የእለት ዜና

አስካለ ተስፋዬን የማዳን ጥሪ

ከሰሞኑ በጠና መታመሟ ሲነገር ሰንብቷል፤ አፋጣኝ ርዳታም እንደሚያስፈልጋት ጭምር። አዲስ ማለዳም በጋዜጠኝነት ሙያዋ ከ20 ዓመት በላይ እያገለገለች ያለችውን ‹የውሎ አዳር› አዘጋጇን አስካለን ለማናገር ወደ ስልኳ ደወለች። ‹በውሎ አዳር› እና በሌሎች ፕሮግራሞቿ የምናውቀው ጆሮ ገብ ድምጿ ዛሬ ተዳክሟል። ስትናገር በዝግታ ነው።

ስለተፈጠረው ሁኔታም ከሕመሟ ጋር እየታገለች እንዲህ በማለት ጀመረች። ‹‹የጭንቅላት ግፊት ነው። ምክንያቱ ያልታወቀ ሕመም ነው›› በማለት በጭንቅላት ውስጥ የተቋጠረ (የተጠራቀመ) ፈሳሽ እንዳለም የሕክምና ባለሞያዎች እንደነገሯት ነው የምትናገረው።
ሕመሟ ራሷን በጣም የሚይዝ እና በጣም የሚያም ከባድ በመሆኑም በአሁን ወቅት ማስታገሻ መድኀኒትም እየወሰደች ትገኛለች። የደም ግፊቱም ይህን ፈሳሽ እንደሚጨምረው እና ዐይንንም እስከመጋረድ ይደርሳል ተብሎ በሐኪም ስለተነገራት ‹‹ከዚህ ቀደም መድኃኒቱን መውሰድ አቁሜ ነበር። አሁን ግን ራሴን ሲያመኝ እና ዐይኔንም ሲወጥረኝ በድጋሚ መውሰድ ጀምሬያሁ።›› ትላለች።

አስካለ አሁን ላይ በዚህ ሕመም እየተሰቃየች ትገኛለች። ይባስ ብሎም ከአምስት ዓመት በፊት የገጠማት የዲስክ መንሸራተት ሕመም ተጨምሮበት ሁኔታውን ከባድ አድርጎባታል። አስካለ ለመጨረሻ ጊዜ የሄደችው ወደ አውራምባ ሲሆን እዛም ስትሄድ ፊቷ አብጦ እንደነበር ታስታውሳለች። ‹‹ሌላው ጊዜ የወገብ ሕመሜ ሲጀምረኝ ወጣ ብዬ ኹለት መርፌን ተወግቼ እመጣለሁ›› ትላለች ብርቱዋ አስካለ። በተፈጥሮ አመመኝ ማለት የማትወደው ‹የውሎ አደር› አሰናጅ፤ ‹‹አሁን የጭንቅላት ሕመም ስለሆነ የግድ ሆኖብኝ ነው ከሥራዬ የራቅኩት።›› ስትልም ትናገራለች።

አስካለ በባልደረባዋ አንደበት
በአንድ የሥራ ክፍል ውስጥ ይሠራሉ፤ አምስት ዓመታትን ከአስካለ ጋር መሥራት ችሏል። ‹ውሎ አዳር›ን መሥራት ከጀመሩ ደግሞ ሦስት ዓመታትን አስቆጥረዋል። ታዲያ በብዙዎች ዘንድ የሚወደደውን የ‹ውሎ አዳር› የአርትኦት ሥራ የሚሠራው ይስሐቅ ጩቱሉ ለአዲስ ማለዳ ሲናገር፣ አስካለ ተስፋዬ ፕሮግራሙን ሕይወት እንደዘራችበት ነው የሚገልጸው።

