የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማነቆዎች

Views: 339

ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለፌደራል እና ለክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች እንዲሁም ለአዲስ አበባ እና ለድሬዳዋ መስተዳድር ምክር ቤቶች ግንቦት 28 እና ሰኔ 05 2013 እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥርዓተ-ፆታ አካታችነትን በተመለከተ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር ከታህሳስ 2019 እስከ የካቲት 2020 በብሄራዊ የምርጫ ቦርድ፣ በተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት(UN Women) እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP) የተጠና አገራዊ ጥናትን ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርጓል፡፡

በወቅቱ የጥናት ውጤቱን ያቀረቡት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሥርዓተ ፆታና ማህበራዊ ጉዳዮች ኀላፊ መድሃኒት ለገሰ፤ በኢትዮጵያ ካሉ እና በጥናቱ ከተካተቱ 70 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሴት ከፍተኛ አመራሮች ያሏቸው ፓርቲዎች ኹለት ብቻ እንደሆኑ መግለጹ ይታወሳል።

በዚህ ጥናት መሰረት አንድ ሴት መሪ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ብቻ እንደሆነ እና መሪዋም ቆንጂት ብርሃነ መሆናቸው ተገልጿል። ኹለተኛዋ ምክትል መሪ ደግሞ ከአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) ማርታ ካሳ መሆናቸው ታውቋል።
ጥናት አቅራቢዋ በጥናቱ ከተካተቱ 70 ዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፤ በአባልነት ለመመልመል በፓርቲ መዋቅሮች ውስጥ የውሳኔ ሰጭነት ቦታዎችን በመያዝ ረገድ ሊደረግ የሚችል በፆታ ላይ የተመሰረተ አድልዎን በግልፅ የከለከሉ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ከሰባዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በ21 ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በፓርቲ መዋቅር ኮሚቴዎች ውስጥ ማለትም በማዕከላዊ ኮሚቴ፣ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና ኦዲት ኮሚቴ ውስጥ ተካተዋል ብለዋል።
ይሁን እንጂ ሴቶች በፓርቲ መዋቅር ውስጥ እንደ ኮሚቴ መሪ ወይም እንደ ምክትል ኀላፊ ሲሆኑ ግን አይታዩም በማለት ገልጸዋል። በጥናቱ ከተካተቱት ውስጥ ደግሞ 21 በመቶ ወይም 15 የሚሆኑት ፓርቲዎች ብቻ በፖለቲካ ፓርቲያቸው የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ለመፍታት የሚያስችል መዋቅር አላቸው ሲሉ ገልጸዋል።

የሴቶች ተሳትፎ በፖለቲካ ፓርቲዎች ወስጥ ለምን ቀነሰ?
በዚህ ጥናት ላይ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሴቶች ቁጥር ለምን ውሱን ሆኑ ለሚለው ጥያቄ ከተቀመጡት ምላሾች መካከል በጠንካራ የአባዊ ስርአት ተጽዕኖ ስር የወደቀ የሥርዓተ ፆታ ግንኙነት ፣ ለሴቶች ምቹ ያልሆኑ የውስጥ ፓርቲ መዋቅሮች ፣ ኃይል እና ጥቃትን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ባህል እና ምህዳር ፣ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ የማይዘግብ ፤ ከዘገበም አሉታዊ እና አፍራሽ ጎኑን ብቻ የሚሸፍን መገናኛ ብዙሃን መስፋፋት መሆናቸው ተጠቅሰዋል።
ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በተለይም ወደ ውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ላይ ያላቸው ውክልና ዝቅተኛ እንደሆነ የጥናቱ ግኝት በግልፅ ያሳያል።

ይህ ለምን እንደሆነ ከሴቶች ሕጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ከተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት (UN Women) ጋር በመሆን በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ያጠኑት ምንያምር ይታይህ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሴቶች በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ እንዳይሆኑ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች አንዱ የፖለቲካ ሥርዓቱ ዴሞክራሴያዊ ባለመሆኑ እና መጠላለፍ የበዛበት ስለሆነ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ፍላጎት እንዲያጡ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
ኹለተኛው ምክንያት ደግሞ የግል ፍላጎት ወይንም የግል ምርጫ አለመኖር እንደሆነ ተናግረዋል። እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ውስጥ በማሕበረሰቡ እና በቤተሰብ የአኗኗር ዘይቤ የሴቶች ኀላፊነት ከፍተኛ በመሆኑ እና ጫናዎች ስለሚበረቱባቸው ፣ሴቶች በፓለቲካ ፓርቲዎች የመሳተፍ ፍላጎት እንዲያጡ ያደርጋቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።

