የካቲት 12 ሲታወስ

Views: 49

የካቲት 12 ሲመጣ ጣልያን ኢትዮጵያን በወረችበት ጊዜ በጀነራል ግራዝያኒ አዛዥነት በሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ 30 ሺህ ዜጎች መጨፍጨፋቸውን ታሪክ ይዘክራል። ይህንን ምክንያት በማድረግ ሰማዕታቱ በዚህ ቀን ታስበው ይውላሉ።
ነገሩ ሲታወስም እንዲህ ነበር የሆነው።በ1929 ለጣሊያን ንጉሳዊ ቤተሰብ አንድ ልዑል በመወለዱ ምክንያት በጀኔራል ግራዚያኒ ትዕዛዝ በአሁኑ አጠራሩ አዲስ አበባ ዩኒቨሪሲቲ 6 ኪሎ ግቢ በቀድሞው ደግሞ ገነተ ልዑል ቤተ- መንግስት ደስታውን ለማክበር የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዲሰበሰቡ ትዕዛዝ ተላለፈ፡፡ብዙ ሰውም ታደመ።

ታዲያ በዚህ ጊዜም ጀኔራል ግራዚያኒ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ የፋሽስቱ ባለስልጣናትና ወታደሮች ለፋሽስቱ ያደሩ ባንዳዎችና መኳንንቶች፣ በተገኙበት አስደንጋጭ የሚባለው አደጋ ተፈጠረ።
ይህንን በተመለከተም አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም ባወጣች ጸሁፍ ላይ፤ በጋዜጠኝነት አገልግሎቱ የሚታወቀው ጳውሎስ ኞኞ የጻፈውን ጽሁፉን እንዲህም አስፍራ ነበር።
«የኢትዮጵያና የጣልያን ጦርነት» የተሰኘው መጽሐፉ ላይ ጣልያን ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረር ተጠቃሽ ሰበብ የሆናትን የወልወል ግጭት ጉዳይን ያነሳል።

«ማንኛውም የጣልያን ወታደር የረገጠው መሬት ሁሉ የጣልያን ቅኝ ግዛት መሆን አለበት። የምኒልክ ጊዜ በ1898 እና ግንቦት 16 ቀን 1908 ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው የወሰን ስምምነት መፍረሱን የጣልያን ሹማምንት ሁሉ እንዲያውቁት» የሚል ትዕዛዝ ከሮም ተላለፈ።
«ኅዳር 26 ቀን ረቡዕ ልክ ከቀኑ 9 ሰዓት ተኩል ሲሆን በድንገት ባንዳዎቹ በኢትዮጵያ ወታደር ላይ አደጋ ጣሉ። ወዲያው በሰማይ አውሮፕላኖች፤ በምድር ታንኮች ደርሰው በጣሊያኖቹ መድፍና ቦምብ መሬቷ ተርገበገበች። ኢትዮጵያውያኑም ያሉበትን ስፍራ ሳይለቁ ባላቸው አሮጌ መሣሪያ እስከ ሌሊቱ 5 ሰዓት ድረስ በጀግንነት ተዋጉ። በዚያም ጦርነት 94 ኢትዮጵያውያን በጀግንነት ሲወድቁ 45 ቆሰሉ።» በማለት ነበር የሆነውን ነገር ጳውሎስ በመጽሐፉ ያሰፈረው።

ጥላሁን ጣሰው «የኢትዮጵያና የጣሊያን ኹለተኛው ጦርነት» በተሰኘ መጽሐፉ ይህን ነጥብ ሲያነሳም ጉዳዩ ከአድዋ ድል ጋር የሚገናኝ ነው ይላል። ጣልያን በአድዋ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀል ቀን ቆጠራ ጊዜ ጠብቃ ነበር ኢትዮጵያን የወረረችው በሚለው ሃሳብም ላይ ይስማማሉ።

በመጽሐፉም ኢትዮጵያ ከአድዋ ድል በኋላ በቀጣይ 40 ዓመታት ከመጠነኛ መሻሻል በቀር የተለየ ለውጥ ያስመዘገበች አለመሆኑ፣ ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ ሞት በኋላ የነበረው የሥልጣን ፍትጊያ የኢትዮጵያን ማእከላዊ መንግሥት እያዳከመው መሄዱ፣ በጥቅሉ ኢትዮጵያ በሽግግር ላይ የነበረችበት ወቅት መሆኑ ለጣልያን ጥሩ አጋጣሚ ሆነ። የንጉሡ ከአገር መውጣት ደግሞ ጉዳቱ እንዲከፋ አድርጓል።