ይስሐቅ ስለ ፕሮግራሙ ሲናገርም ‹‹የገጠሩን ባህል ለውጪው ዓለም እና ከተማ ላለው ሰው የሚያስተዋውቅ ነው። ይህን ፕሮግራም ለመሥራት ለትራንስፖርት አመቺ ባለመሆኑም ብዙዎች አይደፍሩትም። ብዙዎችም ቢሆን የሚናገሩት ይህንን ሥራ ለመሥራት አድካሚ እንደሆነ ነው። በወጪም ደረጃ፣ በማኅበራዊ ሕይወት በኩልም አመቺ አይደለም ይላሉ። አስካለ ግን በዚህ ትመሠገናለች›› ሲል ብዙዎች ለመሥራት የማይደፍሩትን እርሷ ግን ያውም ሥራውን ወዳው እና ደስተኛ ሆና እንደምትሠራው ምስክርነቱን ሰጥቷል።

ይህ ብቻ አይደለም ይላል አርታኢዋ ይስሐቅ ‹‹እርሷ ግን ማኅበረሰቡን ሆና ተገኝታ ነው የምትሠራው። ማኅበረሰቡን ሆና ነው የምትገኘው። ያዘጋጁትን በልታ ጠጥታም ነው የምትሠራው። የ‹ሪያሊቲ ሾው› ነው። ምላሾቹም ጥሩ ናቸው።›› ሲልም ይናገራል።
ይስሐቅ አክሎ ሲናገር እንዲህ ይላል፤ ‹‹አስካለ የሔደችባቸው አካባቢዎች መታመሟን ሲሰሙ በጣም ተደናግጠዋል። እኛንም ደውለው እያጨናነቁን ነው። እንደውም በባህላችን መሠረት መጥተን አንጠይቃትም ወይ የሚሉም ብዙዎች ናቸው።››
ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ 80 ብሔር ብሔረሰቦች አሉ። አስካለ ያልረገጥችው አካባቢ እና ክልል የለም ማለት ይቻላል። ተሠርተው ለተመልካች ያልተላለፉ ብዙ ፕሮግራሞች አሉ። ከሄደችባቸው አካባቢዎች መካከልም በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ስልጤ ዞን ጀረሞ ሰንቦዬ ቀበሌ፣ ሀድያ ዞን ጊቤ ወረዳ ሆመቾ ቀበሌ፣ ሀላባ ዞን አቶቴ ኡሎ ወረዳ፣ የም ልዩ ወረዳ ፎፋ እና አካባቢው፣ ጋሞ ዞን ጨንቻ ልዩ ወረዳ ዶኰ ሎሻ ቀበሌ እና ከፋ ዞን ጨና ወረዳ ኮዳ ቀበሌ ሌሎችም ይጠቀሳሉ።

በአማራ ክልል፤ አዊ ዞን ጓንጓ ወረዳ ስጋዴና ሦስቱ ሹመታ ቀበሌዎች፣ ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ቀበሌ፣ ከሚሴ ዞን ከሚሴ ተጠቃሾቹ ናቸው። በትግራይ ክልል ምሥራቃዊ ዞን ኢሮብ ወረዳ አሊቴና ቀበሌ፣ ኮረም ኦፍላ ወረዳ መንከረ ቀበሌ፣ ደቡብ ምሥራቃዊ ዞን ደጉኣ ተምቤን ወረዳ፤ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ኮፈሌ ወረዳ፣ የአፋር ክልል አፋምቦ ወረዳ ሜጉ ቀበሌ ጋምቤላ ክልል የተለያዩ ቀበሌያት፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ ቀበሌያት፤ ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ ከተማ በተለይም በተማሪዎች ምገባ ላይ የሠራቻቸው ፕሮግራሞችም አይረሱም።

