ወደ ጽልመት የተመለሰችው ትግራይ

Views: 204

ከወራት በፊት ነበር በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል በሚል የፌደራል መንግሥት ሕውሓት ወደ መሸገባት የትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃውን የጀመረው። በዚህ ወቅትም የሕውሓት ቡድን በርካታ የቴሌኮም ፣ የመብራት ፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ ከባድ ጥቃት መፈጸሙየታውቀው። በይፋ እንደተገለጸው በቢሊዮኖች የሚገመት የአገር ሀብት መውደሙ እና አሁንም ድረስ ወደ ቀደመው ቁመናቸው ለመመለስ አስቸጋሪ የሆነበት ደረጃ ላይ መደረሱንም በተለያዩ ጊዜያት የሚመለከታቸው የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በሚሰጧቸው መግለጫዎች ለማወቅ ተችሏል።
ለወራት ከተቋረጡ የመሰረተ ልማት አውታሮች ውስጥ የኤሌክሪክ ኃይል አንዱ እና ግንባር ቀደሙ ነው። ሰፊ እና እልህ አስጨራሽ ስራ በመስራት ወደ አገልግሎት የተመለሰው ክልሉ የኤልክሪክ ኃይል ለድጋሚ ጥቃት ተዳርጎ ከቀናት በፊት ትግራይን ሙሉ በሙሉ ወደ ጽልመት እንድትመለስ አድርጓል። ይህን በተመለከተ የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ ስለ ሁኔታው ሰዎችን በማነጋገር እና የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር የሐተታ ዘማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

ከወራት በፊት የሕወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ አሁንም ድረስ ያልተቋጨ እና ትግራይ ክልልን ለበርካታ ቀውሶች የዳረገ ጥፋት መከሰቱ ይታወቃል። በዚህ ክስተት ወቅትም ፌደራል መንግስቱ በይፋ እንዳስታወቀው በክልሉ ያለውን የመሰረተ ልማት በሙሉ እና በከፊል በሕወሓት ቡድን እንዲወድሙ መደረጉ እና መልሶ ለመገንባትም ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ፤ ይሁን እንጂ አሁንም መንግስት የተቻለውን እያደረገ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱም ይታወሳል።

በሕወሓት ቡድን ትዕዛዝ ሰጪነት እና በክልሉ ልዩ ኃይል ተግባሪነት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው የመሰረተ ልማት አውታሮች ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የቴሌኮም ግንኙነት በግንባር ቀደምትነት የሚነሱ ናቸው። ይህንንም ተከትሎ ከመጀመሪያዎቹ የሕግ ማስከበር ወራት ጀምሮ ለረጅም ጊዜያት ክልሉ ሙሉ በሙሉ በኃይል ዕጥረት ውስጥ የነበረ ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ በርካታ አገልግሎቶች ከስራ ውጪ እንዲሆኑም አድርጎ ቆይቷል።
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው መሰረተ ልማት ውስጥ ቴሌኮም ግንኙነትም አንዱ ቢሆንም ከጉዳቱ ባሻገር ከኃይል ዕጥረቱ ጋር በተገናኘም አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ ክልሉ ከኃይል ዕጥረት ባለፈም ከግንኙነት ውጪ እንዲሆን ተደርጎ ነበር።

ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚዎች እና ከዋና የኃይል ምንጭ ወደ ትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች እና አካባቢዎች የሚያስተላልፉ መስመሮች በቡድኑ ጉዳት ስለደረሰባቸው የትግራይ ከተሞች በርካታ ጊዜያት በጽልመት ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉ ለችግሩ መባባስ ሌላ አቀጣጣይ ችግር እንደነበር ይታወሳል።

መንግስትም ክልሉን መልሶ ለማቋቋም እና የጠፉ እና የወደሙ አገልግሎቶችን ለመመለስ በሚያደርገው ርብርብ ወቅትም ከአካባቢው የጸጥታ ችግር እንጻር በቶሎ እና እንደታሰበው ለማስኬድ ሳይቻል ቀርቷል። በሌላም በኩል የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ እና ለጠፉት መሰረተ ልማቶች መለዋወጫዎችንም ለማግኘት ከባድ በመሆኑ ዘለግ ላለ ጊዜ በጨለማ ውስጥ ትግራይ ክልል ለመቆየቷ ተጠቃሽ ምክንያት ናቸው።