አምስቱ የመከራ ዓመታት ሲታወስ
በጣልያን ወረራ ዘመን አምስቱ ዓመታት ለኢትዮጵያውያን ከባድ የመከራ ዓመታት ነበሩ። የማይረሱ ጦርነቶችና አሳዛኝ እልቂቶችም የተፈጸመባቸው ሲሆን ከነዚህም መካከል እንኳን በደብረ ሊባኖስ የደረሰው መከራ ቀላል እንዳልሆነም በታሪክ ይታወሳል። ሌላው በዚህ የታሪክ ክስተት ውስጥ እንደ አቡነ ጴጥሮስ ያሉ የሃይማኖት አባቶችም ሰማዕት ሆነዋል።

እንዲሁም የማይጨው ጦርነት ፣የአሸንጌ ሐይቅ እልቂትም ይነሳል። ይህን በተመከተም አዲስ ማለዳ ከቀደመው ጽሁፏ ላይ ስታስታውስ «በሰሜን በኩል አርባ የሚሆኑ አይሮፕላኖች ከመስመሩ መጨረሻ ጀምረው በአንድ ጊዜ ሰልፈኛው ላይ ኤፕሪት ጋዝና የቦንብ መብረቅ ያወርዱበት ጀመር።… እንደገና ጋዙን ሊሞሉ ሲሄዱ ሌሎች ደግሞ ወዲያውኑ እነርሱን የሚተኩ ጋዝ የሞሉ አውሮፕላኖች በቦታቸው ይመጣሉ።…በጥቂት ሰዓታት ቆይታ የአንድ ትልቅ ሰልፍ ሙሉ ወታደር ድምጥማጡ ጠፍቶ አፈር ለበሰ።…በማግስቱ ጎህ ሲቀድ የአሸንጌን ሐይቅ ባየነው ጊዜ የሚያሰቅቅ ትዕይንት ተደቅኖ አገኘን። የሐይቁ ዙሪያ በሬሳዎች መቀነት ተከቧል። የሴት የወንድና የእንስሳት ሬሳ አብሮ ተደባልቋል።…ከሬሣው ብዛት የተነሳ ሐይቁ ትልቅ የመቃብር ቦታ ይመስላል…» በማትም በአሸንጌ የነበረውን እልቂት በሚመለከት ጥላሁን በመጽሐፉ የከተበውን ጽሁፍ አስፍራለች።

በአንድ ወቅት ጋዜጠኛና የታሪክ ባለሞያ ጥበቡ በለጠ ክስተቱን ምን ያህል አሳዛኝ እንደነበር ሲገልጹ ‹‹ ልጆች ያለ እናት፣ እናቶችም ሕጻናት ልጆቻቸውን ተነጥቀው ለብቻቸው የቀሩበት ነው›› በማለት ያነሳሉ። ጥበቡ፣ የደራሲና አርበኛ ተመስገን ገብሬ ‹ሕይወቴ› የተሰኘ መጽሐፍ በመጥቀስ፣ የካቲት 12ን በሚመለከት ‹‹እንደሚታወቀው ተመስገን ገብሬ ከጦርነቱ መነሳት አስቀድሞ ስጋታቸውን ያቀረቡ፣ ሲልቪያ ፓንክረስት (የሪቻርድ ፓንክረስት እናት) በኢንግሊዝ ለሚያሳትሙት ጋዜጣም፣ ጣልያን ኢትዮጵያ ላይ ያደባችውን ደባ በሚመለከት መረጃ ሲያቀርቡ የነበሩ አርበኛ ናቸው›› በማለት ይህንንም ያደረጉት ከድርሰት ሥራቸው ጎን ለጎን እንደነበር በማስታወስ።

ተመስገን ገብሬ ፤የካቲት 12 አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒን ለመግደል ያደረጉት ሙከራ ዋና አቀነባባሪ ተመስገን ናቸው በሚል ጣልያኖች ሊገድሉ ከሚፈልጓቸው ሰዎች መካከል እንደነበሩም ይገለጻል።ጥበቡ ታድያ እኚህን ሰው በማንሳት፣ ያንን አሳዛኝ ክስተት የዛሬ ትውልድ መዘንጋት እንደሌለበት በተማጽኖ ማሳሰባቸውንም አዲስ ማለዳ ‹‹አምስቱ የመከራ ዘመን – በየካቲት 12 መነጽር›› በሚል ርዕስ ስያሜ በሰጠችው ጽሁፋ ላይ አመላክታለች።

የካቲት 12 በዘመናት መካከል
ይህ የመታሰቢያ ቀን በተለያዩ ዘመናት በራሳቸው ቀለም እና የአከባበር ሁኔታ ዛሬም ድረስ እየተከበረ ይገኛል።ምንም እንኳን በዓሉ በሚታወስበት ጊዜ እንደ ቀድሞ ሳይሆን አከባበሩ እየቀዘቀዘ እንደሆነ ሲነገርም ይሰማል።
የዛሬ ዓመትም ሐሙስ እለት የዋለው 83ኛው የካቲት 12 የሰማዕታት ቀን መታሰቢያ እንደተለመደው ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት ሃውልት ስር ታስቦ፣ ሰማዕታቱም መዘከራቸውም አይረሳም። በዕለቱም በከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ የሚገኙ ባለሥልጣናት አልተገኙም ማለት ይቻለል።

