5 ሺሕ የሦስተኛ ዲግሪ ምሩቃንን ለማፍራት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

Views: 39

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሀገር ውስጥ ትብብርና ትስሰርን በማጠናከር በመጪዎቹ 5 ዓመታት 5 ሺህ መምህራንን በሦስተኛ ዲግሪ ለማሰልጠን የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ሁርቃቶ የከፍተኛ ትምህርት መምህራንን ሁለንተናዊ ልማት ለማሳደግ ፕሮጀክቱን ወደሥራ ማስገባት አስፈልጓል ነው ያሉት።
ዶክተር ሳሙኤል እንደተናገሩት በትብብርና ትስስር ተግባራዊ የሚሆነው “Home Grown Collaborative PhD Programs” በሁሉም መስክ ብቁ የሆኑ መምህራንን በማቅረብ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ወሳኝ ሚና አለው። “እንደ ሀገር የምናስበውን የልማትና ብልጽግና ጉዞ ለማሳከት ብቃት ያላቸው መምህራን፣ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎችን ማፍራት ወሳኝ “ ነው ብለዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ሀገሪቱ ያላትን ሃብትና አቅም በማስተባበርና በሚገባ በመጠቀም እውቀትና ክህሎት ያለው ዜጋ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የሀገር ውሰጥና አለም አቀፍ ትብብርና ትስስሮችን በማጠናከር ለፕሮግራሙ መሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የሦስተኛ ዲግሪ ሥርዓተ ትምህርት ክለሳና ቀረጻ፣ የሀገር ውሰጥና የውጭ ሀገራት ፐሮፌሰሮችን ማሰማራትና የምርምር፣ የቤተ ሙከራ ግብዓቶችን አጠናክሮ ማሰቀጠል ፕሮግራሙ ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች መካከል እንደሆኑ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com