ይህም ብቻ አይደለም፤ በትግራይ ክልል ከሰላም እና መረጋጋቱ ባሻገር የባንክ አገልግሎትም በኃይል ዕጥረት ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ ሆነው መክረማቸውም የዚህ ሁሉ ተያያዥ ምክንያት ነው። በዚህም ምክንያት ደግሞ በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች በባንክ ውስጥ ያስቀመጡት ገንዘብ ለማውጣት መቸገራቸው፣ ከሌላ ስፍራ ወደ በክልሉ ለሚገኙ ሰዎችም ከወዳጅ ዘመድ ለመላክ የሚፈለጉትን ገንዘቦችም መላክ ሳይቻል መቅረታቸው በእርግጥ ይህን ችግር ጉልህ ያደርገዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ በመቐለ ከሚገኙ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነዋሪዎችን ከጊዜያት በፊት ባደረገችው ስልክ ቆይታ፤ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ገንዘብ ማግኘት የሚችሉበትን አቅም መፍጠር መቻላቸውን እንዲህ ሲገልጹም ነበር። ‹‹ትራንስፖርት አገልግሎት ሲጀመር የኤቲኤም ካርዶቻችን ወደ አዲስ አበባ በመላክ አዲስ አበባ ያሉ ወዳጆቻችን ገንዘብ አውጥተው ወደ ትግራይ ለሚመጣ ሰው ይልኩልናል እኛም እዚህ ያለው ለሌለው እያበደረ ነው ምንኖረው›› ሲሉም የተደመጡበት አጋጣሚ ነበር።
ይህ ደግሞ እንደሚታወቀው የክልሉን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ችግር ውስጥ የሚከት እና እምብዛም የማያወላዳ እንደሆነም አይታጣም በግልጽም እያየነው ይገኛል። ይሁን እንጂ ከረጅም ጊዜ ጥገና እና ውጣ ውረድ በኋላ በአብዛኛው የትግራይ ክልል የመብራት ኃይል አገልጎሎትን መመለስ ተችሎ ነበረ።

ቢሆንም ዳግመኛ ደግሞ ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ የሆነው መስመር በሕወሓት ቡድን መጠቃቱ እና በክልሉ ኃይል ለማዳረስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ በመሆኑ ዳግመኛ ትግራይ ክልል ወደ ጽልመት መመለሷን መንግስት በይፋ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ እንዳስታወቀው፣ የሕወሓት ቡድን አባላት በከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ መስመር ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ በትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ የኃይል መቋረጥ እንደተከሰተ አስታውቋል። መስሪያ ቤቱ ‹‹የጁንታው ርዝራዦች በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በፈፀሙት ጥቃት በመላው ትግራይ ኤሌክትሪክ ተቋርጧል ብሏል።

የጁንታው ርዝራዦች አዲጉዶም በተባለ አካባቢ ከአላማጣ – መሆኒ – መቐለ በተዘረጋው ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ ባደረሱት ጥቃት ነው በክልሉ ኤሌክትሪክ የተቋረጠው። ከዚህ ቀደም መስመሩ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበረና ለመጠገንም ረዘም ያለ ጊዜ እንደወሰደ ይታወሳል።

ክልሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ከሚያገኝባቸው መስመሮች አንዱ የአላማጣ – መሆኒ – መቐለ መስመር ሲሆን የተከዜ አክሱም መስመር ደግሞ የጥገና ሥራው እየተከናወነ እንደነበር መገለፁ አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የወደመውን መሰረተ ልማት ዳግም በመጠገን መልሶ ኃይል ለመስጠት እየሰራ ይገኛል::›› ሲል አስታውቋል።
አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ የስልክ ግንኙነቶችን ወደ ክልሉ ርዕሰ መዲና መቐለ ለማድረግ ሙከራዎችን ያደረገች ሲሆን ከምንጮች የተንቀሳቃሽ ስልኮች የባትሪ መጥፋት እና ከኃይል ዕጥረቱ ጋር ተዳምሮ የኔትወርክ መቆራረጥ በመከሰቱ ጥርት ያለ የስልክ ግንኙት ማድረግ ሳትችል ቀርታለች።