ይሁን እንጂ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጀምሮ በርካታ ዜጎች ሰማዕታቱን ለማሰብ በመታሰቢያ ሃውልቱ ስር ተገኝተው ነበር ። ጉዳዩንም መገናኛ ብዙኀን የዜና ሽፋን ሰጥተውት እንደነበርም አዲስ ማለዳ መመልከት ችላ ነበር።
የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ ሰማዕታቱን በዘከረው በዚህ በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ከቀደሙት አባቶች በብዙ መስዋዕትነት የተቀበሏትን አገር፣ ሰማዕታቱን በማሰብና ሰላምን በመጠበቅ የአሁኑ ትውልድም ድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። ‹‹ከአባቶቻችንን የተረከብናትን አገር ለልጆቻችን ማስተላለፍ የምንችለው አንድ ስንሆን ነው።›› ያሉት ልጅ ዳንኤል፣ ሰማዕታቱን በማሰብ ስርዓቱ በየዓመቱ የሚታዩ ለውጦችን አድንቀዋል አመስግነውም ነበር።

ከዚህ ሃሳብ ጋር በተያያዘም እና በተመለከተም ‹‹በዘመን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት የተለየ ነበር። ጥቁር የለበሱ ሰዎች ትርኢት ያቀርባሉ። ፉከራ ቀረርቶ የሚባል ነገር የለም። ካላንደርም ዝግ ነበር።›› በማለትም የማህበሩ የታሪክ ሰነድ እና የተዛማች ጉዳዮች ኃላፊ – ልጅ ኤርሚያስ ተሰማ እርገጤ አስታወሰዋል ። የካላንደሩ ነገር ሲታወስም በደርግ ዘመነ መንግስትም (በወታደራዊ) ዘመነ መንግስትም ካለንደር ዝግ ሆኖ ነገር ግን ንጉሳዊ ሥርዓቱ ተወግዶ አርበኞች በቦታው ላይ ተሰልፈው የወታደራዊ መኮንኖች እንዲሁም የመከላከ ሠራዊቶች ቦታው ላይ ተገኝተው መታሰቢያ ተደርጎ ነበር የሚታወሰው ይላሉ።

አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ካላንደር የሚዘጋው ተሰርዞ መታሰቢያ በዓሉ እየቀነሰ ስለመምጣቱ በመግለጽ አሁን ባለው መንግስት ደግሞ በልዩ ሁኔታ እንዲከበር የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ስለመሆኑም ልጅ ኤርሚስ ምስክርነቸውን በመስጠት ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።
የዘንድሮ በዓል በተለይም በከተማ አስተዳደሩ በኩል ትልቅ ትኩረት እንደተጠው የሚናገሩት ልጅ ኤርሚያስ፤ ከመንግስት ኃላፊዎች ጀምሮ ተማሪዎች ተገኝተው እንዲያከበሩ ብዙ ድጋፍ ማድረጉንም አልሸሸጉም።

ከዚህ በኋላ እንዴት ይከበር?
ልጅ ኤርሚያስ ከዚህ በኋላ የመታሰቢያ በዓሉ ሲከበር በካለንደር ተዘግቶ ፋሺስቶች ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሱ መነገር አለበት በማለት ከገለጹ በኋላ‹‹ በተለይም የእነሱ ግርፍ የሆኑት ወያኔ ወይም የህውሃት አባላት በእጅ አዙር ከብዙ ዘመናት በኋላ በእነርሱ አማካኝነት ተመልመለው ከሲቪሉ አልፈው የመከላከያ ሠራዊታንም እንዴት እንደጨፈጨፉ በየዘኑም አስጊ ተግባር እንደሆነ እና ሴረኛ ቡድኖች ዛሬም ድረስ እነዳልጠፉ ያሳያል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ህዝብ ላይም ከ84 ዓመት በኋላ ዳግም ጭፍጨፋ ያደደጉ መሆናቸውን እና ሊጠፋ የማይችል ታሪክ በመሆኑም ድርጊቱ በትምህርተ ካሪኩለምና በሌሎቻ ማስተማሪያ መንገድ ማስገዘብ ያስፈልጋል›› ባይ ናቸው። ይህ ግን የሚሆነው ለማስተማር ይረዳል ብሎ በማሰብ እንደሆነ ነው ልጅ ኤርሚስ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com