የእለት ዜና

የጉምሩክ ኮሚሽን ከመቀሌ ቅርንጫፍ በኹለት ወራት ተኩል 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ማጣቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በትግራይ ክልል ጥቅምት 24/2013 በተከሰተው ችግር ምክንያት ላለፉት ኹለት ወራት ተኩል ከመቀሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ መሰብሰብ የነበረበትን አንድ ነጥብ ኹለት ቢሊዮን ብር መሰብሰብ አለመቻሉን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ የሚገኘው የጉምሩክ ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽፈት ቤት በትግራይ ክልል በሕወሓትና በፌደራል መንግሥት መካከል በተፈጠረው ጦርነት(ሕግ የማስከበር ዘመቻ) ምክንያት ከኹለት ወራት ተኩል በላይ ያለ አገልግሎት መቆየቱን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። ኮሚሽኑ ከመቀሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽፈት ቤት በአንድ ወር 480 ሚሊዮን ብር በቀጥታ ይሰበስብ ነበር ብለዋል ደበሌ። ይሁን እንጅ በነበረው የጸጥታ ችግር ቅርንጫፍ ጽፈት ቤቱ ሙሉ በሙሉ አገልገሎት አቁሞ መቆየቱን ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።

ኮሚሽነሩ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ አንደገለጹት ከሆነ የኮሚሽኑ ቅርንጫፍ ጽፈት ቤት ንብረት ሙሉ በሙሉ መውደሙን አረጋግጠዋል። ከኮሚሽኑ ንብረት ውድመትና መዘረፍ በተጨማሪ ሰነዶች እንደወደሙ ገልጸዋል። ከተዘረፉት የኮሚሽኑ ንብረቶች መካከል ተሸከርካሪዎች፣ ጀነሬተርና የቢሮ እቃዎች ይገኙበታል።
“በመቀሌ በነበረው የጸጥታ ሁኔታ የሚሰበሰብ ገቢ አይጠበቅም” ሲሉ ሁኔታውን ያስታወሱት ኮሚሽነር ደበሌ የኮሚሽኑ ንብረት መዘረፉ እና መውደሙ ሌላ ቸግር ነበር ብለዋል።

ኮሚሽኑ ከመቀሌ ቅርንጫፍ ጽፈት ቤት በኹት ወር ተኩል ያገኘው የነበረውን ገቢ በሌሎች ቅርንጫፍ ጽፈት ቤቶች በኩል እንድካካስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ደበሌ ጠቁመዋል። በዚህም ኮሚሽኑ ለኮምቦልቻ፣ ለኤርፖርትና ሞጆ ቅርንጫፍ ጽፈት ቤቶች የመቀሌውን ገቢ ለማካካስ ተጨማሪ ሥራ ተሰጥቷቸው የተሰጣቸውን ሥራ በብቃት መፈጸም ችልዋል ሲሉ ደበሌ አክለዋል።

ኮሚሽኑ ከጥቅምት 24/2013 ወዲህ በመቀሌ ቅርንጫፍ ጽፈት ቤት ይሰጠው የነበረውን አገልግሎት ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሩን ኮሚሽነሩ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። ቅርንጫፍ ጽፈት ቤቱ ለደንበኞች አገልግሎት መስጠት የጀመረው ባሳለፍነው ሳምንት መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ከየካቲት ወር ጀምሮ ገቢ መሰብሰብ ይጀምራል ብለዋል። ኮሚሽን ለአገልገሎት የሚስፈልጉ መሰረታዊ የቢሮ እቃዎችንና አስፈላጊ ነገሮችን ለማሟላት ተጨማሪ በጀትና የቁሳቁስ ድጋፍ እያተደረገ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

አገልግሎቱን የጀመረው የመቀሌ ቅረንጫፍ ጽፈት ቤት በተፈጠረው የጸጥታ ቸግር ምክንያት እቃቸውን ከደረቅ ወደብ ያላነሱ ደንብኞች በልዩ ሁኔታ ከቅጣት ነጻ እቃቸዉን እንዳነሱ እንደሚደርግም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል። በሕጉ መሰረት አስመጭዎች እቃቸውን በደረቅ ወደብ ላይ ማቆየት የሚችሉት እስከ 15 ቀን ብቻ መሆኑ በአዋጅ ቁጥር 1160/2011 ተደንግጓል። በአዋጁ ድንጋጌ ላይ እንደተቀመጠው ከሆነ አንድ አስመጭ በደረቅ ወደብ ላይ ከ15 ቀን በላይ እቃውን ካላነሳ የ20 በመቶ ተጫማሪ ቅጣት ለመክፈል ይገደዳል። ይሁን አንጅ ኮሚሽኑ ሕጉን በልዩ ሁኔታ አይቶ ባለንብረቶች ንብረታቸውን እንዳነሱ ለማድረግ እየሰራ ነው ተብሏል።

ኮሚሽኑ የአገሪቱን የፋይናንስ አቅም ለማመንጨት በ2013 በጀት ዓመት ብር 125 ነጥብ 54 ቢሊዮን ለመሰብሰብ በዕቅድ አስቀምጦ የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በግማሽ ዓመት ብር 58 ነጥብ 72 ቢሊዮን ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ብር 55 ነጥብ 75 ቢሊዮን ወይም የዕቅዱን 94 ነጥብ 95 በመቶ መሰብሰብ ችሏል። ይህም አፈጻጸም ከተያዘው የገቢ ዕቅድ አንጻር ሲታይ የኹለት ነጥብ 97 ቢሊዮን ብር ወይም የአምስት በመቶ መቀነስ ያሳያል፣ እንዲሁም አፈፃፀሙ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው ብር 54 ነጥብ 14 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር በብር አንድ ነጥብ 61 ቢሊዮን ወይም የኹለት ነጥብ 97 በመቶ ብልጫ አለው።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com