አይቀሬ ጦርነት ወይስ በዲፖሎማሲ የሚፈታ ጉዳይ

Views: 284

በጥቅም ት መጀመሪያ ጀምሮ የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቆ ገባው ሱዳን ቶር በርካታ ጥፋቶችን በመፈጸም እና በአካባቢው ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ከቀያቸው በማፈናቀል እና ንብረት በማውደም ስፍራውን ከተቆጣጠረ ወራት ተቆጥረዋል። ይህ ኃይል ከድንበር ማለፉ እና የአንድን አገር ሉዓላዊነት ከመድፈሩ ባለፈ በስፍራው ያለውን ሰፊ ሰሊጥ አርሻ እና ሰብል በመሰብሰብ ወደ ሱዳን መጫኑም እየተነገረ ይገኛል፤ የዓይን ዕማኞችም ይህን ጉዳይ ለአዲስ ማለዳ ያስረዳሉ። ከቀን ወደ ቀን እየተካረረ መጣው ይኸው የኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ውዝግብ የተለያዩ የመፍትሔ ሀሳቦች ተነስተውበታል በተለይም ደግሞ ውጥረቱን ለማርገብ በኹለቱ አገራት መካከል ድርድር እንዲካሔድ ጥሪዎችም ቀርበው ነበር። በዚህም ወቅት ኢትዮጵያ በድርድሩ ላይ ለመገኘት እና ፈቃደኛ ለመሆን በመጀመሪያ ደረጃ ሱዳን ከግዛቴ መልቀቅ ይኖርባታል የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርባለች። ይህን የኹለቱን አገራት ውጥረት በተመለከተ መጻኢ መፍትሄው በእርግጥ ምን ይሆን? ፣ ድምዳሜውስ በምን ይቋጭ ይሆን የሚለውን ጉዳይ የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ ባለሙያዎችን በማናገር እና ከመንግስትም ድምጽን በማካተት ሐተታ ዘማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የሚዋስናትን ድንበር ዘልቃ በመግባት በርካታ መሬቶችን በመያዝ እንዲሁም በስፍራውም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን እንዲፈናቀሉ ማድረጓ ይታወሳል። ከወራት በላይ ቆየው ይኸው የሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ የመግባት እውነት የአንድ የአንድን አገር ሉአላዊነት መጣስ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት የተከለለውን ድንበር ተላልፎ መገኘት በእርግጥም በርካታ የሕግ ምሁራን እደሚናገሩት ፍጹም ጦርነት ማወጅ እንደሆነ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ በውስጥ ችግሮቿ በተወጠረችበት እና በተለይም ደግሞ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በተደረገው የጦር መማዘዝ ጉዳይ ላይ እና መንግሥትም የሕግ ማስከበር እርምጃ ብሎ የጠራው እንቅስቃሴ መኖሩ ልብ ይሏል። በዚህ ወቅት አገር ወደ አንድ አቅጣጫ ትኩረቷን ስታደርግ ሱዳን 1600 ኪሎሚትሮችን ድንበር ከምትጋራት ኢትዮጵያ ጋር በመሬት ይገባኛል ወደ ኢትዮጵያ ዘልቃ ገብታለች አሁንም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሱዳን ጦር ይገኛል። በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በኩል ዘልቃ ገባችው ሱዳን በአካባቢው ያለውን እና ኢትዮጵያ በዋናነት ወደ ውጭ ትልከዋለች የሚባለው እና ለአገርም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ የሆነው የሰሊጥ እና ጥጥ ምርትም ሚመረትበት አካባቢ ነው። ይህ ታዲያ ሱዳን በቅርቡ ዘልቃ ከመግባቷ ባለፈ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የሆነውን በአካባቢው በስፋት የሚገነውን ሰሊጥም በመሰብሰብ ወደ አገራቸው እንደጫኑትም ታውቋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በመጀመሪያው የሱዳን ጦር ሰራዊት ድንበር አቋርጦ ወደ አካባቢው ሲገባ ከጦር መሳሪያ እና ከከባድ የጦር መሳሪያዎች ጎን ለጎን የሰብል ማጨጃ መሳሪያም ይዞ መግባቱን ይህንንም በአይናቸው እማኝ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። እንደ እንግዳችን አስተያየት ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት በአካባቢው እንዲሁ አይነት ተመሳሳይ የታጠቁ ሱዳናዊያን ገብተው አደጋ በመጣል ንብረት በመዝረፍ ይመለሱ እንደነበር እና ይህም ጉዳይ በመንግሥት በኩል ቁርጠኛ እርምጃ ተወስዶበት አቁሞ እንደነበር ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ካለው የውስጣዊ ውጥረት እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ተዳምሮ መንግስት በስፍራው ያለውን ጦር ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀሱን ተከትሎ ነው እነዚህ የሱዳን ታጣቂዎች የገቡት ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አዲስ ማለዳ በአካባቢው በሚኖሩ ሰዎችን ስለ ጉዳዮ ባነጋገረችበት ወቅት ‹‹መሳሪያ ይዘን መዋጋት እና የያዙትን መሬታችንን አስለቅቀን እንደገና መያዝ ለእኛ ቀላሉ ነገር ነበር፤ ነገር ግን አሁን በተደራጀ እና ከፍተኛ ትጥቅ ነው አሟልተው የመጡት ስለዚህ ከመከላከያ ውጪ ሊቋቋማቸው የሚችል ያለም አይመስለንም›› ሲሉም ተናግረዋል። ነዋሪዎች እና በአካባቢው ያሉ የሰፋፊ እርሻ ባለንብረቶች እንደሚሉት ሱዳኖች ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በእርግጥም መሬቱን ለመያዝ አስበው ቢሆንም ነገር ግን የጊዜ እና ሰዓቱ ሁኔታ በእርግጥም የታሰበበት ነው ማለት ይቻላል ይላሉ። እንደ ምክንያት የሚያነሱት ጉዳይ ደግሞ በአካባቢው የተዘራው ሰሊጥ ምርት ለመሰብሰብ ደርሶ ቀን በሚጠበቅበት ወቅት ወደ ስፍራው በመግባት በማሽን ማጨድ እና በመሰብሰብ ምርቱን ወደ አገራቸው መጫናቸውን አዲስ ማለዳ ከስፍራው በስልክ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ። ይህን ጉዳይ እና ተጨማሪ በአካባው የወደሙት ቤት ንብረቶች በአጠቃላይ ወደ 1 ቢሊዮን እንደሚገመትም በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ አስታውቀዋል። “ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችው ወረራ ታሪካዊ ስህተት ነው” ያሉት ዲፕሎማቱ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችው ወረራ ከሞራል፣ ከሕግ ብሎም ኹለቱ አገራት ካላቸው የቆየ ወዳጅነት አንጻር ሲታይ ታሪካዊ ስህተት እንደሆነም ነው ያስታወቁት።

ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ የተናገሩት አምባሳደሩ ሱዳን እንደ በፈረንጆች አቆጣጠር 1972 በኹለቱ መንግስታት የተደረሰውን የድንበር መርህ በጣሰ መልኩ ወረራ መፈጸሟንና ጉዳት ማድረሷን አስታውቀዋል።
ሱዳን በፈጸመችው ወረራ በንብረት እና በሰው ህይወት ላይ ጉዳት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን ጉዳቱም በግምት እስከ 1 ቢሊየን ብር የሚጠጋ መሆኑን አምባሳደር ይበልጣል አስታውቀዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ችግር በተመለከተ አሁንም በሰላም እና በመነጋገር መፍታት ይቻላል የሚል እምነት እንዳላትና ለዚህም ዝግጁ መሆኗን በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር አስታውቀዋል።
አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ሱዳን ይህንን ሰላማዊ ጥሪ የማትቀበል ከሆነ ኢትዮጵያ ራስን የመከላከል ሕጋዊ መብቷን ልትጠቀም እንደምትችልም ገልጸዋል።

“ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችው ወረራ ታሪካዊ ስህተት ነው” ያሉት ዲፕሎማቱ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችው ወረራ ከሞራል፣ ከሕግ ብሎም ኹለቱ አገራት ካላቸው የቆየ ወዳጅነት አንጻር ሲታይ ታሪካዊ ስህተት እንደሆነም ነው ያስታወቁት።
ከዚህም በተመሳሳይም ደግሞ በቀጠናው የመልካ ምድራዊ ፖለቲካ ሁኔታ እና በውሃ ፖለቲካ ከፍተኛ ጥናቶችን የሚያካሒደው እና በዚህም ዙሪያ ‹‹የዓባይ ፖለቲካ እና የባዕዳን ተልዕኮ›› መጽሐፍ ደራሲው ጋዜጠኛ ስላባት ማናዬም በዚህ ጉዳይ ላይ የራሱን ሃሳብ ከታሪካዊ ኹነቶች ጋር በማሰናሰል ሀሳቡን ይሰነዝራል። ‹‹የዲፖሎማሲው ጉዳይ በእርግጥ ፍሬ ያፈራል ወይ የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ትንሽ ጊዜ መስጠት ያለበትን ጉዳይ ይመስለኛል›› ሲል ይጀምራል ስላባት። በአሁኑ ወቅት የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ መግባቱን በተመለከተም ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ ስላባት በሱዳን ካርቱም በመለዮ ለባሹ እና በሲቪል የፖለቲካ ሰዎች መካከል ያለው ቅራኔ እና የስልጣን ንጥቂያ ውጤት ሊሆን እደሚችል እና ይህንንም ተከትሎ የመለዮ ለባሹ ክንፍ የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቆ መግባቱን ለማሳየት ይሞክራሉ። አያይዘውም ሱዳን እንደ አገር በውስጣዊ ችግሮቿ በምትታመስበት በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ መግባቷ በራሱ ለውስጥ ችግሮቿ መፍትሔ ለማግኘት እና ከሕዝብ ለለሚሰነዘርባት አጣብቂኝ ጥያቄዎች መመለሻ ጊዜ መግዣ እንደሆነም እንደሚያስቡ ስላባት ማናዬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሱዳን ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት በ1903 በእንግሊዛዊው የጦር አበጋዝ የተከለለውን ኹነት በመጥቀስ በኢትዮጵያ ላይ የድንበር መግፋት እና ድንበርንም አልፎ በርካታ ኪሎሜትሮችን ዘልቆ እስከ መግባት የመሬት ይገባኛል ጥያቄን ማንሳቷ ነው ለወቅታዊው የኢትዮጵያን መሬት ይዞ ለመቆየቷ እንደ ምክንያት የምታነሳው። ይህን ጉዳይ በሚመለከት ደግሞ ስላባት ሲያስረዱ በእርግጥ ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ይህ አከላለልን በኹለት መንገድ ያሰናስሉታል። ‹‹በወቅቱ ሱዳን በእነግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበረችበት ወቅት ነበር፤ እንግሊዛዊውም የጦር መኮንን ድንጋዮችን እያስቀመጠ የከለለው ጉዳይ ወንዞችን እና ሌላው መልክዓ ምድርን በተመለከተ ጋራውን እና የብሱን ከጦር ስትራቴጂካዊ ስፍራነት አንጸር ሲሆን ወንዙን ደግሞ ከልማት እና ተያያዥ ጠቀሜታዎች አንጻር ነበር›› ሲሉ ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ በግብጽ ካይሮ በ1964 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (በወቅቱ ስያሜ) ባሳለፈው ውሳኔ የቅኝ ግዛት ዘመን የድንበር አከላለል ሙሉ በሙሉ እንዲሻሩ ቢያደርግም የድንበር ውሎች ግን ባሉበት እንዲጸና ማድረጋቸውን የሚጠቅሱት ስላባት ይህ ደግሞ በእርግጥም በተወሰነ መልኩ ከፍተቶች እንዳሉበትም የሚሳይ መሆናቸውን ይናገራሉ። የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ በአሁኑ ወቅት የኢትጵያን ድንበር ዘልቆ መግባቱን ተከትሎም ከግብጽ የኃላ ደጀንነት ጋርም ስላባት ያገናኙታል። ‹‹የሕዳሴው ግድብን የውሃ ሙሊት በተለይም ደግሞ በዚህ ዓመት የተያዘለትን የጊዜ ገደብ ተከትሎ እንዳይሞላ ግብጽ የሚቻላትን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አትልም። እንዲያውም በኢትዮጵያ ውስጥ በዘንድሮው ዓመት ድርቅ ይሁን ብቻም ሳትጸልይ የምትቀር አይመስለኝም›› ሲሉም የግብጽ ዕጅ ከኋላ በመሆን የሱዳንን ወታደራዊ ክንፍ እንደሚያግዘው ያስረዳሉ። ለዚህ ሀሳባቸው ሲያጠናክሩ ደግሞ በመጪው ዓመት ለመሙላት በተያዘው ቀነ ገደብ መሰረት ግንባታዎችም በዛው ልክ እንደመካሔዱ የሚታወቅ ሲሆን ኢትዮጵያን በተለያዩ ነገሮች በመወጠር የሕዳሴው ግድብ ግንባታ እንዲቆም ማድረግ የግብጽ አላማ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህንንም ተከትሎ በ2013 ዓመት መገባደጃ ላይ እንዲሞላ የተያዘለት ኹለተኛው ዙር የውሃ ሙሊት ማስተጓገልን ዓላማ አድርገው ነው የሚንቀሳቀሱት ብለዋል። ምክንያቱም እንደ ስላባት ገለጻ የኹለተኛው ዙር የውሃ ሙሊት መካሔድ ኢትዮጵያ የሚኖራትን የዲፖሎማሲ በላይነት ከወዲሁ ግብጽም ስለምታውቀው እንደሆነ ይጠቁማሉ።

የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ መግባትን በተመለከተ ከኋላ በግብጽ ደጀንነት እንደሚፈጸምም ከስላባት ሀሳብ ጋር የሚመሳሰል በተባበሩት አረብ ኢመሬትስ የኢትዮዮጵያ ባለሙሉ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ ከጊዜያት በፊት በግል የትዊተር ገጻቸው ላይ ማስፈራቸውም ይታወሳል። አምባሳደሩ ሀሳባቸውን በገለጹበት ወቅትም ‹‹ግብጽ በሱዳን ዕጅ የጋለውን ብረት ለመጨበጥ ሙከራ እያደረገች ነው፤ ሱዳንም ታሪካዊ ስህተት እየፈጸመች ነው›› ሲሉም በግልጽ መናገራቸው በእርግጥም በዚህ የድንበር እና ሉአላዊነት መጣስ ከጀርባ የግብጽ ዕጅ መኖሩን አመላካች እንደሆነም ይታያል።

በሕዳሴው ግድብ የውሃ ሙሊት ጉዳይ ላይ በተጠናው መሰረት ከኢትዮጵያ ባልተናነሰ መልኩ ሱዳንም ተጠቃሚ እንደምትሆን በባለሙያዎች የተጠናው ጥናት ያመላክታል። በዚህም ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከወራት በፊት ሱዳን በጎርፍ አደጋ በተመታችበት ወቅት በፍጥነት የሕዳሴውን ግድብ ጨርሳችሁት ቢሆን ኖሮ ይህን አይነት አደጋ አይደርስብንም ነበር የሚል አስተያየት ከሱዳን መቀበላቸውን ገልጸዋል። በዚህም ሱዳን ከኢትዮጵያ ዕኩል ተጠቃሚ የምትሆንበት እንደሆነም የሕዳሴውን ግድብ አስመልክተው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ያስቀመጠችው ቅድመ ሁኔታ ተሟልቶ ወደ ድንበር ድርድሩ ብትገባ የኅዳሴው ግድብ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደማይኖረው አስታውቀዋል። የግድቡ ድርድር የሚያያዘው ከግንባታው ሂደት ጋር መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል። አምባሳደር ዲና እንደገለጹት በግድቡ ዙሪያ የሱዳን ጥቅም ተጠብቆላታል ብለዋል። የድንበሩ ጉዳይም እንዲሁ ከህዳሴው ግድብ ጋር እንደማይገናኝ አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

አሁናዊ ሁኔታው ምን ይመስላል?
በኢትዮጵያ እና ሱዳን በኩል ያለው ውጥረት አሁንም ከመካረር ወደ ላቀ መካረር እንጂ ሚለዝብበት አካሔድ አልታየም። ድንበር አልፎ የገባው የሱዳን መንግስት ወታደራዊ ክንፍ ለመደራደር አዝማሚያዎችን ቢያሳይም ይህ ግን በኢትዮጵያ በኩል በይሁንታ ሚታይ እና ተቀባይነትንም ሳያገኝ ቀርቷል። ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ቀረቡላትን የመደራደር እና የመወያየት ጥያቄዎችን ወታደራዊው ቡድን የያዘውን የኢትዮጵያን መሬት ለቆ ከወጣ በኋላ እንጂ ይህ ባልሆነበት ነባራዊ ሁኔታ ምንም አይነት ድርድር እንደማይሞከር ጠንካራ አቋሟን አስታውቃለች።

ቃል አቀባዩ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት አሁንም የኢትዮጵያ መንግስት ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መከበራቸውን ካረጋገጠ ከመደራደር ወደ ኋላ እንደማይል አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል። በቅርቡ ደግሞ የቱርኩ መገናኛ ብዙኃን እንዳስነበበው አውሮፓ ኅብረት በኹለቱ አገራት መካከል ድንበር ይገባኛል በሚል እየተካረረ የመጣውን ጉዳይ ለማርገብ ለማስማማት ፍላጎት ማሳየቱን ጠቅሷል። በሱዳን አውሮፓ ሕብረት ተልዕኮ እንዳስታወቀው በመግለጫው በአውሮፓ ኅብረት የውጭ እና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ የፊንላንዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ ላይ እንደወከሏቸውም ታውቋል። በዚህም መሰረት ነገ እሁድ ልዑኩ ወደ ሱዳን ካርቱም እንደሚያቀናም ለማወቅ ተችሏል። የጉብኝቱ አላማ በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለውን ውጥረት አለም አቀፋዊ መፍትሔ እንዲፈለግለት ያለመ ነው። ኹለት ቀናት በሱዳን ቆይታ ሚያደርገው መልዕክተኛው በቆይታውም ከሱዳኑ ፕሬዳንት አብደላ ሐምዶክ፣ ከድንበር ኮሚሽኑ አል ቡርሀን እና ከሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል። በዚህ ረገድም አምባሳደር ዲና አደራዳሪዎችን አመስግነው ነገር ግን አስፈላጊ እንዳልሆነም ተቁመዋል። በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ጸረ-ሰላም ሃይሎችን ለከላከል መስማማት ማለት የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ መስማማት ማለት አይደለም ያሉት አምበሳደሩ ሱዳን ከጃርባችን ትወጋናለች ብለን አልጠበቅንም ነበር፣ እንደምንየው ከሆነ አቋሟ የሱዳንን ህዝብ አይወክልም ብለዋል።

አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያ በሱዳን ሰላምና መረጋጋረት ለማምጣት ሰርታለች በቅርቡ እንኳን በሽግግር ወቅት ሚና ነበርት ብለዋል። በድንበሩ ጉዳይ ለማደራደር የሚጥሩት ኃይሎች እናደንቃለን ነገርግን ሌላ ወገን አያስፈልግም ሱዳን ጦሯን ካስወጣች ኹለቱ አገራት ቁጭ ብለው መደራደር ይችላሉ ብለዋል። ይህ ደግሞ በእርግጥም ሱዳን አሁን ባለችበት ሁኔታ ጦሯን ያለምንም ውጫዊ ጣልቃ ገብነት በኃይል ከያዘችው ኢትዮጵያ ክፍል እንደማታስወጣ መገመት አያዳግትም። ይህ ደግሞ አይቀሬውን ጦርነት ማስጀመሪያ ቃታውን ለመሳብ መንደርደሪያ ምክንያት እንደሚሆን ይጠበቃል የሚሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ለአዲስ ማለዳ ሀሳባቸውን የሰጡ ሙሑራን ይናገራሉ።

የወረራው ዓላማ ምንድነው?
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ሱዳን በውስጥ ችግሯ በታመሰችበት ወቅት ጊዜ መግዣ እና አጀንዳ ማስቀየሪያ ነው የሚል ሃሳብ በስላባት ማናዬ የሚነሳ ነው። በሌላም በኩል ደግሞ ስላባት እንደሚያይዙት የሰሊጥ ምርትን አጭደው እና ወቅተው በመሰውሰድ ለዓለም አቀፍ ገበያም በማቅረብ ተሸጦ በሚገኘውም ገቢ ወታደራዊው ክንፍ የራሱን ጉልበት ሊያጠናክርበት ይችላል የሚልም ሀሳብ እናዳለቸው ይናገራሉ። ነገር ግን አሁንም ዞሮ ዞሮ የቀጠናው በተለይም በኢትዮጵያ ላይ የሚነዛው ጫና እና ውዥንበር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከኅዳሴው ግድብ ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ማሳያ ነው የሚሉ ሀሳቦችን ግን ስላባት አሁንም ያስተጋባሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ከሕወሓት አመራሮች ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃ በወሰደበት ወቅት ድንበር ተሸግረው አጥፊዎች እንዳይገቡ ድንበሮቻችሁን አጥብቁ የሚል መልዕክት ማስተላለፉን ተከትሎ የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ ወደ ኢተዮጵያ ዘልቆ መግባቱን ተናግረዋል። አያይዘውም ‹‹ድንበሮቻችሁን በሚገባ ጠብቁ አልን እንጂ ኑ እና የእኛን ድንበር ጠብቁ አላልንም›› የሚል ንግግር ሲያሰሙ ተደምጠዋል።

ከዚሁ በሌላ ወገን ደግሞ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡት የመልክዓ ምድር ፖለቲካውን በተመለከተ ጥልቅ ጥናት የሚያደርጉ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ ፈለጉ ሙሑር፤ አሁን ወታደደራዊ ክንፉን በመምራት ላይ ሚገኘው ግለሰብ ከረጅም ዓመታት በፊት እንዲሁ ተመሳሳይ ድርጊቶች እየመራ ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ወቅት ከፍተኛ አጸፋ እርምጃ ከኢትዮጵያ ወገን በመግጠሙ እና በወቅቱም ሁሉም በሚባ ደረጃ የጦር ጓዶቹ ተሰውተውበት ብቻውን መትረፉ ከዓመታት በኋላ በኢተዮጵያ ላይ ያለውን በቀል ሊያስተነፍስ የመጣ ነው ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

