርስቲው የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አስታውቆ ነበር።

በሌላ በኩል በድሬ ዳዋ ዩንቨርሲቲ እንዲሁ……..
በኦርሚያ ክልል በቡራዩ ከተማ ገፈርሳ ኖኖ ቀበሌ ልዩ ስሙ ገብርኤል በሚባል አካባቢ በደረሰ አደጋ በ16 ሱቆች፣ በ3 መኖሪያ ቤቶችና 3 ምግብ እና መጠት ቤቶች ላይ ውድመት መድረሱ እና በዚህም አደጋ ግምቱ 10 ሚሊየን ብር የሆነ ንብረት መውደሙ ተነግሯል።

በአማራ ክልልም እንዲሁ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ የእሳት አደጋዎች ተከስተዋል። በክልሉ ርእሰ ከተማ በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 3 በተለምዶ ጉዶባሕር ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ከቀኑ 7 ሰአት ላይ በተከሰተው አደጋ የእሳት አደጋ በ22 የመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ሲደርስ፤ በቃጠሎው ከ300 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ተነግሯል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ቃጠሎው እንጀራ በሚጋገርበት ወቅት ከተቀጣጣይ ነገሮች የተነሳ ስለመሆኑ አጣርቻለሁ ባለው መረጃ አስታውቆ ነበር።
በሌላ በኩል በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን መቅደላ ወረዳ ማሻ ከተማ አዲሱ መናኽሪያ ላይ ከምሽቱ 3፡30 ላይ በኤሌክትሪክ ምክንያት በተነሣ እሳት ሁለት የንግድ ቦታዎች በውስጣቸው ከነበረ ሙሉ ንብረት ጋር መውደማቸው ተገልጿል።

በቃጠሎውም የ23 ግለሰቦችና የተለያዩ ተቋማት ንብረት የሆኑ በጥቅሉ ከ1.2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የመቅደላ ወረዳ ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በማህበራዊ ገጹ ባሰፈረው መረጃ አስፍሯል ።

በደብረማርቆስ ከተማ ቀበሌ 05 በተለምዶ ጉልት ገበያ ተብሎ በሚጠራ የገበያ ስፍራ ምሽት 3፡00 አካባቢ በደረሰ የእሳት አደጋ ግምቱ ያልተገለጸ ንብረት መወድሙን፣ ነገር ግን በገበያው የሚገኙ ሱቆችና ኮንቴይነሮች በአብዛኛው መውደማቸውን የተነገረ ሲሆን በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አለመድረሱ ተገልጿል።

የሶማሌ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ጅግጅጋ ከተማ ቀበሌ 02 በልዩ ስሙ ድብኡራሾ ሱቅ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢም የእሳት አደጋ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ተከስቶ እንደነበር ይታወቃል። ከአንድ ሱቅ እንደተነሳ በተገለጸው የእሳት አደጋ በሰው ህይወት ላይ ምንም አይነት ጉዳት ያላደረሰ ሲሆን በፍጥነት በተዛመተው እሳት ሰባት የንግድ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ አደጋ አድርሷል። በዚህም በድምሩ ወደ 1.2 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረት መውደሙ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

በደቡብ ክልል በወላይታ ሶዶ ከተማ “መርካቶ ገበያ” መንስኤው ባልታወቀ የእሳት አደጋ የተከሰ ሲሆን በወቅቱ እሳቱን ለማጥፋት የወላይታ ሶዶ ከተማ እሳት አደጋ መከላከያ ቡድን ጥረት ያደረገ ቢሆንም በነበረው ከባድ ነፋስ እሳቱ በከፍተኛ ፍጥነት መዛመቱ ተገልጿል።

አደጋው በበርካታ የንግድ ሱቆችና ተቋሟት ላይ ውድመት ያስከተለ ሲሆን፤ ማለዳ የተነሳውን የእሳት አደጋ መቆጣጠር የተቻለውም ከ6:20 በኋላ እንደነበር በወቅቱ የከተማው አስተዳደር አሳውቋል።

በሶዶ ከተማ የገበያ ቦታ ተመሳሳይ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ሲደርስ ለ5ኛ ጊዜ ሲሆን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የግብይት ማዕከሉን ዘመናዊ ለማድረግ እንደሚሰራም ተገልጿል።

