በሃዋሳ ከተማ በደረሰ የእሳት አደጋ ከፍተኛ ንብረት ወደመ

Views: 53

በሃዋሳ ከተማ በተለምዶ ቤተሰብ መምሪያ ልዩ ስሙ እርሻ ጣቢያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ደረሰ ቡሳሮ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቃጠሎው የደረሰው ትላንት ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ ነው።
“ቃጠሎው መጠነ ሰፊ ስለነበር በፍጥነት መቆጣጠር አልተቻለም” ያሉት ኮማንደሩ፤ ከሶስት ሰዓት በላይ በፈጀ ጥረት እሳቱን መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል።
የአካባቢው ህብረተሰብ፣ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የእሳት አደጋ መከላከያ እንዲሁም የፀጥታ ኃይሉ ባደረጉት ጥረት ቃጠሎውን መቆጣጠር እንደተቻለ አመልክተዋል።
“በእሳት አደጋው የወደመው ንብረት ለጊዜው ባይታወቅም እስካሁን ባለው መረጃ አራት ባጃጅ፣ አንድ ዶልፊን ተሽከርካሪ፣ አምስት የንግድ ሱቆች፣ ሜሪ ጆይ የአረጋዊያን ማዕከል ሙሉ በሙሉ መውደሙ ተረጋግጧል” ብለዋል።
አካባቢው ሰዎች ተጠጋግተው የሚኖሩበትና የንግድ ሱቆች የሚበረክትበት በመሆኑ ከፍተኛ የንብረት ጉዳት መድረሱን ጠቁመው፤ በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ አረጋግጠዋል። እንደ ኮማንደሩ ገለጻ፤ የአደጋው መንስኤና የወደመውን ንብረት ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com