መፍትሔው ምን ይሆናል?
በኹለቱ አገራት መካከል ያለውን ጉዳይ በተመለከተ የተለያዩ አካላት የየራሳቸውን መላ ምት የሚስቀምጡ ሲሆን አገርን ወክለው እና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉም ሰዎች ግን ይህን ጉዳይ በእርግጥ ዲፖሎማሲን እንደ መጀመሪያ እና ዋነኛ አማራጭ አድርገው ይወስዱታል። ይህ ደግሞ በእርግጥም ለኹለቱም አገራት የሚበጅ እና ያላቸውን ዘመን ተሻጋሪ ግንኙት እንዳያሻክር ጉልህ ሚና የሚጫወት እንደሆነም ይነሳል። በዚህም ረገድ የድንበር ኮሚሽኑ አባል እንደሚሉት “ሱዳኖች እምነትም አጉድለዋል” ሲሉ ይጀምራሉ በድንበር ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የቴክኒክ አማካሪ እና የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ የድንበር ኮሚሽን አባል ውሂብ ሙሉነህ።

በጋብቻ ፣ በንግድ እና በባህል በተሳሰሩት በድንበር አካባቢ ባሉ የኹለቱ ህዝቦች መካከል የጠላትነት ስሜት እንደሌለ የሚያነሱት አቶ ውሂብ ችግሮች የሚፈጠሩት የመንግስት ለውጥ በሚኖርበት ጊዜ ነው ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ መናገራቸውም ይታወሳል።
አክለውም “ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ሕግ በምታስከብርበት ወቅት የሱዳን መንግስት ድንበሩን ለመዝጋት ተስማምቶ ነበር” ያሉ ሲሆን “ይህ በመልካም መተማመን ላይ የተመሰረተ ነበር” ብለዋል። ነገር ግን ሱዳን አጋጣሚውን ተጠቅማ ወረራ መፈጸሟን ነው ያነሱት። ውሒብ ይህን ይበሉ እንጂ ኹለቱ አገራት በዲፖሎማሲያዊ መንገድ ጉዳዩን እንዲፈተቱት አሳስበዋል።

በእርግጥ የኹለቱ አገራት ውዝግብ በምን መንገድ መፍትሔ ሊያገኝ ይችላል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ስላባት ሲናገሩ፤ ‹‹ኢትዮጵያ በታሪኳ ሰው ድንበር ዘልቃ በመግባት የመተንኮስ ልምድ ኖሯትም አያውቅም›› ሲሉ ይጀምራሉ። ነገር ግን ተጀመረው የዲፖሎማሲያዊ ጥረት ከዕለታት በአንዱ ቀን ደግሞ ተሟጦ አማራጩም ሊያልቅ ይችላል፤ ይህን ጊዜም ወደ ማይቀረው በጦርነት መፍትሔ ወደ ማምጣት ሊገባ እንደሚችልም ያስባሉ። በእርግጥ አሁን ያለንበት ሁኔታ ዘለን ወደ ጦርነት የምንገባበት ላያስችለንም ይችላል የሚሉት ስላባት ከተለያዩ አገራዊ ሁኔታዎች አንጻር እንዲሁም ሰላምንም ከመሻት አንጻር ጦርነት መጨረሻው ጉዳይ ሊሆን እንደሚችልም አጽንኦት ይሰጣሉ።

ከጊዜያት በፊትም አምባሳደር ዲና እንደተናገሩት ‹‹አፍንጫህን የመታህን ወዲያው አፍንጫውን ላትመታው ትችላለህ፤ ነገር ግን ቆይተህ አንገቱንም ልትቆርጠው ትችላለህ›› ሲሉም መደመጣቸው የዲፖሎማሲው ሒደት ምናልባትም በኢትዮጵያ በኩል ጊዜ እየተገዛ ይሆን የሚል ጥያቄ ማንሳቱ አይቀሬ ሆኗል። ይህንንም ተከትሎ በእርግጥ ጦርነቱ አሁንም ሆነ በኋላ አይቀሬ ነው የሚሉ አካላትም በርከት እያሉ መምጣታቸውን አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ሰዎች ለመረዳት ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com