በሌላ በኩል በሀላባ ዞን ዌራ ወረዳ ላይኛ በደኔ ቀበሌ ላይ ውስጥ በተከሰተ የእሳት አደጋ 11 መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን የወረዳው አስተዳደር አስታውቋል።
አሁንም ምክንያቱ ባልተወቀ ሁኔታ ከረፈዱ 5:00 ሰዓት አካባቢ የተነሳው ይህ የእሳት አደጋ ያደረሰው የንብረት ጉዳት ግምት አልተገለጸም።

በደቡብ ክልል በሀዲያ ዞን ሁለት ወረዳዎች ላይ ባልታወቀ ምክንያት በደረሰ የእሳት አደጋ 510 የቤተሰብ አባላት መፈናቀላቸውን የዞኑ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ገልጾ ነበር።

በወቅቱ እንደተነገረው በሀዲያ ዞን ምሻ ወረዳ በሦስት ቀበሌዎች ኤራ ጌሜዶ፣ ኩናፋ፣ ጉና ሜጋቾ እንዲሁም በሌሞ ወረዳ ኦሞ ሾራ አራት ቀበሌዎች በደረሰ እሳት አደጋ ሁለት ቆርቆሮና 45 የሳር ክዳን ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ተገልጿል።

በአደጋው በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም በርካታ ቁጥር ያላቸው በድምሩ ከ23 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል።
በተጨማሪም በዞኑ ውስጥ በታኅሣስ ወር ብቻ በሆሳዕና ከተማ እና ወረዳዎች 15 ሱቆች 47 ቤቶች፣ በእሳት ተቃጥለው 33 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ዞን ገልጿል።

በደቡብ ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን ቤሮ ወረዳ ሾላ ቀበሌ ከቀኑ11፤00 ሰዓት በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ586 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ተገለጿል።
ከባድ ጉዳትን ባደረሰው በዚህ የእሳት አደጋ ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ 1ሺህ 840 መኖሪያ ቤቶችና 547 የንግድ ቤቶች እንዲሁም በወርቅ ሥራ የሚተዳደሩ 37 ማኅበራት ንብረታቸ ሙሉ በሙሉ ወድሟል ሲል ቢቢሲ አማርኛ ያጠናቀረው መረጃ ያመለክታል።

በአደጋው 16 ሺህ 709 ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቤታቸው በመፈናቀላቸው በሐይማኖት ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ቤት መጠለላቸው ተገልጿል።
በእሳት አደጋው ምክንያት ንብረት የወደመባቸው ነጋዴዎች በአማካኝ እስከ 200 ሺሕ ብር የሚገመት ንብረት ማጣታቸውን ገልጸዋል። ጉዳታቸውን የበለጠ የሚያወሳስበው የንገድ ሥራቸውን በብድር ገንዘብ መጀመራቸው እንደሆነ እና ያካሄዱት ወደነበረው የንግድ ሥራ ለመመለስ ሁኔታውን አስቸጋሪ እንደሚያደርግባቸው ተናግረዋል።

ከመቶ ሚሊዮኖች በላይ የሕዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ የሚደርሱ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ አደጋዎችን ለመከላከል ያላት ዝግጁነት ደከማ መሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአገር ሃብት እያወደመ ይገኛል።

በከተማችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የእሳት ቃጠሎዎች በከተማው ህዝብና አመራሮች፣ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሰራተኞች፣ የፀጥታ አካላትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ መቆጣጠር ተችሏል ቢባልም ጉዳቱ እና መጠኑ በማሻቀብ ላይ በመሆኑ የሚነግረን የተለየ መልእክት እንዳለ ከከተማ አስተዳደሩ መግለጫዎች መረዳት ይቻላል።

‹የጥፋት አላማቸው ያልተሳካላቸው አካላት ሆን ብለው ህብረተሰቡን ለማሸበር እያደረጉት ያለው ተግባር እንደማይሳካ እናሳውቃለን።ህብረተሰቡ ሳይደናገጥ ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ፣ ሳይዘናጋ ነቅቶ አካባቢውን በመከታተል እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መረጃ በመለዋወጥ ያለምንም ስጋት መደበኛ እንቅስቃሴውን ማስቀጠል ይኖርበታል› ሲል ማሳሰቡን ማንሳት ይቻላል።

የጥፋት ተግባራትን በማክሸፍና ህብረተሰቡን ከአደጋ በመታደግ ከተማ አስተዳደሩ ለነዋሪው ችግር ቀድሞ የመድረስ ግዴታውን በአግባቡ እየተወጣ በመሆኑ እርስ በእርስ የመተጋገዝ አስቸጋሪ ወቅቶችን በጋራ የማለፍ ጉዞአችን በአብሮነት የሚቀጥል መሆኑን እንገልፃለን በማለቱም ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com