የእለት ዜና

በኹለተኛው ግማሽ ዓመት በቀረጥ ነፃ ምክንያት 12 ቢሊዮን ብር የገቢ ጉድለት ሊጋጥም ይችላል

ኢትዮጵያ በ2013 በኹለተኛው በጀት ዓመት ተገቢ ባልሆነ ከቀረጥ ነፃ ተጠቃሚነት ምክንያት 12 ቢሊዮን ብር የገቢ ጉድለት ሊጋጥማት አንደሚችል የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ አንዳስታወቀው በሚቀጥሉት ቀሪ የ2013 በጀት ዓመት ወራት ብቻ 12 ቢሊዮን ብር በቀረጥ ነፃ አማካኝነት የሚታጣውን ገቢ ከዚህ በፊት በተፈጸሙ ክዋኔዎች ላይ የተመሰረተ ጥናት በማድረግ የተሰላ መሆኑን ተጠቁሟል። ኮሚሽኑ ተጠባጭ መረጃዎችን በማሰባሰብ በሰነድ መረጃ በማስደገፍ ያገኘው መረጃ መንግሥት ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መብት የሚሰጣቸው እቃዎች ላይ ገደብ ያስፈልጋል ሲል ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ግምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ለአዲስ ማለዳ አንደተናገሩት ኢትዮጵያ ባለፉት ስድት ወራት ያስተናገደችው ከቀረጥ ነፃ አገልግሎች በጣም ከፍተኛ ነው ብለዋል። ኮሚሽነሩ አክለውም ከቀረጥ ነፃ መብት የተሰጣቸው ድርጅቶች ተገቢ መሆኑንና ለትክክልኛ አላማ የሚውል መሆኑን መመዘን ይገባል ብለዋል።
የሚፈቀዱ የቀረጥ ነፃ መብት ሲፈቀድ በሚፈጥረው የሥራ ዕድል፣ ለአገር ውስጥ ገቢ በሚያስገኘው መጠንና ለተገቢው አላማ እንደሚውል ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ከሆነ ገቢ መሆን የሚችለው ቀርቶ ወደ ኪሳራ የሚከት ነው ብለዋል ኮሚሽነሩ።

ኮሚሽኑ ባደረገው ጥናት መሰረት ከቀረጥ ነፃ የሚታጣው የገቢ ጉድለት ለማስቀረት ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ እቃዎች ለተፈለገው አላማ ካልዋሉ ፍቃድ አለመስጠት አንዱ መፍትሔ አካል መሆኑን ደበሌ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ከሆነ አሁን ያለው የቀረጥ ነፃ መብት ባለበት ከቀጠለ የገቢ ጉድለቱ እየጨመረ እንደሚሄድ ነው።

ኢትዮጵያ በ2013 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የገንዘብ ሚኒስቴር በፈቀደው ከቀረጥ ነፃ መብት 36 ቢሊዮብ የሚገመት እቃ ያለ ቀረጥ መግባቱን ኮሚሽነሩ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የተደረጉ እቃዎች የቀረጥ ገቢ ተመን 36 ቢሊዮን ብር የደረሰው ተገቢ ያልሆነ የከቀጥ ነፃ መብት ስለተጋነነ መሆኑን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

የቀረጥ ነፃ አጠቃቀም ክትትል አፈፃፀም ባለፉት ስድስት ወራት ሲገመገም በቱሪስት ሥም ገብተው ያልወጡ 24 ተሸከርካሪዎች፣ በኮንትሮባንድ የተጠረጠሩ 27 ተሸከርካሪዎች እና ስድስት ተሸከርካሪዎች ደግሞ በቀረጥ ነጻ ገብተው ከታለመለት አላማ ውጭ በመዋላቸው በአጠቃላይ በግማሽ ዓመቱ 57 ተሸከርካሪዎች ተይዘዋል። ከ57ቱ ተሸከርካሪዎች በ24ቱ ተሽከርካሪዎች ቀረጥና ታክስ ብር 63 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ገቢ የተገኘ ሲሆን ቀሪዎቹ 33 ተሸከርካሪዎች ቀረጥና ታክስ አልተሰራላቸውም። 465 የሚሆኑ የጉምሩክ ማበረታቻ ተጠቃሚዎች ላይ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ የተከናወነ ሲሆን 300 ድርጅቶች በሕጉ መሠረት መጠቀማቸው፣ 61 ድርጅቶች ከታለመላቸው ዓላማ ውጭ መጠቀማቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋሉ።

ከቀረጽ ነፃ የሚገቡ የድርጅት እቃዎች ለታለመላቸው አላማ አለመዋላቸውን የሚያመላክቱ መረጃዎች በመገኘታቸው ኦዲት እንዲደረጉ ለድህረ ዕቃ ኦዲት ተላልፈው በ29 ድርጅቶች ላይ ብር 292 ነጠብ አራት ሚሊዮን ብር ቀሪ ሂሳብ ተጠይቆባቸዋል ተብሏል።

የቀረጥ ነፃ ክትትልና ቁጥጥር በዘርፍ ስብጥር በኮንስትራክሽን 114 ድርጅቶች ላይ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጎ 65 ድርጅቶች የተሰጣቸውን ማበረታቻ በአግባቡ ሲጠቀሙ 21 ድርጅቶች መብቱን ከታለመለት አላማ ውጭ አውለው ተግኝተዋል። ኮንስትራክሽን መሳሪያዎች ኪራይ 35 ድርጀቶች ላይ የማጣራት ሥራ ተሰርቶ 28 ድረጅቶች ለታለመለት አላማ ሲያውሉ ቀሪዎቹ 14 ድርጅቶች ከታለመለት አላማ ውጭ ተጠቅመው ተገኝተዋል ተብሏል።

ማምረቻ ኢንዱስትሪ 149 ድርጅቶች ላይ ማጣራት ተደርጎ 114 ድርጅቶች ያገኙትን ከቀረጥ ነፃ ማበረታቻ በተገቢው ሲጠቀሙ ቀሪዎቹ 14 ድረጅቶች ከታለመለት አላማ ውጭ ሲጠቀሙ ተይዘዋል። በሆቴል ዘርፍ 73 ድረጅቶች ላይ ማጣራት ተደርጎ 57 በተገቢው ሲጠቀሙ ስምንት ድርጅቶች ከአላማው ባፈነገጠ መንገድ ተጠቅመው መገኘታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!