እናትነት፣ሚስትነት እንዲሁም በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ ማንኛቸውንም ነገሮች መሸከሙ እነርሱ ላይ ስለሚበረታ ሴቶች ጊዜ እና ፍላጎት ኖሯቸው ወደ ፖለቲካ ፓርቲዎች መቀላቀልን ወደ ጎን እንዲገፉ ያደርጋቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ሦስተኛው ምክንያት ማሕበረሰቡ ለሴቶች ባለው ኋላ ቀር ግምት እና በትምህርት ማነስ ምክንያት ሴቶች በራስ መተማመናቸውን እንዲያጡ ያድጋቸዋል በራሳቸው ሳይተማመኑ ደግሞ አደባባይ ወጥተው ለመናገር እና ለመከራከር እንዲሁም ሀሳባቸውን ለመግለጽ እንዲቸገሩ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

እንደ አራተኛ ምክንያት የጠቀሱት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ ወንዶች የበላይነት እና በፓርቲዎች መስራች አባልነት ደረጃም ስናየው ሁሉም ፓርቲዎች በሚባል ደረጃ በወንዶች የተመሰረቱ መሆናቸው እንዲሁም መስራቾቹ እራሳቸው በኀላፊነት ቦታ ላይ መቀመጣቸው ነው ብለዋል።

ምንያምር አክለውም አሁን እያስተዳደረ ባለው የመንግሥት አካል የሴቶች የስልጣን ደረጃ እና የፖለቲካ ተሳትፎ በፌድራል ደረጃ 50 በመቶ የደረሰ ቢሆንም በክልሎች በዞን እና በወረዳ ደረጃ ግን ከ20 በመቶ በታች መሆኑን ገልጸዋል።
አንደ አገር የምትተዳደርበት ሥርዓት ፌደራላዊ በመሆኑ እና በርካታ ብሄር እና ብሄረሰቦች እንዲሁም ጎሳዎች ስላሉ ሴቶች እኩል ተወክለው ስልጣን እንዳይዙ እንዲሁም የፖርላማ አባል እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።
አብዛኛቹ ሴቶች ኢኮኖሚ ራሳቸውን ያለመቻላቸው እና በወንዶች የኢኮኖሚ አመንጭነት በመተዳደራቸው ራሳቸውን ችለው በግላቸው ለምርጫ እንዳይወዳደሩም አንዱ ተግዳሮት ነው በማለት ተናግረዋል።

በቀጣዩ የ10 ዓመት እቅድ የሴቶች የፓርላማ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድርሻ 50 በመቶ ማድረስ ነው። የፓርላማ አባልነት በኹለት መንገድ የሚገኝ ሲሆን አንዱ በፖለቲካ ፓርቲዎች አባል በመሆን እና ፓርቲያቸውን ወክለው በመወዳደር ሲሆን ኹለተኛው ደግሞ በግል ተወዳዳሪ ሆኖ በመቅረብ ነው።

ነገር ግን አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴት አባሎቻቸው ቁጥር አነስተኛ ነው። ሴት አባላቶች የሌላቸውም ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ በሆነበት ሁኔታ እንዴት የሴት የፓርላማ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድርሻ 50 በመቶ ሊሆን ይችላል የሚለውን ጥያቄ ምንያምር ሲመልሱ እንደ ሴቶች ሕጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ ደግሞ በጣም ተሰሚነት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴት የፓርቲ አባሎቻቸውን ቁጥር 50 በመቶ እንዲያደርሱ የሚያስረዳ መድረክ ማዘጋጀታቸውን አስታውሰዋል።
ይህ ካልሆነ እንደ አጠቃላይ ምርጫ ተወዳድሮ መንግሥት የሚመሰርት አካል በምርጫ አሸንፎ ካቤኔ ሲመሰርት የሴቶች ቁጥር ዝቅ እንዲል ያደርግባቸዋል ብለዋል።

እርሳቸው በተሳተፉበት አገራዊ ጥናት እንደ መፍትሄ ከተቀመጡ ሃሳቦች ውስጥ አንዱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባሎች እንዲኖሯቸው ማሳመን እና ምርጫ ቦርድም ሆነ መንግሥት እነዚህን ፓርቲዎች ቢደግፉ እና ቢያበረታቱ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሴት አባሎች እንዲኖሯቸው እንዲሰሩ ያነሳሳል ፤ ራሳቸው ሴቶችን ማበረታታት እና አርዓያ የሆኑ ሴቶችን መሾም እና መሸለም ፤ ሴቶች እንዲማሩ ማድረግ እንዲም ከወረቀት ባለፈ የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደ መፍትሄ መቀመጣቸውን አሳውቀዋል።
በአገራችን ከሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው ኢዜማ በሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ በኩል የሴት እጩ ተወዳዳሪዎችን ቁጥር 34 በመቶ ለማድረስ እየሰራ እንደሆነ ገልጿል።
የኢዜማ የሴቶች ጉዳይ ተጠሪ ገነት አራጌ በበኩላቸው ኢዜማ በብሄራዊ ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ለምርጫ እጩ የሆኑ አምስት ሴት አባላቶች አሉት ብለዋል።