ነገር ግን ይህ ጽሑፍ በተጠናቀረበት ወቅት ከቀናት በፊት ከትግራይ መዲና መቐለ ወደ አዲስ አበባ የመጡት እና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ግለሰቦች ደግሞ የሚሉት አላቸው። ‹‹ያለው ችግር ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ አይደለም፣ ነገር ግን ከቀን ወደ ቀን መሻሻሎች ቢታዩም መብራት መቆራረጥ ግን የተለመደ ሆኗል። እኛ ከመጣን በኋላ መጥፋቱን ሰምተናል ነገር ግን አሁንም ለቀናት ፣ለሳምንታት፣ ለወራት መብራት አገልግሎት ያላገኙ ሰዎች ግን አሁንም በትግራይ አሉ›› ሲሉ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ሰዎች ተናግረዋል።

በኃይል መቆራረጥ ምክንያት ደግሞ በክልሉ ደርሶ ነበረውን ችግረም ሲናገሩ ‹‹ኃይል ስናጣ ማብሰል የጀመርነው በከሰል ነበር፤ አንዳንድ ጊዜም በቃ የተገኘውን ምግብ ሳናበስል ጥሬ መመገብ ጀምረንም ነበር። ለማብሰል ከሰል መጠቀማችን የከሰል ዋጋ በእጅጉ እንዲንር አድርጎት ነበር። ነገር ግን ሰው ገንዘብ ስለማይኖረው በአጭር ጊዜ የከሰል ዋጋ መውረድ ጀምሮ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን ከሰል ለማክሰል ወጣ በሚሉበት ጊዜም ከሰል የሚያከስሉ ሰዎች ድብደባ ይካሔድባቸው ስለነበር ከሰሉንም ማግኘት በጭንቅ ነበር። ይህ ሁሉ ሆኖ ደግሞ ምግቡን ሳናበስል መመገብ በጀመርንበት ወቅት ልጆቻችን በተለይ ሕጻናት መታመም በመጀመራቸው በእጅጉ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተን ነበር፣ ነገር ግን መብራት ሲመለስልን ያገኘነውን ምግብ ቢያንስ አብስለን መመገብ ችለን ነበር›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት መሰረት የሕወሓት ቡድን አደረሰ ባለው ጥቃት የወደሙ ንብረቶችን እና ኪሳራዎችን አስታውቋል። በዚህም መሰረት ፌደራል ፖሊስ በመግለጫው ‹‹በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊትና የመንግስት ተቋማት ጥበቃ ላይ በነበሩ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ላይ በፈፀመው የሀገር ክህደት ወንጀል፤ በኢትዮ-ቴሌኮም፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድና ኤርፖርቶች ድርጅት እንዲሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚገኘው የደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል ።

በዚህ መሰረት በአካባቢው በሚገኙ የኢትዮ-ቴሌኮም መሰረተ-ልማቶች ላይ ጁንታው ባደረሰው ጉዳት ተቋሙ ማግኘት ከሚገባው 1,370,828,689.35 (አንድ ቢሊዮን ሶስት መቶ ሰባ ሚሊዮን ስምንት መቶ ሃያ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ብር ከ35 ሳንቲም) በላይ ማጣቱትን በምርመራ ተረጋግጧል።

በተጨማሪም በተቋሙ ላይ ከ39.8 ቢሊዮን ብር በላይ የተፈፀሙ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን ማክሸፍ መቻሉ ተጠቅሷል። በተመሳሳይ በሰሜን በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ-ልማቶች ላይ ጁንታው የህወሃት ቡድን ጉዳት ያደረሰ ሲሆን ተቋሙ ከ 329,167,524.00 ብር (ሶስት መቶ ሃያ ዘጠኝ ሚሊዮን አንድ መቶ ስልሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ሃያ አራት ብር) በላይ ማጣቱ ተረጋግጧል።