‹‹ሥራዬን በጣም ነው የምወደው። ሕዝቡም በጣም ይወድልኛል። ራሴ ነኝ ኤዲቲንግ የምሠራው። ቅዳሜ እሁድ የእረፍት ጊዜን በሥራ ነው የማሳልፈው። እንደውም አንዳንዴ ምሳ ሰዓቴን የምረሳበት ቀንም አለ›› በማለት ለሙያዋ ያላትን ጥልቅ ፍቅር ትናገራለች፤ አስካለ።
‹በውሎ አዳር› ይበልጥም ከፕሮግራሙ ስትርቅ ሰው ምን ያህል እንደሚወደው ለማወቅ በመቻሏም ደስተኛ ናት። ‹‹አንድ ሠው ፕሮግራሙን ወዶት ሲያየው ደስ ይላል። ምንም ዓይነት ዲኮሬሽንም የለውም።›› ብላለች። ሕይወትን የሚያሳይ ፕሮግራም እንደሆነም ስትናገር ‹‹ከእኔ ጀምሮ ብትመለከቺ ኩል የለ፣ ሜካፕ (ሠው ሠራሽ መዋቢያ) ያለውን ነገር የሚያሳይ ነው።›› ብላለች።

አስካለ ‹‹ጎበዝ አርታኢ አለ። ይስሐቅ ጩቱሉ ይባላል። ከእርሱ ጋር እየተነጋገርን ነው የምንሠራው።› የምትልለት ባለደረባዋ የእርሷ መታመም በሠራተኞቹ ላይ በጣም መደናገጥ ፈጥሯል ይላል። በሙያው ከ20 ዓመት በላይ የሠራች በመሆኑም ብዙ የተማሩት ነገር እንዳለ ይጠቅሳል።

‹‹ማንም ሰው የሚያውቃት በሥራ ታታሪነትዋ ነው። ታማ እንኳን ለሥራ የመጣችባቸው ቀናት ጥቂት አይደሉም። ሁል ጊዜም ቢሆን ሥራ ላይ ናት። አሁን እኛ የምናስበው እንዴት ነው ማዳን የምንችለው የሚለውን ነው። ለጣቢያው ገጽታም ስለሆነች እኛ የራሳችንን እያጣርን ነው።›› በማለት ይገልጻል።

አያይዞም ‹‹ምንም እንኳን በኮቪድ ምክንያት ለጤናዋ በማሰብ ቤቷ ድረስ ሄደን ባንጠይቅም፤ በስልክ እናወራታለን። በሐኪም ዘንድ በስልክ ብዙ እንዳታወራም ተነግሯታል። ብቻ የእሷን ጉዳይ በዐይነ ቁራኛ እየተከታተለ ነው። ሁሉም ሰው ድና ወደ ሥራ መመለስዋን ነው የሚፈልገው።›› ሲልም ምኞቱንና ተስፋውን ይናገራል።

ስለ ጸባይዋ
አስካለ ለአዳዲስ እና ወጣት ጋዜጠኞች ልምዷን ማካፈልና ምክር መለገስ ታውቅበታለች። በተለይም ወጣት ሴቶችን ስትመክር ዝቅ ብለው እንዲሠሩ ሳትታክት ነው የምትናገረው። ይህን የሚለው አርታኢዋ ይስሐቅ ነው። አስካለ በጣም ታታሪ ሠራተኛ መሆኗን ሲገልጽም፣ ‹‹ለአዲቴንግ ወንበር ላይ ለረዥም ሰዓታትን በመቀመጥ አድራ ትሠራለች። ይህም ለወገቧ ሕመም መንስኤ እንደሆነ እገምታለሁ። እርሷ ትለያለች። ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪም ጥሩ ኤዲተርም (ድምጽ ወ ምስል አቀናባሪ) ናት።›› ብሏል።

አስካለ ‹ውሎ አዳር›ን ለመሥራት ቀናቶችን በሄደችባቸው አካባቢዎች ለማሳለፍ ትገደዳለች። ታዲያ በዚህ ጊዜም ከካሜራ ባለሞያዎች ጋር እና እንዲሁም ሾፌር አብረዋት ይሄዳሉ። አንዳንዴ የዳይሬክተርነቱ ሚናም የምትወጣበት ቀን አለ። አስካለ ትሁት ናት። ወርዳ መሥራት ትወዳለች። ሥራዎች በሚገመገምበት ሰዓት የራሷን በድንብ ትገመግማለች። ሕይወትንም ቀለል አድርጋ የምትኖር ናት። ለምትበላውም ይሁን ለምትጠጣው ነገር እምበዛም አትጨነቅም። ይህን ሁሉ የሰማነው ከይስሐቅ ነው።

