ሲቪክ ማኅበራት በምርጫው ላይ ያላቸውን ሚና አጠናክረው ይቀጥሉ

Views: 59

ኢትዮጵያ ከአንድ ትውልድ ወዲህ ዲሞክራሲን ለማስረጽ በሞከረችበት ሒደት ሁሉ እንደሚጠበቀው የተሟላ ዲሞክራሲን ስርኣት ካለማስፈን ባለፈ አንዳንድ የዲሞክራሲ መገለጫዎችም ጭራሹኑ ሲደፈጠጡም ኖረዋል። ከእነዚህም ውስጥ አገራዊ ነጻ እና ገለልተኛ እንዲሁም ወቅቱን የጠበቀ ምርጫን አካሂዶ ሰላማዊ ድምዳሜ ላይ የተደረሰበት ጊዜም አይታወቅም ነበር። ይህም ኢትዮጵያ እንደ አገር ደህና የሚባል እና ምንም አይነት ስጋት ማይነበብበት የምርጫ ታሪክ እንደሌለውም የሚታወቅ ነው።

በተለይም ደግሞ በሦስተኛው ምርጫ 1997 በተካሔደበት ወቅት አገሪቱ ወደ ለየለት ቀውስ ገብታ በርካቶችም ለአካል መጉደል፣ ለሕይወት መጥፋት እና ከአገር ለመሰደድ የበቁበት አጋጣሚ ብዙ እንደነበር በወቅቱ ነበርን የምናስታውሰው እና በአካልም ተገኝተን ከሕግ አስከባሪዎችም ዱላን የተቀበልን መኖራችን ሕያው ምስክር እንደሆንን ይታመናል። ይህ አጋጣሚ ታዲያ አሁንም መራጩ ሕዝብ እየተሳቀቀ እንዲመርጥ ወይም ደግሞ ምርጫ ሲባል በርቀት እንዲመለከተው የሚደርግ አጉል ትውስታ እንደሆነም ይታወቃል። ከዛም በማስቀጠል በ2007 አገራዊ ምርጫ ላይ ማለትም በአምስተኛው ምርጫ ወቅት ገዢው ፓርቲ 100 በመቶ ማሸነፉን ያሳወቀበት እና ይህም በከፍተኛ ትችት ውስጥ እንዲያልፍ ያደረገው፣ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብም ያስወቀሰው እና ትዝብት ውስጥም ያስጣለው እንዲሁም ከፍ ሲልም ሕዝብ በምርጫ እና በአስመራጩ ላይ አመኔታው በትልቁ ተሸረሸረበት እንደነበር ይታወሳል።

በእርግጥ እነዚህን ሁሉ ካነሳን ዘንድ በምርጫ ወቅት የባለድርሻ አካላት ብዛት በእጅጉ ከፍ ያለ እና ሁሉም ባለድርሻ አካልም በትኩረት እና በትልቅ መሰጠት ስራውን ማከናወን እንደሚኖርበት ይታወቃል። ከዚህ ውስጥ አንደኛው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሲሆን ይህም ስራውን በትክክል እና ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ እያከናወነ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ እና የሚስመሰግነው እንደሆነ አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች።