በዚሁ ጥቃት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በወልቃይት፣ በማይጨው፣ በአላማጣ እና በአሸጎዳ መቀሌ ‹ሰብስቴሽኖች› ላይ ውድመት የደረሰ ሲሆን በእነዚህ ንዑስ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ ጣቢያዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት የምርመራ ቡድኑ በገንዘብ መጠን አስልቶ ወደፊት አንደሚገለጽ ተጠቁሟል።›› ሲል አስታውቋል።

ከዚህ በመነሳት በአሸጎዳ ነፋስ ኃይል ማመንጫ እና አላማጣ ላይ ያለውን ሰብስቴሽን ውድመት በተመለከተ ጠቅለል ያለ ሪፖርት ማግኘት ባለመቻሉ በይደር ያቆየው መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን ይህም ደግሞ በአሁኑ ወቅት ለዳግመኛ የኃይል ዕጥረት የተዳረገችው ትግራይን በተመለከተም ውድመቱን አንድ ላይ አስልቶ ያቀርበዋል ተብሎ ይጠበቃል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ መጡ ግለሰቦች እንደሚሉት በእርግጥም ከሕውሓት ቡድን ወደ ሕዝቡ ሚላኩ መረጃዎች ከቀን ወደ ቀን አስፈሪ እየሆኑ መምጣታቸው በመቐለ ለመቆየት የሚያስደፍር አለመሆናቸውን በማመናቸው ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

‹‹እኛ የመጣነው የካቲት 11 በተመለከተ ሕወሓት በምን መልኩ እንደምናከብረው እኛው እናውቃለን በሚል የተለያዩ መረጃዎችን በመልቀቁ ስለሆነ ሊከሰት የሚችለውን ችግር አስቀድመን ፈርተን ነው የመጣነው ፤ የአሁኑ የመብራት መቋረጥም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው ብለን ነው የምናምነው›› ሲሉም ይናገራሉ።

የትግራይ መጸኢ መልክ
በትክክል የተከሰተውን ጉዳይ በተመለከተ ትግራይ ከዚህ በፊት ወደ ነበረችበት ችግር ትመለስ ይሆን ወይስ ምን አይነት አማራጮች ይወሰዱ ይሆን የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው መንግስት በተቻለ መጠን ያለውን ችግር ለመፍታት እና ከዚህ በፊት ከቆየበት ጊዜ አስቀድሞ ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
መስሪያ ቤቱ ለአዲስ ማለዳ ጨምሮ እንደገለጸው ከዚህ ቀደም ዘለግ ላለ ጊዜ መጥፋቱን ተከትሎ በክልሉ ለዘርፈ ብዙ ችግር መጋለጡን በማውሳት በዚህ ጊዜ ግን ቢያንስ የሚፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ችግሩ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ይህን ይበል እንጂ አሁንም የኃይል መቆራረጥ በሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይም ዳፋው ቀላል እንደማይሆንም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በትግራይ ብልጽግና ከፍተኛ አመራር ተናግረዋል።
ግለሰቡ እንደሚሉት ይህን ጉዳይ በክልሉ የተሾመውን አዲሱን ካቢኔ እና የፌደራል መንግስቱን ለማዳከም የተሰራ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳጣት የተደረገ በመሆኑ ሕዝቡም ይህን ተረድቶ ከጎናችን ሊቆም ይገባል ሲሉም አውስተዋል።
ከሰሞኑ የኃይል መቋረጥ ጋር ተያይዞ ታዲያ ከትግራይ ክልል ውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችም በትግራይ የሚገኙ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ለማግኘት የሚያደርጓቸው የስልክ ጥሪዎች ሳይሳኩ መቅረታቸው እና በተደጋጋሚ የሚደረጉ ጥሪዎች በስልኮች መዘጋት ምክንያት እንዳልተሳኩም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ይህን አይነት ቅሬታ እና ችግር አዲስ ማለዳ ይደርሷት የነበረው በመጀመሪያዎቹ የሕግ ማስከበሩ ወቅት እንደነበርም ልብ ይሏል። የኃይል መቋረጡ ከታወቀበት ቅጽበት እንስቶ ተንቤን እና መቐለ ወደሚገኙ ወዳጆቿ ተደጋጋሚ ስልክ ጥሪ ማድረጓን የምትናገረው ሐና ኃይሌ (ስሟ የተቀየረ) ልታገኛቸው እንዳልቻለች ለአዲስ ማለዳ ትናገራለች።