ታዲያ አስካለ ለሠራችው ሥራ በአሜሪካ ውስጥ የሚገኝ ባህል ላይ የሚሠራ አንድ ድርጅት በ2012 የምስክር ወረቀት አበርክቶላታል። ውሃ ከመቅዳት ጀምሮ የአርሶ አደሩን ኑሮ በመኖር ለእለታትም ቢሆን ኖራዋላች። ‹‹ሕዝቡ ለሰው ያለው ፍቅር ልነግርሽ አልችልም። እኛ እኮ ተጠራጣሪ ነን። የገጠሩ ሠው ጎጆውን በዕምነት የሚሰጥ ምስኪን ማኅበረሰብ ነው።›› አለች፤ በገጠሩ አካባቢ ስለሚኖረው ማኅበረሰብ የዋህነት ስትናገር።

‹‹ጭንቅላትሽ እኮ ደርቋል ብሎ ቅቤ የሚቀባ ነው፤ ተንኮል የሌለበት። ንጹህ ሕዝብ ነው›› ትላለች። እንዲህም ሆና እንኳ ገና ምንም አልሠራንም ስትል ትናገራላች። ‹‹ይህ ሁሉ ተፈጥሮ፤ ወንዝ፤ መልክዓ ምድር ያለን ነን። ገና ብዙ ያልሠራንበት ነገር አለ። እኛ ግን አንድ ቦታ ላይ ብቻ በማተኮር ያዙኝ ልቀቁን እንላለን።›› ትልና ቀጠል አድርጋ ሌላ ጥያቄም ታነሳለች። አሁን እየሆነ ካለው ነገር በማነጻጸር፣ ‹‹ይህ የእኛ አገር ነውን?› ስትል። ‹‹ይህ ለምን እንደሆ እንጃ! ብቻ ፈጣሪ ብቻ ልቦናችንን ይመልስልን።›› ስትልም ትማጸናለች።

መልዕክት
‹‹አስካለን ማዳን እንደ ሠው ኃላፊነት እንዳለብን አውቃሁ። ነገር ግን እንደሚዲያ ባለሙያ መልዕክቴን ሳስተላልፍ አስካለን ብናጣ የኢትዮጵያን ባህል እንደምናጣ እና አንድ ቤተ መጸሐፍ እንደወደመ ነው የምናስበው። ማጣት ሲባልም በሕይወት ብቻ አይደለም።›› የሚለው ይስሐቅ ‹‹ከሥራ ገበታ እርሷን በማጣታችን ብቻ የሚታጎሉብን ብዙ ነገሮች አሉ። ሕይወቷን ማትረፍ አለብን። ይህ ለእርሷ ስንል አይደለም። ለራሳችንም ስንል ነው። ሁሉም መገናኛ ብዘኀን መጣር አለበት። እንዲሁም አሁን ባለንበት ጊዜ በገጠር የሚኖረው ማኅበረሰብ ቁጥር ከ70 እስከ 80 በመቶ ነው ተብሎም ይገመታል። በመሆኑም ሚዲያዎች የምንሠራው ሥራ የገጠሩን ያማከለ ቢሆን ይመረጣል። ልክ የአስካለን ፈለግ በመከተል የማኅበረሰሰቡን ባህልና ታሪክ እናውጣ።›› ሲልም ያሳስባል።
የ‹ውሎ አዳር› አዘጋጅ አስካለ ተስፋዬን ሕይወት ለመታደግ በሥሟ በተከፈተው የንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር ‹አስካለ ተስፋዬ፤ 1000189582505› ነው። የተቻለንን ያህል በመርዳት ሕይወቷን እናትርፍ ስትል አዲስ ማለዳም ትጠይቃለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com