ኢዜማ በሚገኝበት ከ400 በላይ ወረዳዎች ሁሉ ሴቶች ይወከላሉ እንደሚወከሉም አሳቀወል። ይህ ለቁጥር ለይስሙላ ሳይሆን እንደ ፓርቲ ከታች ጀምረን መሥራት ስለሚኖርብን ነው ብለዋል።
ሴቶች ወደ ፖለቲካው እንዳይመጡ ብዙ ፈተናች ያሉባቸው ቢሆን የፖለቲካው ሜዳ በራሱ ሴቶችን የሚጋብዝ አይደለም አይደለም በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
እንደ አንድ ምክንያትም ቤተሰብ ልጆቹ ወደ ፖለቲካ እንዲሳተፍ አለመፍቀዱ ወይንም ባል ሚስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባል እንድትሆን አለመፍቀዱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ገነት ገልጸዋል።
ኹለተኛው ምክንያት የማህበረሰቡ አመለካከት ሲሆን ማህበረሰቡ የሴትን ልጅ ፊት ለፊት መቆምን የማይደግፍ እና እንደ ነውር የሚቆጥር መሆኑ ሴቶች በፖለቲካ እንዳይሳተፉ እንደሚያደርጋቸው አሳውቀዋል።
በተጨማሪም የፖለቲካ ታሪካችን የነበረው ሁኔታ በራሱ ሴቶችን የሚጋብዝ እንዳልሆነ እና የኢኮኖሚ ጥገኝነት እና ሌሎች በሴቶች ላይ ያሉ ችግሮች ሁሉ ነጻ ሆነው ወደ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይቀላቀሉ ያደርጋቸዋል ሲሉ አስተያታቸውን ሰጥተዋል።
የአሕአፓዋ ሊቀ መንበር ቆንጅት ብርሃኔ ኢሕአፓ ወደ አገር ውስጥ ከገባ ኹለት ዓመት እንዳለፈው ገልጸው፣ በመጀመሪያው ዓመት በኮሮና እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች ብዙ ሥራዎች መሥራት ባንችልም የፓርቲው ህልም ሰውን በሰውነቱ የምታከብር እና ለሁሉም ምቹ የሆነች አገርን መፍጠር ስለሆነ አላማችን ሴቶች ተሳትፎ ከፍ ማድረግ ለቆምንለት አላማ እንደ ምርኩዝ ነው በማት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ማህበራዊ መሰረት ሰፊው እና ደሃው ህዝብ በመሆኑ ሴቶች ደግሞ የዚህ ሰፊ ህዝብ ግማሽ አካል በመሆናቸው ከተሳታፊነት የጠነከረ የሴቶች ተጠቃሚነትን ለመጨመር እንሠራለን ብለዋል።
መግቤያችን ላይ እንደተጠቀሰው ጥናት መሰረት የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጨምር በጎ አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው ተብለው ከተቀመጡት መካከል አንዱ የመገናኛ ብዙሃን ነው።
ሴቶችን ወደ ሕዝብ አመራር ለማቅረብ በተለይም እንደ ፖለቲካ ፓርቲ አባል፤ እንደ ጠበቃና የመብት ተከራካሪ፤ እንደ ባስልጣን፤ እንደ መራጭ፤ተመራጭ፤እንደ ምርጫ አስፈፃሚ ወይም እንደ ምርጫ ታዛቢ ወዘተ… ያላቸውን ሚና ለማጉላት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ከተባሉ ተቋማት አንዱ መገናኛ ብዙኃን መሆናቸው ተቀምጧል።

ሌላኛው ደግሞ የሲቪል ማህበራት ሲሆኑ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ሳይሰሩ የቆዩ እና ልምድ ያላቸው ማህበራት ልምድ ለሌላቸው እና ወቅታዊ ጉዳዮችን ላልሰሩ የሲቪል ማህበራት የእውቀት ሽግግርን ለማመቻቸት እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን እንዲተዋወቁና ትብብር እንዲመሰርቱ ለማድረግ እንደሚያስችላቸው ተገልጿል።

የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፎች በተለይም የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጁ ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ማነቆ የሆኑባቸውን ጉዳዮች ስር ነቀል በሆነ መልኩ ለመፍታት የሚያስችሉ ምላሾችን ወይም እርምጃዎችን አካቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡

በመሆኑም የሕግ ማዕቀፉን በዚህ መልኩ መከለስ የሚያስችል የውትወታ ሥራ መስራት በቀጣይነት እና በቋሚነት ትኩረት ሊሰጠውና ጥረት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አስቀምጧል።
ከዚህ በተጨማሪ በተለይ ምርጫ ቦርድ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶች ውክልናን ለማበረታታት ሕጉን መሰረት አድርጎ ከመንግሥት የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ለታለመለት አላማ መዋሉን የሚከታተል ስርአት መዘርጋት ይኖርበታል።
እንዲሁም ቦርዱ በተለይ ሴቶችን በማበረታታት ረገድ መልካም ውጤት ያስመዘገቡ ፓርቲዎችን የሚደግፍበት እና የሚያበረታታበት መንገድ መዘርጋት እንዳለበት በጥናቱ ተቀምጧል።
በፖለቲካ ፓርቲ መርሃ ግብሮች ውስጥ እንዲሁም በአጠቃላይ የፖለቲካ ትርክቶች ውስጥ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ጉዳዮች የተሰጣቸው አነስተኛ ትኩረት የሚያሳየው ትኩረት የሚያሻችው ጉዳዮችን በማመላከት እና የመወያያ አጀንዳዎችን በመቅረፅ የፖለቲካ ተዋናዮችን ትኩረት ከመሳብ አንፃር ተጨማሪ ሥራ እንደሚያስፈልግም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማሕበራዊ ቅንጅት በተለይ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ላለፉት ሦስት አገራዊ ምርጫዎች ሲሠራ እንደቆየ እና በዚህኛው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይም በሥርዓተ ፆታ እና በአመራር ክህሎት እንዲሁም የተግባቦት ክህሎት እና የመልካም አስተዳደር ስልጠናዎች በመስጠት እንዲሁም የሴቶች የምርጫ ማንፌስቶ በማዘጋጀት ማለትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ምረጡኝ ብለው ሴቶች ጋር ሲሄዱ ሴቶችን የሚጠቅሙ ምን ምን ነገሮች አሏችሁ ብለው እንዲጠይቁ የሚያደርግ ማንፌስቶ በማዘጋጀት ላይ እንደሆነ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ጋር በመሆን የተለያዩ ክርክሮች እና ውይይቶች በማዘጋጀት እየሠራ እንደሆነ በኢትዮጵያ ማሕበራዊ ቅንጅት የፕሮግራም ክፍል ኀላፊ መሰረት አሊ አሳውቀዋል።

እነዚህን ሥራዎች ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ከምርጫ ቦርድ እና ከሌሎች ማህበራት ጋር አንድ ላይ በመሆን እየሠራን ነው ሲሉ ገልጸዋል። በዚህ ሳምንት በሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ ከሚሠሩ 23 ያህል የሲቪል ማህበራት እና ድርጅቶች ጋር ስብሰባ እንደነበራቸው እና ሴቶች ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አዲስአባባ ላይ ብቻ ትኩረታቸውን እንዳያደርጉ እና ወደ ተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ወጥተው እንዲሠሩ እንዲሁም የሚሰሩት ሥራ ተመሳሳይ እንዳይሆን ተነጋግረው እንዲሠሩ መወያየታቸውን ገልጸዋል። እዚህ ስብሰባ ላይ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የተገኙ ተሳታፊዎች ነበሩ መካፈላቸውንም ጠቅሰው ከተሳታፊዎቹ የተለያዩ የልምድ ልውውጦች ወስደናል አገሮቻቸው የሴቶችን ተሳትፎ በምን መንገድ እንዳሳደጉ ልምዳቸውን አካፍለውናል በማለት ገልጸዋል።

አክለውም በቀጥታ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሴት አባሎቻቸው ጋር የሚሰሩት ሥራ እንዳላቸው ተናግረዋል። ከምርጫ ቦርድ ጋር ደግሞ ለመራጮች ትምህርት የሚሰጡ ሰዎችን ለማሰልጠን ፍቃድ እየጠየቅን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል። ሌላኛው ሥራችን ከመገኛኛ ብዙኃን ጋር የምንሠራ የምርጫ ዘመቻ ስራዎች ናቸው። በዚህም ከፋና ብሮድካቲንግ ኮርፖሬት ጋር በገባነው ውል መሰረት ላለፉት አምስት እሁዶች የሠራነው ፕሮግራም ተላልፏል ብለዋል። ለሴቶች እንዲመርጡ የሚያነቃቃ የሬዲዮ እና የቴሎቪዥን ፕሮግራሞችም በቀጣይነት እንሰራለን ብለዋል። በተለይ ደግሞ ለሴት እጩ ተወዳዳሪዎች የተለየ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ በአርትስ ቴሌቪዥን በሚተላለፈው ‘መቀነት’ የቴሌቪዠን ፕሮግራም በኩል አመቻችተናል በማለት አሳውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com