‹‹ያልተሳካ ጥሪ በተደጋጋሚ ይደርሰኛል ነገር ግን መልሼ ስደውል ማግኘት እንደማልችል የሚገልጽ መልዕክት ነው የሚደርሰኝ›› ስትል ለአዲስ ማለዳ ትናገራለች።
አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በተከፈቱ የደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ይከፈል ነበረው በክልሉ ለሚገኙ የጡረታ ተከፋዮች ከሕግ ማስከበሩ ወዲህ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መዛወሩን ዘግባ ነበር። በዘገባውም የመንግሥት ሰራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ኤጀንሲው አስቀድሞ ወደ ንግድ ባንክ የማዞር ዕቅድ የነበረው ቢሆንም ነገር ግን በሕግ ማስከበሩ ዕርምጃ የደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ በመታገዱ ወደ ንግድ ባንክ ለማዞር አጋጣሚም እንደተፈጠረ ገልጸዋል።

ምክትል ዳይሬክተሩ ይህን ይበሉ እንጂ ለአዲስ ማለዳ ዝግጅት ክፍል የተለያዩ መልእክቶችን የሚልኩ በትግራይ ክልል የሚገኙ ነዋሪዎች እንደሚሉት በክልሉ የባንክ አገልግሎት እንደተዘጋ የቀረባቸው አካባቢዎች ከመኖራቸው ጋር ተዳምሮ እና ባንክ ሙሉ በሙሉ መስጠት በማይችልበት ሁኔታ የጡረታ ክፍያዎችን ወደ ባንክ ማዞር ተገቢ አይደለም የሚል አስተያየት ሲሰጡ ቆይተዋል።

ይህ በሆነበት ሁኔታ ደግሞ በትክክል ይህን አይነት ችግር ለመፍታት መንግስት ርብርብ በሚያደርገበት ወቅት ተጨማሪ ጥፋት መፈጸሙ ደግሞ የትግራይን ክልል ነባራዊ ሁኔታ የሚቀይር ለመሆኑ አስተያየት ሰጪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከዕርዳታ ጋር በተያያዘም በክልሉ ውስጥ ያለውን የእርዳታ አሰጣጥ በተመለከተ የሰላም ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ በላከው መልዕክት እንዳመለከተው የሰላም ሚኒስቴር በትግራይ ክልል የሰላም ማስከበር ሂደቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል ላለፋት 3 ወራት የተባበሩት መንግስታት ልዩ ልዩ ድርጅቶችን ጨምሮ ከ26 በላይ አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በጥምረት የሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ተግባራን ለማገዝ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል።

