የእለት ዜና

ከ 20 በላይ ኢንዱስትሪዎች ሊዘጉ ነው

ሰባት ኢንዱስትሪዎች ተዘግተዋል

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ከ20 በላይ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በግብዓት እጥረት፣በውጭ ምንዛሬ እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ሊዘጉ እንደሆነ የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በተጠቀሱት ችግሮች ምክንያት እስካሁን በግማሽ ዓመት ውስጥ መዘጋታቸውን እና ሠራተኞቻቸውንም መበተናቸውን የኢንዱስትሪ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ጨምሮ ገልጿል።

በአዲስ አበባ ደረጃ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ የሚባሉት ካፒታላቸው ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑና በውስጣቸውም ሠራተኞችን ቀጥረው የማሰራት አቅም ወይም የሰው ኃይል ብዛት ከአንድ መቶ በላይ የሆኑ እንደሆነም ተነግሯል።
የቢሮው የፋሲሊቴሽን ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ይክፈለው ወልደመስቀል እንደተናገሩት ቢሮው ኢንዱስትሪዎችን ለመደገፍ ከቢሮ በተወጣጡ ባለሙያዎች ፣ ከፐብሊክ ሰርቪስ የተወጣጣ እንዲሁም ከንግድ ሚኒስቴር ተወካይ ባለበት በተሠራ ጥናት ላይ ከ20 በላይ ኢንዱስትሪዎች ሊዘጉ መሆናቸውን እና ሰባቱ ደግሞ መዘጋታቸውን ማረጋገጡን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ይህ የተደራጀው ቢሮ ከፍተኛ የሚባሉ ኢንዱስትሪዎችን እንዲደግፍ የተደራጀ ቢሮ ሲሆን በዚህም ጥናቱ ላይ 667 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።
በመሆኑም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሥራ ያቆሙ እንዲሁም ለማቆም እየተገደዱ ያሉ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸው ተጠቁሟል።

አነስተኛና መካካለኛ ማኒፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ላይ መንግስት ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን በዚህም አደረጃጀቱ በመከፈሉ ምክንያት ኢንዱስትሪዎቹ ማግኘት የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንዳያገኙ አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል።
237 የሚሆኑት ኢንዱስትሪዎች የቦታ ማስፋፊያ እንደሚያስፈልጋቸው ፣ 230 የሚሆኑት የግብአት ጥሬ እቃ እጥረት እንዳለባቸው ፣ 90 የሚሆኑ የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት ችግር እንዳለባቸው ፣ 80 የሚሆኑት ኢንዱስትሪዎች የፕሮጀክት ፋይናንስ አቅርቦት ብድር ማግኘት እንዳልቻሉ እና ለስራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው ፣ 149 ኢንዱስትሪዎች ደግሞ የመብራትና ውሀ መቆራረጥ ችግር እንደገጠማቸው በጥናቱ ለመለየት ተችሏል።
ከአብነት የግብአት እጥረት ካጋጠማቸው ኢንዱስትሪዎች መካከል የዱቄት አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደሆኑም አክለው ተግረዋል።
ከአስራ አምስት ቀን በፊት ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያለባቸውን ችግር እና ሊዘጉ መሆናቸውን አሳውቀናል ብለዋል።

በመሆኑም ችግሮቹን ለመፍታት የተቋሙ አደረጃጃት ችግር መፈታት እንዳለበት እንዲሁም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መስራት ስላለብን የኢንዱስትሪ ግብአት ልማት አቅራቢ ድርጅት ጋር የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ለኢንዱስትሪዎቹ ግብአቶችን እንዲያቀርቡላቸው ስምምነት ተፈራርመናል ሲሉ ገልጸዋል።

ይክፈለው አክለውም ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋርም በመነጋገር ላይ እንገኛለን ብለዋል።
በተጨማሪም ከመብራት ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት የአዲስ አበባ መብራት አገልግሎት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን 149 ኢንዱስትሪዎች ለመፍታት እየሠራን እንገኛለን ያሉ ሲሆን በዚህ ስድስት ወር ውስጥም የ 36 የሚሆኑት ኢንዱስትሪዎች ችግራቸውን ፈተናል ሌሎቹን ለመፍታት አብረን እየሰራን ይገኛል ብለዋል።

ይሁን እንጂ የልማት ባንክ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ብድርን በተመለከተ እየተነጋጋርን ቢሆንም ባንኩ ሪፎርም ላይ ስለሆነ እስካሁን ብድር መስጠት አልጀመረም ሲሉ ገልጸዋል። በዚህም ስራችንን አስተጓጉለውብናል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
20 የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች በእነዚህ ምክንያቶች ስራ ለማቆም እየተገደዱ እንዳሉ እና ለመዝጋትም እንደተቃረቡ እንዲሁም ሰባት የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ መዝጋታቸው አሳውቀውናል ብለዋል።
የኢንዱስትሪዎቹ መዘጋት በአገር ምጣኔ ሀብት ላይ እንዲሁም የስራ አጥ ቁጥርን ከመጨመር አንፃር ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር የተናገሩት ይክፈለው በዚህም ኢንዱስትዎቹ እንዳይዘጉ ከመንግስት ድጋፍ ጋር በተያያዘ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራን ነው በማለት አስታውቀዋል።

የቴክኒካ ድጋፍ ይሰጣል ለኢንዱስትሪዎቹ ከግብአት አቅርቦት ከብድር አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት እየጣርን ነው ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!