ነገር ግን አሁንም ይህ ነገር በቂ እንዳልሆነ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። ከዚህም ውስጥ ደግሞ የሲቪክ ማኅበራት በመጪው ምርቻ ላይ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ የተጣለባቸውን አገራዊ አደራ እና የባለድርሻ አካላትነት ቁመናቸውን በሚገባ እንዲወጡ አዲስ ማለዳ ጥሪዋን ታስተላልፋለች። ከቀናት በፊት በኹለት ዙር ፈቃድ ተሰጣቸው ቢሆንም ነገር ግን አሁንም በቀጣይ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ሚጀምረውን የምርጡኝ ቅስቀሳዎች በተመለከተ ወደሕዝቡ ወርደው በምርጫ ላይ በንቁ እንዲሳተፍ ማድረግም እንደሚኖርባቸው አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ባለፉት ምርጫዎች ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ኖራቸውን መዘንጋት የለበትም። ምርጫ ለአንድ አገር ዕድገት ያለውን ጠቀሜታ፣ ለዲሞክራሲያዊ አገር ግንባታ ያለውን ዋነኛ ግብዓትነት በሚገባ ወደ ሕዝብ አድርሰው እና ሕዝብም ይህን ተረድቶ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን የማድረግ ስራው የሲቪክ ማኅበራት እንደሆነ ማኅበራቱ ሊያውቁት ይገባል። በተለያዩ ምክንያትም በኩርፊያ እና በመንግስትም ላይ ቢሆን ቅሬታ ቢኖርባቸው መንግሥትን ለቃወም ሌላ የኃይል አማራች ከመጠቀም እና ከማሰብም ባለፈ አያንዳንዱ ምርጫ ካርድ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው እና የሚፈልገውንም የፖለቲካ ፓርቲ ወደ ስልጣን ለማምጣት የምርጫ ካርድ ምን ያህል ጉልበት እና ኃይል እንዳለው እንዲያስብ ማድረግ በዋናነት የሲቪክ ማኅበራት ስራ እንደሆነም ይታወቃል። ይህን ጉዳይ በከፍተኛ አገራዊ አጀንዳ በመቁጠር እና በመያዝ ሊንቀሳቀሱ እና ሊያስፈጽሙ ይገባል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ወቅት ያለባቸውን ቅሬታ እና በመንግስትም ሆነ በምርጫ ቦርድ ላይ ሊኖርባቸው የሚገባውን ችግር መሰረት በማድረግ ወደ ሕዝቡ እንዳይወርድ እና በራሳቸው መካከልም ከሆነ እንዲፈቱት የሲቪክ ማኅበራት መድረክ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል። በዚህ ሂደት ላይ ታዲያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳብ ወደ ሕዝብም ወርዶ ከሆነም የመመለስ እና ማስተካከል ስራዎችን ሊሰሩ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ሌላው በሲቪክ ማኅበራት ዘንድ ተጠቃሽ የሆነው ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚኖረውን ሒደት በዋናነት መገናኛ ብዙኃን ወደ ሕዝብ በማድረስ ረገድ ያላቸው ድርሻ ላቅ ያለ እንደሆነ ይታሰባል። ይሁን እንጂ መገናኛ ብዙኃን ይህን ጉዳይ በሚዛናዊነት ከመዘገብ እና ትክክለኛውን መረጃ ወደ ሕዝብ ከማድረስ አንጻር መሆን የሚገባቸውን ሚዛናዊነት በተመለከተ የሲቪክ ማኅበራት ስልጠና ከመስጠትም ሆነ የግንዛቤ መፍጠሪያ ሁኔታዎችን ካመመቻቸት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። በዚህም ሆነ በሌላ መልኩ ደግሞ የዜጎችን የተሻለ እና የዲሞክራሲያዊ መብታቸውን በስፋት እንዲጠቀሙበት እና አሁን ላይ ጠንካራ መሰረትን በመጣል ለመጪው ትውልድም የተገነባች እና ዲሞክራሲ ስርዓት እያበበ የሚሄድባትን አገር ለመፍተር የሲቪክ ማኅበራት ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይገባል።

በተደጋጋሚ ሲባል እንደሚሰማው ከዚህ ቀደም እንደነበረው እና ሲወነጀሉም እንደሚሰማው ወቅታዊ የሆነ ስራቸውን ሰርተው እና በሌላ ቀን ደግሞ ራሳቸውን ቀብረው መኖርም ሳይሆን በአዘቦት ቀን እና ወራትም ላይ ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። በምርጫም ወቅት ምርጫ ማለት ድምጽ ሚሰጥበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከምርጫው በፊት ያሉት ዝግጅቶች፣ የድምጽ መስጫው ቀን፣ እንዲሁም በድህረ ምርጫው ጊዜም ያሉ ጉዳዮች በሙሉ በምርጫ ሂደት ላይ ሚካተቱ በመሆናቸው ሲቪክ ማኅበራት እነዚህን ሁሉ መረጃዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት አገርን እና ሕዝብን የማገልገል ኃላፊነት እንዲሰማቸው አዲስ ማለዳ በጥብቅ ታሳስባለች። ይሁን እንጂ ይህን ሁኔታ በተመለከተ ለገቢ ምንጭነት ይጠቀሙበታል ሚባሉ አሉባልታዎችን ከወዲሁ ለመስበርም በጉልህ ወደ ሕዝብ ቀርበው እና አስቸጋሪውን ወቅት ከሕዝብ ጋር ሆነው በመወጣት አገርን የማዳን ሕዝብን የማገልገል ታሪካዊ ኃላፊነትም እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን። ነገ የጎለበተ፣ በመረጃ የደረጀ፣ በዲሞክራሲ መንገድ የሚመራ ትውልድን ለመፍጠርም የሲቪክ ማኅበራት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው አዲስ ማለዳ ታምናለች። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታም ከግምት ውስጥ በማስገባት በእርግጥ ሕዝቡ እና ኢትዮጵያም እንደ አገር ከምርቻው ጋር በተያያዘ ምን ሊገጥማቸው ይችላል፣ ምንስ በቅድሚያ መደረግ ይኖርበታል የሚለውንም ጉዳይ በትክክል በመገምገም ለመንግስት እና ለሚመለከታቸው አካላት በማድረስ ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣም አስፈላጊውን ርብርብ እንዲያደርጉ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com