ባለፉት 3 ወራት በተለያዩ ጊዜያት ቦታው ተገኝተው ድጋፍ ለማድረግ ላመለከቱ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች አለም አቀፍ መመዘኛውን አሟልተው ለተገኙ 75 አባላት ወደትግራይ ክልል መግባትና የሰብዓዊ ድጋፍ ሂደቱን እንዲያግዙ ፈቃድ ሰጥቷል። የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት (UN-OCHA) በአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል (ECC) በምክትል ሰብሳቢነት የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፉንና የመልሶ ማቋቋም ሂደቱን የማስተባበር ሂደቱን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅንጅት እያስተባባረ ይገኛል።
በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ስርጭት እስከ አሁን በ32 ወረዳዎች በሚገኙ 92 የስርጭት ጣቢያዎች ተጠናክሮ መካሄዱን ቀጥሏል:: በተመሳሳይም ድጋፉ በክልሉ በሚገኙ ኹለት የስደተኞች መጠለያ ካምፖች እየተዳረሰ ይገኛል::
ይህ ከላይ የሰላም ሚኒስቴር ያስቀመጠው መልእክት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግን በትልቁ ሊቀይር የሚችል ጉዳይ ከቀናት በፊት መፈጠሩ ደግሞ በሰብኣዊ ድጋፉ ሒደት ላይ ሊያሳድረው የሚችለው ተጽዕኖ ከባድ እንደሚሆን አስተያየት ሰጪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በኃይል መቆራረጡ ምክንያት ለሚከሰተው የተለያዩ ዓይነት መሰረተ ልማት ተግዳሮቶች ከወዲሁ ሊታሰብ እንደሚገባም እየተጠቆመ ይገኛል። ከላይ እንደተጠቀሰው በ32 ወረዳዎች በሚገኘው 92 ስርጭት ጣቢያዎች ላይ በሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ ላይ የግንኙነት መቋረጦች ከተከሰቱ ስርጭቱን ከባድ ሊያደርው እንደሚችልም ታውቋል።

በቀጣይ የሕወሓት ቅርጽ ምን ይመስላል?
ከታሰበለት ጊዜ አስቀድሞ ተጠናቋል የተባለለት የሕግ ማስከበሩ ሒደት የሕወሓትን ላዕላይ አመራሮች እና መስራቾች በመደምሰስ እና ማርኮ ለሕግ በማቅረቡ ረገድ ከፍተኛ ስራ እንደተሰራበት የሚታወስ ነው። በዚህ ሒደት ላይ ታዲያ አሁንም በሕውሓት ዘንድ ያሉ እና ሕውሓትን በሚመለከት በሕዝቡ ዘንድ ያሉ አመለካከቶች መኖራቸውም ለማወቅ ተችሏል።
ከሳምንታት በፊት የቀድሞ የሕወሓት አባል ነበሩት ሙሉጌታ ገብረሕይወት ከ World Peace Foundation ዋና ዳይሬክተር አሌክስ ደ ዋል ጋር ባደረጉት ስልክ ግንኙነት ሕወሓት አሁንም በትግራይ ተራሮች ውስጥ እንዳለ እና ለመታገልም ዝግጁ መሆናቸውን ያነሱበት ንግግር ይፋ ተደርጎ ነበር።

በተመሳሳይም ወደ ትግራይ አቅንተው የነበሩ ግለሰቦች ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሕወሓት የቅርጽ ለውጥ በማድረግ ወደ ሽምቅ ውጊያ መመለሱን እና አንዳንድ ጊዜም በድንገት አደጋ የመጣል ጸባይ እንዳለው ተናግረዋል። ይህን ደግሞ ለማጠናከር ከሳምንታት በፊት ወደ ትግራይ መዲና መቐለ የተጓዘው ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ በሦስት ክፍል ካስነበበን ጽሑፍ ጋር ከትግራይ መናገሻ መቐለ መውጣት እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ጉዞ ማድረግ እንደማይመከር እና ድንገተኛ አደጋዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ሰዎች እንደነገሩት ማስነበቡ ይታወሳል።

ይህ የደፈጣ ጥቃት እና ሽምቅ ቅርጽ መቀየሩ ደግሞ ዋነኛ መገለጫው በቅርቡ ትግራይን ወደ ጽልመት የመለሰው ይኸው የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚውን መስመር ማጥቃታቸው ነው።
በአንጻሩ ደግሞ ፌደራል መንግስቱ በአሁኑ ወቅት የሕወሓት ቡድን በመጥፋት ደረጃ ላይ መገኘቱን ይፋ እያደረገ ይገኛል። ይህንንም ተከተሎ መንግሥት ፊቱን ክልሉን ወደ ማልማት እና መልሶ ወደ ማቋቋም እመለሰ እንደሚገኝም እየገለጸ ይገኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com